Sunday, 17 September 2023 20:50

ነፃ ዕጣፈንታ (ሰው፣ ጊዜና ፈጣሪ)

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(0 votes)

 በቅድሚያ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለ2016 ዓመታት ለሰነበተችው የኢትዮጵያ ምድር Happy Solar Return በማለት ልጀምር፡፡  
የተቀበልነውን አዲስ ዓመት ምን አይነት ሰው ሆነን እንኑረው? በምን አይነት የአስተሳሰብ ቀመር አንጓዘው? የሚሉት ጥያቄዎች በየአመቱ የሚመጡ የሀሳብ መዘውሮች ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚህን ጥያቄዎች ለማስተናገድ በቅድሚያ አዕምሯችንን የሚመሩትን ስውር ምናባዊ ሀይሎች ነጣጥለን መመልከት አለብን፡፡ እነዚህ ሁለት ፅንፍና ፅንፍ ሆነው የሰውን ልጅ የሀሳብ ርዝመት የሚያሳጥሩም የሚያረዝሙም ሚስጥራዊና ሀሳባዊ ክስተቶች ናቸው፡፡ ስማቸው እጣ ፈንታ (Predestination) እና ነፃ ፍቃድ (Free will) ይባላሉ፡፡
እያንዳንዱ ፈላስፋ የሚባል ሁሉ እነዚህ ሀሳቦች ላይ ሳይፈላሰፍ የሄደ አለ ብዬ አላስብም፡፡ እናም እኔ …የናንተው አሰላሳይ አዲሱን አመት በሁለቱ ሀሳቦች መካከል ግልፅ የሆነ መግባባት ላይ ደርሰን አብረን እንድንጀምረው አሰብኩ፡፡ በየተራ የእውቀታችንን ቅርፅ ጠብቀን ሀሳብ እናምርት፡፡
በቅድሚያ ነፃ ፍቃድ ራሱ ምንድን ነው የሚለው ሀሳብ ላይ እንወያይ፡፡ ነፃ ፍቃድ እኔ በሚገባኝ ሁኔታ የሰው ልጅ ከፈጠረው ፈጣሪ የተሰጠው፤ በምድር ላይ ሲኖር ያሻውን እያደረገ እንዲኖርና በዛም ፍቃዱ ነፍሱን እያረካ ፈጣሪውን እንዲያመሰግን የሚያደርግ ሀሳብ አገኝበታለሁ፡፡ ሆኖም ነፃነቴ የቱ ድረስ ነው? የፈቀድኩትንስ ነገር በሙሉ የማግኘት አቅም አለኝ? እንጠይቅ፡፡ መጠየቃችን ውስጥ ያለውን የህሊና ጩኸት፣ የተስፋ እሪታ፣ ህይወትን የመስራት መቃተታችንን የነፃነት ባለቤቱ ሰምቶን እስኪመልስልን ድረስ እንጠይቅ፡፡
ነፃነት ካለ ህግ ምን ይሰራል? አላማው ነፃነትን መቆጠብ ከሆነ የተቆጠበ ነፃነት ውስጥ ምን አይነት እርግጠኝነት ልናገኝበት እንችላለን? የሰው ልጅ ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ የሞተን አድኗል፣ ደሃን ረድቷል፣ መጠለያ ለሌለው ቤት ገንብቷል፣ አቅም ላጠራቸው ትከሻውን አዘንብሏል፣ የተትረፈረፈ ፍቅርን ለተከፋ ወገኑ አፍስሷል …ይህን ሁላ ለማድረግ ነፃነት ያስፈልጋል፡፡ በራሳችን ላይ የገነባነውን የማንነት ተራራ ለመናድና እንደ አዲስ ለመስራት ነፃነት ያስፈልገናል፡፡ የሰው ልጅን ሀዘን ለመረዳት፣ ስቃዩ ስር ተጉዘን የልቡን ለቅሶ ለማልቀስ፣ ስሜት ባጣ፤ ትርጉምን በሳተ ማንነት ውስጥ ያለ ወዳጃችን ህሊና ውስጥ ገብተን ከምንምነቱ ጋር አብረን ዝም ለማለት…ነፃነት ያስፈልገናል፡፡
