Sunday, 17 September 2023 21:00

ከዓለም ዜጎች ጋር በቡዳፔስት

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

 በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ከተሳተፉ ጋዜጠኞች አንዱ ነቀርኩ። በቡዳፔስት በነበረኝ የ15 ቀናት ቆይታ ሻምፒዮናውን በጋዜጣ፤ በብሮድካስት ሚዲያና ቀማህበራዊ ሚዲያዎች ከሰጠሁት ሽፋን ባሻገር ከዚምባቡዌ ታዋቂ የአትሌቲክስ ዘጋቢ የድረገፅና የራድዮ ስርጭቶች፤  በቀን 1.5 ሚሊዮን ኮፒ ከሚታተመው The Answer ከተሰኘ የጃፓን ግዙፍ ጋዜጣ፤ Athleticspodium የተባለውን ድረገፅ ከሚሰራው የቱርክ ጋዜጠኛ ፤ ከስፔን፤ከራሽያና ከእስራኤል ሚዲያዎች ጋር ልዮ ቃለምልልሶችን ሰጥቻለሁ። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ፤ አትሌቶች እንዲሁም በዓለም አትሌቲክስ ዙርያ ያተኮሩ ነበሩ። ከዚህ በታች የቀረበው ደግሞ በቡዳፔስት ከተለያዩ የዓለም ዜጎች ጋር ያደርግኳቸው አጫጭር ቃለመጠይቆች ናቸው።"የኢትዮጵያ ሯጮች የዓለም ምርጦች መሆናቸውን እናውቃለን፡፡”
   የእስራኤል ማራቶን ሯጭ ደጋፊ ከደቡብ አፍሪካ

“ወደ ሃንጋሪ የመጣሁት ከባለቤቴና ሁለት ልጆቼ ጋር ነው፡፡ የዓለም ሻምፒዮናውን በስታድዬም ገብተን ብንከታተልም ዋናው ቀጠሯችን ከማራቶን ውድድሮች ጋር ነበር፡፡ ቡዳፔስት ከተማ የተገኘነው ከደቡብ አፍሪካ ተነስተን ነው፡፡ በማራቶን የሚሳተፍ አንድ እስራኤላዊ ጓደኛችንን ለመደገፍ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ወደ አዲስ አበባ መጥቼ ከኃይሌ ገብረስላሴና ከቀነኒሳ በቀለ ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሯጮች የዓለም ምርጦች መሆናቸውን እናውቃለን፡፡”
"አትሌቲክስ ቁጥር አንድ ስፖርት ነው፡፡”
ኤድዊን ከሆላንድ
“የዓለም ሻምፒዮናውን በስታድዬም በመገኘት በሙሉ ተከታትየዋለሁ፡፡ ማራቶን ለእኔ የምንግዜም ምርጥ ስፖርቴ ነው፡፡ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ ያገኘውና የሮተርዳም ማራቶንን ያሸነፈው የሆላንድ ሯጭ አብዲ ነገዬ ደጋፊ ነኝ፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ ሯጮችንም አውቃለሁ፡፡ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ተፎካካሪ ያጡት የተሻሉና ምርጦች በመሆናቸው ነው፡፡ ማራቶንን ያወቅኩት በአቴንስ ወታደር የሮጠውን ርቀት ከሸፈንኩ በኋላ ነው፡፡ አትሌቲክስ ቁጥር አንድ ስፖርት ነው፡፡”
“እያንዳንዱ ማራቶን የራሱ ታሪክ አለው”
ፋብዮ ከቤልጅየም
"ዓለም ሻምፒዮናውን ስከታተል ሳምንቱን ሙሉ በቡዳፔስት ነው ያሳለፍኩት፡፡ በተለይ ደግሞ የማራቶን ውድድሮችን ለማየት የመጣሁት የማራቶን ሯጭ በመሆኔ ነው፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው ላይ ቤልጅዬም በጉዳት ሳቢያ በርካታ ምርጥ አትሌቶችን አለማሳተፏ ይቆጫል፡፡ ማራቶን እጅግ ልዩ ስፖርት ነው፡፡ እያንዳንዱ ማራቶን የራሱ ታሪክ አለው። 7 ማራቶኖችን ሮጫለሁ፡፡ 34 ኪሜ ከሸፈንክ በኋላ የማራቶን ውድድር ክብደትን ትረዳዋለህ፡፡በባዶ እግሩ ማራቶንን የሮጠውን አበበ ቢቂላ ታሪክ አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጲያ በማራቶን ብቻ ሳይሆን በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር የዓለማችንን ታላላቅ ሯጮች ማፍራቷን አውቃለሁ፡፡ በስም እየጠራሁ ባላውቃቸውም፡፡”
"ማራቶንን ስትወዳደር ፉክክሩ ከራስህ ጋር ነው፡፡
ጃፓናዊ የማራቶን ደጋፊ
“የጃፓን ማራቶን ሯጮችን ለመደገፍ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቡዳፔስት ተገኝተናል፡፡ ማራቶን እጅግ አስደናቂ ስፖርት ነው፡፡ ማራቶንን ስትወዳደር ፉክክሩ ከራስህ ጋር ነው፡፡ ራስን ለማሸነፍ በቂ ዝግጅትና ጥንካሬ ያስፈልጋል፡፡ ራስህን ካሸነፍክ ማራቶኑን ድል ታደርጋለህ፡፡”
"አትሌቶቻችን አምባሳደሮቻችን ናቸው፡፡”
ምንያህል ከኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ደጋፊዎች ማህበር
“ቡዳፔስት ላይ አትሌቶቻችን በማራቶንና በሴቶች ሺ ላይ ካሳዩት መደጋገፍ ብዙ እንማራለን። ማህበራችን የተቋቋመው በአሜሪካ ዩጂን ከተመዘገበው ውጤት በኋላ ነው፡፡ ለአትሌቶች የምንስጠው ክብር ያንሳል፡፡ መሻሻል ማደግ ይኖርበታል፡፡ አትሌቶችን በውድድር ሰሞን ብቻ ይሆን ሁሌም የምናወድስበት የምናደንቅበት ነው፡፡ አትሌቶቻችን አምባሳደሮቻችን ናቸው፡፡ በየትኛውም የዓለም አገር ይታወቃሉ፡፡”

