የተከራየኋትን አንዲት ክፍል ቤት፣ ንፋስ እንዲገባ በሚል በሯን ገርበብ አድርጌ በማንበብ ላይ ሳለሁ፣ ከጎረምሳው የአከራዬ ልጅ አንደበት እንግዳ የሆነ ቃል ሰማሁና ከንባቤ ተናጠብኩ።
“እር.. ጎ.. መንግሥት ! እር..ጎ.. !” ይላል ድምፁን ዘለግ አድርጎ እየደጋገመ .... ። ቤተኛ የሆነው ጓደኛው እያዳመጠ ሲስቅ ከስር ከስር ይሰማል። “እግዚኦ መንግሥት" እንጂ "እርጎ መንግሥት" ሲባል ሰምቼ ስለማላውቅ፣ ነገሩን በደንብ ለማጣራት ጆሮዬን አስልቼ ማድመጥ ያዝኩ።
“ምን ሆነሃል አንተ… ምንድነው የሚያስጮኽህ ?” እናቱ ወደ ደጅ ወጥታ ጠየቀች።
”እር ..ጎ.. መንግሥት !” የእናትየውን ጥያቄ ችላ ብሎ በ"እግዚኦ መንግስት" ዜማ ደገመው።
“ ህእ-- ” ጓደኛው የግርምት ሣቁን አስከተለ።
“ምንድነው ነው ደግሞ እሱ ? ይሄ ልጅ እኮ የማያመጣብን የለም !” እናትየው በአግራሞት ተሞልታ ጥያቄዋን ደገመች። እውነት አላት፡፡ ልጁ ፈላስፋ ቢጤ ነው፡፡ የማያመጣው የለም። የዛሬው ግን ባሰ፡፡ “የረጋ የሠከነ መንግሥት ሊል አስቦ ከሆነ ተሳስቷል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ኃይለስላሴ ብቻ ናቸው ከረጋ ወተት አልፈው ቅቤ የወጣው መንግሥት የነበራቸው” የእሳቸውን ተከትሎ "በመንግስቱ ቅቤ ጠገበ ድስቱ” ተባለና እሱን አልፎ አሬራው መጣ .... ከዚያ የአሁኑ ውሉ ያለየለት ግራ ሆኖ አረፈው። ወተት የለ…አይብ የለ… ማለቢያ ቅሉ ብቻ ቀርቷል ፤ "ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል" አደል ተረቱም። የአሁኑን ታዝቦ የሚነግረን እስኪመጣ፣ እኔ 'ቅል' ብዬዋለሁ፡፡ "ቂል" አላልኩም- ይሠመርበት። እንኳን ድንጋይ የሚሰባብር ቅል።
“እርጎ አምሮት እኮ ነው።” አለ ጓደኛው፤ በጎርናና ድምፁ ሳቅ እያለ።
”ምን አምሮት ?” እናት ጥያቄዋን ሠለሰች።
”እርጎ !” አለ ልጁ ረገጥ አድርጎ፤ “እርጎ ነው ያማረኝ ! እር..ጎ.. መንግሥት ...”
“አፈር ብላ ቱ ! ለእርጎ ነው እግዜር የሚጠራበትን ቃል የቀየርከው? ኧረ ተው አንተ ልጅ ፈጣሪን ፍራ... !” ቆጣ አለች።
“አማረኛ አሀ ! አምሮ አምሮ ሲያስጮኸኝስ?” ጓደኛው ይስቃል።
“ቢሆንም እንደዚህ መዳፈር ልክ አይደለም።”
“እንዴ መዳፈሬ እኮ አይደለም ፀሎት ነው። በፍጥነት የእግዜርን ጆሮ ለማግኘት የሚደረግ ቴክኒካል ፀሎት ነው።”
“እንዴት ባክህ ?” ከቁጣዋ ለዝባ በአግራሞት ተሞልታ፣ እናታዊ ማባበሏን ቀላቅላ ጠየቀች።
“ያው እንደ እናንተ ግራ ተጋብቶ ለምን እግዚኦን በእርጎ እንደተካሁት ለማወቅ ትኩረቱን ወደ እኔ ሲያደርግ፣ በዚያው እርጎ እንዳማረኝ ይገባዋል፤ ፀሎቴ ደረሰልኝ ማለትም አይደል!” ኮራ ብሎ ሙያዊ ትንታኔውን አብራራላቸው።
“ወይ አንተ አታመጣው የለ መቼስ! በል ና እንካ ይሄን ያዝና እምታረገውን አርግበት… እርጎዋም!”