በሌላ መልኩ ስናየው ደግሞ በዛው የተቆጠበ ነፃነት ውስጥም ሆነን ወንድሞቻችንን ገድለናል፣ የገዛ ቤተሰቦቻችንን በትነናል፣ የተበቀልነውን ጠላታችንን እሪታ እንደ ሙዚቃ እያደመጥን ደንሰናል፣ የህይወትን ስልት ስተን ስንቶችን ከእውነት አርቀን በባዶ እውቀት ውስጥ ሰደናል፣ ምን አገባን ብለን የወደቀውን እያየን ተራምደነው አልፈናል፣ ህይወታችን ላይ በፍፁም የማንመኘውን መከራ እንደ መብት አድርገን በመሰሎቻችን ላይ ተግብረናል፣ ስንቱን ምስኪን ደሀ በተስፋ ልጓም አስረን እድሜውን ጨርሰንበታል። የሰው ልጆች ስንጨክን መሪር ነን፡፡ ይህ ደግሞ የነፃነታችን ውጤት ነው፡፡
ስለዚህ የሚመጣውን አመት በነፃ ፍቃዳችን ነው የምንኖረው የምንል ከሆነ …..
እኔ ይህንን እላለሁ…
ነፃነታችሁ የናንተም ሆነ የሌላ ሰው ህሊና ላይ ወህኒ ቤት ከመሆኑ በፊት ቀደምት የሆነው እውቀታችሁን አማክራችሁ በነፃነታችሁ ላይ ጌታ ሁኑ፡፡ ነፃነታችሁ በሰው የሚሰጥ …ሰው ሰራሽ ያልሆነ የተፈጥሮ ስጦታ መሆኑን ከሀሳብ ውቅያኖሳችሁ ውስጥ አጥምዳችሁ አውጥታችሁ ተረዱት፡፡ ነፃነታችን ግን የማንንም ሰው ነፃነት እንዳይነካ እንጠንቀቅ፡፡ እንዲህ አታድርግ፣ እንዲህ ባታደርግ ጥሩ ነው፣ ይሄን ካደረክ በእንደዚህ አይነት ቅጣት ትቀጣለህ እየተባለ ለሺህ አመታት በዝግ ነፃነት አሁን ድረስ እየመጣና ወደፊትም እንደሚሄድ የሚታወቀው የሰው ልጅ አንድ ቀን ይነቃል፡፡ እውቀት የነፃነት መንገዱ ነው፡፡ ያለ እውቀት ነፃነት የለም፡፡ ይሄን ደግሞ ማንም ሊያስተምረን አይገባም፡፡ ተፈጥሮ ለዚህ ሀሳብ ተነግሮ የማያልቅ መልስ አላት፡፡
በምድር ላይ ምድርን እንዲገዛ ተፈጥሮ ሳለ በመገዛት ብቻ እየኖረ ያለው የሰው ልጅ ነው። ምድሪቷ ፍቅር ከፀነሰው ማህፀኗ ውስጥ አምጣ በነፃ የምትሰጠንን ሀብት እየከፈልን የምንገለገለው  እኛው የሰው ልጆች ነን፡፡ የምድር የመጨረሻው ሀብታችን ነፃነታችን ሆኖ ሳለ፣ እኛ ግን በንዋይ ፍቅር ተጠምደን ነፃነታችንን  ሸጠንለት ማንም እንዳሻው እንዲያመናሽረው እንፈቅድለታለን፡፡ ነፃነትና ፍርሀትን ቀያይጠን እየኖርን ለምን እንደምንንበረከክ ሳናውቅ፣ ጌታና አስተዳዳሪ ፍለጋ ሌት ተቀን እንተጋለን፡፡  
ወይስ የሰው ልጅ እንዲሁ አፈጣጠሩ ድንጉጥ ነው? ወይስ አሰራሩ መንጋዊነት የተጠናወተው በግሉ ማሰብ የማይችል (የሚመስለው) ፍጡር ነው? የምር ፍፁምና ንፅህና ያለበት ነፃነቱን መለማመድ የማይችል ፍጥረት የሆነው በራሱ ላይ በፈጠረው የምድር ህግ ይሆን?
