Sunday, 03 September 2023 21:17

“ወይ መቀደስ፣ ወይ መተኮስ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንኳን አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡- እንዴት ነህ፣ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምንም አልል አንድዬ! ይኸው መድረስ አይበለውና እዚህ ደርሰናል፡፡
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ የእናንተ ነገር እንደው ሲገርመኝ ይኑር ማለት ነው! ይኸው ደርሰሀል፣ አይደል እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ ልክ ነው፣ አንድዬ!
አንድዬ፡- ታዲያ መድረስ አይበለው ብሎ አነጋገር ምን ማለት ነው! የመድረስ ትንሽና ትልቅ አለው እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደሱ ለማለት ፈልጌ ሳይሆን እንደው ያለፍንበት መከራ ሁሉ…
አንድዬ፡- ቆየኝማ… እንኳን አደረሰህ፣ እንኳን አደረሰሽ ትባባሉ የለ እንዴ!!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ መች ይቀራል አንድዬ!
አንድዬ፡- ታዲያ መድረስ አይበለው ብሎ ተቀጥላ ምን አመጣው! ምስኪኑ ሀበሻ የእናንተ ችግራችሁ፣  ያለምንም ሀጢአታቸው መድረስ ያልቻሉ ብዙዎች መኖራቸውን ትረሳላችሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ እውነት ነው አንድዬ! ግን ምን መሰለህ…
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ፣ የሚመስለኝን እንተወውና እስቲ አስታውሰኝ፣ ባለፈው ጊዜ የሆነ ቃል ገብቼልህ ነበር እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ፣ ቀኑ ሲቃረብ ብቅ ብለህ እንኳን አደረሰህ በለኝና፣ ያኔ እንጨዋወታለን ብለኸኝ ነበር፡፡
አንድዬ፡- እኮ እንኳን አደረሰህ በለኛ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ! እንደሱ አይባልም፡፡ አንተ እኛን ታደርሰናለህ እንጂ…አንድዬ፣ እንደሱ ያልን ዕለትማ አንደኛውን ለይቶልናል ማለት ነው፡፡
አንድዬ፡- አንደኛውን ከለየላችሁማ ትንሽ ሰንበት አላችሁ እኮ፣ ምስኪኑ ሀበሻ! የእኔ የሚባለውን ስልጣን ሁሉ ወስዳችሁ፣ ወስዳችሁ እኮ ባዶዬን ልታደርጉኝ ምንም አልቀራችሁም፡፡ አሁንማ ጭራሽ ላቦራቶሪ ነው በምትሉት ሰው ለመፍጠር መከራችሁን እያያችሁ፣ እኔ እናንተኑ ላመስግን እንጂ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እሱ እኮ ሀጢአታችን ልክ አጥቶ የሚሠራንን እያሳጣን ስለሆነ ነው፡፡ ምን እላለሁ መሰለህ አንድዬ!...
አንድዬ፡- ምን ትላለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ… አሁን አዳምና ሔዋንን አስነስተሀቸው፣ እነዚህ የስልጣኔ ጫፍ ደረስን የሚሉት ጭራሽ ሴት፣ ወንድ የሚባል ነገር የለም የሚሉትን ነገር ቢሰሙ  ምን ይሉ ይሆን እላለሁ፡፡
አንድዬ፡- እኔም አላስነሳቸውም፣ እነሱም እሺ ብለው አይነሱልኝም፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ለምን አንድዬ! ለምን አይነሱልህም?
አንድዬ፡- እናንተው አበላሽታችሁ፣ እናንተው ጥለናት ካልሄድን ለምትሏት ዓለም ምን በወጣን ብለው ይነሳሉ? ይልቅ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እስቲ ስለ አዲሱ ዓመታችሁ እናውራ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ምን የሚወራ አለው፣ አንድዬ! ምን የሚወራ ነገር አለው!
አንድዬ፡- እኔ እኮ የእናንተ ነገር፡፡ በአንድ በኩል በመሸጋገራችሁ ደስ ብሏችሁ እንኳን አሸጋገረህ፣ እንኳን አሸጋገረሽ ትባባላላችሁ። ከተሸጋገራችሁ በኋላ ደግሞ አዲሱ ዓመት ምንም ነገር ይዞ የማይመጣ ይመስል ምን የሚወራ አለው ትላላችሁ፡፡ የእናንተ ነገር እኔን ግራ ማጋባቱን የሚያቆመው መቼ ይሆን!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! እኛ ራሳችን እኮ ግራ የተጋባን ስለሆንን ነው አንተን እንዲህ ግራ የምናጋባህ፡፡ ምን የሚወራ አለው ያልኩህ እኮ በቃ ነገሩን ሁሉ ስናየው፣ ጭጋግና ደመና እየመሰለን ነው፡፡
አንድዬ፡- ስለዚህ ደግ ነገር እንዳይመጣ ለማድረግ ከአሁኑ ራሳችሁን አሳምናችኋል ማለት ነው፡፡ ነው፣ ወይስ አሁንም እኔ ላይ ልታሳብቡ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- በጭራሽ አንድዬ! እኛ ባመጣነው መከራ ምን ቆርጦን  አንተ ላይ እናሳብባለን!
