ኤግል ኮሌጅ በመጀመሪያ ድግሪ መርሃግብር ያስተማራቸውን 405 ተማሪዎች፣ በትላንትናው ዕለት ቅዳሜ ከጠዋቱ 2፡00 እስከ 5፡30 በኦሮሚያ ባህል አዳራሽ አስመረቀ፡፡
ከማኔጅመንት የትምህርት ክፍል የላቀ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫ አሸናፊ የሆነው ተመራቂ ዮናስ ገ/አማኑኤል፤ በትጋት የሰራና የደከመ ተማሪ ሁሌ ለላቀ ውጤት እንደሚበቃ ተናግሯል፡፡
ቂሊንጦ ዋልያ ፋብሪካ እንደሚሰራ ለአዲስ አድማስ የጠቀሰው ተመራቂው፣ ለሁለተኛ ድግሪው የመማር ዕቅድ እንዳለው ጠቁሟል፡፡
ከአካውንቲንግና ፋይናንስ የትምህርት ክፍል 3.4 በማምጣት በከፍተኛ ውጤት የተመረቀችው ወጣት ቃልኪዳን አንጋሳ በበኩሏ፤ ከሥራ ጋር መማር ከባድ ቢሆንም ተግታ በማጥናት ለዚህ ውጤት መብቃቷን ተናግራለች፡፡
”መጀመሪያ ላይ አጋዥ መምህራን በቀላሉ ስለማናገኝ ትንሽ ተቸግረን ነበር፤ ነገር ግን ጥሩ መምህራን ነበሩን፤ ኮሌጁም ጥራት ያለው ትምህርት ነው የሚሰጠው፡፡” ስትልም አክላለች - ተመራቂዋ፡፡
የኤግል ኮሌጅ ምክትል ዲን ዶ/ር ሃብታሙ አበራ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤ ኮሌጁ በ2011 ዓ.ም በትምህርት ባለሙያዎች የተመሰረተ ሲሆን፣ ዓምና 114 ተማሪዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁን አስታውሰዋል፡፡
“ኮሌጃችን የትምህርት ጥራት ላይ አይደራደርም ፤ እኛ ለጥራት ነው የምንሰራው፤ጥራትና ትርፍ ደግሞ አብሮ አይሄድም፤” ያሉት ምክትል ዲኑ፤ በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ እዚህ አገር ኮሌጅ ከፍቶ ትርፍ ለማግኘት መሞከር ከባድ ነው ብለዋል፤ መሰረታዊ ወጪዎችን መሸፈን እስከተቻለ ድረስ ብዙ ለማትረፍ እንደማይጨነቁ በመግለጽ፡፡
ኤግል ኮሌጅ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መርሃግብሮች አሰልጥኖ ሲያስመርቅ የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ኮሌጁ ከኢፌዲሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ባገኘው ዕውቅና መሰረት፣ ከመማር ማስተማር በተጨማሪ በጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ በንቃት የሚሳተፍ ሲሆን፤በማህበረሰብ አገልግሎት በዙሪያው ላሉ የመንግሥትና የግል ተቋማት የማህበረሰብ ተኮር ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ ማህበረሰባዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas
,
Sunday, 10 September 2023 21:08
ኤግል ኮሌጅ በመጀመሪያ ድግሪ ፕሮግራም ያስተማራቸውን 405 ተማሪዎች አስመረቀ
Written by Administrator
Published in
ዜና