Saturday, 23 September 2023 21:16

ሃሜት - ዘ ፍጥረት

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

“--ሀሜት ይሞቃል ወይንም ይቀዘቅዛል እንጂ አይሻርም፡፡ የሰው የማወቅና የመፍረድ ባህሪ እስካለ ሁሌ ሀሜት አለ፡፡ ሀሜቱ በወሬ
ዝውውር የደም ግፊቱን ከለካ በኋላ፣ የሀሜቱ ኢላማ የሆነውን ሰው በመግደል ወይንም መጠቃቀሻ በማድረግ ጊዜያዊ እረፍቱን ያገኛል፡፡--”


የማወቅ ፍላጎት የሌለው ካለ እሱ ሰው አይደለም፡፡ የማወቅ ፍላጎት ያለው ሁሉ ፈራጅ ነው፡፡
… ቀድሞ ከፍ ከፍ ያለ እሱ ቀድሞ የሚነጠፍ ነው፡፡ የሀሜት ትርጉሙ ይሄ ነው፡፡ የማወቅ ፍላጎት፤ ሲለጥቅ ደግሞ... የመፍረድ ፍላጎት፡፡
ሁሉም ሰው ነኝ ባይ በውስጡ ይሄንን ይዞ የሚዞር ነው፡፡ በውስጡ… ስለማንም … መጀመሪያ የተደበቀውን ማወቅ… ቀጥሎ መፍረድ፡፡ ሚስጥር የሚያስፈልገው ይሄ ፍላጎት የግድ መርካት ስላለበት ነው፡፡ ሚስጢሩ መደበቁ ላይ ይታሰራል፡፡ የተደበቀውን አነፍንፎ፣ አዋዝቶና አባዝቶ የገለጠው… በችኮላ ቀጥሎ ወደ ሀሜት መዞር ይችላል፡፡ ፍርድ ሰጥቶ፣ ለሌሎች ዝግጁ ፈራጆች ያወቀውን ሚስጢር እንዲያውቁ ለማድረግ ይነሳል፡፡ የሃሜት አሰራጩ ባህሪ ከተቀባዩ ጋር በሰውነት ጉጉት ተሳስሮ የተጋጠመ ነው፡፡
በምድር ላይ ይሄንን የጉጉት ሰንሰለት ሊሰብረው የሚችል ማንም የለም፡፡ “ሀገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው” ሆኖ፤ የሚስጢሩ የወይን ዘለላ…. ወደ ጠወለገ ዘቢብነት እስኪቀየር ድረስ፡፡ ከከፍታው ውስጥ ነው የመውደቂያው ሸርተቴ የሚዘጋጅለት፡፡ አወጣጡ ላይ ያኮበኮበው በረራ ውድቀቱ ላይ ሚስጢሩ እንቆቅልሽ መሆኑ ያከትምለታል፡፡ ዝም ማለት የሚያስፈልገው ሚስጢሩን ለመጠበቅ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ሀሜት በራሱ ላይ የሚናገረው፣ እውቀቱን ይዞ በዝምታ ሚስጢሩን ጠብቆ መቀመጥ ያቃተው… ራሱ የታሪኩ ባለቤት ነው፡፡
ለምሳሌ… “ደመቀ ሶስት ጉልቻ መሰረተ” የሚለው ሊሆን ይችላል እውቀቱ፡፡ ከፍፍ ከፍ የሚያደርግ ክብር የሚጨምር ነገር ስለሆነ… የታሪኩ ባለቤት ስለ ጉልቻው ጉዳይ እንዲታወቅለት ይፈልጋል፡፡ ድግስ ይደግሳል። ተሰብሰቡልኝ ይላል፡፡ ምርቃትም ሊሆን ይችላል፡፡ “ደመቀ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቆ ከአውሮፓ ተመለሰ” ሊሆን ይችላል እንዲታወቅ የተፈለገው ጉዳይ፡፡ ሚስጢር የሚሆንበት ምንም ምክኒያት የለም፡፡ የኩራትና የክብር ምንጭ ነው፡፡
ግን እንዲታወቅለት ከፈለገው ጋር የሚጣረስ ሌላ ሚስጢር ከመጣ፣ ያኔ የሃሜተኛ ስራ ይጀምራል፡፡
