Saturday, 07 October 2023 20:19

”በትንባሆ የተገዛ ጦር እገበያ መሀል ቢወረውሩት ጓያ ጫፍ ላይ ይቆማል!”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

እንቁራሪቶች ጦጣዎች፣ አይጦችና የዱር አራዊቱ ንጉስ አንበሳ የሚኖሩበት ትልቅ ደን አለ፡፡
እንቁራሪቶቹ ከደኑ አጠገብ ካለው ኩሬ ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ አንበሳ የሚጠይቃቸውን ሁሉንም ለመታዘዝ ነው ሌሎቹ የሚኖሩት፡፡ አንድ ቀን እንቁራሪቶቹ፣ ጦጣዎቹና አይጦቹ በአንድነት መስክ ላይ በየበኩላቸው እየለቃቀሙ ሳሉ፤ አዳኞች አንበሳውን ሲያሳድዱት ተመለከቱ፡፡ እንቁራሪቶቹም፤ “ለጌታም ጌታ አለው! ሰው እኮ የአንበሳ ጠላት ነው አይለቀውም፡፡ ከዚህ መአት ለማምለጥ በሉ ወደ ኩሬአችን እንሂድ” አሉና ወደ ኩሬአቸው አመሩ፡፡ አይጦቹም፤ የደኑ ገዢ አንበሳ ነው ብለው ስለሚያስቡ “ሰዎችና አንበሶች አጥፊና ጠፊ ናቸው፡፡ የዚህ አንበሳ ጣጣ ለእኛም እንዳይተርፈን በጊዜ ወደ ጎሬአችን  ገብተን እንሽሽ” አሉና ሄዱ፡፡ ጦጣዎቹ፤ “ሰው አንበሳን ሲጠላ እንደ ጉድ ነው፡፡ በጊዜ ዛፋችን ላይ እንውጣ” ብለው በየዛፎቻቸው ላይ ተንጠላጥለው ወጡ፡፡
አዳኞቹ አንበሳውን ገድለው ቆዳውን ገፈው ወሰዱ፡፡ አዳኞቹ ከሄዱ በኋላ እንቁራሪቶቹ፣ ጦጣዎቹና አይጦቹ እንደገና ተሰባስበው፤ ጦጣ ስለ ዛፍ ላይ ኑሮ፣ እንቁራሪት ስለ ኩሬ ኑሮ፣ አይጥ ስለ ከመሬት በታች ኑሮ አወጉና የአንበሳውን አሟሟት እያነሱ በየበኩላቸው የሚያስተዳድሩት ግዛት እንዳላቸው በመጥቀስ ወጋቸውን ሲሰልቁ ቆዩ፡፡
በነጋታው በኩሬ ውስጥ ያሉትን ነብሳት ሁሉ ለመብላት የሚፈልጉ አጥማጆች ሲመጡ ጦጣዎች ወደ ዛፋቸው፣ አይጦች ወደ ጉድጓዳቸው ሮጡ፡፡ እንቁራሪቶች ግን ሁሉም ከኩሬው ተለቃቅመው ተወሰዱ፡፡ ጦጣዎችና አይጦች እንደ ልማዳቸው በሦስተኛው ቀን ተገናኝተው እያወጉ፤ “እንቁራሪቶቹን ምን አድርገዋቸው ይሆን?” እያሉ ተጠያየቁ፡፡  “ሰው እኮ ጨካኝ ነው፡፡ በልተዋቸው ይሆናል” አሉ ጦጣዎቹ፡፡ “ምናልባት እስኪበሏቸው በእንክብካቤ ያኖሯቸው ይሆናል” አሉ አይጦቹ፡፡
ይህንኑ እያወጉ ሳሉ የአይጥ ወጥመድ የያዙ በርካታ ሰዎች መምጣታቸውን አዩ፡፡ ጦጣዎቹ ፈጥነው ወደ ዛፋቸው ወጡ፡፡ አይጦቹ ወደ ጉድጓዳቸው ሮጡ፡፡ ባለ ወጥመዶቹ አድፍጠው ወጥመዶቻቸውን በጥንቃቄ በየጉድጓዳቸው አፋፍና ውስጥ አኖሩባቸው፡፡