በቅዱስ መፅሐፍት ውስጥ የሚነገረን… ነፃነት ሀጥያትን የማርቢያ የሀሳብ ማህፀን ነው፡፡ አንድ ሰው በነፍሱም በስጋውም ነፃ ከሆነ ተንደርድሮ ሄዶ የሀጥያት ታሪኩን ከምድር መልክ ላይ መቸክቸክ ይጀምራል ተብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትነው ቅዱስ መፅሐፍቶች ውስጥ ነው፡፡ ይህንንም ስላደረገ የፈጣሪ ቁጣ በሰው ልጅ ላይ በርትቶ ሲታይ አንብበናል ተነግሮናልም፡፡ በፈጣሪው ነፃነት ተሰጥቶት መኖር የጀመረው የሰው ልጅ ብዙም ከነፃነቱ ጋር ሳይቆይ በህግ  ነፃነትን በሰጠው ፈጣሪው ተመልሶ ሲነጠቅበትም አስተውለናል፡፡ የሰው ልጅ ነፃነቱን ሊለማመድና በአንድነትም አብሮ ለመኖር የወሰነበተ ወቅት ላይ በገዛ ፈጣሪው ሲወገዝና መዓት ሲወርድበት በተደጋጋሚ ተተርኮልናል፡፡ ከፈጣሪ ጀምሮ ሙሉ የተፈጥሮ አካላት በነፃነታችን ላይ የሚያምፁብን ከሆነ ወይ ነፃ ነን ብለን እያሰብን ያለነው እኛው ብቻ እንሆን እንዴ?  ነፃነት የሚባለው ነገር ገና የሚሰጥና ከምድር ላይ የሌለ ነገር ይሆን እንዴ?
አዲሱ አመት ግን ለማን ነው የመጣው? ለአንተ አላማ? ላንቺ ህይወት? የኑመሮሎጂ (numerology) እና ጌማትሪያን (Gematria) ቀመራት ቀላቅለን አመታትን ብንመለከት፣ በሀገራችን ደግሞ በአቡሻኅር (ባህረ ሀሳብ) እውቀት አዕምሯችንን አጥበን የጊዜን ቀመር ለመረዳት ብንሞክር… በስተመጨረሻ ላይ ጊዜ ቅዠት እንደሆነና ታሪክም ውሸት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ስታስቡት የጥንቱ የታሪክ አመለካከትና እውቀት አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን በትውፊቱና ተረኮቹ ሲያንገላታት እንመለከታለን። በታሪክ ውስጥ ስማቸው ሆን ተብሎ እንዲጠፋም እንዲለማም የተደረገባቸው የነገስታት የአስተሳሰብ ስልት አሁንም ድረስ አለ፡፡ በትዝታ የሰከርነው እኛ ደግሞ ከጎናችን እየተነፈሰ የሚያስበውን፣ በህይወት ያለውን ሰው ትተን፣ ያላየነውን እየኖርን ያልሰማነውን እውነት አድርገን እየሰበክን የህይወታችንን ቀለም እናፈዘዋለን፡፡ እኛ መታየት ሲገባን የአያታችንን መልክ ፍለጋ እድሜያችንን እንገላለን፡፡ በኔ አመለካከት ይህ ሁሉ የሆነው …የመፍቀድ ስልጣናችንን እንጂ የነፃነት ስልጣናችንን መጠቀም ባለመቻላችን ያመጣነው የድክመታችን ደሞዝ  ይመስለኛል፡፡
