Sunday, 03 September 2023 21:23

ተብከንካኝነት በ‹‹ቤባንያ››

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(5 votes)

‹‹የሰው ነፍስ ለሁሉም ነገር ፍቺ ለመስጠት አትሰንፍም፤›› (ገጽ 204)

እንደ_መነሻ፣
ሥነ-ጽሑፍ ማኅበረሰባዊ ዕድፍ ወ ጉድንፍን እንዲከረድድ የተደነገገ ገራገር ሕገ-ደንብ አለ፤ ዓለማየሁ ገላጋይ በተብከንካኝ ብዕሩ ያልከተበው ማኅበረሰባዊ ሕጸጻችን እምብዛም ነው። ክታቦቹ ተባራሪ አረር ቢነዙብንም ልባዊ መሻቱ (የደራሲው) በሰብዕና የበለጸገ ማንነት እንድንይዝ ኖሯል። ከዚህ በዘለለ፣ ዓለማየሁ ገላጋይ ከማኅበረሰብ፣ ከፈጣሪ፣ ከእራሱ… ወዘተ. ጋር አተካራ ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል። የነጻ ተፈጥሮ ጥያቄ፣ ዕጣ-ፈንታ፣ ሰብዕና፣ መፍጠር ብሎም መፈጠር… ማዕከሎቹ ሆነው ከርመዋል። ያልተመረመረ ሕይወት እርባና ቢስ ነው እንዲል ሶቅራጠስ (አሃ! አማርኛ ዘልቆት?)፣ የዓለማየሁ ገላጋይ ገጸ-ባሕርያት አተካራ የሚገጥሙ፣ የሚሞግቱ፣ ፈጨርጫሮች፣ ተግለብላቢዎች፣ ሽመል የሚማዘዙ ናቸው፤ ደራሲው በግል ሕይወቱም መጠየቅ እንደሚቀናው ዕሙን ነው፤
እንሆ ዛሬም የዓለማየሁ ገላጋይን ማለፊያ መገመት ነፋስን እንደመግራት ሆኖ አገኘሁት….
….ውርክብ!...
….መዝግቡልኝ….
….በምናብ የኖረች ሀገር እያስተዋወቀን ነውን! ሌጣ ምናብ ነው ብዬ እንዳልደመድም ወዲህ እንደ ውሃ እያሳሳቀ፣ እያወበራ አሰጠመኝ! በእርግጥ ‹‹ሆሴዕ›› በገጽ (196) ‹‹ከመቅፀፍታችሁ አይደለሁም! ከመጨራረሳችሁ አልቋደስም!›› እንዲል፣ በበኩሌ የአሁኗን በቁሟ ናዋዥ፣ እየሄደች ተካዥ አገሬን አልፈልግም። መጨራረስና መቅሰፍታችሁ በመቁነናችሁ ይቁነን!
ከድርሰቱ ተነስተን ጉዳዩ እውናዊነት የተጫነው ምናብ ነው ብንል፣ ከመጠነኛ መቀያየም የከፋ ነገር አይከተልም፤ ለዚህ ምክንያቴ አሁናዊዋ ኢትዮጵያ - የድርሰቱ መቼት ሸኖ እንድትሆን መገርገር አይከፋም የሚል ነው!  
ጉዳዩ ‹‹Too many cook spoil the broth›› ነውና ስለምን ይኼን ያክል ቀላመድኩ?....
….ወደ አሁኔ ልስከንተር….
….‹‹ቤባንያ›› እንደ መቀርቀሪያ አንዴ ወደ ትውፊታዊነት ንፍቀ-ክበብ፣ ሌላ ጊዜ ወደ ድኅረ-ዘመናዊነት ጎሬ የሚሽከረከር ድርሰት ነው፤ ንሱ! በድርሰቱ ገላ የተስተዋሉ ነጥቦችን በጥቂቱ እንገርምም፡-
ነገረ-ማሕበረ-ባሕል
(Socio-Anthropological aspects)
አስቀድሜ እንዳልኩት፣ ደራሲው የዘመመን ለማቅናት ሲድህ እናስተውላለን- በዚህ ድርሰት፤ ለዚህ መዋጮ እንዲገብርለት ትውፊታዊ ወደ ሆነው ጉዳይ ይዶላል - ትረካውን! ጣዕር እና ጋዕር ትራስጌዋ የመሸገባትን ሀገር ከሞቷ ለመመንተፍ ሀገር-በቀል ዕምነት ያለውን ሚና ሹክ እንደማለት ዓይነት ይትባሃል - በ‹‹ጋሽ ይማም›› በኩል አውሊያ ይለማመናል። ሐድራው እና ዝየራው ይደራል -  ‹‹ጋሽ ይማም›› ቤት፤ ለዘማማው-ቅናት፣ ከዳፍነት-ነዳፊ፣ ከሌሊት መንታፊ…. ጸሎት ይይዛሉ!