በነጋታው አይጦች የወጥመዶቹ ሲሳይ ሆኑ፡፡ ጦጣዎቹም፤ “አንበሳው ሰው ጠላቱ መሆኑን እረስቶ ጉልበቱን ተማምኖ በደን ውስጥ ሲንጎማለል ተበላ፡፡ እንቁራሪቶቹም ማምለጫ በሌለው ኩሬ ውስጥ እንደተወሸቁ መውጫ ሳያበጁ ቀለጡ፡፡ እነዚህ አይጦችም ገብተው ከማይወጡበት ጉድጓድ ውስጥ ተቀርቅረው ብቅ ሲሉ በወጥመድ እየታነቁ ሲጥ አሉ፡፡ እኛ ግን ዛፍ ላይ ነንና  ሰው ወደ እኛ ሲመጣ በቀላሉ ስለሚታየን፣ ከዛፍ ዛፍ እየዘለልን ደብዛችንን እናጠፋበታለን” ተባባሉ፡፡
ጥቂት ቀናት ሰነባብቶ ሰዎቹ ወደ ጫካው መጡ፡፡ ጦጣዎቹም ማንም አይነካን ብለው ዛፋቸው ላይ እንዳሉ ቆዩ፡፡ የሰው ልጅ ጥፋት ሰለባ መሆናቸውን ያወቁት ግን ከዳር ዳር ደኑ በእሳት  መያያዙን ያዩ ጊዜ ነበር፡፡ ዛፍ ላይ ያሉት እዚያው እንደተንጠለጠሉ ተቃጠሉ፡፡ የወረዱትም በሰዎቹ አለቁ፡፡  የሚገርመው ግን አዳኞቹ ሰዎች ቤታቸው ሲደርሱ ቤታቸው በጠላቶቻቸው ተቃጥሎ ዶግ አመድ ሆኗል!
***
አለም የአጥፊና ጠፊ መድረክ ናት፡፡ ነግ በኔ ብሎ ገና በጠዋት ያልተጠነቀቀ፣ እጣ-ፈንታው እንደ ቀዳሚዎቹ ሟቾች ነው፡፡ የፋሲካ በግ፣ በገናው በግ እንደሳቀ መሞቱ ከአመት አመት የምናየው ሀቅ ነው፡፡ እኔ የራሴን ታሪክ እሰራለሁን እንጂ ሌሎች እኔን መሰሎች በታሪኩ ውስጥ ምን ጽዋ ደረሳቸው? ብሎ አለመጠየቅ፣ ምላሹን ካገኙም፣ የኔንስ ክፉ እጣ እንዴት እመክተዋለሁ ብሎ አለማውጠንጠን የአለምንም የሀገራችንንም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ቡድኖች፣ መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ታሪካዊ እጣ-ፈንታ ሳይታለም የተፈታ እንዲሆን ካደረገው ውሎ አድሯል፡፡ ነግ-በኔ አለማለት ክፉ እርግማን ነው፡፡
ለማርቲን ኒየሞይለር መታሰቢያ የተደረገው ፅሁፍ ይሄንኑ ይነግረናል፡፡ ማርቲን ኒየሞይለር (1892-1984) የፕሮቴስታንት ክርስቲያን የነበረ ጀርመናዊ ቄስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ናዚዎችን በመቃወም ከባድ ዘመቻ በማካሄዱ እ.ኤ.አ ከ1938 እስከ 1945 ዓ.ም ለስምንት አመታት ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ አስገብተው ሲያሰቃዩት ከርሞ ኋላ ተፈትቶ፣ ከ1961 እስከ 1968 ዓ.ም ለሰባት አመታት የአለም አብያተ-ክርስቲያናት መማክርት ፕሬዚዳንት ሆኖ የመራ ጠንካራ ሰው ነበር፡፡ ለሱ መታሰቢያ የተደረገው ጽሁፍ እነሆ፡-
