Saturday, 16 September 2023 00:00

አዲስ አበባ ከፍተኛ የተፈጥሮ አደጋ ያሰጋታል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

“ከፍተኛ ሙቀት፣ ድርቅና የጎርፍ አደጋ ዋነኛ ስጋቶቿ ናቸው”
               
          አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የተፈጥሮ አደጋ ስጋት ያጠላባት ከተማ እንደሆነች ሰሞኑን ይፋ የተደረገ አንድ የጥናት ሪፖርት አመለከተ፡፡ ከፍተኛ ሙቀት፣ ድርቅና የጎርፍ አደጋ ዋነኛ የከተማዋ ስጋቶ ናቸው ተብሏል፡፡
የውድ ዌል ክላይሜት ሪሰርች ሴንተርና የቱፍት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በጋራ ባደረጉት ጥናት፤ ከተማዋ በቀጣዮቹ 67 ዓመታት ከፍተኛ የተፈጥሮ አደጋ ያጋጥማታል ብለዋል፡፡ የከተማዋ ዋንኛ ስጋቶች ናቸው ተብለው የተጠቀሱት ከፍተኛ ሙቀት፣ ጎርፍና ድርቅ በከተማዋ ነዋሪ ህዝብና በመሰረት ልማቶቿ ላይ ከፍ ያለ አደጋን ያስከትላሉ ተብሏል፡፡ አደጋው በኢ-መደበኛ አሰፋፈር በከተማዋ በሚኖሩ ዜጎች ላይ ከፍ እንደሚል ያመለከተው የጥናቱ ውጤት፤ ኢ-መደበኛ አሰፋፈሮች በባህርያቸው እጅግ አነስተኛ መሰረት ልማቶችን የያዙ በመሆናቸው የአደጋ ተጋላጭነት ስጋቱን ይጨምረዋል ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ህዝብ ቁጥር 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን እንደሚደርስ የጠቆመው የጥናቱ ሪፖርት፤ ይኸው ቁጥር በ2035 ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ይደርሳል ሲል ትንበያውን አስቀምጧል፡፡ በከተማዋ ኢ-መደበኛ አሰፋፈር በስፋት እንደሚታይና ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የሚፈልሱ ዜጎችና ከተለያዩ የጎረቤት አገራት ወደ ከተማዋ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ እንደሚሄድም አመላክቷል፡፡
ከተማዋ ለተፈጥሮ አደጋ ስጋት ያላትን ተጋላጭነት ለመመርመር ጥናት ማካሄዳቸውን የጠቆሙት የምርምር ተቋማቱ፤ በተለያዩ ጊዜያት በከተማዋ የተመዘገቡ የሙቀት መጠኖችን በማየት  ከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሙቀት መጠኗ እየጨመረ ከዝቅተኛው የጤና መሰረት ልማት ጋር ተያይዞ እንደሚሄድና ይህም በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ከፍ ያለ ስጋትን የሚፈጥር ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የተወሰኑ ደቡባዊ የከተማዋ አካባቢዎች ማለትም፡- አቃቂ ቃሊቲ፣ ቦሌና ንፋስ ስልክ-ላፍቶ በተለይ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ሞቃት ጊዜያት ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያስተናገዱ ሲሆን፤ በ2040 እና 2060 ባሉት ዓመታት ንፋስ ስልክ-ላፍቶ በአማካይ የሙቀቱ መጠን ወደ 26.210C ከፍ ይላል ተብሎ ተተንብይዋል፡፡
በዚህ ከተማዋ ያጋጥማታል የሚል ስጋት ባጠላበት የተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ነዋሪዎቿ የወባ በሽታን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸው እንደሚጨምርና በተለይም ህፃናት ሴቶችና በእድሜ የገፉ ነዋሪዎቿ ለበሽታ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ይኸው ጥናት አመልክቷል፡፡Read 2090 times