Tuesday, 12 September 2023 20:05

በአዲሱ ዓመት ለአገሬ የምመኘው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

መመኘት አልተከለከለም አይደል?

 ጊዜው በትክክል ትዝ አይለኝም። ግን የአዲስ ዓመት በዓል ላይ እንደነበር አስታውሳለሁ። አንድ የኢቲቪ ጋዜጠኛ ለአንድ በሥራ ላይ ለነበረ የትራፊክ ፖሊስ ጥያቄ ያቀርብለታል። “የአዲሱ ዓመት ዕቅድህ ምንድነው?” የሚል። ትራፊክ ፖሊሱም ሲመልስ፤ “እኔ እንኳን የግል ዕቅድ የለኝም፤ መ/ቤቴ ዕቅድ ካለው ግን እሱን ለመፈጸም ዝጁ ነኝ” አለ። የእኔም ነገር እንዲሁ ነው የሆነው ዛሬ። የመጀመሪያ ሃሳቤ በራሴ የአዲስ ዓመት ዕቅድ ወይም ምኞት ዙሪያ የሚያጠነጥን ፅሁፍ መከተብ ነበር፡፡ በኋላ ግን የራሴን ትቼ  በአዲሱ ዓመት ለአገሬ የምመኘውን ብተነፍስ ወደድኩ። “በመጀመሪያ የመቀመጫየን” አለች - እንደተባለው መሆኑ ነው።
እነሆ አሮጌውን ዓመት አጠናቅቀን አዲሱን (2016) ዓመት ልንቀበል ከ72 ሰዓታት ያነሰ ጊዜ ብቻ ነው የቀረው። እንዳለመታደል ሆኖ 2015 ዓ.ም ከቀደሙት ሁለት ዓመታት የባሰና የከፋ እንጂ የተሻለ ሆኖ አላለፈም። የተሻለ ዓመት ልናደርገው አልቻልንም ቢባል ይሻላል (ለእውነት የቀረበ ነውና!) ለምን ቢሉ? ተጠያቂው ራሳችን ነንና!!
ከሁለት ዓመቱ የህወሃትና የፌደራል መንግስቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ፣ በስንት ፀሎትና በእነ አሜሪካ ተፅዕኖና ግፊት ሳቢያ እፎይ ያልን ቢመስለንም፤ ወዲያው ግን ወደ አዲስ ጦርነት መሸጋገራችን፣ ትልቁ  የአገራችን - (የክፍለ ዘመኑ) ትራጄዲ ነው ማለት ይቻላል።
አሁንስ በአማራ ክልል እንደ ዘበት ከገባንበት ጦርነት እንዴት ነው የምንወጣው? እንዴት ነው በዘላቂነት በክልሉ ሰላምና መረጋጋት የምንፈጥረው? አሁንም ለሰላም ድርድር እነ አሜሪካና የአፍሪካ ህብረት መምጣት አለባቸው ማለት ነው? ምክንያቱም በራሳችን መንገድ በውይይትና በድርድር የመፍታት አዝማሚያ በፍፁም እየታየ አይደለም።
በሌላ በኩል አሜሪካ ደግሞ ስስ ብልታችንን ጠንቅቃ አውቃዋለች። (አንዴ ወደ ጦርነት ከገባን፣ በቀላሉ እንደማንወጣ ገብቶታል) ስለዚህም የፕሪቶሪያው የሰላም ድርድር ዓይነት የአጋፋሪነት ሚና ለመውሰድ የቋመጠች ትመስላለች። በእኛ በኩል በማንም አደራዳሪነት ይሁን ዜጎችን በከንቱ ከሚፈጀውና ለሰቆቃ ከሚዳርገው ዘግናኝ ጦርነት ብንወጣና ሰላምና መረጋጋት ቢሰፍን ባልጠላን ነበር። ክፋቱ ግን እነ አሜሪካ የገቡበት ነገር ጣጣው ማብቂያ የለውም፡፡ ሽምግልና ብለው የባሰ ቀውስና ብጥብጥ ፈጥረውም ሊወጡም ይችላሉ፡፡ እነ ኢራቅ… ሊቢያ… አፍጋኒስታን… ሶሪያ… ምን እንደሆኑ አይተናል፡፡
የፈረሱ አገራት ነው የሆኑት። እውነታው ይህን ቢመስልም ቅሉ፣ በራሳችን ጊዜና በራሳችን አቅም ከጦርነቱ ወጥተን ወደ ሰላም ድርድር መግባት እስካልቻልን ድረስ ሌላ አማራጭ አይኖረንም - የአሜሪካና አጋሮቿን የሰላም ድርድር ሃሳብ ከመቀበል ውጭ። (ወደን ሳይሆን ተገደን!) ያኔ ደግሞ አዲስ ወጥመድ ውስጥ ገባን ማለት ነው።