“ፈጣን ምላሽ ! ፀሎቴ ተሠማ ማለትም አይደል እር..ጎ ... መንግሥት ሀሀሀ...” ከጓደኛው ጋር እየተሣሣቀ የግቢውን በር ከፍቶ ሲወጣ ሰማሁት። እውነትም ”እርጎ መንግሥት !” ብዬ ለራሴ ፈገግ አልኩ። ምን ያህል ቢጠማው እንዲህ ርቆና ጠልቆ እንደተፈላሰፈ እያውጠነጠንኩ ብዙ አሰብኩ።
እንደ ልጁ የእርጎ አምሮት አይነት እጅግ ቀላል ጉዳዮች ተደማምረው እኮ ነው ለሁላችንም የብሶት ምንጭ የሚሆኑት። የአዳም ረታ መዝገቡ ዱባለ ትዝ አለኝ፡፡ “ፖለቲከኞች ደግሞ ሀገራቸውን ስለሚያፈቅሩ በመላጣ ሽሮ ምሣሌ በመስጠት ዓላማቸውን ትንሽ አድርገው ማሣየት አይወዱ ይሆናል፤ ምናልባት ሶሻሊዝምና ህዝቡ ሲያሸንፉ ለእያንዳንዳችን የሚሞቅ ጓንቲ ይታደለን ይሆናል ፤ ምናልባት ወደ ፊት ፖለቲከኞች ለህዝቡ ሽሮ ሲያድሉ የሽሮ አቀማመም አፈር ስለሚበዛው ጣቶቻችን እንዳይቆሽሹ ለእያንዳንዳችን ጓንቲ ይታደል ይሆናል። ኢምፔሪያሊዝም ፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ፊውዳሊዝምን እናወድማለን ከሚሉ ቀጭን መላጣ ሽሮን ከምድረገፅ እናጠፋለን ቢሉ የፈለጉትን አደርግላቸው ነበር።” ብሏል።
እውነቱን ነው 'ኮ መዝጌ ፤ እሱን ያማረረው መላጣ ሽሮ እንጂ የኢምፔሪያሊዝም ጫና ጫንቃው ላይ አላረፈም። መንግስትና ስርዓት ቢለወጥም የእሱ ህይወት ያው ነው። አብዮቱ ግን ለጭቁኖች ደርሻለሁ የሚለው ፣ ኢምፔሪያሊዝምን ካልገረሰስኩም የሚለው ለእነ መዝጌ ነው። ሀ..ሀ..ሀ... የእሱ ምኞት ግን ቅቤ ያለው ሽሮ መብላት ነበር። አንዳንዴ ፖለቲከኞች እንደ መዝጌ እንጀራ እናት ያደርጋቸዋል .... የራሳቸውን ህመም የእኛ አስመስለው የዳቦ ስም ይሰጡትና ላልታመምንበት ለማናውቀው በሽታ መድኃኒት ያስውጡናል ... የራሳቸውን ልጆች በጉያቸው ሸሽገው እኛን መሞከሪያ አይጥ ያደርጉናል።
እኛ ብቻ መድሀኒቱን የምናውቀው፣ በየግላችን የምንታመመው ፈዋሽና አስታማሚ የራቀው በሽታዎች አሉን። በእርግጥ መንግስት የሚጠግነው የተሠበረውን ድልድይና መንገድ ነው። ወለም ያለው እግራችን ተጠግኖ መሻገር አለመሻገራችን ጉዳያችን እንጂ ጉዳዩ አይደለም። እንኳን መፈወስ ህመማቸውን ለማስረዳት ፈተና የሚሆንባቸው ብዙኃኑ፣ እንደ መዝገቡ ኢምፔሪያሊዝምና ሌላው ሌላው ትላልቅ ተብዬ ጉዳይ ብሔራዊ አጀንዳ ሆኖ ሲያዩት የሚደርስልን ይኖራል ብለው ተስፋ ማድረግ እንደማይደፍሩ ግልፅ ነው።
ዘመኑም ቢሆን በግብዞች የውዳሴ ሽሚያ የጦፈ ነውና፤ ሁሉም አይቶ ሊያስጨበጭብለት የሚችለውን እንጂ የአንተን ብቻ የግል የልብ ስብራት ጠግኖ የአንድ ሰውን ብቻ ምርቃት ፣ ውዳሴና ጭብጨባ የሚሻ የለም። ህመምህን ችሎ ቢፍቅልህ እንኳን መልካም ሰው የሚያሰኘውን ጭንብል ለማጠናከር ነው። እነሆ በዘመናችን ለጋሽነት የምትገለጠው በካሜራ ፊት ብቻ ሆኖዋልና፣ የድሀ ጓዳ በለጋሽ እጆች የምትዳበሰው ለፕሮፓጋንዳ ብቻ ሆኖዋል።
የእነ ኢምፔሪያሊዝም ሠፊ ትከሻ መላጣ ሽሮን የመቀልበስ ጥያቄን ሲጋርደው፣ "እግዚኦ" በ "እርጎ " ቢተካ አይገርምም!! ድፍረትና ብልሀቱ ቢኖረን ሁላችንም እንደ "እርጎ መንግሥት!" ብዙ አዳዲስ ቃላትን ፈብርከን ስንጮህ በተገኘን ነበር። እውነትም "እርጎ መንግሥት" ይህቺ ናት ፀሎት!
Saturday, 07 October 2023 20:38
“እርጎ መንግሥት!
Written by የአብፀጋ ተመስገን /maddbn/
Published in
ልብ-ወለድ