Monday, 11 September 2023 09:30

ለአዲስ አመት - አዲስ ምዕራፍ!

Written by  ዮፍታሄ
Rate this item
(1 Vote)

ምናልባት በድንገት ደርሶ ብስጭት የሚያደርግ ነገር አጋጥሟችሁ ያውቅ ይሆናል። ወይም ቢያንስ በሆነ አጋጣሚ አንዳች “የሚያስደነግጥ አልያም የሚያስደነግጥ” ነገር ትሰሙና ምንም እንኳ ጉዳዩ እናንተን በቀጥታ ባይመለከትም ግን የሁኔታው ተገቢ አለመሆን፤ አፍራሽነቱ፤ ከቅንነት በተቃራኒ መንገድ ታስቦ የሚደረግ መሆኑ ክፉኛ ይከነክናችኋል፡፡
በምንኖርበት ማህበራዊ ህይወት ውስጥ በርካታ እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች ያጋጥማሉ፡፡ በየጊዜው ከምንሰማቸውና ከሚያጋጥሙን ደስ የሚሉን፤ ልብን በሃሴት የሚሞሉ፤ አንጀትን የሚያርሱ፤ ይበል የሚያሰኙ ተግባሮች ጎን ለጎን፤ እናንተ አሪፍ ነው፤ ይመቻል፤ ድንቅ ነው፤ የተቀደሰ ይሆናል የምትሉትን ነገር ሁሉ ድምጥማጡን የሚያጠፋ፤ የሚያፈርስ፤ የሚኮንን ፍፁም አሉታዊ አላማ ያለው ድርጊት ጋር ትጋፈጣላችሁ፡፡
ለእነዚህ ነገሮች እንደ ምሳሌ አንድ ፍንጭ ልስጣችሁ፡፡ አንድ ሰው ያለ የሌለ አቅሙን አሟጦ፤ ያለ የሌለ ጊዜውን መስዋእት አድርጎ፤ ያለ የሌለ ገንዘቡን ከስክሶ አንድ አዲስና ለየት ያለ ግን በብዙዎች አይን፤ “ድንቅ” የሚባል ተግባር ይጀምራል፡፡  ይህ ሰው ከእኛ መካከል ማንኛውም አንድ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሰውየውን ከሀገራችን ኢንቨስተሮች አንዱ እንደሆነ አድርጋችሁ ቁጠሩት፡፡ ኢንቨስተር ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ፤ ምን አይነት መስዋእትነት ከበስተጀርባው እንዳለ በመዘርዘር አላደክማችሁም፡፡
ነገር ግን ብዙዎቻችን ከምናውቃቸው በሺ የሚቆጠሩ “ኢንቨስተሮች” መካከል ብዙዎቹ ታላላቅ ራእይ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው ዘወትር የምናውቀው፤ በተለመደውና ስናየው በኖርነው የኢንቨስትመንት መስክ መሰማራት፤ የዛን ያህል የብዙዎችን ቀልብና ትኩረት የሚስብ ላይሆን ይችላል፡፡
በሌላ በኩል በተለይ ለእኛና ለሀገራችን ያልተለመዱ፤ እንግዳ የሆኑ፤ በአዲስነታቸው ብቻ እንኳን ፈታኝ የሆኑ፤ ተግባር ላይ ሲውሉ ግን የሚያመጡት ለውጥ የሚፈጥሩት እድገት፤ ለሀገራችን የሚያበረክቱት ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ  ወዘተ  ወደር የለሽ የሆነ የሚባልላቸው መስኮችም አሉ፡፡
ከእንደዚህ ያሉ አዳዲስ አይነት የኢንቨስትመንት ተግባሮች በስተጀርባ በርካታ እንቅፋቶች፤ አስቸጋሪ ጎዳናዎች፤ የበጀትና የፋይናንስ ማነቆዎች፤ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ወዘተ ሞልተው ተርፈዋል፡፡
ከሁሉም በፊት ሃሳቦቹ እራሳቸው አዲስ እንደመሆናቸው፤ “አይዬ አሁን ይሄ ይሳካልኛል ብለህ ነው የተነሳኸው?” የሚሉ አይነት በጥርጣሬ የተሞሉ፤ እሩቅ የማሰብ ሃይል የሌላቸው፤ በውጤታቸውም ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ አስተያየቶች መስማት አዲስ ነገር አይሆንም፡፡
እንደዚህ አይነት የተጨበጠ መሰረት የሌላቸው የዋህ መሳይ ግን መራራ አስተያየቶችን “አዎን ይሳካልኛል!... አስቤበታለሁ፤ ችግሮቼን ለመወጣት እችላለሁ” ብሎ ማለፍ ከተቻለ ደግሞ ከሌላ ወገን ሌላ ፈታኝ የሚመስል፣ ህሊናን ለመጉዳት ከሆነ በፍጹም አቅም የማያንሰው፤ ደካማ በሆነ ልፍስፍስ ሎጂክ የተዋዛ አስተያየት ይገጥማችኋል፡፡
