ከእለታት አንድ ቀን በህይወቱ ሁሉ ነገር የተሳካለት ሚስትም፣ ልጆችም አፍርቶ ጥሩ ስራ እየሰራ የሚኖር ሰው ነበር፡፡ በህይወቱ ግን፤ ቅር የሚለው አንድ ሰው ነበር፡፡ ስለዚህም አንድ ቀን፤
“ዕውነት መጥፋቷ በጣም ቅር ይለኛል” አላት ለባለቤቱ፡፡
“እንግዲያው እውነትን ራስህ ፈልጋት” አለች ባለቤቱ፡፡
ሰውየው ሁሉንም ንብረቱንና ቤቱን ሁሉ ለባለቤቱ ተወላት፣ በስሟ አደረገላትና ተሰናበታት፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ መንገድ ወጥቶ ዕውነትን ለማግኘት ከለማኝ ጀምሮ ማነጋገር ጀመረ፡፡
ተራሮችን ፈተሸ፡፡ ሸለቆዎችን አየ፡፡ ትናንሽ መንደሮችንና ከተሞችን ጎበኘ፡፡ ጫካዎችን ዳሰሰ። በሰፋፊ ባህር ዳርቻዎች ሁሉ ዞረ፡፡ ጨለማን አየ፡፡ የቆሸሹ ቦታዎችንና በአበባ የተሞሉ አትክልት ቦታዎችን ሁሉ ዘልቆ አስተዋለ፡፡ ቀኖችን አጠና፡፡ ሳምንታትን ቃኘ፡፡ ወራትን ተመራመረ፡፡ ዕውነትን አላገኛትም፡፡
አንድ ቀን ከተራራ አናት ላይ፤ አንድ ትንሽ ዋሻ ውስጥ እውነትን አገኛት፡፡
እውነት አንዲት የጃጀች አሮጊት ናት፡፡ ብልህ ናት፡፡ አስተዋይ ናት፡፡ በመላ ድዷ ላይ የሚታየው አንድ ጥርስ ብቻ ነው፡፡ ፀጉሯ ሸብቶ በትናንሹ ተገምዶ ወደ ማጅራቷ ወርዶ ቅባት የበዛበት ቀጭን ዛብ ፈጥሯል፡፡ የፊቷ ቆዳ የደረቀ ብራና ከመምሰሉም ባሻገር በአጥንቷ ላይ ያላግባብ የተጣበቀ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ፤ በእድሜ ብዛት የተንጨፋረረ እጇን በለሆሳስ ስታወዛውዝ፣ ድምጿን ዝቅ አድርጋ ስታወጣውና በዜማና ጥርት ባለ ምት የተቃኘ ቅላፄ ስትሰጠው ሰውዬው አየና፤ እውነትን ማግኘቱ ገባው፡፡
ከእሷ ጋር አንድ አመት ከአንድ ቀን ለመቆየት ወሰነ፡፡ የምታስተምረውን ሁሉ ተማረ፡፡ አንድ አመት ከአንድ ቀኑ እንደተገባደደ፤ በዋሻው መግቢያ በር ላይ ቆሞ፤ ወደ ቤቱ ለመሄድ እየተዘጋጀ፤
“የእውነት እመቤት ሆይ! እስካሁን ይሄን ያህል እውነት አጎናፀፍሽኝ፡፡ ማወቅ ያለብኝን እውነትም ሰጠሽኝ፡፡ ከዚህ ተለይቼ ስሄድ ግን ለውለታሽ አንድ ካሳ ልሰጥሽ የግድ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ምን ባደርግልሽ ትወጃለሽ?”