ነፃነት ቅርፁ ብዙ ነው፡፡ የምመራውን ህዝብ ነፃነት ዛሬ ላይ በእጄ ይዤዋለሁ ብሎ የሚያስብ መሪ፤ ያኔ ምናልባት ነፃነቱን ላያዳግም ያጣበት ቅፅበት ሊሆን ይችላል፡፡ የሚመራውን ህዝብ ሀሳብ በሙላ መረዳት እችላለሁ የሚል መሪ፣ መረዳት የሚገባውን ሀሳብ የዛች የእውቀቱ ቅፅበት ላይ ደግሞ ላያገኛት የሚሸኛትም አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው በነፃነት ወይን ሲሰክር ነው፡፡
እናም በአዲሱ  አመት ነፃነታችሁ መሪያችሁ፤ ፍቃዳችሁ ደግሞ የእውቀት ከፍታችሁ ድረስ የሚያነጉዳችሁ መሰላላችሁ እንዲሆን እየተመኘሁ፣ ሁለተኛውና የመጨረሻው ሀሳቤን ልከትብ፡፡    
የማነሳው ሀሳብ እጣ ፈንታ ስለሚባለው ጉድ ነው፡፡ ይህ ሀሳብ በቀለለ መረዳት ስንተረጉመው፣ በምድር ላይም ሆነ በሌሎች አለማት ላይ የሚከሰቱት ወይንም የተከሰቱት ነገሮች በሙላ ከሰው ነፃ ፍቃድ ውጭ በሆነ ሀይል ተመርተው እንደሆነና ሁሉም ነገሮች ቀድመው ታስበው እንደተፈፀሙ የሚነግረንን ሀሳብ እናገኝበታለን፡፡ በእጣ ፈንታ ህይወት ውስጥ የሰው ልጅ ምርጫ ምንም አይነት ትርጉም የለውም። ለፈጣሪ የሚደረግ ፀሎት ምንም እርባና የሌለው፣ ለራስ ከራስ የሚላክ የግል ንስሀ ነው፡፡ ማሰብ ቅዠት ነው፡፡ ማፍቀርና መጥላት ግዴታ ነው፡፡ ወንጀለኛ በፈፀመው ጥፋት አይቀጣም፤ ሀላፊነትም አይወስድም፡፡ ሁሉም ነገር ታስቦና ታቅዶ የተሰራ ነገር ነው፡፡ እጣፈንታን ለመቀየር መሞከር ፈጣሪን እንደመፈታተንም ሊቆጠር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ፈጣሪ አንድ ጊዜ የፈቀደውንና ያሰበውን ሀሳብ፣ በሰው ልጅ አመለካከት ላይ መሰረት አድርጎ አላማውን የመቀየር እሳቤ የለውም ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡
የሰው ልጅ ገና ሲፈጠር በነፃ ፍቃዱ ነው ወይንስ እጣ ፈንታው ሆኖ ነው የተፈጠረው? ማን ፈቅዶ ወደ ምድር የመጣ አለ? ማን በነፃ ፍቃዱ ተመርቶ የሚሞትበትን ቀን መረጠ? ማን የፈቀደው ቤተሰብ ጋር ተወለደ? የሰው ልጅ የፍቃዱን መኖር የጀመረው ከመቼ ጀምሮ ነው? የሰው ልጅ ሀሳብ የሚፀነሰው በየትኛው የነፃነቱ ክፍል ውስጥ ነው? ሁሉም ነገሮች በሰው ልጅ ነፃ ፍቃድ ላይ ተመስርተው የሚፈፀሙ ከሆኑ ለምን የምድርም የሰማይም ህግ አስፈለገ? የህግ መምጣት ይሆን የሰው ልጅን የአውሬነት ባህሪይ ያላበሰው? የነፃነት ትርጉም የመረዳት አቅሙ ነው የሰው ልጅን የሌላን ሰው ነፃነት የአላማው ማስፈፀሚያ ሊያደርገው እንዲነሳ ያስገደደው? እነዚህ ጥያቄዎች በእጣ ፈንታችን ልክ ነው የምንኖረው ብለው በሚያስቡ የሰው ዘሮች የሚነሱት ሀሳቦች ናቸው፡፡ እናንተ ለዚህ መልሳችሁ ምንድነው?
