Sunday, 17 September 2023 20:51

“ልብ አድርጉልኝ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ከረማችሁሳ!
ስሙኝማ… አንዳንዴ’ኮ አያምጣው ነው። ይሄን ሰሞን ‘ወረድንባቸው’ አይደል! “ማን ከመጤፍ ቆጥሯችሁ” አትሉኝም! የምር ግን… በቃ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… “እንደባቢሎን ግንብ ሰዎች…” ያድርጋችሁ ተብለን ‘የተረገምን’ ይመስለኛል፡፡ አሀ… አለ አይደል… ‘ሁለት አበሻ አብሮ አይሰራም፣’ የሚሉት ዘመን ላይ ደረስና!
‘መጻፍ ከቺስታነት አላወጣም ሲል ስብከት ጀመርክ ወይ’ አትበሉኝና… ሲሆን መዋደድ ሳይሆን አብሮ መሥራት ምን አለበት! እንደውም… ዘንድሮ ምን በዛ አትሉኝም! “ዋ… መንጋጭላህን እንዳላጣምመው፣” ዓይነት ነገር።
ነገሬ ብላችሁልኝማል!... ዘንድሮ በብዙ ነገር የተያዘው ምን መሰላችሁ? ክልከላ፡፡ አሀ… የምር የሚያሳስብ ነገር ነው፡፡ ‘ከሚፈቀደው ነር የሚከለከለው’ እየበዛ ሲሄድ እኮ… አለ አይደል፣… ሜዳ ላይ መቅረታችን ነዋ! “ይሄን መስራት፣… ይህን ማድረግ ትችላለህ…” ከማለት ይልቅ “ይህን ማድረግ አትችልም…” ዓይነት ነገር… አለ አይደል… ‘ኮምፐልሰሪ’ ሆነሳ፡፡
(ስሙኝማ… እግር መንገዴን…. አንዳንድ ነገር ላይ ከልካይ ሳያስፈልገን … ራሳችን ለራሳችን “እዚህ ላይ ታቆማለህ!” ማለት መቻል አለብን። ልጄ… ነገርዬውን ስታዩት ያሳስባል፡፡ እንዲህ ‘ጥንቃቄ’ በሚጠይቅ ዘመን… የብዙዎቻችን ነገር “የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ…” ዓይነት እየሆነ ነው፡፡ እናማ … “ሁልጊዜ አበባዬ” የለም፡፡ ለምኑም፣ ለምኑም ‘ጠንቀቅ’በሉማ!)
እናላችሁ… ብዙ ቦታ ከማበረታታት ይልቅ… በቃ ‘ተስፋ ማስቆረጥ’ ነገር ነው የምታዩት። ልጄ… ድሮ ዘፋኙ እንኳ “ማን አለኝ ከልካይ ቆንጆ ልጅ ባይ…” ነበር፡፡  ዘንድሮ ይሞክራት። (ቂ…ቂ..)
ምን ይመስልሀል አትሉኝም!... በቃ ትንሽ ‘ኮርኮም’…‘ገጨት’ ማድረግ እንደ ‘ኖርማል’ ተወስዷል፡፡ ተውት መገፍተር… ወይ ምናምን… የሆነ መስሪያ ቤት ዘብ በጥፊ ዓይነ ስባችሁን ቢያበረው… አለ አይደል… እሱን “ልትመታውማ አትችልም!” ከማለት ይልቅ… እናንተን “አንተስ ካልጠፋ ቦታ እዚህ ምን ታደርጋለህ!” ነው የምትባሉት፡፡ እናላችሁ… በቃ “ካልቾ ቢጤ…” የ’ሀበሻ ቀለብ’ ነው የሚል ህግ ሳናውቀው የወጣ ነው የሚመስለው!
እና ግርም የሚለኝ… በቴክኖሎጂ ዘመን ሁሉም ነገር “ጠብ ያለሽ በዳቦ…” ለምን ይሆናል! አለ አይደል “ይህን ታደርግና፣ ወዮልህ!” ማለት ማንን የት አደረሰ!
