በቅርቡ በደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ ተዘጋጅቶ ‹‹የአማርኛ ‹ጥበበ-ቃላት› ቅኝት›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን በቀረበው መጽሐፍ፤ ለመጻሕፍት ሕትመት መበራከት አስተዋጽኦ ያደረጉ ሀገራዊ ክስተቶች ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መሐል፤ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ተቀልብሶ በ1933 ዓ.ም ነጻነት መመለሱ፤ የ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ሙከራ … የመሳሰሉት ዘመናት በማሳያነት ቀርበዋል፡፡
ከመጻሕፍት ዝግጅት፣ ሕትመትና ስርጭት ጋር በተያያዘ ይህ እውነታ እስከዛሬም መዝለቁ ይታያል፡፡ በ1983 ዓ.ም ደርግ በኢሕአዴግ ከተለወጠ በኋላ የተከሰቱ አንኳር ጉዳዮችን ማዕከል በማድረግ ብዙ መጻሕፍት ታትመዋል። ስልጣን በያዙና በተቃዋሚ ኃይሎች፣ በአሸናፊና ተሸናፊ ወገን ደጋፊዎች፣ ለእስር በተዳረጉ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች፣ በባድመ ጦርነት መቀስቀስ፣ ምርጫ 97ትን ርዕስ ባደረጉ ጉዳዮች፣ ‹‹መደመር››ን ርዕዮተ ዓለም ለማድረግ ከመጣው ‹‹ትውልድ››፣ ህወሓት ‹‹ወደ ቀፎው›› መመለሱና መሰል ታሪኮች የተከናወኑባቸው ዘመናትን ማዕከል በማድረግ ተዘጋጅተው ለሕዝብ የተሰራጩ መጻሕፍት ቁጥር ቀላል አይደሉም፡፡
‹‹የዓለም ፍጻሜ›› ደረሰ ይሆን ? የሚያሰኝ ስሜት ፈጥሮ የነበረው የኮሮና (ኮቪድ-19) መከሰትም ለመጻሕፍት ዝግጅትና ሕትመት አስተዋጽኦ ማድረጉን ካመለከቱን መሐል የፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‹‹ኅብር ሕይወቴ›› መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡ ግለ-ሕይወት ታሪኬን አዘጋጅቶ የማሳተም የቆየ እቅድ ነበረኝ የሚሉት ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፤ እቅዳቸው ለመፍጠኑ የወረርሽኙ መከሰት አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥተዋል፡-
‹‹…በ2012 ዓ.ም ኮቪድ 19 ዓለምን ቀስፎ ሲይዝ፤ በየቤቱ መክተት ሕይወትን መጠበቂያ ዋነኛው አማራጭ ሆነ፡፡ ጊዜም ተትረፈረፈ፡፡ በዚያን ወቅት ነው እንግዲህ የዚህን ግለ ታሪክን አብዛኛውን ክፍል ለመጻፍ የበቃሁት›› ብለዋል።
‹‹ኅብረ ሕይወቴ››፤ ባለታሪኩ ከቁንጮነት ተነስተው በአፍሮነት በኩል አልፈው ለበራነት የደረሱበትን ‹‹አካዳሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ›› ሕይወት በጥልቀትና በስፋት የሚያስቃኝ መጽሐፍ ነው፡፡ በሽፋን ስዕሉ ላይ ከግራ ወደ ቀኝ በቀጥታ መስመር ጎን ለጎን የሚጓዙት ሁለት ገመዶች፣ መሐል ሲደርሱ ቀለል ያለ ቋጠሮ ፈጥረው በመጡበት መልክ ወደ ቀኝ ተዘርግተዋል፡፡ ገመዱም በሦስት የቃጫ ሽርብ የተሠራ ነው፡፡ ከታች ተነስተው ወደ ላይ (ከግራ ወደ ቀኝ) የተሰደሩት የባለታሪኩ የሕይወት ጉዞ አመልካች ሦስት ፎቶዎች እርስ በእርስ በገመድ እንዲያያዙ ተደርጓል፡፡
ከገመዱና ከፎቶዎቹ በስተጀርባ የሚታየው መልክአ-ምድር በክረምት ጭጋጋማ አየር ምክንያት ሜዳ፣ ተራራ፣ ሸንተረርን አደብዝዟቸው አይታዩም፡፡ በጠቆረው ሰማይ ላይ ጎልቶ ለመታየት የፈራ የሚመስል ቀስተ ደመና ከግራ ወደ ቀኝ ተዘርግቷል፡፡ ዓይናፋሩ ቀስተ ደመና፤ ልታይ ልታይ የማይሉ የሀገሪቷን ልጆች እንዲወክል ታስቦበትና ይሁነኝ ተብሎ ወይም ተፈጥሮም የራሱን አስተዋጽኦ አድርጎ የተቀናበረ ይመስላል፡፡
