Sunday, 17 September 2023 21:14

ትናንትም ዛሬም…. ሰልፍ ሜዳ

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(2 votes)

 እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግርማ ተስፋው የተባለ ደራሲ፣ ከዚህ  መጽሐፉ ውጭ ሌላ ስራ እንዳለው ፈጽሞ አላውቅም ነበር፡፡ በአንድ የበልግ ቀትር በፒያሳ ጎዳናዎች ስዘዋወር ከአሮጌ መጻሕፍቶች መካከል ሌላኛው የጥበብ ትሩፋቱ ገጥሞኝ ተዋወኩ፤ የግጥም መድበል ነው፡፡ “የጠፋችውን ከተማ ሀሰሳ” ይሰኛል። ያልጠበቅኩት ደስታ ፈንቅሎኝ አይኔን ከመድበሉ ማሸሽ ተሳነኝ፡፡ ባገኘሁት እለት፣ ምሽቱን አጠናቅቄው አደርኩኝ፡፡ ውስጤ የቀሩ ግጥሞቹን ለመሰንበቻዬ ለማጣጣም በለሆሳስ መላልሼ እያመነዠኩና እያሰላሰልኳቸው ከረምኩ-ለወራት፣ ለአመታት፡፡ የዛሬ ዳሰሳ አቢይ ትኩረቴ “ሰልፍ ሜዳ” እንደመሆኑ፤ በአጫጭር ውብ ግጥሞቹ እያዋዛሁ ቅኝቴን  ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ሁለቱን ክንፎቹን በእጆቼ ጠፍሬ
እግሩ እንዳይላወስ በገመድ አስሬ፣
ሆዴ እየተመኘው ልቤ እያዘነለት
ዶሮዬን አረድኩት እየራራኹለት፡፡
ንጉሴ ለምን ሞተ? ብሎ በጥያቄ ይጀምራል ትረካው፡፡ ጥያቄው ከሀዘን የመነጨ ሙሾ ለማውረድ የተነሳ ስሜታዊ ሳይሆን በተጠየቅ የመጣ ምክንያታዊ ነው፡፡ ንጉሴ የመጽሐፉ ዐቢይ ማጠንጠኛ ሆኖ ከዋና ገጸባህሪነት ላቅ ያለ ሚና ያለው ምልክት ነው፡፡ ተኖረና ተሞተ… ይሉት የአለቃ ገብረ ሀና ምሳሌ፣ የንጉሴ ጥጋቡ ህይወትን የሚወክልና የሚመጥን ተረት-ተረት ነው፡፡ ዱቄት ለብሶ፣ ዱቄት መስሎ ሰልፍ ሜዳ ውስጥ የኖረ ምስኪን የወፍጮ ቤት ሰራተኛ፣ ወዛደርና ዛፍ ቆራጭ ነው እሱ፡፡ (ሰርቶ አይመስገን፣ ከሰውም አይቆጠር እንጂ፣ እሱ ያስፈጨውን የጤፍ እንጀራ ያልበላ አለ እንዴ በሰፈሩ!) ዘመኑን በሙሉ ደፋ ቀና ሲል ኖሮ፣ በአንድ ዝናባማ ቀን በመኪና አደጋ ህይወቱ ያለፈ፡፡ የእግዜር ቀልድ እሚጀምረው እንግዲህ ከዚህ ነው፡፡ ፍትህ በጎደለው ከይሲ አለም ውስጥ እየኖርን የመሆናችንን ሀቅ በይበልጥ አጉልቶ እሚያስረግጥልን፤ እግዜር በድሀ ልጅ ሲያላግጥ በንጉሴ ህይወት በኩል ደራሲው ምሳሌ አድርጎ ሲያስነብበን ነው፡፡ አዎ! እግዜር በርግጥ በአለምና ሰዎቿ እንደጉድ ይቀልዳል፡፡ ግን አይስቅም፡፡ እርሱ ፈጥሮ፣ እርሱ ስቆ እንዴት ይሆናል፡፡ ሹፈቱን፣ ብሽሽቁን፣ አቅምና ጉልበት ፍትትሹን…ተፈጣሪ ብዙ ጊዜ ልብ አይልም፡፡
ተራኪው መምህር ታሪኩ፣ በንጉሴ ህይወት በኩል አጮልቆ ከፈጣሪም ጋር ይነታረካል። አምላክ በዚህች አለም የብዙኃኑ የሰው ልጆች ኑሮና አኗኗር እንዲሁም አፈጣጠር ላይ ከንጉሴ ባሻገር ቀበሌ ሰላሳን ቆሎ ገዢ ፍለጋ የምታካልለው እሙ፣ ባለሻይ ቤቱ ሙሰማ፣ ሹፌር ትጉሀን ፍርድ ያውቃል…እንደማሳያ በማቅረብ፣ በማነጻፀርና በመመርመር ልክ አለመሆኑን በፍልስፍና መነጽር ይሞግታል። ሙግቱና ጥያቄዎቹ ሁሉ ደግሞ በለት-ተለት ኑሮዋችን ውስጥ የምናነሳቸው ተጠየቆች ናቸውና ሚዛን ያነሳሉ፡፡
እንጀራ አዳኝ ሆድ አምላኩን ፈጥሮ ፈጥሮ
የፈጠረው ማቲ ሁሉ እንደ’ንጀራ ዐይኑ ታውሮ፡፡  
እግዜርም ልፊያ ሲያምረው ያቆብን
ሳይቀሰቅስ
አንተን ያሸፍትሀል፤
ሊሰማኽ “ለምን ስትል?”