የጀርመን ናዚዎች መጥተው በመጀመሪያ ያጠቁት ኮሙኒስቶችን ነበር፡፡ የኮሙኒስቶቹን በር እያንኳኩ ሲጨፈጭፏቸው እያየሁ እኔ ዝም አልኩ፡፡ ምክንያቱም ኮሙኒስት አልነበርኩም፡፡
ቀጥለው አይሁዶቹንም ወረዱባቸው፡፡ የአይሁዶቹን በር ሲያንኳኩም እኔ ዝም አልኩ፡፡ ምክንያቱም እኔ አይሁድ አይደለሁም፡፡
ከዚያ ወደ ሠራተኛ ማህበራቱ ዞሩ፡፡ የሠራተኞቹን በር ሲያንኳኩም እኔ ጭጭ አልኩ፡፡ ምክንያቱም የሠራተኛ ማህበሩ አባል ስላልነበርኩ አይመለከተኝም፡፡
ቀጥለው ካቶሊኮቹን ይፈጁ ጀመር፡፡ የካቶሊኮቹንም በር ሲያንኳኩ አሁንም እኔ ዝም አልኩ፡፡ ምክንያቱም እኔ ፕሮቴስታንት ስለሆንኩ አይመለከተኝም፡፡
በመጨረሻ የእኔን በር አንኳኩ፡፡ በዚያን ሰአት ግን ተነስቶ ሊናገር የሚችል ምንም ሰው አልተረፈም ነበር፡፡
(ለማርቲን ኒየሞይለር [ፍሬድሪሽ ጁስታቭ ኤሚል] መታሰቢያ የተፃፈ- 1949)
የፈለገው መንግስት፣ ይመቸኛል ባለው መንገድ ያሻውን ሀገር ሲረግጥ፣ ያሻውን መሳሪያ ሲጠቀም፣ በእኔስ ላይ ፊቱን ያዞረ እለት ምን ይውጠኛል?  የእኔስ በር የተንኳኳ እለት ማን አብሮኝ ይቆማል? ብሎ አለመጠየቅ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ዛሬ በየቻናሉ በቀጥታ ስርጭት በቴሌቪዥን የምናየው ጦርነት፣ እንደተዋጣለት የሲኒማ አልያም የትያትር ዝግጅት የውሸት እልቂት እስኪመስል ድረስ ያስገርማል፡፡ በአለም ታሪክ የመጀመሪያው ሳይሆንም አይቀር፡፡ የጋዜጠኞቹም ድምፀት “ጦርነቱ ሊጀምር ነው፤ አብረን እንከታተል” እንደማለት ሆኗል- የሰው ልጅ ሞት ምፀት! እንደ ትላንት ወዲያ “ኢምፔሪያሊዝም ውርደት ቀለቡ ነው”… የሚባልበት የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አልፎ፤ እፎይ ብሎ አለም ለመተንፈስ አለመቻሉ ከመደገም የማይቀሩ ብዙ የታሪክ ስላቆች መኖራቸውን ያስገነዝበናል፡፡ እግረ-መንገዱንም ሃያላን መቼም በቃኝን እንደማያውቁ ዳግም ያስታውሰናል፡፡ የወታደራዊ ሃይል ግሎባላይዜሽን የት እንደሚደርስም ይጠቁመን ይሆናል፡፡ “ወተት ሰርቆ ከመጠጣት ይልቅ አፍ አለመጥረጉ ያሳፍረዋል” እንዲሉ፣ ትላልቁን የሃያላኑን ጥፋት ትቶ በእንጭፍጫፊ ላይ ማተኮር፣ ሌላ ጥፋት እንደመፈፀም መሆኑን ሳያስገነዝበን አያልፍም፡፡ ትንሹን አንባገነን ትልቁ አንባገነን፣ ሚጢጢውን ጉልበተኛ ግዙፉ ጉልበተኛ ሊውጠው ይመኛል፡፡ ይንጠራራል፡፡ ይስፋፋል፡፡ እስከዚያው እንቅልፍ የለውም፡፡ ህዝቡና አገሩ ከመጤፍ አለመቆጠሩ ግን የየዘመኑ ትራጀዲ ነው፡፡ የዛሬም፡፡ የታዋቂው ገጣሚ መንግስቱ ለማ፤ “ባንተ አልተጀመረም ያዳሜ ምኞት” “ከተጠቃው ‘መራቅ' አጥቂን ‘መጠጋት' የሚለውን ስንኝ እንደ መርህ የያዘው በርካታ መሆኑ ደግሞ መራር ትራጀዲ ያደርገዋል፡፡ “ጠባይ ያለው ልጅ ኑክሊየር ይሰጠዋል፡፡ ጠባይ የሌለው ልጅ የአሻንጉሊት ሽጉጥንም ይነጠቃል” አይነት ሆኗል፤ የሃያላኑ የአባትነት ባህሪ፡፡ ጉዳዩ ግን  የእኔን በር እስካላንኳኳ ድረስ “ለእኔ አገር አማን ነው” ብሎ ማሰብን መተውን ይጠይቃል፡፡ ሃያላን አልጠግብ ማለታቸው የስር የመሰረት ነውና፡፡
የሃያላኑን ተወት አድርገን አገራችን ስንገባም ነግ-በኔ ቁልፍ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሌላ አገር ሲጠቃ ምን ግዴ ማለት፣ ሌላ ፓርቲ ሲገፋ ምን ቁቤ ማለት፣ ሌላ ሰው ሜዳ ሲወድቅ እንደ ፍጥርጥሩ ማለት፣ ቀን የጨለመ እለት ክፉ ነገር ነው፡፡ ትላንት በራሳችን መጥነንና ለክተን ያሰፋነውን የድንጋጌና የመርህ መጎናፀፊያ፤ ዛሬ ዳር እስከዳር አገሬውን ካላለበሰነው ብለን የምንታገልበት ሁኔታ የኋሊት ጉዞ ይመስላል፡፡ “ትንሽ ስንቅ የያዘ አስቀድሞ ይፈታል” እንዲሉ፤ አገርን የሚያህል ሰፊ ባህር የትንጧን ህልማችንን መፍቻ ለማድረግና አንዲቷን ቀጭን ኩታችንን ለልጁም ላዋቂውም አለብሰዋለሁ ብሎ፣ አይሆኑም ሲባሉ ግትር ማለት ደግ አይደለም፡፡ ቢያንስ የዋህነት፣ ሲበዛ በሰፊው ተወጥሮ መሰነጣጠቅ ነው ውጤቱ፡፡
“ከቆየን አንድ አመት፣ ከበላን የተከለከለ ሣር!” እንዳለችው ላም በድርጅታዊ አሰራርና ወገናዊነት፣ በዘመዳምነት፣ በእከክልኝ-ልከክልህ፣ “በአራዳነት” በወደቀው ዛፍ ምሳር በማብዛት፣ በእቁብም በእቁባትም በመመነዛዘር ለጊዜው ሙስናን ቢያስፋፉ፣ የስር የመሰረት ብቅ በሚልበት ሰአት ምነው አፌን በቆረጠው፣ ምነው እግሬን በሰበረው ማለትን አልያም “እኔ ከሞትኩን” መድገምን ያስከትላል፡፡ የተሰራንበትን ንጥረ ነገር በምንም አይነት ካባ ብንሸፍነው የማታ የማታ ብቅ ማለቱ ከቶ አይቀርም፡፡ “በትንባሆ የተገዛ ጦር፣ እገበያ መሃል ቢወረውሩት፣ ጓያ ጫፍ ላይ ይቆማል” የሚለው የወላይታ ተረትም የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡  


Read 1613 times