በዚሁ ሀሳብ ላይ ሆነን አንድ ጊዜ እንጠይቅ። ፈጣሪ የመጀመሪያዎቹ የሰው ፍጥረቶች በሀጥያት እንደሚጠመዱና ህጎቹን እንደሚጥሱበት እያወቀ ነው ህግጋትን የሰጣቸው? ህጉንስ እንደሚስቱና ከዛም ባለፈ በሰሩት ሀጥያት ይቅር እንደማይላቸው እያወቀ ነው የፈጠራቸው? በቅዱስ መፅሐፍት ውስጥ ነፃነትን የምንለማመድባቸው ስርዓቶች የቱ ጋ ነው የተገለፁልን? የስጋ ፈቃድ የሀጥያት ማርቢያ ነው ከተባለ የሰው ልጅ የትኛው የሰውነቱ ክፍል ነው ነፃ ሆኖ ስጋውን ከፍቃዱ እንዲያግተው የሚያስገድደው? ነፃ እንደሆንን የሚነግረን የማንነታችን መገለጫ የቱ ጋ ነው የተሸከምነው? ሁሌስ አብሮን ያለ ነገር ከሆነ ስለምን እለት ተእለት ነፃነታችንን ፍለጋ ስንታገል እንከርማለን?
የምድርን ስርዓት ብንመለከት ሁሉም ነገር እንደተፈጠረው ሆኖ ስርዓቱን ጠብቆ ነው እየሄደ ያለው፡፡ እኛ የሰው ልጆች የፈለግነውን ብናደርግ በነፃ ፈቃዳችን ተመርተን መራብንና መጠማትን ማስቆም አንችልም፤ አዝነን ከማልቀስ፣ ተደስተን ከመሳቅ ውጭ የተለየ ተፈጥሮን የሳተ የስሜት ቀመር ማምጣት አንችልም፡፡ እውቀታችን በተፈጥሯችን ስፋት ልክ ውሱን ነው፡፡ ፍፃሜው በማይታወቅ የጊዜ ቀመር ውስጥ ዘላለማችንን ከራሳችን ነጥለን ህልውናችንን ከጊዜ ውጭ ማድረግ አንችልም። የመሬት ስበት እንዳሳደገን ሁሉ እድሜያችንንም በዛው ልክ መዝምዞ ከአፈር ይቀላቅለናል፡፡ አለመሞት አንችልም፡፡
በዛው ልክ ሞትን ለማስቀረት የምናማክረውና ሀሳቡን የምናስቀይረው ፈጣሪ አሁን ከአጠገባችን የለም፡፡ በዚህ ሰዓት ከፊታችን የሚጠብቀን ርዝመቱ የማይታወቅ ጊዜና ተስፋችን ብቻ ናቸው፡፡ እኔ ይህን ሀሳብ የተረጋጋው አልጋዬ ላይ ጋደም ብዬ፣ አልጋ ልብሴን አድርጌ ያሰብኩት ነው፤ ነገር ግን በጥይት ወጥጭፍ ጆሮው ደንቁሮ የሞት መልዓኩን ከጎኑ ቆሞ የሚያየው፣ ነፍስን ለማዳን በተሮጠ ሩጫ ተበትኖ የተነሳውን አቧራ በላዩ ላይ አልባስ ሆኖት እንባ የራቀው አይኑን ወደ ሰማይ ከፍ አድርጎ ተዓምር ከሰማይ የሚጠብቅ ህፃን ግን እኔ የሚታየኝ ሊታየው ይችላል? በገጠር ያለች አንዲት ኮረዳ አያቷ መሆን ለሚችል ሽማግሌ በቤተሰቦቿ ተላልፋ ስትሰጥ የሚሰማት ስሜት ለብቻው አውጥተን ስቃዩዋ ድረስ ብናዳምጣት፣ የምናደምጠው ነፃ ፍቃዷን ነው ወይንስ እጣ ፈንታዋን?
