Saturday, 14 October 2023 00:00

“ሁለቱም ወገኖች ከጦርነት ቢቆጠቡ!”... የማይሳካ የሰላም ምኞች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የሰላም ምኞት ብዙ ጊዜ የማይሳካው፣… የተጣራና የተሟላ ምኞት ስላልሆነ ነው። “ምናለ ወንድማማቾች ባይገዳደሉ” ብለን መመኘት እንችላለን። ግን አይሳካም። ለምን? አራት ምንያቶችን እንመልከት፡፡ አንዳንዴ  የሐሳባችን ብዥታ ነው ችግሩ። አባራሪ ተግባራት፣ ገዳይና ሟች፣ በዳይና ተበዳይ… ያለ ልዩነት “ፀበኞች” ብለን የምንሰይማቸው ከሆነ፣ ሐሳባችን ደፍርሷል።አንዱ ሰውዬ ነውጠኛ፣ ወንድምዬው  ደግሞ ሰላምተኛ ሊሆን ይችላል። ነውጠኛው ሰላምተኛውን ሲገድለው፣… እንዲሁ በደፈናው ነገሩን አድበስብሰን “ወንድማማቾች ተገዳደሉ” ብለን የምናስብ ከሆነ፣ ሐሳባችን ተዝረክርኳል።
የዘረፋ እና የተዘረፉ፣ ማንና ማን እንደሆኑ ለመለየት ደንታ ሳይሰጠን፣ “የተዘራረፉ” እያልን ለማውራት የምንቸኩል ከሆነ፣ ለሰው ህይወትና ንብረት እንዴት ደንታ ይኖረናል?  ሰዎች ባይዘራፉ?” ብለን ብናስብና ብንመኝ፣ ሐሳባችን የተምታታ ነውና ምኞታችን ትርጉም የሌለው ይሆናል።
ጎጂ እና ተጎጂ፣ ነውጠኛና ሰላምተኛ፣ ሥርዓት አልበኛና ሕግ አክባሪ ሰዎችን ለይተን ማስተዋል፣ በትክክል ማረጋገጥና አጣርተን ማሰብ ካልቻልን፣ ምኞታችን ባይሳካ አይገርምም። ስለምን እየተነጋገርንና ምን እየተመኘን እንደሆነ በቅጡ አናውቅም ማለት ነውና። ወይም የማወቅ ፍላጎት የለንም፡፡
ይህም ብቻ አይደለም።
የሰዎችን ባሕርይ በግል ለይቶ ማወቅ በጣም አስፈላጊ የመሆኑን ያህል፣ ለድርጊታቸውም በቂ ትኩረት ካልሰጠን፣ የሰላም ምኞታችን ከንቱ ይቀራል።
ነውጠኛው ሰውዬ፣ ሁልጊዜ የሁሉም ጥፋቶች ተጠያቂ ብናደርገው ደስ ይለን ይሆናል። ማጣራት ሳያስፈልገን፣… “ያ ልማደኛው መሠሪ ነው የሁሉም ነገር  አጥፊ። የነውጠኛው ሥራ ነው!” ብለን መፍረድ እንችላለን።
ሰላምተኛው ሰውዬ በአንዳች ምክንያት ነውጠኛ ተግባር ሊፈጽም ይችላል። “አይ! እሱ እንዲህ አይትት  ጥፋት አይሰራም፡፡ አድርጎት ከሆነም በደል ቢደርስበት ነውና አይፈረድበትም ከመስመር ተሻግሮ ከልክ አልፎ ክፉ ጥፋት ቢፈፀም እንኳ፣ ሰላምተኛ ሰው ስለነበረ ጥፋቱን አንቁጠርበት። ጠላት ደስ አይበለው” ለማለት እንፈልግ ይሆናል።
በዚህ ዐይነት የተጣመመ ሐሳብ ግን የሰላም ምኞት ወደ ሦስተኛው ችግር እንለፍ።… ሁለት ሰላምተኛ ሰዎች ሲጣሉ፣… ወይም ሁለት ነውጠኞች እርስ በርሱ ጸብ ሲፈጥሩ፣… በተመሳሳይ መፍትሔ ውጤታማ ለመሆን ከተመኘን ተሳስተናል። ሰላምተኛ ሰዎች በአንዳች ሰበብ አለመግባባት ሲያጋጥማቸው፣ ሲነጋገሩና ሲመላለሱ፣ በግልፍታና በስጋት ስሜት፣ ወደ ክፉ ንግግርና ወደ ትንቅንቅ ሊያመሩ ይችላሉ። በነገር ሲመላሱና ሲሰናዘሩ፣ ሁለቱም አጥፊ ሁለቱም ተጎጂ ይሆናሉ። ሁለቱም በዳይ፣ ሁለቱም ተበዳይ እየሆኑ የየራሳቸው ጉዳት ገንኖ እየታያቸው የፀብ ስሜት ውስጥ ይዘፈቃሉ።
መፍትሔውስ? በባህሪያቸው ሰላምተኛ የሆኑ ሰዎች በስህተትና በአለመግባባት ወደማይፈልጉት ፀብ እንዳይገቡ፣… ከተቻለ በእርጋታ መነጋገር ወይም ገላጋይ ዐዋቂዎችን ማማከር፣ ካልሆነ ደግሞ ወደህግ ሙያተኞችና ወደ ዳኝነት ሥርዓት መሄድ ይችላሉ፡፡