“የሆነ ከባህር ማዶ የመጣ ሰው አግኝቼ ትምህርቱን ሳይጨርስ ነው የተመለሰው ብሎ አጫወተኝ” ይላል አንዱ እደመቀ ሰፈር ተከራይቶ የሚኖር ወሬ ቀለቡ የሆነ ሰው፡፡ ይሄንን የሚላት ለሚስቱ ነው መጀመሪያ፡፡
“ሂድ- ሂድ” ትላለች ሚስቱ፤ ማመን እንደማትፈልግ በሚያሳምን አኳኋን፤ ልቧን በእጇ ደግፋ፡፡ “ወይኔ ሚስቱን! ወይኔ እሷን! ደግሞ መንታ መንታ ነው የወለደችው… ምን አብልታ ታሳድራቸው ይሆን?... ውይ! ውይ! በእመቤቴ አያድርግባት!.. አንተ ግን ከማን ነው የሰማኸው?” ትለዋለች ባሏን፡፡ ባሏ ይዞላት የሚመጣውን ወሬ በቀላሉ ለማመን አትፈልግም፡፡ ባታምንም ግን…ባታረጋግጥም… አንድ ሚስጢር ግን አውቃለች፡፡ ያሳወቃት ባሏን የምትጠረጥር መስላ የሀሜት መነሻ በማግኘቷ ግን ደስተኛ ናት፡፡
ብዙውን ጊዜ ልቧን በእጇ የሚያስድፍ ድንጋጤ ሲገጥማት ደስተኛ ናት፡፡ በአፏ ግን… ደስታዋን ለመቃወም ደጋግማ ታማትባለች። ባሏ ከአጠገቧ ዞር ሲል ስልክ መደዋወል ትጀምራለች። ደመቀን የሚያውቁ ጓደኞቿ ጋር። በእርግጥ ሀሜቱን በቀጥታ ስልክ እንደተነሳ… ላነሳው በቀጥታ አትነግርም። በሰላምታ ጀምራ…. ስለ ልጆች ጤና እና ስለ አዘቦቱ ቀን ውሎ ስትጠይቅ ቆይታ በመሃል…” አንቺ ደመቀ ከስራ የተባረረው የተማረበትን የትምህርት ማስረጃ አስገባ ሲባል የለኝም ብሎ ነው የሚባለውን ሰምተሻል …የሆነ ሰው ወሬውን ነግሮኝ ክው አልኩኝ… ለመአዛ እና ለልጆቹ ሲባል እውነት ባልሆነ…” በስልክ ውስጥ ባይታይም ታማትባለች፤ ጨዋዋ ሀሜተኛ፡፡
“ሊሆን ይችላል…” ትላለች ሚስጢርና እውቀት በስልክ እየተላለፈላት ያለችው አድማጭ፡፡ “ይሄ ደመቀ የተባለ ሰውዬ ነገረ-ስራው በጠቅላላ አላማረኝም ነበረ፡፡ የተማረ ሰው እኮ ጥላው ትንሽ ይከብዳል… የፍራሽ ተራ ነጋዴ ነው እኮ የሚመስለው… ቆይ ግን እስቲ አጣራለሁኝ” ትላለች የሃሜት ዘረ መሏ በመነቃቃት ላይ ያለችው አድማጭ፡፡ ዋናው ወሬ ከተላለፈ ተልዕኮው ተጠናቋል፡፡
ግን የተደዋወሉበት ዋና ጉዳይ ለሃሜቱ እንዳይመስል ሌላ ነገር ደርተው ያወራሉ፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ዋናው ጉዳይ ሃሜቱ እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ እንደተላለፈ እርግጠኛ ሲሆኑ ስልኩን ይዘጋሉ፡፡
