ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው የጦር ጉዳተኞች የሚገለገሉበት ማዕከል ተመርቆ ተከፍቷል
በሁለት ዓመታቱ የሰሜኑ ጦርነት የሞቱ ታጋዮችን መርዶ ለቤተሰቦቻቸው ለመንገር ዝግጅት እየተደረገ ነው ተባለ። በጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች መሞታቸውና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተገልጿል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በመቀሌ ከተማ የተገነባውንና በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው የጦር ጉዳተኞች ይገለገሉበታል የተባለውን ማዕከል ሰሞኑን በይፋ መርቆ ከፍቷል።
በማዕከሉ የምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ እንደተነገሩት ጊዜያዊ አስተዳደሩ በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ ይሰራል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የጦር አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ያመለከቱት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ እነኚህ ወገኖች በተገቢው ሁኔታ ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው አይደለም ብለዋል።
በጦርነቱ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ታጋዮችን መርዶ ለቤተሰቦቻቸው ለመንገር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ጊዜያዊ አስተዳዳሪው፤ የመርዶ ማርዳቱ ሥነ-ስርዓት መቼ እንደሚደረግ ግን አልተናገሩም። ማንኛውም የትግራይ ሃብትና ንብረት ሁሉ የጦር ጀግኖቻችን ሃብት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የጦር ጉዳተኞቹን ለመንከባከብና የጦርነት ሰለባ ወገኖችን ቤተሰቦች ለመደገፍ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ሰሞኑን በመቀሌ ተመርቆ በተከፈተው የቀድሞ ተዋጊዎችና ከፍተኛ የጦር ጉዳተኞች መኖሪያና መንከባከቢያ ማዕከል ውስጥ 235 ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ታጋዮች የገቡ ሲሆን፤ 57 የሚሆኑት ደግሞ በቅርቡ እንደሚገቡ ተጠቁሟል።
Saturday, 23 September 2023 21:14
በትግራይ ክልል በጦርነቱ የሞቱ ታጋዮችን መርዶ ለመንገር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ
Written by መታሰቢያ ካሳዬ
Published in
ዜና