Saturday, 09 September 2023 00:00

በመጪው ህዳር ወር “አጋርነት ለዘላቂ የፊልም ዕድገት” በሚል መሪ ቃል የፊልም ፌስቲቫል ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሊንኬጅ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ማዕከልና የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች ድርጅት፣ በመጪው ህዳር ወር፣ የፊልም ፌስቲቫል በትብብር እንደሚያካሂዱ ተገለጸ።
“አጋርነት ለዘላቂ የፊልም ዕድገት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የፊልም ፌስቲቫል፤ ከህዳር 23 እስከ ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ለ8 ቀናት፣ በልዩ ልዩ ኹነቶች እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
የፊልም ፌስቲቫሉንና በመንግስት አካላትና በግል ድርጅት የተፈጠረውን አጋርነት አስመልክቶ አዘጋጆቹ ከትላንት በስቲያ ሃሙስ፣ በአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሊንኬጅ የኪነጥበብ ስራዎች ማዕከልና የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት፣ የፊልም ፌስቲቫል በትብብር ለማዘጋጀት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው   የተጠቀሰ ሲሆን፤ የዚህ አጋርነት ዋነኛ ዓላማው የኢትዮጵያን የፊልም ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ መሆኑ ተብራርቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና ለአገራዊ የገፅ ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ዓላማን ያደረገ ነው ተብሏል - አጋርነቱ፡፡
“ይህ አጋርነት  ከሚኖሩት ዘርፈ ብዙ ክንውኖች አንዱ፣ በ2016 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረገውን 18ኛውን የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል (ኧርዞፕያ)ንና የአዲስ አበባ ከተማ ሲኒማ ቤቱን የፊልም ፊስቲቫልን በድምር ይመለከታል፡፡” ብለዋል - አዘጋጆቹ በመግለጫቸው፡፡
በመጪው አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ ፊልም መታየት ከጀመረ 100ኛ ዓመት መሙላቱ ደግሞ ለፊልም ፌስቲቫሉ እራሱን የቻለ ድምቀትና አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡  የፊልም ፌስቲቫሉን በትብብር ለማዘጋጀት የመንግስት አካላትና የግል ድርጅት የፈጠሩት ይህ አጋርነት በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን እንደማይቀር የገለጹ አስተያየት ሰጪዎች፤ መሰል አጋርነቶች መቀጠላቸው ለኪነጥበቡ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡Read 306 times