በነገራችን ላይ በአሜሪካ አጋፋሪነት የተካሄደው የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት፣ ጦርነቱን በማቆሙ እፎይ ብንልም፣ የምንከፍለውን ዋጋ (ዕዳችንን) ግን ገና በቅጡ አላወቅነውም። (Free Lunch የሚባል ነገር የለማ!) እናም በጦርነት መፍትሄ እንደማይመጣ እያወቅን፣ በማያዋጣ መንገድ ከመባከን የሰላምን አማራጭ መውሰድ ብልህነት ይመስለኛል። ወደድንም ጠላንም ከጦርነትና እርስ በርስ ከመጠፋፋት አዙሪት ወጥተን፤ ወደ ሰላማዊ ውይይትና ድርድር መግባት  ይኖርብናል - በእነ አሜሪካ ሳይሆን በራሳችን መንገድ።
የፖለቲካ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት የመፍታት ባህል በአንድ ጀንበር እንደማይመጣ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ግን በሂደት ባህል ይሆን ዘንድ ዛሬ መጀመር አለበት፡፡ ጨክነንና ቆርጠን ዛሬ - አሁኑኑ ልንጀምረው ይገባናል። ከዛም የሁልጊዜ ልምምዳችን ማድረግ፡፡ በትጋትና በፅናት ከቀጠልንበት፤ ያለጥርጥር በሂደት ባህል እናደርገዋለን፡፡ ከዚህ ውጭ ደግሞ ሌላ መፍትሄ የለንም። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ችግሮችና አለመግባባቶች ሁሉ ጦር እየሰበቅን፤ የጦርት ነጋሪት እየጎሰምን መቀጠል አንችልም። እውነት ለመናገር አቅሙ የለንም። የአገሪቱ ወገብ ተሰብሯል። ህዘቡ በጦርነትና ተያያዥ መከራዎች ጫንቃው ጎብጧል። ተጨማሪ ጦርነትም ሆነ ግጭት የመቋቋም አቅሙም ሆነ ችሎታው ጨርሶ የለንም!! እንደ አገር መፍረስ ካልፈለግን በስተቀር እስቲ ከሁለት ቀናት በኋላ በምንቀበለው አዲስ ዓመት ለአገሬ የምመኘውን ልነቁጥ እነሆ፡-
በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የጦርነትና ግጭት ወሬ የማንሰማበት፤
የዜጎች ግድያና መፈናቀል፤ እንግልትና ሰቆቃ በዘላቂነት የሚያከትምበት፤
ፖለቲከኞችም ይሁኑ አክቲቪስቶች ጦርነትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ ተንኳሽ ቃላትን መወራወር በህግ የሚከለከሉበት፤
ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውረውና ሰርተው የመኖር ህገመንግስታዊ መብታቸው የሚረጋገጥበት፤
የሰብአዊ መብቶች የሚከበሩበትና የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፤
የፖለቲካ ልዩነቶችን በሃይል አማራጭ ሳይሆን በውይይትና በድርድር የመፍታት ልምምድ የሚጀመርበት፤
ለኢኮኖሚ ስብራቶቻችንንና ለማህበራዊ ቀውሶቻችን ልሂቃኖቻችን ተግባራዊ መፍትሄ የሚያፈልቁበት ዜጎች በሰላም ከቤታቸው ወጥተው በታጣቂዎች የማይታገቱበት፤  ዘመን እንዲሆን እሻለሁ።
2016 ዓ.ም የሰላምና መረጋጋት፤ የፍቅርና አንድነት ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ!!
ቅድም እንደጠቀስኩት ለአዲሱ ዓመት የራሴ ዕቅድና ምኞት ስለሌለኝ ሳይሆን አገራችንና ህዝባችን ተራራ የሚያህል ችግርና መከራ ተጋፍጠው የግል ጉዳይን ማንሳት ቅንጦት መስሎ ስለታየኝ ነው። በእርግጥም በውዱ ጋዜጣ ቦታ ላይ ያለውም በዚህ ክፉ ጊዜ ስለግል የአዲስ ዓመት ዕቅድና ምኞት ቅንጦት ነው የሚሆነው። ስለዚህም ተዘርዝሮ ከማያልቀው የአገራን አያሌ ችግሮችና መከራዎች መካከል አንገብጋቢዎቹን እያነሳሁ፤ በአዲሱ ዓመት እንዴት እንዲለወጥልን እንደምሻ ወይም እንደምመኝ የበዓል ሃሳቤን ልገልፅ እወዳለሁ።

Read 679 times