“ኢትዮጵያዊ እኮ ለአውሮፓውያን (ለምእራባዊያን) ምርቶች እንጂ እዚህ ለምትፈበርካቸው ነገሮችህ ብዙ ደንታ የለውም። የገበያውን ነገር እንዴት ትወጣዋለህ? ብትከስርስ?” ትባላላችሁ፡፡
እንዲህ ያለ ደካማ አስተያየት በአንድ ወቅት የቀረበለት አንድ ወዳጄ በአጭሩ የሰጠው ምላሽ፤ “ገበያውን እፈጥረዋለሁ፤ ሀገሬውንም አለማምደዋለሁ” የሚል ነበር፡፡ ችግሮቹ ግን በዚህ ብቻ የሚገቱ አይደለም፡፡ እጅግ ደፋር የሆነና ፈተናን የማይፈራ፤ እንቅፋቶች የማያሸብሩት፤ ያቀደበት ደረጃ ለመድረስ ሲል ሩቅ አልሞ የሚንቀሳቀስ ሰው በየአንዳንዱ እርምጃ የሚያደነቃቅፉት ነገሮች ቢገጥሙትም ጥርሱን ነክሶ ሁሉንም በማለፍ ያሰበበት ደረሰ እንበል፡፡ መፍጠር የፈለገውን ፈጥሮ፤ መገንባት ያሰበውን ገንብቶ፤ መፈብረክ የጀመረውን ለገበያ ሲያቀርብ ደግሞ ሌሎች ያልተጠበቁ ከቶም ልናልማቸው የማንችላቸው  “የጥላቻ፣ የትችት፣ የማጥላላት፣ የማንኳሰስ” ዘመቻዎች ይከፈቱበታል፡፡
በተለይም ያ ሰው ገና ከጅምሩ ስኬታማ መስሎ ከታየን፤ ስሙ ከፍ ከፍ ብሎ መነሳት ከጀመረ፤ የሚሰራው ስራ (ምንም ይሁን ምን ለምሳሌ የፋብሪካ ውጤት ይሁን የጥበብ ስራ፤ ፈጠራና ግኝት ይሁን ወዘተ)  በብዙዎች ተመልካቾች አይን “አቦ እንዴት አሪፍ ነው! ተሳክቶለታል… ድንቅ ነው” መባል ከተጀመረ፤ እነዚያ ቀድሞ ጅምሩን በአሉታዊ አይናቸው ሲያዩ የነበሩ ሰዎች የሚከፋቸው ይመስለኛል፡፡
ገና ከጅምሩ አመለካከታቸው እንደ ግመል ሽንት የኋልዮሽ የሚሄድ ስለሆነ “ተሳካ፣ ተመቸው፣ አሪፍ ሆነ፣ ለስኬት በቃ” የሚሉ አይነቶች አድናቆቶችም ይሁን አስተያየቶች በፍፁም ባይጥማቸው ልንገረም አይገባም፡፡
እዚህ ላይ ልብ እንድትሉልኝ የምፈልገው ሁሉም ሰው ሁሉንም ነገር ወዶት፣ ደስ ብሎት፣ ተመችቶት፣ እያጨበጨበ ሊቀበለው ይገባል የሚል አመለካከት እንደሌለኝ ነው፡፡ ግን ቢያንስ ለነገሮች ሁሉ መነሻ የሰዎች አዲስን ነገር የመፍጠር፣ የማደግ፣ ወደፊት የመራመድ፣ የመለወጥ የጥረት አቅጣጫና ተነሳሽነት፤ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በቅንነት “ልናየው የሚገባ” ነው ባይ ነኝ፡፡
እናም እነዚያ የነገሮች ስኬት፣ ብርሃንን የተላበሰ ድል፣ የአሸናፊነት ተምሳሌት መሆን ወዘተ የማይጥማቸው ሰዎች ቀድሞ ከጅምሩ ሊያጣጥሉት የሞከሩት ነገር ገፍቶ ሄዶ… (ምናልባትም በልባቸው ተንገዳግዶ ይወድቃል ብለው አምነው ይሆናል) በሚያጋጥሙት ጋሬጣዎች ውስጥ ሁሉ አልፎ ለስኬት ሲበቃ ምን የሚሉ ይመስላችኋል? ምናልባትም ከእነዚህ ሃሳቦች አንዱን ቢሰነዝሩ በፍፁም አትገረሙ፡፡
“ተወው ባክህ ጊዜያዊ ነው፡፡ ሰው እኮ ወረተኛ ነው የትም አይደርስም”
ወይም
“ምን እሱ በቲፎዞ ነው እንጂ እኮ የሰራው (ወይም የሰራችው) ነገሩ ያን ያህል የሚደንቅ መስሎህ ነው? በፍጹም አይደለም - ተራ ነው”
ወይም “እንዴ ልብ ብለሃል? ዝም ብሎ እራሱ (ስራውን) ከፍ ከፍ ያደርጋል እንጂ እኮ ውጤታማ የሆነ እንዳይመስልህ - ሲያስመስል (ስታስመስል) ነው”
ወይም … ሌሎች ብዙ ጊዜ የሰማችኋቸው መሰል አስተያየቶች ይሰነዘሩ ይሆናል፡፡
ያ መከረኛ ሰው በእነዚህም ሊሸነፍ የሚበቃ ደካማ ሰው አይሆን ይሆናል፡፡ ወይም እነዚህን ሁሉ ተጋፍጦ፤ ችሎ፤ ተፋልሞ፤ ከሁሉ በይበልጥ ደግሞ በስልትና በብቃት በስራው አሸንፎ መውጣት ይጀምራል፡፡
ነገሩ ይህ ከሆነ ወይም እዚህ ከደረስን በኋላስ ምን ይከተላል? ወይም ምን የሚከተል ይመስላችኋል? ምን ትጠብቃላችሁ ከእነዚያ ሰዎች?
