Monday, 11 September 2023 09:26

ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ጠራርጎ ይውሰደው!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

-እናላችሁ በኤኮኖሚውም፣ በቦተሊካውም፣ በማህበራዊ ኑሮውም ብቻ በሁሉም መስክ ያለው እያገሳ የሌለው እየከሳ የሚኖርባት አገራችን፣ ታሪክ ሆናና በቃችሁ ብሎን እየተሳደድን ሳይሆን፤ እርስ በእርስ እየተሳሰብን፣ እየተሰባበርን ሳይሆን እርስ በእርስ እየተጠጋገንን፣ እየተደነቃቀፍን ሳይሆን እርስ በእርስ እየተደጋገፍን የምንኖርባት አገር አንድዬ “ይህችውላችሁ፣ ተረከቡኝ!” ይበለንማ!--”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለዘመን መለወጫ አደረሳችሁ!
ክረምት አልፎ በጋ መስከረም ሲጠባ
አሮጌ ዓመት አልፎ አዲሱ ሲገባ
ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ተውሳኩን ይወሰደው
ጤና መሆንን ነው እኛ የምንወደው
አዎ ፈሳሽ የወንዝ ውሀ አብሮ አላስኖር፣ አብሮ ማዕድ አላስቀምጥ፣ “አንቺ ትብሽ፣ አንተ ትብስ!” እንዳንባባል ያደረጉንን አስተሳሰቦች ጠራርጎ ይውሰድልንማ! የሆነ ቁም ነገር ሳይኖራቸው በባዶ ቃላት አስተሳሰብ እንዲመስሉ የሚደረጉ የለየላቸው በአንደኛው ወገን ጉዳትና ሰቆቃ ሌላኛውን ወገን “ለእኔም አምጪ፣ ለአንቺም ጠጪ!” አይነት ዳንኪራ ለማስረገጥ የሚረጩ የክፋት ትርክቶችን ፈሳሽ የወንዝ ውሃ ጠራርጎ ይውሰድልንማ! ያለምንም  ምክንያት አንደኛው ወገን ምንም ያላደረገውና አጥሩን ያልነቀነቀበትን፣ ከብቱን ያልነዳበትን ሌላኛው ወገን ሲወድቅና እንደሚባለው “አፈር ሲልስ” ማየትን “ናፈቀኝ! ናፈቀኝ!” የሚያስብሉ የለየላቸው የጥላቻ ትርክቶችን፣ ከመሻገሪያ ድልድዮች ይልቅ መለያያ ግንቦችን የሚያቆሙ ትርክቶችን፤ ተቃቅፎ ከመሳሳም ይልቅ ተናንቆ መናከስን “ይበል! ይበል!” የሚሉ ትርክቶችን ሁሉ ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ጠራርጎ ይውሰድልንማ!
አዎ፣ አሳፋሪና አሸማቃቂ ሊሆኑ በሚገባቸውና ምናልባትም አብዛኛው ዓለም በረሳቸው የክፋት፣ የ“ከእኔ በላይ ላሳር፣” ጥላቻ፣ ክፋት፣ ምቀኝነትና የመሳሰሉ ባህሪያት በራቸውን ያላንኳኳ ዜጎችን ማየት የምንናፍቀበት ጊዜ አይመጣም ብሎ ማሰብ ከመልካም ምኞትነቱ ይልቅ በጊዜያችን ያለው እውነተኛው በግልጽ በሚታይ ስዕል ላይ ጀርባ ማዞር ይሆናል፡፡  
የአምናን ቀን ረገምኩት ለአፌ ለከት የለው
የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው
የሚለውን ከድግምግሞሹ የተነሳ ወደ እንጉርጉሮነት እየተለወጠብን ያለውን ስንኝ፣ ለዘለዓለሙ የምንረሳበት ዘመን ይፍጠንልንማ!
ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ክፋቱንም፣ ተንኮሉንም፣ ምቀኝነቱንም፣ ጥላቻውንም ሁሉንም እርግማን ጠራርጎ ይወሰድልንማ! 