አንድዬ፡- አይ ምስኪኑ ሀበሻ፣ የእውነትም ምስኪን እኮ ነህ! ታች ስትሆኑ ሲላችሁ ምን አድርገንህ ነው ይህንን ሁሉ መከራ የምታበዛብን፣ ደግሞ ሲላችሁ ወይ ውረድ ወይ ፍረድ ትሉኛላችሁ፡፡ እዚህ ስትመጡ ደግሞ በአንተ አናሳብብም ትላላችሁ፡፡ እኔ ግራ ያልገባኝ ማን ግራ ይግባው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! ኸረ እኛኑ ለዘለዓለም ዓለሙ ግራ ግብት ይበለን!
አንድዬ፡- እና ለአዲሱ ዓመት ያሰብነው ነገር የለም እያልከኝ ነው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ምኑን እናስበው ብለህ ነው!
አንድዬ፡- አዲስ ዓመት ሲደርስ ሁልጊዜ እንዲህ አደርጋለሁ፣ እንደዛ እፈጽማለሁ ትሉ አልነበረም እንዴ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ በፊት ነበር አንድዬ፡፡ አሁን እኮ ማሰቢያ አእምሯችን ተዛነፈ መሰለኝ፣ እንኳን የነገውን የዕለቱን ማሰብ አቅቶናል፡፡
አንድዬ፡- ስለዚሀ  ጭራሹን አእምሮ የለንም እያልከኝ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ፤ ብዙዎቻችን እንዲሁ አካል ስለሆነ ጭንቅላታችንን ተሸክመነው እንዞራለን እንጂ ባዶ ነው፡፡
አንድዬ፡- ባዶ! ባዶ ነው ያልከው ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አዎ፣ አንድዬ፡፡ ባዶ ባይሆንማ ኖሮ ይህ ሁሉ መከራ ባልደረሰብን ነበር፡፡
አንድዬ፡- ባዶ ስትለኝ እኮ ልክ እኔ ረስቼው፣ ወይም ሆነ ብዬ ለሌላው የሰጠሁትን ማሰቢያ አእምሮ ለእኛ ከለከልከን ልትለኝ መስሎኝ ነው። 
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ እንደሱ አይደለም አንድዬ! በጭራሽ እንደሱ አይደለም፡፡ እኛ ራሳችን በሚሆነውም በማይሆነውም ክፋትና ተንኮል አጭቀነው ነው እንጂ አንተማ እንደማንም ማሰቢያ አእምሮ ሰጥተኸን ነበር፡፡
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ አንዳንድ ሃሳብ ባቀርብ ትፈቅድልኛለህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! ኸረ…
አንድዬ፡- በቃ፣ ፈቅደህልኛል ማለት ነው፡፡ መጀመሪያ ነገር ሁላችሁም ያለባችሁ አንድ ችግር ምን መሰለህ…ስለራሳችሁ ያላችሁ አመለካከት ልክ ነው ያጣው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ እሱማ…
አንድዬ፡- ቆይ አታቋርጠኝ፡፡ እናንተ በሁሉም ነገር ልክ ናችሁ፡፡ እናንተ በሁሉም ነገር ቅዱስ ናችሁ፡፡ ሌላው ሁሉ የእናንተን ያህል ማሰብ አይችል ይመስል፣ ሌላው ሁሉ እንደናንተ በእኔ አምሳል ያልተፈጠረ ይመስል እኔ፣ እኔ፣ እኔ ብቻ! እኛ፣ እኛ፣ እኛ ብቻ! የእናንተ ነገር እኮ ጉድ ከመባል ያለፈ ነው! በእናንተ ቤት እኮ እናንተ ብቻ ምንም የምትሳሳቱት፣ ምንም የምታበላሹት፣ ምንም የምታቃውሱት ነገር የለም! ሌላውን ማንቋሸሽ፣ ሌላውን አሳንሶ ለማሳየት መሞከር፣ ሌላውን ምን የነካው እንጨት የምትሉትን ማድረግ! ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አቤት አንድዬ!
አንድዬ፡- አስተያየት ሳትሰጥ ዝም ብለህ ትሰማኛለህ እንዴ?!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ ጣልቃ አትግባ ስላልከኝ እኮ ነው፡፡
አንድዬ፡- ጣልቃ መግባት ስላልከው… እንደናንተ ሁሉም ነገር ውስጥ ጣልቃ ካልገባን የሚል አለ እንዴ!  ሁልህም እኮ እውነተኛ ራስህን አውቀህ፣ ሁልህም ችሎታህንና ልትሄድ የምትችልበትን እርቀት  አይተህ በየችሎታህ፣ በየእውቀትህ ብትሠራ ኖሮ፣ አሁን የዓለም መዛባበቻ ባልሆናችሁ ነበር!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እሱማ አንድዬ…
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እንደ ድሮው ዓለም ይወደናል፣ ዓለም ያደንቀናል የምትሉትን ነገር  ተዉኝማ፡፡ አሁንም እንደዛ አይነት ነገሮች ስትናገሩ ስሰማ ግርም ይለኛል፡፡ ድሮ’ኮ እናንተ ስትዘባበቱባቸው የነበሩት የአፍሪካ ሀገራት ዛሬ በተራቸው እየተዘባበቱባችሁ ነው! ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ…
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እየሰማሁ ነው አንድዬ!
