Sunday, 17 September 2023 21:07

“ነጩ በሽታ (አባ ጋረደው)” ለንባብ በቃ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 የፖርቹጋላዊው ፀሃፊ ሆሴ ሳራማጎ ድርሰት የሆነውና በተስፋዬ ይመር የተተረጎመው “ነጩ በሽታ (አባ ጋረደው)” የተሰኘው መፅሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡
የመፅሐፉ ተርጓሚ በመግቢያ ገፁ ላይ ባሰፈረው ማስታወሻ፡- “…የአባጋረደው ደራሲ ፖርቹጋላዊው ሆሴ ሳራማጎ በሥነፅሁፍ የኖቤል ሽልማት በ1990 ዓ.ም አሸንፈዋል። አባ ጋረደው (1987 ዓ.ም) ለዚህ ክብር ካበቃቸው ሥራዎቻቸው አንዱ ነው፡፡ ድርሰቱ፤ መንስኤውና መፍትሄው በውል ባልታወቀ የመታወር ወረርሽኝ ላይ አተኩሯል፡፡ ችግሩ ሲስፋፋ መንግስትም ህዝቡም ተደናግጠዋል። ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከተደረጉት ጥረቶች መካከል በመቅሰፍቱ የተያዙትንና ከእነሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ማግለያ (ኳራንቲን) ማስገባት ይገኝበታል፡፡ የዓይንና የነርቭ ሃኪሞችም በችግሩ ዙሪያ መፍትሄ ለማፈላለግ ምክክር አደርገዋል፡፡ ሚዲያዎች ተስፋም ስጋትም የቀላቀሉ መረጃዎች ስለቸነፈሩ ዘግበዋል፡፡ የተለያየ ጥረት ቢደረግም መፍትሄ አልመጣም---” ብሏል፡፡
የመፅሐፉን የአርትኦት ሥራ የሰሩትና  የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው፤ “ይህን መፅሐፍ ማንበብ የትልቅ ታሪክና ሃሳብ ባለቤት መሆን ነው፡፡ የዕውቀት፣ የምናብ ጥልቀት ባለቤት መሆን ነው፡፡ በህይወት ዘመናችን ምን አነበብን ተብለን ብንጠየቅ አባ ጋረደው ወዲያው ስሙ ይመጣል፡፡ እኔም ካነበብኳቸው ታላላቅ መፃሕፍት ምድብ ውስጥ የማስቀምጠው ነው፡፡ አንብቡት፡፡ ትርፉ ብዙ ነው፡፡” ሲሉ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ አስፍረዋል።
የቃላት መፍቻን ጨምሮ በ309 ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ በስፓርያል ማተሚያ ቤት የታተመ ሲሆን በ450 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡


Read 1871 times