‹‹ናፈቀኝ ሀገሬ፣ ጎራው ሸንተረሩ፤
ፍየልና በጉ፣ ደጉ ሳይቀር ክፉ፤
ሰዎች አለቁ አሉኝ፣
እንደምነው ዛፉ፤›› ይሉናል፡፡
ከዕምነት ባለፈ ሥነ-ጽሑፋዊ (ሥነ-ቃላዊ) ፋይዳ እንዳለው እንረዳለን። ተመልከት! ዕምነቶቻችን እንኳን ለሰው ለዛፉም ለወፉም ይሳሳሉ፤ ዛፍ ፍሬ ይሰጣታል፤ የሕይወትም አምሳል ነው!
በዚህ ረገድ ሥዩም መርጋ የተባለ አጥኚ (ባልደረባዬ ነው) ‹‹An Archaeological Survey Of Islamic Shrines In Jimma Zone, South Western Ethiopia፣ 2012›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ጥናት፤ የዝየራን መልካም ገጽ እንዲህ ሲል ቃኝቷል፡- ‹‹the pilgrimage is conducted during the major Muslim festivals, the Arafa (idal-Adha), the Mawlid (Mawlid an-Nabi), and the Mi’raj. In addition to this, on the Thursday night people also gathered for religious program known as hadara. This is regularly held religious gathering with the specific purpose for reciting litanies. The Miracles of Abba Arabu is also narrated at locally held weekly gatherings where followers alternated between chewing chat (Catha edulis) and giving supplication (du’a). During the annual festivals, said the informants, 20,000-30,000 pilgrims come to the shrine of Abba Arabu from different parts of Jimma zone and the surrounding zones such as Silte and Illubabor zones. Reasons for conducting the pilgrimage to Abba Arabu shrine are diverse. Some pilgrims go to Abba Arabu’s cult to fulfil their votive offerings (nazri), and others go to the shrine because they have troubles of their own, often personal illness or the illness of a close relative. They have in common their reverence or love for Abba Arabu. The pilgrims mostly arrive at the site a day before the annual celebration.››
በገጽ 31 ላይ በ‹‹ኮርማ ብሩ›› ሥም የተጣላ ይታረቃል፣ የካደ ያምናል….ወዘተ.
ከዚህ በዘለለ፣ ከባንክና ከገንዘብ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የወደቀውን የሰው ልጅ ዕሴት በሚገባ የሚቃኝ ድርሰት ሆኖ ተገኝቷል።
ነገረ-ሐያሲነት
ዓለማየሁ ገላጋይ በዚህ ድርሰት የማሔስ፣ የሐያሲነት ነገር እንደሚገደው አስተውዬአለሁ። ከዚህ ድርሰት ውጭ በሐያሲነቱ ቅያሜ ባይኖረኝም፣ ይበልጥ ቀልቤን ሊስብ ችሏል። ‹‹መፍትሔ›› ‹‹ጅል›› የተሰኘ ተቀጺላው እንዲፋቅ ያስቻለውን ጀብድ ሲፈጽም እናያለን - በሒስ ደረጃ ፈታኙን የግጥም ትንታኔ ሲያደርግ - በገጽ 52 ላይ ‹‹ቤባንያ›› ‹‹…ዋናው ነጥብ እንዳልከው የመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞች ላይ ነው ያለው›› ትለዋለች ለ‹‹መፍትሔ››።
ዓለማየሁ ገላጋይ በቆረቆረው ገጸ-ባሕርይ ታግዞ የከበደ ሚካኤልን ግጥሞች ያብራራል፤ ከገጽ 53 ላይ ‹‹የከበደ ሚካኤልን ግጥሞች የነቃሁበት መሰለኝ። ዓይኔን ጨፍኜ አውቶቡስ እንደተሳፈረ ሁሉ ብዙ የግጥም ፌርማታዎችን አልፍና ድንገት መውረጃዬ ሲደርስ ይታወቀኛል። ብዙ ጊዜ ግጥሙ ሲጀምር በማስረጃ ይሆንና መጨረሻ ላይ የተፈለገው ምክር ይመጣል።›› ይለናል፤ ይኼ አባባል ከበደ ሚካኤል እንደማይቀኙ፣ ይልቅ እንደ ሚመክሩና እንደሚዘክሩ የሚናገር እንደሆነ ዕሙን ነው።
