አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ፤ ለ34 ወራት የሚዘልቅ የ3.854 ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ስምምነት ከየምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር መፈራረሙን አስታወቀ፡፡
በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበሮች መሃል የሚገኙ ስደተኞችን ጨምሮ ለአደጋና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህብረተሰቦችን ለመርዳት ያስችላል የተባለው የፕሮጀክት ስምምነቱ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ነው የተፈረመው፡፡
ስምምነቱን ኢጋድን በመወከል የኢጋድ ዋና ጸሃፊ የተከበሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የፈረሙ ሲሆን፤ አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢትዮጵያን በመወከል ደግሞ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አቶ ሳሊሁ ሱልጣን እንደፈረሙ ታውቋል፡፡
የአክሽን ዘ ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳሊሁ ሱልጣንና የቦርድ ሊቀመንበሩ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ሳር ቤት በሚገኘው የድርጅቱ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በቅርቡ ከኢጋድ ጋር በተፈራረምነው የትብብር ማዕቀፍ፣ ድርጅታችን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የኢጋድ አባል በሆኑ የአፍሪካ አገሮችም ለአደጋና ችግር ተጠቂ የሆኑ ዜጎችን ለመርዳት ተገቢውን ድርጅታዊና ተግባራዊ ዝግጅት በማሟላት ላይ ነን ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት በተወሰኑ የምስራቅ አፍሪካ አገራት አክሽን ፎር ዘ ኒዲ፣ ከኢጋድ ጋር በመተባበር ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን መክፈቱን ጠቁመዋል - ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፡፡
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አካላት ስደተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች እንደሚሆኑ የገለጹት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ የፕሮጀክቱ ወጪ ሙሉ በሙሉ የተሸፈነው በክልላዊ ስደተኞች መርጃ ፈንድ በኩል በጀርመን ልማት ባንክ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ከሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከልም፤ በኦሮሚያ ሞያሌ አካባቢ ልዩ ስሙ ለጋ ሱሬ በተባለ ቦታ የውሃ ጉድጓድ መቆፈር፣ በሶማሌ ሞያሌ አካባቢ ልዩ ስሙ ኤል ካሉ በተባለ ቦታ የውሃ ጉድጓድ መቆፈር፣ በሶማሌ ሞያሌ ከተማ የእንስሳት ገበያ ማደስ፣ በኦሮሚያ ሞያሌ ከተማ የእንስሳት ገበያ ማደስ፣ በሶማሌ ሞያሌ ከተማ የቄራ ቦታ ሰፊ የተቋም ግንባታ፣ በሞያሌ ከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራዎችና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡
ፕሮጀክቱ ችግረኞችን ከመርዳት ባሻገር በኢትዮጵያ ሞያሌና በኬንያ ሞያሌ ድንበሮች የሚገኙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሮችን ለማጠናከር እንደሚረዳ ታምኖበታል ተብሏል፡፡
በ2022 የበጀት ዓመት የተለያዩ የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎችን ማከናወኑን የጠቆመው አክሽን ፎር ዘ ኒዲ፤ በዚሁ ወቅት 1.3 ቢሊዮን ብር በሥራ ላይ ማዋሉንና ከዚህ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የገንዘብ ድጋፍ ያገኘው ከዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ (UNHCR) መሆኑን አመልክቷል፡፡
አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢን ኢትዮጵያ፤ በ2004 ዓ.ም በጥቂት ለጋሾችና በጎ አድራጊዎች የተመሰረተ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ 11 ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመክፈትና ከ700 በላይ ቋሚና ከፍተኛ ባለሙያዎችን በመቅጠር፣ በሁሉም ክልሎች ሰብአዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ድርጅት መሆኑ ታውቋል፡፡
Saturday, 09 September 2023 00:00
“አክሽን ፎር ዘ ኒዲ” ከኢጋድ ጋር የ3.854 ሚ. ዩሮ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረመ
Written by Administrator
Published in
ዜና