የጀርባው ገጽታ (ባክግራውንዱ) መደብዘዝ፣ የባለታሪኩን ኅብር ሕይወት እንዲገልጹ የታሰቡት ገመድና ፎቶዎች ጎልተው እንዲታዩ አድርጓል፡፡ የመጽሐፉ ርዕስና የባለታሪኩ ስም ደምቀው እንዲታይ በተደረገው መጠን፣ የሕይወት ዘመን ጉዞን እንዲያመለክቱ የተጻፉት (አካዳሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ) ቃላት እንዲጎሉ ያልተደረገው ታስቦበት ነው የሚመስለው፡፡ ቃላቱ በገጹ ላይ ደምቀው እንዲታዩ ካልተፈለገ ‹‹ቢቀሩስ ምን ያጎድሉ ነበር ?›› የሚል ጠያቂ ቢመጣ፤ በገመዱ ግራና ቀኝ በቀጥታ መስመር ላይ ከተጻፉት ሁለት ቃላት ይልቅ፣ በቋጠሮው ላይ የሰፈረው ቃል፣ የባለታሪኩን ከባድ የሕይወት ጉዞና ዘመን እንዲያሳይ የተፈለገም ይመስላል፡፡
ሦስቱ የባለታሪኩ ፎቶዎች የሕይወት ዘመን ጉዞን እንዲያመለክቱ ብቻ የቀረቡ አይመስልም። የሕፃንነት ዘመኑ ፎቶ፣ መነሻን አመልካች ነው፤ ነጭ ጠመኔ (ቾክ) ሊቀበል ዝግጁ የሆነን ጥቁር ሰሌዳን ያስታውሳል፡፡ ጥቁር ሰሌዳው ላይ ወላጆች፣ ቤተ ዘመድ፣ ጎረቤቶች፣ ጓደኞች፣ መመምህራን፣ የስራ ባልደረቦች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ መሪዎች … የሚፈልጉትን ለመጻፍ ዕድል አግኝተዋል፡፡ የ‹‹ኅብር ሕይወቴ›› ታሪክ መፍሰስ የጀመረውም ከልጅነት ትዝታና ትውስታ በመነሳት ነው፡፡ የልጅነት ፎቶው፣ ብዙ ልጆችና ትውልዶችን ይወክላል፡፡ በሀገራችን ልጆችና ትውልዱ፣ በክፉና ደግ ብዙ አይተዋል፤ ብዙም አሳልፈዋል፡፡
በተቋጠረው ገመድ መሐል ላይ ያለው የባለታሪኩ ፎቶ የአንድ ትውልድ፣ አንድ ልዩና የተለየ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል የታሪክ ዘመንን ያስታውሳል፡፡ በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ወደ ሀገራችን የገባው ዘመናዊ ትምህርት፤ መድረስ የሚጠበቅበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ፤ ወደ ኋላ የተንሸራተተበትና ለዛሬ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ሕመማችን መነሻ የሆነበትን ወቅት እንድናስታውስ ይጋብዛል፡፡ ፕሮፌሰር ባሕሩ የውጭ ሀገር ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው በተመለሱ ማግስት ለእስር የተዳረጉበት ታሪክ ለዚህ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡
ሦስተኛው ፎቶ እንደ ቀዳሚዎቹ ሁለት ፎቶዎች በዝምታ የታጀበ አይደለም፡፡ የባለታሪኩ የተመጠነ ፈገግታ ለተመልካቹ የሚያስተላልፈው ብርታት፣ ፍቅር፣ ቆራጥነትና ተስፋ አለ፡፡ ስለ ትላንት የሚነግሩን፣ ነገ መከተል ያለብንን አዎንታዊ አቅጣጫ የሚያመላክቱን፣ በጥረትና ስኬታቸው አርአያ ሆነው ሊታዩ የሚችሉ፣ ሀገርና ትውልዱን የሚያስተምሩ … ዛሬም ሰዎች አሉን የሚል ስሜት ይፈጥራል። የመጽሐፉ የፊት ለፊት ገጽ ሽፋን ታስቦበት የተዘጋጀ ድንቅ ስራ ነው፡፡ ከመጽሐፉ ሽፋን ገጽ ወደ ውስጥ ሲዘለቅም ይኸው እውነታ ጎልቶና ፈክቶ ይታያል፡፡
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‹‹ባለ አእምሮ›› እና ለዕውቀት የተፈጠሩ ስለመሆናቸው በመጽሐፉ ጥቂት የማይባሉ ማሳያዎች ቀርበዋል፡፡ ባለታሪኩ ከብላቴናነት ዘመናቸው አንስቶ ‹‹ለገበሬ ዕውቀት›› የሰጡት ክብርና ዕውቅና አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በልጅነታቸው ከአያታቸው የተማሩትን አንድ ታሪክ በዚህ መልኩ አቅርበውታል፡፡
