Sunday, 10 September 2023 00:00

ከሁሴን ማኬይ ጋር (የESMM ዲያሬክተር)

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

• ESMM እና ከ25 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበተባቸው ስራዎቹ
• "ከምናገኘው 5 ዶላር መልሰን ከ4 ዶላር በላይ ወጭ እያደረግን ነው።"
• “ኢትዮጵያ በ5ሺ፤ በ10ሺና በማራቶን ብቻ መወሰን የለባትም። በመካከለኛና በአጭር ርቀት ውድድሮች ውጤታማ
አትሌቶችን ማግኘት ይቻላል”
• “ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ወደአውሮፓ ተጉዘው ልምምድና ዝግጅት እንዲሰሩ ግፊት ማድረጋችንን ቀጥለናል”
• “የኢትዮጵያን አትሌቶችን ከቤተሰብ መለየት አንችልም”

ሁሴን ማኬይ ከአትሌቲክስ ስፖርት ጋር የተገናኘው  በአጭርና መካከለኛ ርቀቶች ሯጭነት ነው። በፕሮፌሽናል ደረጃ ተወዳድሮ ያሳለፈ ሲሆን በ1990ዎቹ መግቢያ ላይ በታዋቂው የስፖርት ትጥቅ አምራች ሪቦክ ስፖንሰርሺፕ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሮጧል። በ400 እና 800 ሜትር ሯጭነት ይታወቅም ነበር፡፡ በ1992 እኤአ ላይ በባርሴሎና ኦሎምፒክ እንዲሁም በ1993 እኤአ በስቱትጋርት በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፏል፡፡ የሩጫ ውድድሮችን መሣተፉን እንዳቆመ በቀጥታ ወደ አሰልጣኝነት ሙያው ገብቷል። በተለይ ኑሮውን በአሜሪካ ካደረገ በኋላ በአሰልጣኝነት ብቁ ሆኖ ለመሥራት ከፍተኛ ትምህርት ተከታትሏል፡፡ የስፖርት አስተዳደርና ማርኬቲንግ ኩባንያ ያቋቋመው ከዚህ በኋላ ነው። ኤሊት ስፖርት ማኔጅመንትና ማርኬቲንግ በሚል ስያሜ የአትሌቲክስ ኩባንያውን ከ25 ዓመታት በፊት መሠረተ፡፡
ESMM በዋናነት በአትሌቶች ወኪልነት የዓለም አትሌቲክስ ደረጃና ደንብ ጠብቆ የሚሰራ ነው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ የወቅቱን ታላላቅ አትሌቶች  አሰባስቦ ይገኛል።  የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮኖች ይገኙበታል።  ዲያሬክተሩ ሁሴን ማኬይ ሲሆን  በዓለም አትሌቲክስ ማህበር  በአትሌቶች ወኪልነት ፍቃድ ተሰጥቶታል። የዓለም አትሌቲክስ አሰልጣኞች ማህበርም አባል ሆኖ ያገለግላል። የአትሌቲክስ ኩባንያው ESMM ተቀማጭነቱን በቼስተር ፔንሲልቨኒያ አሜሪካ ያደረገ ቢሆንም በ13 የተለያዩ አገራት ከ150 በላይ አትሌቶችን በወኪልነት እያስተዳደረ ነው።  የአሜሪካ፤ የሞሮኮ፤ የፈረንሳይ፤ የኳታር፤ የቻይናና የኢትዮጵያ አትሌቶች ተሰባስበዋል። ከኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል በጎዳና ላይ ሩጫና በማራቶን ከወንዶች ሌሊሳ ዴሲሳ፤ ጌታነህ ሞላ፤ ሹራ ኪታታ ... ከሴቶች ማሬ ዲባባ፤ ጎይተቶም ገብረስላሴ፤ ሩቲ አጋና ሰንበሬ ተፈሪ ይጠቀሳሉ። በትራክ ውድድሮች ሰለሞን ባረጋ፤ ለሜቻ ግርማ፤ ጌትነት ዋለ በሴቶች መካከለኛ ርቀት እነ ሐብታም አለሙ ከኩባንያው ጋር አብረው የሚሰሩ ናቸው።
ESMM እና ከ25 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበተባቸው ስራዎቹ
