Monday, 18 September 2023 00:00

ዘመኑ፣… ያገኘውን የሰጠነውን ነገር ያፈጥናል፤ ያበዛል፤ ያዛምታል።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

ታላቋ አገር አሜሪካ፣ ከሞባይል ስልክና ከኢንተርኔት ዘመን በፊትም፣ ከጥንት ከጥዋቱ፣ ‘የወከባ አገር ሆና ነው የተፈጠረችው’ ይሏታል። ወዳጆቿ፣ በእቅፏ ውስጥ ሆነው ያመሰግኗታል፣ ከሩቅ ሆነው ይመኟታል። ሥራ የበዛላት ወይስ ልፋት የበዛባት አገር? ‘ሥራ የበዛላት የተባረከች አገር ናት’ በማለት ያደንቋታል። the land of opportunity… እንዲሉ ነው። የታታሪ ሰዎች ፍጥነት ነው - ወከባው።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የቀድሞዋ አሜሪካ ዛሬ የለችም።’ሥራ እንደ ድሮ አይደለም። እንደ ልብ አይገኝም። ሥራ ሞልቶ ቢትረፈረፍስ፣ ኑሮው መች ይሟላል?’ ብለው ይዝኑባታል። ኑሮ እያሯሯጠ ያዳፋል፤ ምንም ቢሠሩ ሁሌም እንደጎደለ ነው! መቅኖ ቢስ ሕይወት፣ ልፋት የበዛባት እረፍት የለሽ አገር!... ብለው ይማረሩባታል። የከውካዋ ሰዎች ሩጫ ነው ወከባው።
ለነገሩ አገሩ እንደ አህጉር ሰፊ ነው። ካልፈጠኑ አይሆንም።
የዛሬ ዘመን ወከባ ግን ይለያል።  በእርግጥ በየዘመኑ ሕይወትን የሚያፈጥኑ አዳዲስ ፈጠራዎች መምጣታቸው አዲስ ጉዳይ አይደለም። ባቡር፣ መኪና፣ አውሮፕላን፣… ሬድዮ፣ ቴሌቪዥን፣ የስልክ መስመር፣… ከባቡር በስተቀር በሌሎቹ ሁሉ፣ የአሜሪካ የፈጠራ ሰዎች ቀዳሚ ናቸው። ባለፉት 120 ዓመታት ምን ያልሰሩት ያልፈበረኩት ነገር አለ?
አንድ ቴክኖሎጂ ለሌላ አዲስ ቴክሎጂ እያሻገረ በሃያ በሃያ አምስት ዓመት ርቀት አዲስ ታሪክ የሚሰሩ ተአምረኛ ሰዎችንና ኩባንያዎችን የምታፈራ ልዩ አሀር መሆኗ አያጠራጥርም። ሄንሪ ፎርድና መኪና፣ ቶማስ  ኤድሰንና ኤሌክትሪክ፣ ሮክፌለርና ነዳጅ፣ ካርኒጌና ብረታ ብረት፤… እነዚህ ታሪክ ሰሪ ሰዎችና ኩባንያዎቻቸው ሁሉ በተቀራራቢ ጊዜ የተወለዱ ናቸው።
በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ቁሳቁስ የተፈጠሩት ከዚያ ወዲህ መሆናቸውና የዐይናቸው ብዛት አይገርምም? ፂም መላጫና ፀጉር ማድረቂያ፣ ምድጃና ፍሪጅ፣ ልብስ ማጠቢያ፣… ብዙ ነው። ከኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ የሞባይልና የኢንተርኔት ፈጠራዎች ላይም አሜሪካ  ቀዳሚ ናት። ከዚህም ጋር ፍጥነትና ወከባ ጨምሯል።
ወከባው ግን እንደድሮው ዐይነት አይደለም። በአዳዲስ ፈጠራ አዲስ ታሪክ የሚሰሩ ወጣቶች ዛሬ ዛሬ ቁጥራቸው ቀንሷል ይላሉ የማህበረሰብ ሳይንስ አጥኚ አቶ ጆናታን ሄይድ።
የሰዎች ወከባ በአሜሪካ በከንቱ የመባከን ወከባ እየሆነ ነው። ከቅርብ አመታት ወዲህ ብሶባታል ይላል - አዲሱ የወ/ሮ ግሎሪያ ማርክ ጥናት። የትዝብትና የግምት ጉዳይ አይደለም። በቢሮ ሰራተኞች ላይ በተደረገ ጥናት እርግጡን መስክሯል።
በ2005 ነው የመጀመሪያው ጥናት የተካሄደው። ያኔ የቢሮ ሠራተኞች፣ ስራዬ ብለው አንድ ጉዳይ ይዘው ከጀመሩ፣ በሙሉ ትኩረት ለሁለት ደቂቃ ያህል ይሰሩ ነበር፡፡ በአማካይ ማለት ነው። ከዐሥር ዓመት በኋላ እንደገና ጥናት ተካሄደ። በ2016 ማለት ነው። ወከባው ጦዟል።