የሚነሳ ስም ላይ ሁሌ አንዳች ሚስጢር አለ። አንሺው አንዳንድ ጊዜ ጠይቆት የማያውቀው ሰው ቤት ድረስ አውቶቢስ ተሳፍሮ ወይንም ራይድ “እንደው ሰው ሲጠፋ እንኳን የት ገባ አትሉም?” ብሎ ሰተት ብሎ ሳሎን እንዲገባ ሊያደርገው ይችላል፡፡ አመሳጥሮ፣ በሰምና ወርቅ አደናግሮ፣ ስሜትን ወጥሮና የተዘጋ የወሬ አፐታይትን ከፍቶ ሀሜት ተሸክሞ የመጣው ጭነቱን፣ ለማድመጥ በተቁነጠነጠ ጆሮ ላይ ይዘረግፋል፡፡ ከዘረገፈ በኋላ የተፈላውን ቡን እንኳን ሳይጠጣ እንደገና ለመሄድ ሊነሳ ይችላል። የሚቸኩለው፤ ሌላ ያልሰማ ዘንድ (ወሬው ተረጋግጦ ሳይቀዘቅዝ በፊት) የሀሜት ብቸኛ ምንጭና አከፋፋይ ሆኖ ለማድረስ ነው። ብቸኛ የሃሜቱ አስመጪና ወኪል መሆኑ ሳይደረስበት ነው፣ በነፍስ ወከፍ በእየደጃፉ ማራገፍ የሚፈልገው፡፡
ወሬ ይዘው መጥተው ዳር ዳር እያሉ በገደምዳሜ አድርገው የሚያወሩ እንዳሉት፣ እንዳልሰሙ መስለው… “አልሰማሁም እኮ!” ብለው… አውቀው የቆዩትን… በሌላ ሰው አንደበት ሲተረክላቸው፣ ከሀሜት ፍቅራቸው ብዛት በድጋሚ እየተደነቁ የሚሰሙትን የቤት ቁጥር ያለው ቤታቸው ይቁጠራቸው፡፡ እንደ አዲስ ሙዚቃ፣ ወሬው የተከፈተለት ሁሉ፣ እንደ አዲስ አድማጭ፣ ከተለያየ ሀሜተኛ የውድቀቱ ዜማ ሲዜም የልባቸው ትርታ ከጆሮአቸው ጋር በአንድ ዳንኪራ ይጨፍራል፡፡ ቅኝቱ የግለሰብ ክፉ ዜና ነው፡፡ በፊት ገፅታ ላይ የሃዘን ጭንብልን ስሎ በልብ ውስጥ ግን በጉጉትና ደስታ የሚደመጥ የዜማ አይነት ነው - ሃሜት፡፡፡
የታሪኩ ባለቤት ጋ  የሚደርሰው ቆይቶ ነው፡፡ የሚደርሰው እንደ አካሄዱ፣ ዙር ሰርቶ ከጨረሰ በኋላ ወሬውን ባዳረሰው ሀሜተኛ ራሱ በኩል ሊሆን ይችላል፡፡ ሀቀኛ መሳዩ ወሬኛ፣ ለራሱ ለታሪኩ ባለቤት ወሬውን ይዞለት የሚመጣው የመልካም ፈራጅን ቅርፅ ተላብሶ ነው፡፡
“… ደመቀ እኔ እንደሌላው ሰው የሚወራብህን ካንተ ልሸሽግህ አልፈልግም፡፡ አልችልምም፡፡ በዛ ላይ ሳላረጋግጥ ሌላው የሚያወራብህን ተቀብዬ ማጋጋል…ህሊናዬ ፈፅሞ አይቀበለውም..… ከስራ የተቀነስከው የትምህርት ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻልክ ነው ብለው እያስወሩብህ ነው። እነማ አትበለኝ! እኔ ሃቁን ለማወቅ ፈልጌ እንጂ በሰዎች መሃል መሻከር እንዲፈጠር ፈልጌ አለመሆኑ ይሰመርበት፡፡”
ደመቀ የሚሰጠው መልስ ሀሜቱን መሰረት አልባ የሚያደርገው ቢሆን እንኳን የተከፈተው የሀሜት በር እንዲሁ በቀላሉ አይዘጋም። በደመቀ ላይም ባይሆን፣ በሌላ ተረኛ ላይ ሀሜት ሁሌ ይቀጥላል፡፡ የሚያማውም ራሱ መልሶ ይታማል፡፡ የሚያሳምመው ይታመማል። ሲታመም፣ አዙሪቱ፣ እሱን የታሪኩን ባለቤት “ጆሮ ለባለቤቱ” አስብሎ በሚያስተርት ሁኔታ አግልሎ፣ እሱ ሲያፋፍም የነበረው ወሬ በራሱም ላይ ይቀጣጠልበታል፡፡
ስምን ፅዱ አድርጎ መቆየት የሚቻለው እስኪቆሽሽ ብቻ ነው፡፡ ወይንም መቆሸሹ እስኪወራ፡፡ “አትንገር ብዬ ብነግረው አትንገር ብሎ ነገረው” የአዙሪቱ የደም ስር ነው፡፡ አትንገር ብሎ የነገረው ለራሱ ታሪክ ባለቤቱ መሆኑም አይደል?