ኤሊት ስፖርት ማኔጅመንትና ማርኬቲንግ በዓለም አትሌቲክስ ውስጥ አስደናቂ ውጤቶችን በማስመዝገብ እየታወቀ ነው፡፡ በስሩ የሚገኙ አትሌቶች ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮችን ያሸነፉ፤ በዓለም ሻምፒዮናና በኦሎምፒክ ከ10 በላይ ልዮ ልዮ ሜዳሊያዎችን የተጎናፀፉ፤ በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ቋሚ ተሳትፎ የሚያደርጉና ውጤታማዎች ናቸው። የአትሌቲክስ ተቋሙ በአትሌቶች ውክልና ያገኘውን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ከዓለም አትሌቲክስ ማህበር፤ ከአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን፤ ከአሜሪካው ትራክ ኤንድ ፊልድ አሶሴሽን በአጋርነት መሥራቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡  በዓለምአቀፍ ውድድሮች ከአትሌቶች፤ ከፌደሬሽኖች፤  ከአሰልጣኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል። የአትሌቶችን  የስልጠናና  የውድድር መርሐ ግብሮች በማሰናዳት ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኙ የመጡ የውድድር እቅድና ዝግጅቶችን ይነድፋል፡፡ ከዓለም አቀፍ ውድድር አዘጋጆች በሚፈጥረው ግንኙነት ውጤታማ ተሳትፎዎች የሚያደርግም ነው። አትሌቲክሱን ከታዋቂ የስፖርት ትጥቅ አምራቾች፤ የስፖርት ምርቶችና ቁሳቁስ አቅራቢዎች በማስተሳሰር ለጋራ ጥቅም የሚሰራ ነው፡፡
ኢኤስኤምኤም ESMM በስፖርት አስተዳደር ከሚያከናውናቸው ተግባራት ባሻገር በማርኬቲንግም ከፍተኛ እንቅስቃሴ አለው። አትሌቶች፤ አሰልጣኞችና የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ከስፖርት ትጥቅ አምራቾችና ሌሎች የስፖርት ምርት አቅራቢዎች ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ያቀላጥፋል። ሁሉንም ወገን የሚያስማሙ ውሎችን በማርቀቅ ያቀርባል። በገቢ  በኩል ተመጣጠኝ ክፍፍል እንዲኖርም ይንቀሳቀሳል። ከስፖርት ትጥቅ አምራቾች የአሜሪካው ናይኪና የጀርመኑ አዲዳስ ጋር ተቀራርቦ ይሰራል። ከተለያዮ ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት ጋር አጋርነት በመፍጠር ከፍተኛ ልምድ አካብቷል፡፡ ማውርተን፤ ጋቶርዴ፤ቮልቮ  ፓናሶኒክና ሌሎች ኩባንያዎች ጋር እየሰራ መሆኑን በኩባንያው ድረገፅ ላይ የታተመው መረጃ ያመለክታል። ከኩባንያው ጋር የሚሰሩ የኢትዮጵያ አትሌቶች በተለይ ከአሜሪካው ናይኪ እና ሞርተን ጋር በስፖንሰርሺፕ ተሳስረዋል። ሞርተን በካርቦሐይድሬት የበለፀጉ ኃይል ሰጭ መጠጦችና ምርቶችን የሚያበረክት ሲሆን ናይኪ ደግሞ በስፖርት ትጥቅ አቅራቢነቱ ይታወቃል።
የስፖርት ኩባንያው በድረገፁ ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች ዘርዝሯል። አትሌቶች ከስፖንሰሮች  ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያደራጃል። ሙሉ ሃላፊነት በመውሠድም የገቢ ምንጫቸውን እንዲጠናከርና ተጨማሪ የንግድ  እድሎችን በመፍጠር እንደሚሰራ ያብራራል፡፡ በአትሌቲክሱ የሚነድፋቸው የማርኬቲንግ ስትራቴጂዎች የአትሌቶችን ፍላጎትን የተንተራሱ ናቸው። በሕትመት፤ በዲጂታል የሚዲያ አውታሮች፤ በቲቪ ብሮድካስትና በድረገፅ እያስተዋወቀ  የአትሌቶችን የሩጫ ዘመናቸውን ያስተዳድራል።   