______________


"በጀግኖች አደባባይ የተገኘነው የኢትዮጲያን አትሌቶችን ለመደገፍ ነው፡፡"
 ፍቃዱና ቤተሰቡ

“በሃንጋሪነዋሪነታችን በቡዳፔስት ነው። በጀግኖች አደባባይ የተገኘነው የኢትዮጲያን አትሌቶችን ለመደገፍ ነው፡፡ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ከሆነበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጲያ ባህላዊ ስፖርት ለመሆን የበቃ ነው። ማራቶን ጠንካራ ዝግጅት የሚያስፈልገው፤ ጥሩ የሚጠይቅና የአትሌቱን ጀግንነት የሚያሳይ ስፖርት ነው፡፡ በቡዳፔስት የምንኖር ኢትዮጲያውያን በቡድናችን እጅግ ደስተኞች ነበርን፡፡እኔ እንደውም የኢትዮጲያ ቡድን ከመምጣቱ በፊት ስለቡዳፔስት ሙቀት ለፌደሬሽኑ መረጃ በመላክ ሁሉ ቡድኑን ለመደገፍ ጥረት አድርጊያለሁ፡፡ ማራቶን የእኛ ባህል መገለጫ ሆኗል፡፡ በዓለም ዙርያ በበርካታ ከተሞች ይደረጋል፡፡"
የኢትዮጲያን አትሌቶች በቡዳፔስት ጎዳናዎች ላይ በማየቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ የእኛ ሯጮች ከሙቀቱ አንጫር በጣም ጠንካሮች ናቸው፡፡ ሩጫ በጣም እወዳለሁ፡፡

________________


“ስለማራቶን ሳስብ በጭንቅላቴ የሚመጣው በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በመሮጥ ያሸነፈው አበበ ቢቂላ ነው፡፡"
  ሮናን ከእስራኤል

በዓለም ሻምፒዮና ላይ በማራቶን  ለእስራኤል የሜዳልያ ድል ማስመዝገብ ታላቅ ታሪክ ብቻ ሳይሆን እውነት የማይመስል ልቦለድ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ስለማራቶን ሳስብ በጭንቅላቴ የሚመጣው በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በመሮጥ ማራቶንን ያሸነፈው አበበ ቢቂላ ነው፡፡ አበበ የመጀመርያውን የማራቶን ድል የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገበ የማራቶን ነብይ ለማለት ይቻላል፡፡ ከዚያም በኋላ የማሞ ወልዴን ታሪክ አውቃለሁ፡፡ ኃይለ ገብረስላሴንም እጅግ የማደንቀው አትሌት ነው፡፡ ማራቶን የአትሌቲክስ ንግስት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመላው አለም በበርካታ ከተሞች የማራቶን ውድድሮች ይዘጋጃሉ፡፡ በርካታ ተሳታፊዎችንም ያገኛሉ፡፡ በእኔ እምነት አትሌቲክስ የዓለማችን አንጋፋውና ተወዳጁ ስፖርት ነው፡፡ እግር ኳስና ቅርጫት ኳስ በዓለም ዙርያ የገነኑ ስፖርቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አትሌቲክስ ግን በእነ አበበ ቢቂላ፤ ፓቮ ኑርሚ እና ኪፕኬኖ ዘመን ሲጠቀስ እንድም ኳስ ተጨዋች ስሙ አይታወቅም ነበር፡፡

Read 166 times