ስትሸነፍ ስታለቅስ፣ ስታሸንፍ ስታለቅስ፡፡
ህይወት ለራሷ ታዳላለች
ያንተ ዐይነት ትንግርት ፍጡር ለዘመን ጉድ
ታቆማለች፡፡
በ”ሰልፍ ሜዳ” ውስጥ እግዜር በሰው ልጆችና በፍጡራኑ በጠቅላላ አብዝቶ ጨክኗል። ህዝብ በህዝብ ላይ፣ መንግስት ደግሞ በቀበሌ ሀያ ዘጠኝ ላይ የተነሳው፣ የፍጻሜው ምልክት በመሆኑና መጨረሻችንም ስለተቃረበ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በነዋሪውና በእግዜር መሀል ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ክፍተቱን ያኖረው ደግሞ ኑሮ የሚባል ፍትህ የራቀው፤ ልዩነት የበዛበት ጨካኝና ጨለማ፤ ጊዜ፣ ዕድል፣ ዕጣ…በተባሉ ወሰኖች የተደለደለ የእግዜር ፌዝ ነው፡፡
(እዚህ ጋ  አንድ  የጋሽ ስብሃትን ንግግር አስታወሰኝ፡፡ ወጉና ጭውውቱ እንዲሁም አጥብቆ ጠያቂው ጋዜጠኛ ከበደ ደበሌ ሮቤ ነው፡፡…
 “ዋቢ ሸበሌ ሆቴል መጽሐፍ ስናስመርቅ በመነካት ጋሼ ስብሃት፤ እንደው እግዜርን ለመሆን ፈልገህ ታውቃለህ? አልኩት፡፡ እግዚአብሔርን ለመሆን ፈልጌ አላውቅም አለኝ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን ፊት-ለፊት አግኝቼ ለማፋጠጥ ፈልጌ አውቃለሁ፡፡ ይሄንን ድሃ፣ ይሄንን ሃብታም፣ ይሄንን አካል ጉዳተኛ፣ ይሄንን ጤናማ---አድርገህ ለምን ፈጠርክ? ብዬ ለማፋጠጥ፡፡…” የኛ ፕሬስ.2008)
ሁሉም ኑሮውን ማዕከል አድርጎ ወደ አምላኩ ይጮኻል፡፡ ወይ ፍረድ ወይ ውረድ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔርን መጎንተል ሁለተኛ ተፈጥሮአቸው ይመስላል፡፡ ሙሰማ እንኳን በዋጋ ንረቱ፣ በኑሮ ውድነቱ በማማረር እግዜርን ነክሶ ይዟል፡፡ ጊዜው  ይሄው ዘመን ነው፡፡ ትንቢትም ይመስላል፤…“ወያኔ ከመጣ በኋላ ምን ያልመጣብን ነገር አለ? የዕቃ ዋጋ ሰማይ እየወጣ ነው! ዳቦ የለ÷ ጋዝ የለ! ዓለም የምትጠፋው በዋጋ መናር እንጂ በምን ሊኾን ይችላል?” (ገጽ.12)
ደራሲው ግርማ ተስፋው ይህን ሲል መጻኢ ጊዜያችን አስቀድሞ ገብቶት ይሆን? በሙሰማ በኩል ያለንበትን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያስቀመጠልን ምናልባት እንደ ወልይ እግዜሩ አሳይቶት ይሆን? በዚህ ስራ ውስጥ የቀረቡ ገጸባህሪያት ሁሉ ባሉበት የቆሙ፣ ዘመኑ ብቻውን አልፏቸው የሚሄድና እጣ ፈንታቸው በአንዲት ስስ ልጅ ነፍስ ውስጥ ታጭቆ የተደለደለና በንጉሴ ሞት ላይ የተገመደ ይመስላል፡፡ የህይወት ውበት የሚባል፣ በግንኙነትና በማህበራዊ የኑሮ መስተጋብር ውስጥ ያለ ደስታ…የከንቱነት ማስታወሻ ደውል ሆኖ ቀርቧል፡፡ አቀራረቡ ግን ይህ ቀረሽ የማይባል ለዛና ውበት አለው፣ ህይወት አለው፣ ተስፋ አለው፡፡ ነገ ብሩህ እንደሚሆን በአንድ በኩል ያመሰጥራል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይፈክራል፡፡
ነሀሴ ግም ሲል ሐምሌ እንደቀልድ አልፎ
ፍቅር ይዞኝ ነበር፤
ከሰማዩ ለቅሶ ከጣለው ወጨፎ
ላፈቀረ መንፈስ
ዝናቡ ወይን ነው
ነጎድጓድ መብረቁ፣ የሐሤት ሻማ ነው፡፡
በመጪው  ሳምንት ደራሲው በ“ሰልፍ ሜዳ” ውስጥ ያነሳቸውን እምቅና ሞጋች ፍልስፍናዎች አስቃኛችሁና ዳሰሳዬን እቋጫለሁ፡፡ የነገ ሰው ይበለን፡፡
Read 582 times