ከ25 ዓመታት በላይ ልምድ ባካበተው ኤሊት ስፖርት ማኔጅመንትና ማርኬቲንግ የሚገኙ ሰራተኞች አትሌቶች የነበሩ ናቸው። በአትሌቲክስ የተለያዩ ዘርፎች የመሥራት ልምድ ያላቸው፤ በአትሌቲክስ ስልጠና የተማሩና የላቀ እውቀት ካላቸው ሌሎች ሙያተኞች ጋር ተረዳድተው የሚሰሩ ናቸው፡፡ የአትሌቲክስ ዝግጅት በጥናትና በምርምር እንዲታገዝ የሚጥሩ፤ የልምምድና የስልጠና ሳይንስን በመከተል እንደሚሰሩም ገልፀዋል። ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁ የሚያደርጉ የስልጠናና የልምምድ መርሃ ግብሮችን ይነድፋሉ። አትሌቶችን በውክልና ሲይዙ  ለረጅም ጊዜ በሚቆይና ዘላቂነት ባለው የስራ ግንኙነት ነው፡፡
ESMM ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጋር
"ከምናገኘው 5 ዶላር መልሰን ከ4 ዶላር በላይ ወጭ እያደረግን ነው።"
“ኢትዮጵያ በ5ሺ፤ በ10ሺና በማራቶን ብቻ መወሰን የለባትም።  በመካከለኛና በአጭር ርቀት ውድድሮች ውጤታማ አትሌቶችን ማግኘት ይቻላል”
ከሁሴን ማኬይ ጋር የተገናኘነው ቡዳፔስት ባስተናገደችው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ነው። ቡዳፔስት ለምን እንደተገኙ ጥያቄ  የቀረበለት ዲያሬክተሩ ሁሴን “በዓለም ሻምፒዮናና በሌሎች መድረኮች የምንገኘው ለምንወክላቸው አትሌቶች ያለብንን ኃላፊነት ለመወጣት ነው። ፌዴሬሽኑንም ለማገዝ ነው። አትሌቶች አገርን ወክለው ከሚሳተፉት ውድድር በኋላ ሌሎች ውድድሮች እንዳሏቸው ይታወቃል። በዚያ በኩል ዝግጅት ለማድረግ በቅርበት መገኘት ያስፈልጋል። ወቅታዊ ብቃታቸውን ለመከታተል በዓለም ሻምፒዮናው መገኘት አለብን፤ በምክርና በሙያዊ ድጋፍ አትሌቶችን እንጠቀማለን። ከስፖንሰሮች ጋር የገቡትን ውል ማስፈፀም ይኖርብናል።” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ESMM በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሲንቀሳቀስ ከ18 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን የሚገልፀው ዲያሬክተሩ፤ በሁሉም የአትሌቲክስ ውድድሮች እንደሚሰሩ  ከ800ሜ እስከ ማራቶን አትሌቶችን እንደያዙና የኢትዮጵያ አትሌቶችን በቤተሰባዊ ግንኙነት የሩጫ ዘመናቸውን እያስተዳደርን ነው ብሏል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአትሌት ተወካዮችና ማናጀሮች ስላለው ግንኙነት ሲያብራራ ደግሞ “በምንከተለው አሰራር ከፌደሬሽን ጋር ምንም አይነት ግጭት ውስጥ አንገባም፡፡ በመካከላችን የሃሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል። የምንሰራው ግን በአንድ አላማ ነው፤ አትሌቶችን ለስኬት ማብቃት፡፡ ኢትዮጵያ ለስራችን እጅግ ምቹ የሆነች አገር ናት፡፡ ለስራ በቆየንባቸው ዓመታት በፌደሬሽን በኩል ለውጦች ተፈጥረዋል። በአትሌቶችም ትውልዶች እየተፈራረቁ ቆይተዋል። ከሚለዋወጡ ሁኔታዎች ጋር ስራችንን አጣጥመን እየሄድን ነው፡፡ በመካከላችን ያለው ግንኙነት እየጠነከረ ሄዷል።  ያሉን ግንኙነቶች በጋራ ጥቅም የሚያስማሙን እንዲሆኑ ትኩረት እናደርጋለን፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የቻልነውን ምርጥ አስተዳደር እያሰፈንን ነው። በማርኬቲንግ መነቃቃት እየፈጠርን ቢሆንም በቂ ግን አይደለም፡፡” ሲልም ተናግሯል።