ሀሳባችንን እንሰብስበው፡፡ ከፍርድ ውጭ ሆነን እየገባንበት ያለነውን አመት በሁለቱ ፅንፍ ሀሳቦች ውስጥ ሆነን እንመልከተው፡፡ በነፃ ፍቃድ በሚያምን ትውልድና እጣ ፈንታውን ተቀብሎ በሚኖር ትውልድ መካከል ያለው የሀሳብ ልዩነት ላይ ቆመን፣ ሁለቱን ለማስታረቅ ወይንም ዳግም እንዳይገናኙ አድርገን አፋተን ለማሰብ ፍልስፍናችንን ወጠር አድርገን እንጀምር፡፡
በነፃ ፍቃዱ የሚኖር ማህበረሰብ ውስጥ አምባገነን አስተሳሰብ ያለው መሪ ሊፈጠር አይችልም፡፡ የፍቃድን ሀያልነት የነፃነትን ፍስሀ የተረዳ መሪ፣ ደስታና እርካታው ያለው የሚመራው ህዝብ ሳቅና ፌሽታ ውስጥ ነው፡፡ ነፃ ፍቃዱ የሚመራው ማህበረሰብ ነፃነትን የመረዳት አቅሙ ከተጣለበት ህግ በላይ በግብረገብነት እንዲኖር ሊያግዘው ይችላል፡፡ ነፃነት እውነት ነው፡፡ ነፃነት ሀይል ነው፡፡ ነፃነት የህይወት ግንድ ነው፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ የምኖረው ህይወት በፈጣሪ የተመረጠልኝ ነው፣ ሞቴን የፈጠረኝ በፈቀደው ሰዓት ላይ እሞተዋለሁ፣ ድህነቴን የፈጠረኝ ፈጣሪ ካልሆነ ማንም ሊያነሳልኝ አይቻለውም፣ አሁን እያሰብኩ ያለሁትና እየኖርኩ ያለሁት ህይወት በኔ እቅድና አላማ የተበጀ ሳይሆን ፈጣሪ ለአላማው ብሎ የወከለልኝ የፍቃዱ ውጤት ነው ብሎ የሚያምን የማህበረሰብ ክፍል ለሚያደርጋቸው ነገሮች ሀላፊነት መውሰድ የማይፈልግ፣ በላዩ ላይ የሚመጣበትን መከራ እንደ ፈጣሪ ስጦታ አድርጎ የሚያስብ፣ የግል ሀሳቡን ሰይጣናዊ ብሎ የሚጠራ፣ ፍላጎቱን ለመሸሽ ሰውነቱን የሚንቅ፣ ደስታውን ከውስጡ ሳይሆን ከመንጋ ውስጥ ሊፈልግ የሚወጣና የነፍስ ጥያቄን መጠየቅ እንደ መናፍቅነት አድርጎ የሚያስብ ማህበረሰብ ሊፈጥር ይችላል፡፡
እያንዳንዱ እውቀት መሀከል ባለ ክፍተት ውስጥ ራስን ከቶ ማንነትን መመርመር በግድ ያስፈልገናል። በአዲስ አመት አዲስ አላማ ለመስራት ለአዲስ እውቀት ራሳችንን ማበጀት ይገባናል፡፡