በገጽ 153 ላይ በዲያሎግ አስታኮ ስለ ጎርኪ መጻሕፍቶች እና በ‹‹ኞኞ›› ስለተተረጎመው መጻሕፍ አንድነት እና ልዩነት ይተነትናል፤ ይነግረናል።
ነገረ-ደራሲ
‹‹ቤባንያ›› ስለ ድርሰት ህይወት እና ስለ ደራሲነት ትርጉም የሚሰጡ ትረካዎች የታጨቀበት ድርሰት ነው፤ የደራሲን ፈታኝ ህይወት ይነግረናል፤ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ሊበለጽግ ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ አርአያ የሆነ ደራሲዎችን ሥራ (በድርሰቱ ገላ ውስጥ በተለያዩ ዐውዶች ሥር - ለምሳሌ ገጸ-ባሕርያቱ የሚጠቅሱዋቸው ደራሲያንና ጸሐፊዎች) ታላላቅ ደራሲያንን በመዘከርና በዓለም-አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነትን ያተረፉ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎችን በእኛ አገር ቋንቋ ተርጉሞ በመሰነድ እንደሆነ ይነግረናል።
ድርሰቱን የትርጉም መጻሕፍት በምን መልኩ መተርጎም እንዳለባቸው መንገድ የሚጠቁም ሆኖ አገኘሁት፤ ብሎም የትርጉም ሥራ ድካም አውስቷል (ገጽ 153)።
ነገረ-ሥነ-ልቡና
ዋናው ገጸ-ባሕርይ ፌዝ የሚመስሉ አንኳር-አንኳር ምክረ-ሀሳቦችን ያነሳል፤ ሥነ-ልቡና ላይ ማዕከል ያደረጉ ነጥቦች በቧልት መልክ ተሰንዝረዋል። ማሳያ በገጽ 38 ለነባር ከተሞች ዕቃ-በዕቃ ልውውጥ እንጂ በገንዘብ መገበያየት የሞራል ዝቅጠት ውስጥ እንደሚከት ይነግረናል።
ስለ ባንከሮች አለባበስ ይነግረናል፤ የባንከሮች አለባበስ የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ አለባበስ መምሰል እንዳለበት እያፌዘ ይተርካል፤ ውጤቱንም ጭምር ነው ግና።  
ነገረ-አላዝቤ
ዓለማየሁ ገላጋይ የአርባ ቀን ዕድሉ ጨዋታ አዋቂ አድርጎታል። በዚህ ድርሰትም ከራራ ጉዳይ እያወሳን ማለዘብን እንደተካነ መስክሯል፤ በጭንቀት ውስጥ ሳቅ መፍጠርን ያውቅበታል፤ በዕውቀቱ ሥዩም፡-
‹‹ላባ ላረጉልን፣ የሕይወትን ሸክም፤
በቸከ ዘመን ላይ፣ ቀልደው ላሳቁን፤
ቺርስ!›› ይለናል!
በ‹‹ቤባንያ›› ድርሰት ገላ ውስጥ ከሳቡኝ ሐረጋት፣ ዓረፍተ-ነገሮችና አንቀጾች ጥቂቶቹን ልበል….
‹‹ለሸኖ የምመኝላትን ያሸበረቀ ጥንታዊነት ሆሴዕ ያሟላ መስሎ ተሰማኝ፤›› (ገጽ 9)
‹‹ስሜቴ ጠየመ›› (ገጽ 10)
‹‹ሊስትሮው ለአፍንጫ የተቋጠረ ጥቁር አዝሙድ መስሎ ሳጥኑ ስር ተጥሏል›› (38)
‹‹ከመሞት በላይ ለመሞት መቁረጥ ውስጥ ጀግንነት የለም?›› (45)
‹‹ፍቅር መንፈሳዊነት ካለበት እንዴት የሥጋን መሽቀርቀር መስፈርቱ አድርጎ ተነሳ?›› (ገጽ 48)
‹‹በህልም መውደቅ የለም፤ ማፈር አይከተልም›› (ገጽ 49)
‹‹በነጠላ የተከበበ ፊቷ የአመሻሽ ጀምበርን ብርሃን ተቀብሎ ያበራል›› (ገጽ 51)
‹‹የትክክለኛ ተሳዳቢ ባህርይ ሌሎችን ከሚሳደቡት ጉድለት አንፃር እራሱን አለመመዘን ነው። የዲዮጋኖች ግን እራስን አንፅቶ በመመልከት ሰው ለመሆን መለኪያነት እራስን ማጨት ነው›› (ገጽ 57)
‹‹የማይበሉ ዶሮዎች የሚበሉት አይቆጭ ይሆን?›› (ገጽ 72)
‹‹መጠግያዬ እምነት ነው፤ መተማመኛዬ ፍቅር ነው፤ ዋስትናዬ ደግነት ነው…›› (ገጽ 103)
‹‹በፊት ቢሆን የቤባን ወንድሞች ስምሪት ሰልላልኝ ትመጣ ነበር›› (ገጽ 138)
‹‹ከእናንተ እኩል፣ የእናንተን ‹ጠበል ጠዲቅ› ለመካፈል የሚያበቃ ንፅህና ለኝም›› (ገጽ 162)
‹‹እግዚአብሔር የተፈጥሮ ሕግ ከሚዛባ ፍጡሩ እንደፍጥርጥሩ ቢዳኝ ይመርጥ አልነበረምን?›› (ገጽ 171)
‹‹አንድ የማይረባ ደራሲ እጅ ገብተን ለአዙሪታም ትርክት ተጋልጠናል›› (172)
‹‹አስቦ የማጽፍ ደራሲ ነው የገጠመን ጓዶች›› (ገጽ 173)
‹‹አሁን ይሄ ኑሮ ጠላት የሚያስፈልገው ሆኖ ነው?›› (ገጽ 179)
‹‹ከመቅፀፍታችሁ አይደለሁም! ከመጨራረሳችሁ አልቋደስም!›› (ገጽ 196)
‹‹ለዚህ ይሆናል ህይወት ከፀጥታ እንዳትፋታ የምጠነቀቅላት›› (ገጽ 203)…. እና ሌሎችን ዐውዱን ባማከለ ሁኔታ ውስጥ እየሰገሰገ ለማለዘብ እና ፈገግታን ለማጫር ጥሯል። ከላይ የቀረቡ መዘርዝሮች ለፌዝ ብቻ የታለሙ አይደሉም!