አንድዬ፡- እንደው እስቲ ካላችሁ ዞር፣ ዞር ብላችሁ፣ ወይም በየጽሑፉ ላይ  መልከትከት አድርጉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደእናንተ መላቅጡ የጠፋበት የሚመስል ስንት ሀገር አለ፡፡ እነሱም፣ ለይቶላቸው፣ ለእኔም አስቸግረው ሲታኮሱ ውለው ሲታኮሱ የሚያድሩትን አይነት ማለቴ አይደለም፡፡ ሌሎቹ ትናንት ፍራሽ አንጥፋችሁ ሙሾ ልታወርዱላቸው ምንም ያልቀራቸው እኮ ቢያንስ፣ ቢያንስ የእናንተን ያህል መላቅጡ አልጠፋቸውም፡፡ እየሰማኸኝ ነው ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አዎ አንድዬ! በደንብ እየሰማሁ ነው፡፡
አንድዬ፡- ስማኝ በባዶ ሜዳ፣ በተራቆተ ማሳ፣ ወና በሆነ ጓዳ ራሳችሁን ከፍ፣ ከፍ የምታደርጉትን ነገር አንተው አላችሁ! እናንተ ብዙ ሀብትና ንብረት ስላላችሁ፣ እናንተ ብዙ እውቀት ስላላችሁ ወይም አላችሁ ስለሚባል፣ እናንተ ብዙ ስልጣን ስላላችሁ ከእኔ ዘንድ ከሌላው የተለየ አትኩሮት እናገኛለን ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ ገንዘብና ንብረትህም፣ እውቀትህም፣ ስልጣንህም ብን ብሎ ነው የሚጠፋው፡፡ በእውቀትህ፣ በስልጣንህ፣ በገንዘብህ፣ በአምቻ ጋብቻህ አልመዝንህም፡፡ አሰለቸሁህ ምስኪኑ ሀበሻ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡-  ኸረ በጭራሽ!
አንድዬ፡-  ስማኝ  ለእኔ ስለጠመጠምክ ብቻ እውነተኛ ቄስ አይደለህም፡፡ መድረክ ላይ ወዲህ፣ ወዲያ ስለተውገረገርህ ብቻ እውነተኛ የሃይማኖት ሰባኪ አይደለህም። ሺዎችን አስለቅስህ ባገኘኸው ገንዘብ በእኔ ወይም በመላእክቶቼ ስም ዝክር ስላደረግህ ብቻ እውነተኛ ለጋስ አይደለህም፡፡ እና ዋሸሁ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡-  በጭራሽ አንድዬ! ግን እኮ አንድዬ! እኛም እኮ ጸሎታችንን ሳትሰማን ስትቀር…
አንድዬ፡- ቆየኝማ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡ እናንተ እኮ እየጸለያችሁ አይደለም፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ! በደንብ እየጸለይን ነው፡፡
አንድዬ፡- ስማኝ፣ ብዙዎቻችሁ እየጸለያችሁ ሳይሆን ምንም የማላውቅ ይመስል ልታሞኙኝ ወይም በእናንተ ቋንቋ ልታጭበረብሩኝ እየሞከራችሁ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- አንድዬ! ዛሬ በጣም ተቆጥተሀል፡፡
አንድዬ፡- እየው እንግዲሀ ዝም ስል ዝም አልከን፣ ስናገር ደግሞ ተቆጣኸን!
ምስኪኑ ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ! ይቅርታ…
አንድዬ፡- እና ብዙዎቻችሁ ከልባችሁ እየጸለያችሁ ሳይሆን ልታጭበረብሩኝ እየሞከራችሁ ነው እያልኩህ ነው፡፡ ሌሊት ራቁታችሁን ስትደንሱ አድራችሁ ማለዳ ተከናንባችሁ የምትመጡ ናችሁ እኮ! በአደባባይ ሰላም፣ ሰላም እያላችሁ በየጓዳችሁ ፍለጠው፣ ቁረጠው የምትሉ ናችሁ እኮ! ሰው ሲያይ ተሳስማችሁ ሰው ሳያይ በጥርስ ካልተዘነጣጠልን የምትሉ ናችሁ እኮ!  በአደባባይ ተሳስማችሁ በየጓዳችሁ በጥርስ ካልተዘላዘልን የምትሉ ናችሁ እኮ! ይልቅ ምስኪኑ ሀበሻ ስማኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡- እየሰማሁ ነው፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- የምሰጣችሁ ምክር አንድ ብቻ ነው፡፡ ወይ መቀደስ፣ ወይ መተኮስ! ነገሩን ሁሉ እያደበላለቃችሁ መከራችሁን አታራዝሙት፡፡ በል መልካም በዓል ይሁንላችሁ፡፡
አንድዬ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1211 times