ሆኖም በየቀኑ ነፃ ፍቃድ አለን የምንል ሰዎች፣ የፈጣሪን ስራ እየሰራን የሱን ተግባራት በመፈፀም ልናግዘው ሲገባን በየቅዱስ ስፍራዎች እየተጓዝን ይሄን ካላመጣህ እንዲህ ልንሆንብህ ነው እያልን ማስቸገራችንን አናቆምም፡፡ በየእለቱ የፈጣሪን እውቀት ተናግረነውና ሰብከነው ረክተን የማይወጣልን ፍጥረቶች፣ ልክ መከራ ሲመጣብን ምነው ፈጣሪ ሆይ አታየንም እሳ ብለን በፀሎት ሰበብ እውቀቱን እየደጋገምን እንፈትነዋለን፡፡ የፈለግነውን እንድናደርግ፣ ፍፁም የሆነ ፍቃድ ከሰማይ በስጦታ መልክ ተሰጥቶናል እያልን፤ ይህንኑ ነፃነታችንን እየረገምን፣ በኔ ፈቃድ ሳይሆን ባንተ ፍቃድ ልኑር እያልን ስጦታችንን ባሰኘን ሰዓት ከፈጣሪያችን ጋር እንጓተታለን፡፡
እኔ ግን ይህን ፀሎት የአለማት ፈጣሪ ለሆነው እየፀለይኩ፣ ወደ አዲሱ  አመት ልስፈነጠር ወደድኩ።  
ፈጣሪ ሆይ፤ የምኖረው ህይወት ያንተ ፈቃድ ከሆነ፣ የማስበው ሀሳብ ቀድመህ የሰራኸውና የምታውቀው ከሆነ፣ በምድር ላይ ያለው ጥፋትም ሆነ ልማት አንተ አቅደህና አልመህ ያመጣኸው ከሆነ፣ የደስታዬ ምክንያት የኔ ልፋት ሳይሆን ያንተ ዓላማ ከሆነ፣ ሁሉም እጣፈንታውን የሚኖር ሆኖ  ነፃ ፍቃድ የሚባል ቅዥት ከምድር ላይ ከሌለ፣ ከዚህ በኋላ የሚመጣው አመት ውስጥ የኔ አላማ ምንም አይነት ትርጉም ከሌለው፣ እስካሁን የሰራሁት ሀጥያት በኔና በእርኩስ መንፈስ ተፅዕኖ ሳይሆን አንተ ቀድሞ ባወክልኝና በሰጠኸኝ እውቀት ላይ ተመስርቶ የተሰራ ስህተት ከሆነ፣ ቀን ከሌሊት ተንበርክኬ እየፀለይኩ ሳመሰግንህ የነበረው… አንተ ራስህ በዛ ሰዓትና ቦታ እንዳመሰግንህ አድርገህ ቀምረህ በሰጠኸኝ ምክንያት ከሆነ፣ አሁን በሀገሬ ኢትዮጵያ ሰማይ ላይ አርግዞ ያለው የጥላቻ፤ የመናናቅ፤ የመለያየትና የመገዳደል ጥልቅ ፍላጎቶችና በገዳዮች ሀሳብ ውስጥ የተበጁት የጭካኔ እብደቶች ምክንያት የህፃናት ለቅሶ፣ የእናቶች የደረት ድቅድቅታ፣ የወንድ ልጅ ቁጭት፣ የአባቶች የወደመ ተስፋን እንደሚፈጥሩ ቀድመህ ከመከሰታቸው በፊት የምታውቃቸውና ቀድመህ ሳይጮሁ በፊት እነዛን ለቅሶዎች አድምጠኻቸው የነበረ ከሆነ…
በእርግጥም ፈጣሪዬ ሆይ ዝምታዬ ፀሎት ይሁነኝ፡፡ የተቀበልነው አዲሱ አመት ያንተን እውነት የምረዳበት የጊዜ ዥረት ይሁንልኝ፡፡ የሀገሬን …የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ሰላምና ፈገግታ የማይበት አመትም ይሆን ዘንድ… በዘመኔ ላይ ይህን ሳላይ ሞት እንዳይቀድመኝ በምድር ላይ አዘግየኝ፡፡
መልካም የነፃነት አመት ይሁንላችሁ፡፡  Read 1257 times