Sunday, 03 September 2023 21:31

”መርካቶን በሚሊኒየም” የአውዳመት የንግድ ባዛር እየተካሄደ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በባሮክ ኤቨንት ኦርጋናይዘር የተዘጋጀው “መርካቶን በሚሊኒየም” የአዲስ ዓመት የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ ባለፈው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በሚሊኒየም አዳራሽ በይፋ ተከፍቷል፡፡
 እስከ ጳጉሜ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ለ17 ቀናት የሚዘልቀው የንግድ ባዛሩ፤ ለሸማቹ ማህበረሰብ መሰረታዊና የበዓል ፍጆታዎች በስፋትና በቅናሽ የሚቀርብበት መድረክ ነው ተብሏል፡፡
“ይዝናኑ ይሸምቱ“ በሚል በሚካሄደው በዚህ የአውዳመት የንግድ ባዛር ላይ፣ የ40 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንደሚደረግ  ተጠቁሟል፡፡ “መርካቶን በሚሊኒየም” በተሰኘው የንግድ ባዛር ላይ  በርካታ የአገር ውስጥና የባህርማዶ አምራቾች፣ አስመጭና ላኪዎች እንዲሁም ጅምላ አከፋፋይና ችርቻሮ ነጋዴዎች እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡
አዘጋጆቹ በሰጡት  መግለጫ፤ ይሄ  ታላቅ የአውዳመት የንግድ ትርኢት፤ ነጋዴዎች ለሸማቹ እጅግ ቅናሽ በሆነ ዋጋ ጥራት ያላቸው ፍጆታዎችን በሰፊ አማራጭና ዓይነት የሚሸጡበት፣ ሻጭና ገዥ በአንድ ቦታ ላይ የሚገበያዩበት፤ እንዲሁም መሰረታዊና የበዓል ፍጆታዎች በስፋት የሚቀርቡበት ይሆናል ብለዋል፡፡
እስከ አዲስ ዓመት ዋዜማ ለተከታታይ ቀናት የሚዘልቀው የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ፣ ትርፍን ብቻ ታላሚ አድርጎ የተዘጋጀ አይደለም የተባለ ሲሆን፤ ባለፈው ቅዳሜም  የተከፈተው ባልተለመደ መልኩ  500 ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች  ማዕድ በማጋራት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም፣ 15 የሚሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሥራቸውንና ዓላማቸውን ለህብረተሰቡ የሚያስተዋውቁበት ቦታ በዚሁ በሚሊኒየም አዳራሽ በነጻ እንደተሰጣቸው የባዛሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል፡፡    
 “መርካቶን በሚሊኒየም”  የንግድ ባዛር፣ የተለያዩ ምርቶችና የበዓል ፍጆታዎች ለሽያጭ የሚቀርቡበት  ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ የሚዝናናበትም መድረክ ነው ያሉት አዘጋጆቹ፤ ለዚህም በየቀኑ ታዋቂና ተወዳጅ ድምጻውያን የሚያቀነቅኑበት የሙዚቃ ድግስ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል፡፡  


Read 222 times