ለእኔ እንደሚመስለኝ አድርጌ ቀጣዩን “የፀረ-ቅንነት”  ደረጃ ፍንጭ ልስጣችሁ፡፡ ብዙ ጊዜ እንዳየሁት እነዚህ ሰዎች በቀጣይ እርምጃቸው እነሱም አንድ እርምጃ ይራመዱና፤ ጊዜ ይወስዱና ከዚያ ብዙዎች “ድንቅ ነው” ካሉት፤  ብዙዎችም ካወደሱት ስራ (ውጤት/ምርት) ፈጠራ ውስጥ “እንከን መፈለግ” ይጀምራሉ፡፡ ለሚፈልጉት አፍራሽ አላማቸው የሚመች ትንሽዬ “የድክመት ሰበዝ” ካገኙ ያንን መዘውና በብዙ ሺ መቶኛ አባዝተው፤ ጥሩ በሚመስሉ የዋህ “ሎጂኮችና አባባሎች” አዋዝተው ሊያቀርቡላችሁ ይችላሉ። በአብዛኛው የምትሰሙዋቸው ነገሮች ለምሳሌ፡-
“ነገርዬው ጥንካሬ (ጥራት/ብቃት) ብስለት ወዘተ የለውም” የማለት ነገር ወይም፤
“ሃሳቡ የተሰረቀ፤ የታወቀ፤ የተለመደ፤ የተናቀ፤ የማይጥም ነገር ነው” የሚሉት አይነት አልያም፤
“ነገርየው ከዚህ ከዚህ… ወይም ከዚያ ከዚያ የተሰራ/ የመጣ/ኮፒ የተደረገ… ብዙም ተቀባይነት የሌለው ነው” ልትባሉ ትችላላችሁ።
ለምን ናልባቱ እነዚህ ወገኖቻችን ለነገራቸው ማጣፈጫ የሚበጅ “የእንከን ሰበዝ” ማግኘት ባይችሉ፤ ነጩን ጥቁር፣ “ቀዩን ቢጫ” ከማለት የማይመለሱ፤ ሃሳባቸውን ለማዳበር የሚረዳቸው ከሆነ ከመዋሸት የማይመለሱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ አድሮ አድሮ በነገር ብዛት የ “ነገር አረሩ” ድብደባ መጠነኛ ስኬት ያገኝ ይሆናል፡፡ ይህ ግን እኔ እንደማስበው ደካሞችን እንጂ ጠንካሮች ከሚጓዙበት ምህዋር ፈቅ የሚያደርጋቸው አይመስለኝም፡፡ በተለይም አነሳሳቸው አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ ከተገነባ፡፡ ግን ግን እስከ መቼ ነው እንደዚህ ያሉ አፍራሽ፣ አውዳሚ፣ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን ተጋፍጠን የምንኖረው? እንዴት አድርገንስ ነው በእነዚህ አይነት ጥላቻ፣ ጥፋት፣ አሉታዊነት፣ ክፋት የተጠናወታቸው ሃሳቦችን አካሄዶችን፣ አስተያየቶችን ድርጊቶችን ተሸክመን ለግልም ሆነ ለሀገር ለውጥ፣ እድገት ብልጽግና መሰረት የምንጥለው?
እኔ እንደማስበው፤ በእጅጉ መለወጥ ያለብን ይመስለኛል፡፡ የለውጣችን ጅማሮም አንድ ደረጃ ላይ “ሀ” ብሎ ሊነሳ፣ ያለፈውን አሮጌ ምእራፍ ዘግቶ አዲስ ምእራፍ ሊከፍት ይገባዋል፡፡ ለዚህ እርምጃ የግድ ቀን መቁረጥ ካለብንም፣ ከአዲስ አመት መግቢያ የተሻለ ጊዜ አይኖርም ያ ደግሞ እነሆ ሁለት ቀናት ብቻ ነው የቀሩት - 2016 አዲስ አመት! እንኳን አደረሰን!
Read 1665 times