“በስፖርቱ ዙርያ ያሉትን ባለድርሻ አካላትን ትኩረት እየጠየቅን ነው። በተለያዩ አዳዲስ ስትራቴጂዎች አብረን የምንሰራባቸውን እድሎች ማበረታት ይገባል። ፌዴሬሽኑን ወደ ጠቃሚ አቅጣጫዎች መገፋፋት ነው የምንፈልገው፡፡ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ገበያቸውን ለማስፋትና የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፊ ጥረት አድርገናል። በቂ ትኩረት ባለማግኘታችን የተወሰኑ ክፍተቶች አሉብን። በምንሰራቸው ተግባራት በደንብ ባለመደራጀታችን ብዙውን እያጣን ነው፡፡ የሌላው ዓለምን የማርኬቲንግ እንቅስቃሴ ማካሄድ አለብን፡፡ በስፖርት ዙርያ ያለውን ንግድ፤ ወቅቱን የጠበቀ የስልጠና ስርዓትና ልምምድ፤ ከውድድር የማገገም ስራዎችን መተግበር ይኖርብናል።” ይላል  ዲያሬክተር ሁሴን በኢትዮጵያ ውስጥ ኩባንያቸው ያለውን ግንኙነት ሲያብራራ “በኩባንያችን ከተለያዩ ፈተናዎች ጋር በመጋፈጥ ነው የምንሰራው ኢትዮጵያ ውስጥ በገንዘብም በዕውቀትም ኢንቨስት አድርገናል። አትሌቶችን በመደገፍ ፌዴሬሽኑም በተለያየ መንገድ በማገዝ ነው የቆየነው። በእርግጥ ኪሳራ ውስጥ አልገባንም። ግን ከምናገኘው 5 ዶላር መልሰን ከ4 ዶላር በላይ ወጭ እያደረግን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው ቢሯችን ከ20 በላይ ሰራተኞች አሉን። አሰልጣኞች፤ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ ፌዝዮቴራፒስቶች፣ ጉዳዩ አስፈጻሚዎችና ሾፌሮች የምንሰራውን የወደፊቱን ስኬት እያሰብን ነው። የአትሌቲክስ ባለድርሻ አካላት እንደ አጋር መታየት እንፈልጋለን።”
“ባለፉት 5 ዓመታት ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ የተለመዱ ውጤቶች እየራቁ መጥተዋል። በሌሎች አገራት እየተነጠቁ ናቸው። በምንሰጠው ስልጠና ከድሮው አሠራር ጋር ተጣብቀን መቆየት የለብንም። በአዳዲስ የስልጠና መርሃ ግብሮችና እቅዶች በመስራት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን መሳተፍ አለብን። አትሌቲክሱን የሚመሩ አካላት በአትሌቶች ውጤታማነት ላይ የሚተጉ ባለሙያዎችን በመደገፍ መስራት አለባቸው። ስፖርቱ ተለውጧል፣ ኢትዮጵያም ተቀይራለች የሚያስብለኝ ሁሌም የሚያሳስበኝ አትሌቶችን ለስኬት የሚያበቃ አስተያየት እንዲቀርና ቀጣይ ትውልድ የሚሄድበት የትኩረት አቅጣጫ ነው።” በማለትም ሁሴን ማኬይ ያሳስባል።
ሁሴን ማኬ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት የትራክ ውድድሮችና በጎዳና ላይ ሩጫዎች  ላይ በውጤታማነት ለመቀጠል ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት መሰረተ ልማቶች መገንባት አለባቸው። በኢትዮጵያ ስፖርቱን የሚመሩት የተቻላቸውን እያደረጉ ሊሆን ይችላል ያለው ዲያሬክተሩ፤ ግን ተጨማሪ ስራዎች እንደሚጠብቃቸው ሲያስረዳ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ትራኮች፣ ጅናዚየሞችና ካምፖች የሚገነቡበትን ስራዎችአቅጣጫ መከተል  አለባቸው ይላል።