አንድ ስራ ይጀምራሉ፡፡ አንድ ሀሳብ ይመጣላቸዋል፡፡ ገና በወጉ ሳይጀምሩት ሀሳባቸው ይበታተናል፡፡ የጀመሩት ጉዳይ ላይ ከ50 ሴኮንድ በላይ መቆየት አይችሉም። ምን ይሄ ብቻ? ከዚያ ወዲህ የሞባይል ኢንተርኔት በ5 ዕጥፍ ጨምሯል። የዓለም ሩጫ ከእርምጃ አይደለም ከሐሳብም የፈጠነ ሆኗል።
 ከዚህና ከዚያ በኩል የሚመጡ እልፍ ጉዳዮች በአእምሯቸው ይንጫጫሉ፡፡ የተከፈተውን ፋይል በቅጡ ሳያዩ ደርዘን ፋይሎችን ይከፍታሉ፡፡ የመጣ ኢሜይል መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ስንት ጊዜ እየተመላለሱ እንደሚያዩ አስቡት።
በአንድ ቀን ውስጥ፣ 80 ጊዜ። ሌላ ሌላው የማህበራዊ ሚዲያ ወከባ ሳይጨመርበት ማለት ነው።
በትኩረት ማስተዋልና ማዳመጥ፣ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። በጥሞና ማንበብና ጠንቅቆ ማሰብ ደግሞ እጅግ ከብዷል። የሰው ውሎ እረፍት በሌለው ወከባ ደፍርሷል። አመሻሹ ላይ ወይም ወደማታ ሰላም ያገኛል ማለት አይደለም፡፡
ከአሁን አሁን ይረግባል የምትሉት ሃይለኛ ነፋስ፣ አቧራ እያስነሳ፣ ቀኑን ሙሉ ሲረብሻችሁ አስቡት፡፡ እንደ ሚበርድለት ትጠብቃላችሁ፡፡ ግን መረጋጋት ብሎ ነገር የለም፡፡ በሮችንና መስኮቶችን ሲያንገጫግጭ፣ የላሉ ቆርቆሮዎችን እያወራጨ ሲያስጮህ፣ እረፍት ሳይሰጥ  ቀኑን ሙሉ በግርግር እየበጠበጠ ሲውል ይታያችሁ። የዛሬው ዘመን እንደዚያ ሆኖባቸዋል።
“ያችንና ይህችን አይቼ፣… ከዚያ በኋላ ተረጋግቼ ወደ ስራዬ!”… ብለው ገና አስበው ሳይጨርሱ፣ ሌላ ይታያቸዋል። “ይሄስ ከየት መጣ? ያኛው ደግሞ ምንድነው የሚያወራው? እነዚያስ?”… ማለቂያ የለውም።
በቪዲዮ፣ በድምፅ፣ በጽሑፍና በምስል… እልፍ ጉዳዮች እየተከታተሉ እየተደራረቡ ይግተለተላሉ ፡፡ “እዩኝ፣ ስሙኝ” እያሉ ይወተውታሉ። ከጥዋት እስከ ረፋድ፣ ከቀትር እስከ ምሽት፣ ፍጥነቱና ብዛቱ ከዐቅም በላይ ሆነ። በእልፍ ብጥስጣሽ ውልብታዎችና በመዓት ቅንጥብጣቢ ጩኸቶች የተዘበራረቀ የሰው ውሎ ቅዠት እየመሰለ ነው። መዋከብ፣ መቅበዝበዝ በዝቶበታል - ኑሮም አእምሮም።
ታዲያ፣ ለሆነ ስራ ተፍተፍ እንደማለት አይደለም። የሆነ ስራ ቶሎ ለመጀመር እንደመቻኮል በጊዜ ለመጨረስ እንደመጣደፍ አይደለም - የዘመኑ ወከባ። ያማ መልክ አለው። በሙሉ ትኩረት የሚጠመዱበት ነው፡፡ በሙሉ ሃሳብ መመሰጥን የሚጠይቅ ነው።
የዛሬው የወከባ ልክፍትና የመቅበዝበዝ አባዜ፣ ግን መያዣ መጨበጫ ያሳጣል። በአንዳች ሰበብ ጎትቶ ካስገባ በኋላ፣ እልፍ አእላፍ ቅርንጫፍና ቅያስ እያግተለተለ ውጦ ያስቀራለ ነው፡፡ እስከ ማፍዘዝና ማደንዘዝ ያደርሳል። መነሻውን ለማስታወስ እንኳ ጊዜና እድል አይሰጥም።
በላይ በላዩ፣ በየዓይነቱ እልፍ የችርቻሮ ጉዳዮችን በእሩምታ እያንጋጋ ያጣድፋችኋል።  በአንድ ጉዳይ ላይ ቪዲዮዎችን በጅምላ ንግግሮችን በገፍ እያራገፈ በሁሉም አቅጣጫ እንደመጣ ማእበል እየከበበ እያካለበ፣ ሌላ ሕይወትና ሌላ ዓለም የሌለ እስኪመስላችሁ ድረስ ትንፋሽ ያሳጥራችኋል።
ከመጥፎ ቅዠት ለመባነን እንደሚሟሟት ሰው እንደምንም ለመባነን መሞከራችሁ አይቀርም። እፎይ፣… በቃኝ! “ይሄ በሽታ ነው” ትላላችሁ፡፡ መዝናኛ ይመስላል፡፡ ግን ያደክማል፡፡ ማረፍና ወደ ስራ መመለስ ትችላላችሁ።
ግን፣ ያላያችሁት ነገር አለ… የደወለ ሰው ይኖራል? የፅሁፍ መልዕክትስ? ዩቱብ ደግሞ አለ፡፡ ፌስቡክን እንጂ ቴሌግራምን ገና አላያችሁም። ቲክቶክስ?