ቅያሜ
ዓለማየሁ ገላጋይ በዚህ ድርሰት ሴትን የሚሸሽ፣ ተሸናፊ፣ ንጡል…ወዘተ. ገጸ-ባሕርይ የድርሰቱ አካል እንዲሆን አድርጓል፤ ይኼም ከዚህ ቀደም ከነበሩ (በድርሰቶቹ) ገጸ-ባሕርያት ጋር ያዛምደዋል/ያመሳስለዋል፤  
ደራሲው ጥልቅ የንባብ ባህሉን ከማሳየት ተቆጥቧል፤ አብሽቆኛል! እዚህ ላይ የተቀረጹ ገጸ-ባሕርያትን እንመልከት ‹‹መፍትሔ›› የእነ‹‹ታለ››ን ያህል ጉምቱ አንባቢ ባይሆንም፣ ከንባብ የተነጠለ እንዳይደለ በተለያዩ ቦታዎች ብቅ ብሎ ግብረ-መልስ ሲሰጥ አስተውለናል፤ ሆኖም አሌክስ በእሱ በኩል ጥቂት ተጨማሪ ነገሮችን ሊያሳየን ይገባ ነበር፤ ‹‹ኞኞ›› ደራሲ/ተርጓሚ ገጸ-ባሕርይ ነው፤ ሆኖም ጠለቅ ብሎ ስለንባብና መጻሕፍት ሲያወሳ አይስተዋልም፤
‹‹ሆሴዕ›› ስለምን ራሱን ችሎ አልቆመምን? ከግሪኩ ዲዮጋን የተቀዳ ባህርይ/ጠባይ መላበስ ነበረበትን? ነገ ሊዘንብ የተንጠረበበው ድኝ (የሰልፈር ዝናብ) የሚያሰጋው ተንባይ ሆኖ ሳለ በአካል በሚመስል ደረጃ ከምናውቀው ሰው ጋር ተላክኮ መቅረቡ ራሱን እንዳይችል የተደረገ መስሎ ታይቶኛል።
‹‹መፍትሔ›› እንደ ሥሙ ለመፍትሔ ሲተጋ አይስተዋልም፤ የቸከው፣ የደበተው፣ የጣመነው… ነው፤ ለችግሮች መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ ጣጥሎ መሸሽን ኑሮው አደረገ፤ ልቡ ስለምን የሴቶቹን ዕንባ ጭንጫ ሆኖ ዋጠ?
መውጫ
     ‹‹ቤባንያ››ን ዕሴት የሚገደው፣ ሥነ-ስርዐት ጉዳዩ የሆነ ድርሰት ሆኖ አገኘሁት፤ ዕውን ልውስ ምናብ ድርሰት፤ ዛሬም ዓለማየሁ ገላጋይ እንደ ባሕታዊ ለበቅ የሚፋጅ ጉዳይ አቅርቦልናል፤ ሥነ-ጽሑፍ እንደ ጥላ ወጊ ከኋላ የሚደርስ ተከታይ እንዳይደለ ለማሳየት፣ ነገ የሚሆነውን ዛሬ ላይ ይተነብያል፤ ዕጣ-ፈንታችንን፣ ትልማችንን፣ ግባችንን አሻግሮ ያስገረምመናል! ‹‹አንድ የማይረባ ደራሲ እጅ ገብተን ለአዙሪታም ትርክት ብንጋለጥም››፣ አሌክስ ምስ እንካችሁ ይለናል! ክብረት ይስጥልን!!     

Read 696 times