የምር ግን… በተለይ የሆነ ‘ፓወር’ የሚያገኙ ለምንድነው “ክንዴን ባላሳየው!” ከማለት ይልቅ “ጥይት ሰራተኛ አደርገዋለሁ” የማይሉት! አለ አይደል… ሥልጣን ማለት፣ አርጩሜ ተሰጥቷቸው “የፈለግኸውን ጠብጥብ…” የተባሉ ያደርጉታል፡፡ (ይቺን ይቺንማ ኖረንባታል! አለ አሉ ነገር አላምር ያለው የእኔ ቢጤ!
‘ማሳወቅ ‘እኮ ክፋት የለውም፡፡ “ሳትከፍል ከቀረህ በተዘዋዋሪ አንተም ልትጎዳ ትችላለህ…” ማለት የመሰለ ‘የሰከነ’ አነጋገር እያለ “ካልፈለክ… አንተን አያድርገኝ!” ዓይነት ‘ጉልቤነት’ ምን ያደርጋል፡፡ (ስሙኝማ… አሁን ለምሳሌ አንዳንድ ‘ዲክታተር’ እንትናዎች እንትናዬዎቻቸውን ‘ይዞ ማቆያ’ ዘዴያቸው ምን መሰላችሁ “ዋ!” “ኋላ እንዳይቆጭሽ!” “ይሄ የምትኮሪበትን አፍንጫሽን ንፋስ ያፈረሰው አጥር እንዳላስመስልልሽ!” (ቂ…ቂ…) ዓይነት ነገደር፡፡ እንትናዬዎች ደግሞ … በቃ በፍርሀት “ቀን እስኪያልፍ…” ይሉና ሙሉ ‘ዲክሽነሪያቸውን’ ወደ አንድ ቃል ይጠቀልሉታል - “እሺ”.. ዘንድሮ… አለ አይደል.. እኛም እንደ “እሺ” የናፈቀን ነገር የለም!)
እናላችሁ…ሌሎቹ በኮምፒውተር “ተአምር እየሰሩ” እኛ ከ “ጎራዴው ሰው በላው…” ላንላቀቅ ነው! የምር ‘ኮ ድርጅቶችም ቢሆኑ እንደ ግለሰብ “የተወለድክባትን ቀን እንዳትረግማት!’ አይነት አባባል ለምዶባቸው… ይኸው ‘ቦምብ’ ቃላት ነው የሚወረውሩብን፡፡ የምር አይገርማችሁም! አንዳንድ ጊዜ የሆነ ‘መመሪያ’ ወይ ‘ትእዛዝ’ ይተላለፍና ምን ይባል መሰላችሁ! “ይህንን በማይፈፅሙ ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል፡፡” እንዴ… እንዴት ነው ነገሩ… በቃ ‘ይቀጣል’ ወይ ምናምን አይሉንም እንዴ! (ልጄ… እኛ ‘እርምጃ…’ የሚሉት ‘ማስፈራሪያ’… ስንት ቅዠት እንደሚሰበስብብን ማን በነገራቸው!)
እናላችሁ… እኔ ‘የማያዳግም እርምጃ’ ሲሉ… ምን ትዝ ይለኛል መሰላችሁ? ‘የፈረንሳይ አብዮት’ (ቂ…ቂ…) አሀ… ልክ ነዋ! እኛ ‘የማያዳግም’… ሁሉ ነገር የምናውቀው የ‘ሪቮሊዩሽን’ ጊዜ ነው! ታዲያ… ገና ለገና የሆነ ወርሃዊ ሂሳብ አልከፈልንምና “የማያዳግም እርምጃ…” ምን ለማለት ነው!
