የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (Editors Guild of Ethiopia)ሳምንታዊ የቁርስ ላይ ስብሰባውን በሂልተን ሆቴል አካሂዷል ። የዕለቱ የመወያያ ርዕስ ጉዳይም ”Media and Gender“ የሚል ነበር፡፡
እንደወትሮው ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ጽሁፍ፣ በጾታ እኩልነት ላይ ትኩረቷን አድርጋ በምትሰራው የሚዲያ፣ አድቮኬሲ እና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዋ ቤተልሔም ነጋሽ የቀረበ ሲሆን፤ የማህበሩ አባላትም በርዕሰጉዳዩ ላይ የሞቀ ውይይት አድርገዋል፡፡ ከሌላው ጊዜ በተለየ በዛሬው የውይይት መርሃ ግብር ላይ በርከት ያሉ ሴቶች ሃሳብና አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ የሚሰሩ ሴቶች ውክልና 30 በመቶ ብቻ መሆኑን የጠቆመችው የጥናት ጽሁፍ አቅራቢያዋ፤ ሴቶች በኢትዮጵያ ሚዲያ ያላቸው ውክልና እንዲጨምር በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብላለች፡፡
በሚዲያው ላይ የሴቶች ጉዳይ በስፋትና በጥልቀት የማይነሳውና የማይዳሰሰው አንድም፣ የኤዲተርነት ቦታው በአብዛኛው በሴቶች ሳይሆን፣ በወንዶች የበላይነት በመያዙ ነው የሚል ሃሳብም ተነስቷል፡፡ ሴቶች ለተወሰነ ጊዜ የኤዲቶርያሉ ቦታ ሲሰጣቸው፣ አስገራሚ የይዘት ለውጥ እንደሚስተዋልም ተጠቁሟል ፡፡
በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ሴት ባለሙያዎች፣ በዜና ምንጭነት ያላቸው ቦታ እጅግ አናሳ መሆኑም ተነስቷል፡፡ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት፣ ከሴቶች ይልቅ ወንድ ባለሙያዎችን እንደ መረጃና ዜና ምንጭነት የመጠቀም አዝማሚያና ልማድ እንዳላቸውም ነው በውይይቱ ላይ የተነሳው፡፡
በውይይቱ ማብቂያ ላይ፣ ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የመረጃ ዳይሬክቶሬት ”Women Experts Directory” ለአርታይያኑ ተሰጥቷል ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣ ”Women Experts Directory” የተሰኘ ለጋዜጠኞችና ሚዲያ ተቋማት በመረጃ ምንጭነት የሚያገለግል ባለ 162 ገጽ ዳይሬክቶሪ አሳትሟል፡፡ ዳይሬክቶሪው በ18 የተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ የተሰማሩ የ200 ሴት ባለሙያዎችን የትምህርትና የሥራ ልምድ መረጃ፣ ከስልክ ቁጥርና ኢሜይል አድራሻቸው ጋር አጣምሮ አቅርቧል፡፡ ዳይሬክቶሪው፤ የዜና ምንጭ የሚሆኑ የሴት ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ ያግዛል፤ በሚዲያ ያለውን የጾታ ውክልናንም ያሰፋል፤ የጾታ ተመጣጣኝነትን (ሚዛናዊነትን) ያማከለ የሚዲያ ከባቢ ለመፍጠርም ያግዛል ተብሏል፡፡
በዋናነትም ሴት ባለሙያዎች ለሚዲያው የበለጠ ተደራሽ ሆነው፣ የዜና ምንጭነት ድርሻቸው እንዲጎላ በማለም ነው፣ ዳይሬክቶሪውን በህትመትና በዳታቤዝ ያዘጋጀሁት ብሏል - የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር።
በኢትዮጵያ ሚዲያ ሴቶች በመረጃ ምንጭነት ያላቸው ቦታ ባለፉት አስር ዓመታት ከተሰራ የጥናት መረጃ ጋር ሲነጻጸር ምንም መሻሻል አለማሳየቱን የጠቆመው የማርች 2021 የFOJO-IMS የጾታ ውክልና ግምገማ ሪፖርት፤ የጋዜጠኞችን የዜና ምንጮች በማስፋትና በተለያዩ መስኮች የሚሰሩ የሴት ባለሙያዎችን ዳታቤዝ በመፍጠር ሴቶች በሚዲያው ያላቸው ውክልና ሊያድግ እንደሚችል ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
”Women Experts Directory” የምክረ ሃሳቡ ውጤት ነው ተብሏል ።
Published in
ህብረተሰብ