‹--በተለይ የማልረሳው ሰማዩ ደመና ጨልሞ፣ መብረቅ ሲያብለጨለጭ፣ ነጎድጓድ ሲያስገመግም እኛ የከተሜ ልጆች ዝናብ ሊመጣ ነው ብለን ስንሰጋ፤ እርሱ (አያታቸው) ሰማዩን ቀና ብሎ ያይና በተረጋጋ መንፈስ ‹‹አይዘንብም፣ ወደ አጠበላ ሄዷል›› ይለናል፡፡ አጠበላ ማለት ከበበሲ በስተምዕራብ የሚገኘው የገጃ ክፍል ነው፡፡ እንዳለውም ሳይዘንብ ይቀራል፡፡ ይህ የአየር ትንበያ ለረጅም ጊዜ አብሮን ኖሮ አዲስ አበባም ሆነን ዝናብ ለመዝነብ ሲከጅል ‹‹አይ አይዘንብም፤ ወደ አጠበላ ሄዷል›› ማለት ለምዶብን ነበር፡፡›
ፕሮፌሰር ባሕሩ እንደዘመናቸው ልጆች በቄስ ትምህርት ቤት በኩል ነበር ከዕውቀት ጋር መገናኘት የጀመሩት፡፡ በዚያ ዘመን ክፉኛ ታመው ቤት ለመዋል ሲገደዱ፣ ጓደኞቼ ሊቀድሙኝ ነው የሚል ስጋት አድሮባቸው፣ ለሊት ተነስተው በኩራዝ ዳዊታቸውን ገልጠው በማንበብ ላይ እያሉ፣ ቁንጯቸው በእሳት ተያይዞ ሽታው የተኙት ቤተሰቦቻቸውን ለመቀስቀስ ምክንያት መሆኑን ይነግሩናል፡፡
በቄስ ትምህርት ቤት በኩል አልፈው ወደ አስኳላ ከዘለቁ በኋላ በልዑል መኮንን (አሁን አዲስ ከተማ) ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህራቸው የነበሩት ሚስተር ግርሃም ታየር፣ ‹‹ባሕሩ ወደ ፊት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን አትገረሙ›› ብለው አድናቆት የሰጡበት ምስክርነትና ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ የእጅ ሰዓቱን ሊሸልማቸው የበቃበት ታሪክ፣ ‹‹ባለ አእምሮ›› ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ የተደነቁበት ክስተት ነበር፡፡
መርካቶ ውስጥ ሲኒማ ራስ ፊት ለፊት መድኃኔዓለም መድኃኒት ቤት ነበር የሚሉን ፕሮፊሰር ባሕሩ ዘውዱ፤ ወደዚያ ፋርማሲ አዘወትሮ ይሄድ ከነበረው አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሰዓት ስለተሸለሙበት አጋጣሚ ምስክርነታቸውን በዚህ መልኩ አኑረዋል፡፡ ‹‹ስመ ጥሩው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ እዚያ ብዙ ጊዜ ለመጨዋወት ይመጣ ነበር፡፡ ስለኔ ጎበዝ ተማሪ መሆንም ይነግሩታል፡፡ አንድ ቀን ይህን ስጡት ብሎ›› ሮመር የእጅ ሰዓት እንደሸለማቸው ይነግሩናል፡፡
የልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪ እያሉ አዘወትረው ይሄዱበት የነበረው መድኃኔዓለም መድኃኒት ቤት፣ ከበስተጀርባው 5 ወጣቶች ለማንበቢያነት እንዲጠቀሙበት በተመደበ ክፍል ‹‹የድርሰት ክበብ›› አቋቁመው እንደነበር ሲናገሩ፤
‹‹…የድርሰቱ ቋንቋ እንግሊዝኛ ሲሆን፤ ተዋናዮቹ ፍስሃ ዘውዴ፣ በጋሻው ዘለቀ፣ ጌታቸው ሚናስ፣ እኔና አስተናጋጃችን ጌታቸው ዋቅጅራ ነበርን፡፡ ቦታዋ የጌታቸው ወንድም የአቶ ኃይሌ አምቢሳ ንብረት የሆነውና ሲኒማ ራስ ፊት ለፊት የሚገኘው መድኃኔዓለም መድኃኒት ቤት ጓሮ ለጌታቸው የተሰጠች ክፍል ነበረች፡፡ በየሳምንቱ ተራ በተራ ድርሰት እየጻፍን እየመጣን እዚያች ትንሽ ክፍል ውስጥ እያነበብን፣ ሐሳብ እንለዋወጣለን፡፡ ደረቅ ውይይት እንዳይሆንም ጌታቸው በአቅራቢያው ካለው ሻይ ቤት በራድ ሻይና ፈታ ወይ ፉል ያዝልናል፡፡››