…የልቡን ሚስጢር፣ የከበደውን፣ እንዲጋራው መጀመሪያ የተነፈሰው ሰውዬ፣ ራሱ ዘንድ ወሬው ዙር ሰርቶ ተመልሶ ሲደርስ… ያኔ ጥበቡ ተሰርቶ ተጠናቀቀ ይባላል፡፡

የደመቀ ጉዳይ እንኳን በቀላሉ እልባት ያገኛል፡፡ የተማረበትን ዲግሪ አውጥቶ ማሳየት ብቻ ነው ያለበት፡፡ ካሳየ በኋላ የሀሜት ምትሀቱ ወዲያው ካባውን ይገፈፋል፡፡ ግን ወደፊት የሄደው ወደኋላ ሲመለስ የሀሜተኞቹን አንደበት ዘግቶ ወይንም በይፋ ያልተጣራ ወሬያቸውን ባፋፋሙበት ሰው ፊት ራሳቸውን አዋርደው ይቅርታ በመጠየቅ አይደለም፡፡ ሀሜት ይሞቃል ወይንም ይቀዘቅዛል እንጂ አይሻርም፡፡ የሰው የማወቅና የመፍረድ ባህሪ እስካለ ሁሌ ሀሜት አለ፡፡ ሀሜቱ በወሬ ዝውውር የደም ግፊቱን ከለካ በኋላ፣ የሀሜቱ ኢላማ የሆነውን ሰው በመግደል ወይንም መጠቃቀሻ በማድረግ ጊዜያዊ እረፍቱን ያገኛል፡፡ ከአንዱ ተልዕኮው ሲያርፍ ወዲያው ሌላ ተልዕኮ አንግቦ ነው፡፡ ስለዚህ ሀሜት የጥቂት ሰዎች ባህሪ ሳይሆን ሰው የመሆን ፀጋ ነው፡፡ መገለጫው ነው፡፡
ይኼንንም ያንንም ማወቅ፡፡ በዚህም በዚያኛውም መደንገጥ፡፡ በሁሉም ሁሌም መፍረድ፡፡ ሰው ለሆኑት ፀጋው የሚሰጣቸው አቅም ነው፡፡ ግን ፀጋ ስለመሆኑ ማንም ማመን አይፈልግም፡፡ ሀሜተኛ እያማ ባለበት ቅፅበት እያማ ስለመሆኑ ቢነገረው፣ ወይንም አድማጩ እያደመጠ ባለበት ቅፅበት ሃሜት ስለመውደዱ እወቅ ቢባል… ይቀየማል እንጂ አይቀበልም፡፡ አይመለስም፡፡
ለነገሩ ጮማ የሆነ ሚስጢር ገላጭ ወሬ እየተወራ ሳለ አዙሮ ስለ አውሪው/ አውሬ መመዘን የሚችል የለም፡፡ ወሲባዊ ተራክቦ መሃል ሳለ ከሱቅ መልስ አጉድሎ እንደተቀበለ እንደማስታወስና አቋርጦ ለመቀበል መሄድን እንደማሰብ ነው፡፡ መልሱ በኋላ ይደረስበታል። የሚወራው ወሬ ሀሰት መሆኑን ከሚታማው ሰው ባልተናነሰ እርግጡን የሚያውቅ እንኳን ቢሆን አድማጩ…ከቅፅበታዊ ሃሴቱ መናጠብ አይፈልግም፡፡ ስቆና ተዝናንቶ ከጨረሰ በኋላ ምናልባት ሊፀፀት ይችላል፡፡ “አይመስለኝም” ብሎ ማቅማማት ከቻለ ራሱ ከህሊናው ጋር የሚከባበር ሰው ነው፤ “አልሰማም” ብሎ መሸሽ ግን አይታሰብም፡፡ የደመቀም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው፡፡

Read 1204 times