ለትንሽ ደቂቃ ብቻ! አየት አየት ለማድረግ ብቻ! ይጀምሩታል፡፡ በዚያው ይዞ፣… አንዱ ለሌላው እያቀበለ፣ እሱም በተራው ወደ አስር ገመዶች እያስተላለፈ፣ ወዲህና ወዲያ እየጎተተና እያሾረ ይወስዳችኋል፡፡ … ከዚህ ቅዠት ውስጥ ለመውጣት ይፍጨረጨራሉ፡፡ በትግል ይባንናሉ።
ግማሽ ሰዓት አለፈ?
ሳይታወቃችሁ የስራ ሰዓት መውጫ ደርሷል። ሌሊቱ ተጋምሶ ሄዷል።
“ውድቅት ሌሊት” ይሉት የነበረ አባባል ዛሬ ድራሹ ጠፍቷል። ሁሉም ነገር ፀጥ ረጭ የሚልበት፣ ሰው ዝር የማይልበት የእረፍትና የእንቅልፍ ሰዓት፣ “ጊዜ” ራሱ የተኛ የሚመስልበት የማታ እርጋታ፣… ዛሬ የት ተፈልጎ ይገኛል?
መተኛትንና መንቃትን፣ ማንቀላፋትንና መንቀሳቀስን እርስ በርስ እያቀላቀለ ግራ የሚያጋባ፣ በውን ይሁን በሕልም ልዩነታቸው የሚያምታታ አዲስ ዘመን ውስጥ መሾር፣ መንከውከው፣ በቀንም በማታም በሽበሽ ነው።
ከንጋት እስከ ምሽት  አይደለም ነገሩ። ከንጋት እስከ ንጋት ነው። ወይም ከምሽት እስከ ምሽት። በየእለቱ፣ ከሳምንት እስከ ሳምንት አይቋረጥም፡፡ በሁሉም ወራት፣ ዓመቱን ሙሉ እረፍት የለውም።
 ለስራ ቢሆንኮ፣ መልክና ልክ ይኖረው ነበር። በሁለት አይደለም በሦስት ፈረቃ እየተቀባበሉ መስራት ችግር አያመጣም። “ሰባቱንም ቀናት 24 ሰዓት ሙሉ እንሰራለን” የሚሉ ቢኖሩ፣ ደግ አደረጉ። 24/7 እንደሚባለው።
ገሚሶቹ በፈረቃ ሲሰሩ፣ ሌሎቹ በተራቸው የየቤታቸውን ነገር መልክ ለማስያዝና ዘና ለማለት ይሞክራሉ። በእንቅልፍ ሰዓትም ሃሳባቸውንና አካላቸውን አረጋግተው ያርፋሉ። ኑሯቸውና አእምሯቸው አነሰም በዛ ስርዓት ይይዛል።
 ጣፈጠም መረረም፣ ሕይወታቸው አንዳች ጣዕም ይኖረዋል።
የዘመናችን የኢንተኔት ዓለም ግን ለህይወት ጊዜ የለውም፡፡ በእርጋታ ለመተንፈስ ሕይወትን ለማጣጣም ጊዜ የሚነፍግ፣ ወይ ከስራ አልሆኑ፣ ወይ አልተዝናኑ፣ ወይ እረፍት አላገኙ፣… እዚህና እዚያ መናጠብ፣… መስመር የሌለው ውሎና አደራ ምን ይባላል?
 አንዳች ምስል የማይሰራ የዘፈቀደ ነጠብጣብ ላይ መቅበዝበዝ፣… በግርግር መሃል እዚህና እዚያ እየተጎተተ እየተገፈተረ፣ ግርግሩ ወደ መራው አቅጣጫ እየተላተመና እየተደናበረ መንደፋደፍ የሰው ዕጣፈንታ መስሏል፡፡
መውጫ አጥቶ ግርግር ውስጥ የተቀረቀረ ሰው ምን ያድርግ? እልህ እየያዘው ግራ ቀኝ መጓተትና መወራጨት… እንደ መደበኛ ስራ ወይም የህይወትና የተፈጥሮ ፍርጃ ይሆንበታል።Read 915 times