ምን መሰላችሁ… እነኚህ ‘መንጋጭላ የሚያጣምሙ’ ቃላት ‘እኮ… አለ አይደል ከ’ጉልቤነት‘ ባህሪ የሚመጡ ናቸው፡፡
በድሮ ጊዜ’ኮ… “ዋ እንደእንትና በጭንቅላትህ እንዳልደፋህ” ብሎ ‘ቴረር’ ሲለቅባችሁ “ልብ አድርጉልኝ!” ብሎ ‘መከላከል’ ይቻል ነበር፡፡ ልጄ… ዘንድሮ እንኳን “ልብ አድርጉልኝ”… “እኔ ነገር አልፈልግም… በቃ ተሸንፌያለሁ ብትሉ እንኳን… ምን ይባላል መሰላችሁ፡፡ “ተዋቸው… ይዋጣላቸው”… እንዴት ነው ነገሩ! ‘መዋጣትን’ ምን አመጣው!
ምን መሰላችሁ….የ“ሰርኑን በለው” ዘመን ስለሆነ… አለ አይደል … ተወያይቶ ‘ልዩነት ማጥበብ’ የሚባል ነገር የለም፡፡ በቃ ነገር ሁሉ ‘የሚፈታው’ እንደ ቡጢ ስፖርት አንዱ ‘ሲዘረር’ ወይም ‘ፎጣ ሲወረውር’ ነው፡፡ ታዲያ ልክ የሚያስገባው ‘ጎበዝ’ በበዛበት አገር … በየቀኑ ስንት ፎጣ ስንወረውር ልንውል ነው (ቂ…ቂ…)
እናላችሁ… አሁን ትልቁ ችግር “ልብ አድርጉልኝ” የማንለው ሃይለኛ በዛብን፡፡ በ‘ጭንቅላት ማቆም’ የለ… ‘መንጋጭሌ ማለት’ የለ… በወረቀትና በማህተብ ብቻ ‘ደቁሶ’ መጣል።
አሁን ለምሳሌ… አንዳንድ ህግ አስከባሪዎች የሆነ ጠብ ቦታ ሲደርሱ ‘ለመገላገል’ ሁለቱንም ትንሽ ‘ዠለጥ’ ካደረጉ በኋላ… አለ አይደል… ወደ ‘መሰረታዊው ጉዳይ’ ይገባሉ “እሺ… ምንድነው ጠቡ!” አሀ… እንዴት ነው ነገሩ! ‘ቅደም ተከተል’ ይጠበቃ! ‘መቅመሱ’ በ‘መመሪያ’ የፀደቀ ነገር ከሆነ… ወደ ኋላ ይቆይልና! እኔ የምለው… ‘መኮርኮም’ እንዲህ ቀላል የሆነው… እንዴት ነው ነገሩ!
ስሙኝማ… እነዚህ ‘ፈረንጆች’ አንዳንዴ “ያበዙታል” የምንላቸው ነገር አለ፡፡ አሁን ለምሳሌ… እንትናዬን “የመስሪያ ቤቱ ልጅ ነች…” ብሎ ክንዷን እንኳ ነካ ማድረግ… በቃ ወደ ‘ፈረንጅ ከርቸሌ’ ያስወረውራል፡፡ አንዳንዴ… በቃ ልክ ያልሆነ ድርጊት ስታዩ … አለ አይደል… “ኧረ እንዲህ አይነቱማ እኛም ጋ በተለመደ…” ያሰኛችኋል!
(በቃ… የእንትናዬዎቹ ክፍል ‘ለሌላ ዙር’ ይቆይልንና… ሌሎች በሆነ ባልሆነው ‘እንዳያቀምሱን’… በቃ እንዲህ አይነት ህግ ይውጣልን!)
የምር… ከዚህ በማያስፈልገው ሁሉ “ይህን አታድርግ…” “ኋላ እንዳይቆጭህ” “ልክ እንዳላስገባህ…” አይነት አስተሳሰብ ካልወጣን፤ ሳንከባበር… እንደተናናቅን እንከርማታለን፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1399 times