በተለያየ ጊዜና ቦታ በፍላጎት እየተሰባሰቡ፣ ‹‹የንባብ ክበባት›› በማቋቋም የሚታወቁ ባለታሪኮች አሉ፡፡ በ1980ዎቹ መጀመሪያ መሳለሚያ አካባቢ ይገኝ በነበረው ህሩይ ሚናስ ቤት፤ እነ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ ስዩም ተፈራ … የመሳሰሉት የስነ ጸሑፍ ሰዎች አቋቁመውት የነበረው ‹‹የንባብ ክበብ››፣ ዝናው ከትላንት አልፎም እስከዛሬ የሚነገርለት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ በ‹‹ኅብር ሕይወት›› መጽሐፋቸው ስለ ‹‹የድርሰት ክበብ›› የሰጡት መረጃ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ፋይዳው ቀላል አይሆንም፡፡
ንባቡ ‹‹ደረቅ›› እንዳይሆን ለወጣቶቹ በራድ ሻይ፣ ፉልና ፈታ ያቀርብ የነበረው ሻይ ቤት፣ መርካቶ ውስጥ ተመሳሳይ አገልግሎቱን እየሰጠ እስከ ዛሬ መዝለቅ ችሏል፡፡ በትንሽዬ የሻይ ማቅረቢያ ብረት ጀበና፣ ከትናንሽ ብርጭቆዎች ጋር በትሪ ይቀርብ የነበረው ‹‹በራድ ሻይ›› ግን እንደ መድኃኔዓለም መድኃኒት ቤት ታሪክ ሆኗል፡፡ ሻይ ቤቱ ከ60 ዓመት በፊት መሐመድ ሳላህ በተባሉ ነጋዴ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ነው፡፡
የፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የሕይወት፣ የትምህርትና የስራ ታሪክ የተሰነደበት መጽሐፍ፤ ግለሰባዊ፣ ሕዝባዊ፣ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ የሆኑ፤ በርካታ ጉዳዮች ተካተውበታል፡፡ መርካቶ ውስጥ የዕድር አመሠራረት ታሪክ ምን እንደሚመስል፣ ጥምቀትና በመሳሰሉት የበዓል ወቅቶች ‹‹መንፈስ ወርዶባቸው›› ልዩ ልዩ ተግባር በመፈጸም ይታወቁ ስለነበሩት ‹‹አዶ ከበሬ››ዎች ሁለት ሰብዕና፣ ከአስፋወሰን ሆቴል ይወጣ የነበረ ‹‹ተረፈ ማዕድ›› ችግረኞችን ለመርዳት ስለነበረው ሚና፣ በ1933 ዓ.ም ከእንግሊዞች ጋር ወደ አዲስ አበባ የገቡ የሱዳን ወታደሮች በአዲስ አበባ አበባ ልጃገረዶችን እየተተናኮሱ ስለማስቸገራቸው ተተርኳል፡፡
በ1953 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግስት የተሳተፉ ከሞቱ በኋላ አስከሬናቸው በመንገድ ተጥሎ ሕዝብ ይመለከተው እንደነበር፣ የ1966 ዓ.ም የወሎ ርሀብ ምን እንደሚመስል ፎቶግራፉ በዩኒቨርስቲ ግቢ ከተለጠፈ በኋላ ስለተፈጠረው ተቃውሞ፣ ጥላሁን ግዛው ስለተገደለበት ሁኔታ፣ ለአድዋ ድል መታሰቢያ ለማኖር ስለተደረጉ የተለያዩ ጥረቶች፣ የጽሕፈት ሚኒስቴርን ሰነድ ከጥፋት እንዴት ማዳን እንደተቻለ፣ የደርግ ዘመን አብቅቶ ኢሕአዴግ በሚተካበት ዋዜማ፣ ግንቦት 19 ‹‹የሰላምና እርቅ ኮሚቴ›› በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እየመከረ እንደነበር … እና መሰል ብዙ መረጃዎችን የሚያቀብል መጽሐፍ ነው፡፡
በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም ፖለቲከኞች አራት ኪሎ ቤተ መንግስትን ማዕከል አድርገው አንዱ ለመግባት ሌላው ላለመውጣት ሲፋለሙ በነበረበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‹‹መቀመጫውን ወደ ናይሮቢ አዙሮ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ሳይፋለሱ ማካሄድ ችሎ ነበር›› የሚልና ሌሎች ብዙ ያልተነገሩና ያልተሰሙ አስደማሚ ታሪኮችን የያዘው መጽሐፍ፤ ‹‹ፕሮፌሰር እንኳንም ታሪክዎን ጻፉልን›› የሚያስብል ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡
Sunday, 03 September 2023 21:22
የፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‹ኅ‹ ብር ሕይወቴ››
Written by ብርሃኑ ሰሙ
Published in
ጥበብ