እመቤት እውነት ወደ አንድ አቅጣጫ ጭንቅላቷን ዘመም አድርጋ ማሰብ ጀመረች፡፡ ከዚያም የአረጀ ጣቷን ወደ ላይ ከፍ አድርጋ አንስታ፤
“ወደፊት ወደ ዘመዶችህና ማህበረሰብህ ስትሄድ፣ መቼም ስለእኔ መናገርህ አይቀርም፡፡”
“አዎ መናገሬማ አይቀርም፡፡”
“ያኔ አደራህን፤ ወጣትና ቆንጅዬ መሆኔን ንገራቸው” አለችው፡፡
***
ከላይ የተነገረውን ተረት የሰሙ አያሌ ፈላስፎች፣ ስለ እውነት ያላቸውን ግምት በተለያየ አቅጣጫ ገልፀውታል፡፡
አንደኛ፡ እውነት፤ አሮጊት ሆና ስታበቃ፣ ስለራሷ የሚነገረው እውነት የወጣት እንዲሆን ትፈልጋለች፡፡
ሁለተኛ፡ እውነት፤ አስቀያሚ ሆና ስታበቃ፣ አስቀያሚ መሆንዋን መገንዘብ እንዲቻል የማትሻ መሆኗን ይጠቁማል፡፡
ሶስተኛ፡ እውነት፡ እውነት ትሁን እንጂ ስለእሷ የሚነገረው የተለየና ስሟን የሚያስጠራ መሆኑን መፈለጓን ልታሳይ ትመኛለች፡፡
አራተኛ፡ እውነት፤ እርጅናዋ ሳይሆን ወጣትነቷ እንዲታይላት እንደምትፈልግ መገንዘብ ተፈላጊ መሆኑን አስተውሉ ትላለች፡፡
አምስተኛ፡ እውነት፤ ምን አስቀያሚና መልከ-ጥፉ ብትሆን፣ ቆንጆና ወጣት መሆንዋን በመንገር ስለራሷ ለመዋሸት መቻልዋን ለማረጋገጥ ትፈልጋለች፡፡
በሀገራችን አያሌ እውነቶች ውሸት የሚመስሉበት፤ አያሌ ውሸቶችም እውነት የሚመስሉበት ሁኔታ መኖሩን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እውነት አንፃራዊ ነው የሚለው እውነታ በተደጋጋሚ የተወሳ ቢሆንም፤ አንፃራዊነቱ በማን እይታ እንደሆነ ማስተዋልም አንድ አይነተኛ አስተውሎትን መጠየቁ ዋና ነገር ነው፡፡ የተማረ ሁሉ የተማረ ተብሎ መወሰዱ፤ ያልተማረም ሆኖ እንደተማረ የሚያስቆጥር የልምድና የስልጣን አቅም ሊያበጅ መቻሉ፤ አገር-ወዳድ የሚመስለው ሁሉ አገር-ወዳድ አለመሆኑ፤ ዝም ያለ ሁሉ ከአላዋቂ መቆጠሩ፤ በአንፃሩ የሚናገር ሁሉ አዋቂ መምሰሉ፤ በአንድ ወንበር ላይ ረጅም ጊዜ የተቀመጠ ሁሉ ለወንበሩ በልክ የተሰፋ መምሰሉ፤ ለውጥ የጠየቀ ሁሉ ተፃራሪና አፍራሽ ተብሎ መፈረጁ ወዘተ… በአንድ ታሪካዊ ወቅት እውነት ከተባሉ የማያወላውል እውነት እንደሆኑ መጣፋቸው በተደጋጋሚ የሚታዩና የታዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ስለ ዲሞክራሲ የለፈፈ ዲሞክራሲያዊ፣ ስለ ፍትህ የለፈፈ ፍትሃዊ፣ ስለ መልካም አስተዳደር የተናገረ መልካም አስተዳደር ወዘተ… ተደርጎ መታሰቡ፤ ሁልጊዜ እውነት ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ በተግባር የተፈተሹ አያሌ ሰዎች የሚለፍፉትን አልሆኑምና እውን የሚሰብኩትን የሚተገብሩ ሰዎች ናቸውን? ብሎ፤ ቆም ብሎ ማሰብ ያባት ነው፡፡ ስለማያምኑበት ነገር ጮክ ብለው የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። “አስተውለህ ተናገር፤ ዋኝተህ ተሻገር” መባል ያለባቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በእውቀት፣ በልምድ፣ በመስዋእትነትና በመሳሰሉ መለኪያዎች ሳይሆን ጠባብ-የወፍ ቤት ያስተቃቅፋል በሚለው መሰረት ብቻ ያወቁ፣ ልምድ ያዳበሩና ለጉዳዩ አግባብ ያላቸው በመምሰል ወደ ሰገነቱ የተጠጉ ምን ያህል ናቸው? መስሎ- በማደርና በማስመሰል ካባ ከሞቀው ጎራ የተቀላቀሉ ምን ያህል ናቸው? ተቃዋሚ በመምሰልስ ብቻ ሃቀኛ ለመምሰል የሚሞክሩ ሃሳዊ-መሲሃን ምን ያህሉ ናቸው? በሙስና ተዘፍቀው ስለ ሙስና የሚያወሩስ? ይህን መመርመር ተገቢ ነው፡፡
“ጉንዳን መንገድ ሳይቸግረው ይጋጫል” እንዲሉ፣ በሆነ ባልሆነው ለግጭት ሲሉ የሚጋጩ ምን ያህል ጠብ-ጫሪዎች አሉ? ያጠያይቃል፡፡ ያነጋግራል፡፡ በጠቡ ማን ተጠቃሚ ይሆናል? የሚለውም የዛኑ ያህል ያጠያይቃል፡፡ ጠብ ያለሽ በዳቦ ማለት እንደ ትግል ሥልት ከተያዘ፣ አገር የጠብ መናኸሪያ እንዳትሆን ያሰጋል፡፡ በፍርሃት ላይ የተመሰረተ፣ በአለማወቅ ላይ የተመሰረተ፣ በሀገርና በህዝብ ጥቅም ላይ ያልተመሰረተ አካሄድን ተጠንቅቆ ማስወገድ ያሻል፡፡ በማናቸውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገዢና ተገዢ፣ ተዋናይና ተንቀሳቃሽ፣ ተቃዋሚና ተቃውሞ-ተቀባይ ምኔም ተለዋጭ ናቸው፡፡ አገርና ማረፊያቸው መድረክ ብቻ ነዋሪ ናቸው፡፡ ኢኮኖሚ ቢዳከም፣ ፖለቲካ ቢጣመም፣ ማህበራዊ ህይወት ቢቃወስ፤ አገር ነዋሪ ናት! ገደል የገባ ነው እንጂ ገደል ይሰበራል ወይ? ይላሉ አበው፡፡ ይሄንኑ ሊያስረዱን መሆኑን በጥሞና ማስተዋል ይበጃል፡፡
እንግዲህ አሮጌውን 2015 ዓ.ም ሸኝተን፣ አዲሱን 2016 ዓ.ም ልንቀበል ዋዜማ ላይ ነን፡፡ ከሁለት ቀናት በኋላ አዲሱ ዓመት ይጠባል፡፡ አዲሱ ዓመት በእውነት አዲስ እንዲሆን አምስቱ ህዋሶቻችንን በሚገባ እናንቃቸው፡፡ ዐይናችን በቅጡ ይይ፡፡ ጆሮአችን በተገቢው መጠን ይከፈት፡፡ ምላሳችን ሃቅ ይልመድ፡፡ አፍንጫችን መዓዛ ይለይ፡፡ እጃችን መጨበጥ ይወቅ፡፡ ከአምስቱ ህዋሶቻችን የሚያመልጥ አንዳችም የአገር ጉዳይ የለም፡፡ ልብ ለልብ፣ አዕምሮ ለአዕምሮ፣ ቋንቋ ለቋንቋ የማንጠፋፋበት፣ የምንደማመጥበት፣ አዲስ ሃሳብ የምንቀበልበት የሰለጠነ መድረክ ይፈጠር ዘንድ ጠባቡ እንዲሰፋ፣ አምባገነኑ እንዲገራ፣ ጥጋበኛው እንዲበርድለት፣ አመጸኛው እንዲገታ፣ ለእኔ ብቻ ባዩ እንዲያጋራ፣ ዕብሪተኛው እንዲጨምት፣ ዳተኛው እንዲተጋ፣ ሃሞት-የለሹ እንዲጀግን፣ ሞራለ-ቢሱ እንዲጸና፣ መሃይሙ እንዲማር --- አዲሱን ዓመት በቀና ልቦና ማየትና ዝግጁ መሆን ይገባናል፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!!
Published in
ርዕሰ አንቀፅ