Thursday, 14 September 2023 00:00

የአርታኢያን ማህበር በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ጉዳይ ላይ ተወያየ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኀበር (Editors Guild of Ethiopia) 6ኛ ዙር የቁርስ ላይ የውይይት መርሐግብሩን  ዛሬ መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም  በሒልተን ሆቴል አካኺዷል።
የዕለቱ የውይይት መርሐግብር ያተኮረው “ሰብዓዊ መብቶች እና መገናኛ ብዙሃን፤ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጉዳይ የአርታኢው ሚና (Media and Human Rights: Role of Editors in Protection of Human Rights)” በሚል ርዕሰጉዳይ ላይ ነው። የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት  ጋዜጠኛ ፍሬው አበበ ናቸው፡፡
አቶ ፍሬው በፅሑፋቸው፣ የሰብዓዊ መብቶች የሰው ልጆች ሰው በመኾናቸው የተጎናጸፏቸው ስለመኾኑ፣ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ህገመንግሥት መሠረታዊ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ጭምር ተቀብሎ ማካተቱን በጠንካራ ጎኑ አንስተዋል።
ኾኖም በአፈፃፀም ሒደት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ቢኾንም፣ መገናኛ ብዙኃን በችግሩ ስፋት ልክ በቂ ሽፋን እየሰጡ አለመኾኑን በአሳሳቢነቱ አብነቶችን በመጥቀስ አስረድተዋል።
መገናኛ ብዙኃንና አርታኢያን፤ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን በመደበቅ ለተጠርጣሪ ወንጀለኞች ሽፋን እንዳይሰጡ በብርቱ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ፣ ዘገባዎች በሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንዳይጠለፉ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ  እንደሚገባ አመልክተዋል። በርዕሰ ጉዳዩ ላይም በማህበሩ አባላት  ሰፋ ያለ ውይይት ተካኺዷል።
የመንግስት መገናኛ ብዙኃን፣ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን የሚያነሱት፣ ከዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ኢትዮጵያን የተመለከቱ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሪፖርት ሲወጣ፣ ምላሽ ወይም ማስተባበያ ለመስጠት ብቻ እንደሆነም በውይይቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በመንግሥት ባጀት የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የተሻለ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በቂ ሽፋን እንደማያገኙም በማህበሩ አባላት ተነስቷል፡፡
የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በበላይ አለቆች “የአገር ገጽታ ያበላሻሉ” በሚል ሽፋን እንደማያገኙም ተጠቅሷል - በውይይቱ ወቅት፡፡
ሪፖርተሮችም  ሆኑ አርታኢያን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በቁርጠኝነት እንዲዘግቡ ከተፈለገ ከተቋማቸው ዋስትና ሊያገኙ እንደሚገባም ተነስቷል፡፡

Read 1975 times