እናላችሁ… የሆነ በሀገሩ አይደለም ለሚዲያ ሊበቃ፣ አክስትና አጎቶቹ እንኳን የማያስታውሱት ‘ቦሌ በገባ በማግስቱ’…አለ አይደል…ገና በቅጡ ሊያያት ያልጀመራትን ሀገራችንን… “በእውነቱ ሀገራችሁ በጣም ውብ ነች፣” ይላል፡፡ እኛ ደግሞ እንግዲህ ፈረንጅ ሲባል የሆነ “አዙረኝ አታዙረኝ፣” አይነት ወዲህ ወዲያ የሚያደርገን ነገር አለ አይደል…“ኢሮ!” ብለን እናጨበጭባለን፡፡ ያለምንም ተቀጥላ፣ ያለምንም የነገር አፔንዲክስ ራሳችን ለሀገራችንና ለህዝባችን የምናጨበጭብበትን ጊዜ ያፍጥንልንማ፡፡
ስንሰማቸው የኖርናቸው፣ እውነት ብለን ተቀብለናቸው የኖርናቸው ነገሮች…አሁን እየተለወጡ፣ የራሳችን የሆነችውን እናት ኢትዮጵያን፣ እኛ ልጆቿ ልናደንቃት አይገባን ይመስል፣ “ፈረንጆች ይወዱናል” አይነት ነገሮች እስከ ወዲያኛው ከስመው፣ እኛው በእኛው ሀገራችንንና ህዝባችንን የምናደንቅበት ዘመን ፈጥኖ ይምጣልንማ፡፡ እኛው ራሳችን በታሪካችን አይደለም መግባባት መቀራረብ እንኳን አቅቶን እያለ፣ “ዓለም በታሪካችን ያውቀናል” አይነት ነገር በአሁኑ ጊዜ ትንሽ አስቸጋሪ አይሆንም! አውቀን ቅሽም ባለ ‘ብልጥነት፣’ ሳናውቅ ቀርተን ያልሆነው ነገር የሆነ እየመሰለን፣ “ፈረንጅ! ፈረንጅ!” የምንል ሰዎች፣ ቀልባችንን የምንገዛበት ዘመን ይምጣልንማ!
ስለሆነም ከትናንት ወዲያ ይሁን ትናንት ከነበርንበት የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ የቆየን ምን ያህላችን እንደሆንን ዕለት በዕለት የምናየው ነን! ከዲስኩራችን ይልቅ ድርጊታችን ይናገራልና፡፡ ብዙ የዘንድሮ የሀገራችን ችግሮች የአስተሳሰብ ማሽቆልቆል ምልክቶች አይደሉም እንዴ! እናማ… ዘመኑ ሲለወጥ ቢያንስ፣ ቢያንስ በቦተሊካውም ሆነ በሌላው ያለው አመለካከታችንን የሚያርቅልን፣ ትክክለኛውን ጎዳና የሚያሲዝልን፣  ትርክቶቻችንን ባዶ የቃላት ድሪቶ ከመሆን ይልቅ በጎ ሀሳቦችን ያዘሉ መልካም ፍሬዎችን ያንዠረገጉ እንዲሆኑልን መመኘት፣ ጸሎት ቢጤ ማድረግ ክፋት የለውም፡፡ እርስ በእርስ መደማመጥ እስካቃተን  አንደኛውን አንድዬ ጣልቃ ገብቶ እንደምንሆን ያድርገን እንጂ፣ የእኛኑ የራሳችንን ነገርማ እርግፍ አድርገን ልንተወው ኮረብታዋ አፋፍ ላይ ነን፡፡ መጪውን ዘመን ከዛች አፋፍ የምንመለስበት ያድርግልንማ!
እናማ…የችግሮቻችን ዋነኛ ምንጮች የተዛቡ፣ የተሳከሩ፣ እርስ በእርሳቸው የሚደነቃቀፉ  አስተሳሰቦች አይደሉ አንዴ!  ከሁሉ አስቀድሞ ሁላችንም በእሱ አምሳል የተፈጠርን የሰው ፍጥረታት መሆናችንን መቀበል ብልህነት ነው፡፡ ከዛ በላይ፣ ከዛ በታች ብሎ ነገር የለም። እንዲህ ማለቱ ትንሽ ለአፍ ሊከብድ ይችላል አይደል! ግን ሀቁ አንዳንዶቻችን ልናደርጋት እንደምንሞክረው፣ ሀገር እኮ የአገልግሎት ጊዜው ያበቃ ‘ዩዝ ኤንድ ስሮው’ ዕቃ አይደለችም። አለቀ! ፈረንጅ እንደሚለው ‘ላይክ ኢት ኦር ኖት’ ምንም ቅጥልጥሎሽ፣ ምንም ማብራሪያ፣ ምንም “አንድ ፈላስፋ በአንድ ወቅት እንዳለው…”  ቅብጥርጥሮሽ ሳያስፈልገው፣ ሀገር ‘ዩዝ ኤንድ ስሮው’ ግዑዝ እቃ አይደለችም!
እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ የሰውኛ ባህሪያችንን ወደዛ አሽቀንጥረን፣ ነገሮች ሁሉ የበሳል አስተሳሰቦች ውጤቶች ከመሆናቸው ይልቅ የባገኝ ባጣ አይነት የነሲብ ሲሆኑ መልካም አይደለም፡፡ ደራሲው “ነገም ሌላ ቀን ነው፣” ያለው ለእኛም ነው፡፡ ጥያቄው ሌላ ቀን ነው የሚባለው ነገ፣ በእርግጥ ምን አይነት ቀን ይሆናል የሚለው ነው፡፡ አንደኛው ትውልድ ቢሄድ ሌላኛው ትውልድ ይተካል፡፡ ሰልጥነናል የሚሉት፣ ወይም ሰልጥነዋል የምንላቸው ማህበረሰቦች እኮ ሁሉንም ነገር ሲሠሩ የነገና የተነገወዲያ ትውልዶችን እያሰቡ ነው፡፡  እኛ ግን አይደለም ስለነገና ስለተነገ ወዲያ ትውልዶች ልናስብ፣ እርስ በእርሳችን ጀርባ የተዟዟርንበት ዘመን ውስጥ አይደለንም እንዴ!
ሌሊት ከጭቃ ላይ ፈረስ ቢጥልሀ
ወንድሜ አትናደድ ማንም አላየህ
ይልቁን ተጠንቀቅ ቀን እንዳይጥልህ
የምትል ስንኝ አለች፡፡ አዎ ቀን እየጣለን ነው የተቸገረነው፡፡ ግን ደግሞ እውነት እንነጋገርና ቀን ነው የጣለን ወይስ እኛው ነን ራሳችንን  በራሳችን  እየጣልን ያለነው! አሁን ቀጥ ብሎ የቆመው ነገ፣ እሱም ዘጭ ብሎ አይንከባለል ይመስል የወደቀውን እያየ፣ “አሲዮ ቤሌማ…” መጨፈሩ እስከቀጠለ ድረስ “ዘ ፊኒሽ ላይን” የምንለው ሪባኑ የሚበጠስበት ስፍራ የት ነው! “አሲዮ ቤሌማው…” ቀርቶ ሁላችንም ሪባን መበጠሻው ላይ እኩል የምንደርስበት ዘመን ይሁንልንማ!
ቃል መግባት የሚሉትን ነገርማ ተዉት፡፡ እንደ ድሮ መጠጥ አቆማለሁ፤ ጎጆ እቀልሳለሁ ምናምን አይነት አባባሎችን ለነገር ማሳመሪያነት እንኳን መጠቀም ትተናል፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…መቼም የዘንድሮው የኑሮ ልዩነት የበዓሉ ግርማን ብዕር አይነት ጉልበት ያለው ብዕር ቢያገኝ ሌላ ‘ኦሮማይ’ አሳምሮ ይወጣው ነበር፡፡ የኑሮ ልዩነቱ እኮ…አለ አይደል…አስከፊ በሚባል ሁኔታ እየሰፋና እየተለጠጠ ሄዶ፣ እንደው ለከርሞዎቹ ዓመታት የት እንደርስ ይሆን የሚያሰኝ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ለነገሩ ያሁኑ ባሰ እንጂ ያለው እያገሳ፣ የሌለው እየከሳ የኖረባት አገር ነች፡፡
አንድ ጸሐፊያችን በአንድ መጸሐፋቸው ላይ ያስቀመጧት ቀደም ያሉት ዘመናት ስንኝ አለች፡፡
ብሩንዶ በልተው ጠጅ የጠጡ
ቆሎ ቆርጥመው  ውኃ ያጡ
ሁሉም እኩል መቃብር ወረዱ
ምን ይሆን የፈጣሪ ፍርዱ፤
ትላለች፡፡ አንድ መቼም ቢሆን ልንዘነጋው የማይገባው፣ ግን ደግሞ የረሳነው የሚመስለው ጉዳይ፣ የመጨረሻ ማረፊያችን ተመሳሳይ መሆኑን ነው፡፡ ለሁላችንም… 
ሁሉም እኩል መቃብር ወረዱ
ምን ይሆን የፈጣሪ ፍርዱ፤
ነው ነገሩ፡፡
እናላችሁ በኤኮኖሚውም፣ በቦተሊካውም፣ በማህበራዊ ኑሮውም ብቻ በሁሉም መስክ ያለው እያገሳ የሌለው እየከሳ የሚኖርባት አገራችን፣ ታሪክ ሆናና በቃችሁ ብሎን እየተሳደድን ሳይሆን፤ እርስ በእርስ እየተሳሰብን፣ እየተሰባበርን ሳይሆን እርስ በእርስ እየተጠጋገንን፣ እየተደነቃቀፍን ሳይሆን እርስ በእርስ እየተደጋገፍን የምንኖርባት አገር አንድዬ “ይህችውላችሁ፣ ተረከቡኝ!” ይበለንማ!
ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ክፋቱንም፣ ተንኮሉንም፣ ምቀኝነቱንም፣ ጥላቻውንም ሁሉንም እርግማን ጠራርጎ ይወሰድልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1143 times