“ኢትዮጵያ በ5ሺ፤ በ10ሺና በማራቶን ብቻ መወሰን የለባትም። በሌሎችም የውድድር ዓይቶች ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። በመካከለኛና በአጭር ርቀት ውድድሮች ውጤታማ አትሌቶችን ማግኘት ይቻላል። በሜዳ ላይ ስፖርት አዳዲስ አትሌቶች ለማውጣትም ፍላጎቱ አለን።” በማለትም ኤሊት ስፖርት ማኔጅመንትና ማርኬቲንግ ያለውን እቅድ አመልክቷል።በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ ከስነ-ምግብ ባለሙያዎችና ከፌዝዮቴራፒስቶች ጋር በተገናኘ እቅድ መስራት ተገቢ መሆኑን በመምከርም አትሌቶችን ከሚጠቅሙ ዘመናዊ የስልጠና ስርዓቶች ጋር መላመድ አለብን ሲል ተናግሯል ።
“ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ወደአውሮፓ ተጉዘው ልምምድና ዝግጅት እንዲሰሩ ግፊት ማድረጋችንን ቀጥለናል”
“የኢትዮጵያን አትሌቶችን  ከቤተሰብ መለየት አንችልም”
“የዓለምን አትሌቲክስ በወቅታዊ በብቃት ለመወዳደር አትሌቶችና አሰልጣኞች ወቅቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲወስዱ ማድረግ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ ብዙዎቹ ለለውጥ ዝግጁ አይደሉም። አዳዲስ ሃሳቦችን ለመቀበል አይፈልጉም። ኩባንያችን የሚያምነው ሁልጊዜም በአዳዲስ የአትሌቲክስ አቅጣጫዎች መስራት ያስፈልጋል። ወደኋላ መቅረት የለብንም። ለምሳሌ ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ጋር በተገናኘ የሚደረገውን ዝግጅት መመልከት ይቻላል። ኢትዮጵያውያን በሞቃት አገር ለሚካሄድ ውድድር በክረምት ወራት መሰልጠን የለባቸውም በማለት ተደጋሚ ምክር ሰጥተናል። የኢትዮጵያ አትሌቶች በክረምት ወራት ልምምድ መስራቸው ለጉዳት ሲያጋልጣቸው ውጤታችንን ሲያበላሽ  ነው የታዘብነው። ስለዚህም ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ወደአውሮፓ ተጉዘው ልምምድና ዝግጅት እንዲሰሩ ግፊት ማድረጋችንን ቀጥለናል። ይህን የምንመክረው ያሉት በቂ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በመጠቀም በከፍተኛ አልቲትዩድ የተሟላ ብቃት ለማምጣት ለሌሎችም ምክንያቶች ነው። በቀጣይ ለፓሪስ ኦሎምፒክ ይህ ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ ነው የምንፈልገው።”
በመጨረሻም ሁሴን ማኬይ በአትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር ማነፃፀር ልክ አለመሆኑን ነው የገለፀው። “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ናት። ከቤተሰባዊ ግንኙነት፤ ከባህል አንፃር፣ ከአኗኗር ዘይቤ ጋር አትሌቲክስን ካያያዝነው ። ኢትዮጵያውያን ከዘመዶቻቸው ጋር አርቀህ ማሰራት አትችልም። ከወንድሞቻቸው፣ ከእህቶቻቸውም፣ ከባሎቶቻቸው፣ ከሚስቶቻቸው ጋር መስራታቸውን ለመቀየር አዳጋች ነው። የኢትዮጵያን አትሌቶችን  ከቤተሰብ መለየት አንችልም። እኛም  ያንን በመረዳት ነው ስራችንን የቀጠልነው።” ብሏል፡፡

Read 336 times