Monday, 11 September 2023 00:00

ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ያሰራውን የህጻናት ማቆያ ማዕከል አስመረቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)
• ከሄሪሜክስ ትሬዲንግ ባለቤት ባገኘው ድጋፍ ለ100 ችግረኛ ወገኖች ማዕድ አጋርቷል
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፣ በትላንትናው ዕለት ረፋድ ላይ በአራዳ ክ/ከተማ ገዳም ሰፈር በሚገኘው ወረዳ 5 አስተዳደር ግቢ ውስጥ ያደራጀውን የህጻናት መንከባከቢያ ማዕከልና ፕሮጀክት ቢሮ የመንግሥት ሃላፊዎች፣ የድርጅቱ የህይወት ዘመን አምባሳደሮችና ባለሃብቶች በተገኙበት አስመረቀ፡፡
ድርጅቱ ያስመረቀው ይሄ የህጻናት የቀን ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከል፣ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የህጻናት፣ እናቶችና ወጣቶች የጎዳና ህይወት ተጋላጭነት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ተብሏል፡፡
በመዲናችን አዲስ አበባ 10ሺ500 ህጻናትና 13ሺ500 አዋቂዎች፣ በድምሩ 24ሺ ሰዎች የጎዳና ህይወት እንደሚመሩ በ2010 የተደረገ ጥናት የሚያመለክት ሲሆን፤ የጎዳና ልጆች ፕሮጀክት ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው ተነግሯል፡፡
የህጻናት መንከባከቢያ ማዕከሉን እውን ለማድረግ ዶ/ር ኢያሱ የተባሉ ግለሰብ የራሳቸው የሆነውን ቤት ለሜሪ ጆይ በስጦታ ያበረከቱ ሲሆን፤ ኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም ዴንቨር የኢትዮጵያ ኮሙኒቲና ዓለምጸሃይ ወዳጆ የጥበብ መድረክ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ የጎዳና ህጻናትን ህይወት ለመለወጥ በሚያደርገው ጥረት ኢትዮ ቴሌኮም በቀጣይነትም እንደሚያግዛቸው ቃል ገብቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሜሪ ጆይ ከሄሪሜክስ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ሃርሞን ሃጎስ በተደረገለት የ250ሺ ብር የገንዘብ ድጋፍ 100 ለሚደርሱ ችግረኛ ወገኖች በዛሬው ዕለት ማዕድ አጋርቷል፡፡
የመንግሥት ሃላፊዎችና ባለሃብቱ በተገኙበት ለእነዚህ ችግረኛ ወገኖች ምሳ የማብላት ሥነስርዓት ከመደረጉም በተጨማሪ ለአዲስ ዓመት መዋያ የሚሆኑ እንደ ዘይት፣ ዱቄት፣ ዶሮና የመሳሰሉት የአውዳመት መሰረታዊ ፍጆታዎች ተበርክቶላቸዋል፡፡
የገንዘብ ድጋፉን ያደረጉት ከሜሪ ጆይ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት መሆኑን የገለጹት የሄሪሜክስ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ሄርሞን ሃጎስ፤ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ለችግረኛ ወገኖች የአቅማቸውን በማድረጋቸው ደስተኛ መሆናቸውንና ወደፊትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የሚለውን ፕሮጀክት ከጀመርን 17 ዓመት ሞልቶናል ያሉት የሜሪ ጆይ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር በበኩላቸው፤ በእነዚህ ዓመታትም ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ መደጋገፍ እንደምንችል በተግባር አስመስክረናል ብለዋል፡፡
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፤ በ1986 ዓ.ም የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡
Read 862 times