አንዱ ሌላኛውን የማጥፋት ነውጠኛ ፍላጎት እስከሌለው ድረስ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ ሀሳብ ሊያስማማቸው ይችላል፡፡ ካልሆነም ዳኝነት ያከባብራቸዋል፡፡ ሁለት ነውጠኛ ሰዎች እርስበርስ ለመጠፋፋት ሲዘምቱ፣ በተመሳሳይ የውይይትና የሽምግልና መንገድ ለማስታረቅ መሞከር ውጤታማ ይሆናል ብለን ካሰብን ግን፣ በከንቱ ደከምን።
 አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የሚዘምቱ ከሆነ፣ ሌሎች ሰላምተኛ ሰዎችን ከማጥቃት አይመለሱምና ዋና ጥንቃቄያችን እንዴት አደብ ልናስይዛቸውና ልንቆጣጠራቸው እችላለን የሚል መሆን አለበት፡፡
ነውጠኞችን መቆጣጠር የማይችል አገር፣ የነውጠኞች መጫወቻ ይሆናል፡፡ ልዩነቱም እዚህ ላይ ነው፡፡ የቁጥርና የደረጃ ጉዳይ እንጂ፣
“ነውጠኞች በሁሉም አገር በሁሉም ዘመን መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡
ነውጠኞችን መቆጣጠር የቻሉና ያልቻሉ ሰዎች፣ ሰላምተኛ ወይም ነውጠኛ አገር ይኖራቸዋል፡፡
በሌላ አነጋገር፣… “ሰላምተኛ አገርና መንግስት” ማለት… ነውጠኞች የሌሉበት ወይም ነውጠኛ ተግባር የማይፈፀምበት አገር ማለት አይደለም፡፡ ነውጠኛ ተግባርን በአጭር ማስቆም ነውጠኞችን መቆጣጠር የተቻለበት አገር ነው ሰላምተኛ አገር።
ነውጠኛ አገርና መንግስት ማለት የአገሬው ሰዎች ነውጠኞች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የነውጥ ተግባራትን ማስቆምና ነውጠኞችን መቆጣጠር የሚችል ሥርዓት ያልተገነባበት ወይም የፈረሰበት አገር ማለት ነው- የነውጥ አገር ማለት፡፡
አንድ ሁለት ገናና ነውጠኞችን በማስወገድ ብቻ አገሬው ሰላም አያገኝም፡፡ ተተኪ ነውጠኞች ይነሱበታል፡፡ የነውጥ ተግባራትን የሚከላከል ሀሳብ፣ ጥፋቶችን የሚያስቆም አቅም፣ ነውጠኝነትን መቆጣጠር የሚችል ስርዓት እየገነባ ሲጓዝ ነው የህሊናም የኑሮም ሰላም የሚያገኘው፡፡
እነዚህን ስህተቶች አጥርተን፣ ሐሳባችንን አስተካክለን፣ የፍልስጥኤምንና የእስራኤልን ታሪክ፣ የሐማስ የሽብር ዘመቻና የእስራኤል መንግስት የአጸፋ ወታደራዊ ዘመቻዎችን መመልከት እንችላለን።
ወይስ ገና የራሳችንን መከራ መመርመር፣ የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ጦርነትና ትርምስን በቅጡ ማስተዋልና ማገናዘብ ሳንችል የሌሎች አገራት ጦርነት ላይ ጥልቅ ትንታኔ ለማቅረብ ብንሞክር አቅማችን ይፈቅዳል? ብንችልስ ያምርብናል?
በእርግጥ፣ ከየትኛውም አገር የሚገኝ የታሪክ ትምህርት ጠቃሚ እንደሆነ አያከራክርም። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ ኢትዮጵያን የሚነካ ጉዳይ መሆኑም አይቀርም።
የዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሲቃወስ፣ ለኛም ጦሱ ይደርሰናል።
በዚያ ላይ በርካታ የኢትዮጵያ ተወላጆች የጭካኔ ጥቃት ደርሶባቸው፣ በአሳዛኝ ሁኔታ መሞታቸውንና መጎዳታቸውን ሰምተናል። በአጭሩ የእስራኤልና የፍልስጥኤም ጉዳይ እጅግ ቅርባችን ነው።
ቢሆንም ግን… እዚህ ከቤታችን ከደጃችን ብዙ ጦርነትና ብዙ ሞት፣ ብዙ ትርምስና የኑሮ ችግር አለብን።
አገራችንን በቅጡ ሳናገናዝብ  ውጭ አገራትን  ጦርነት መተንተን ይሆንልናል? ቢከብድም ያስፈልጋል። ከሆነ አይቀር ደግሞ በትክክለኛ ሐሳብና በትክክለኛ ሚዛን ነው ፋይዳ የሚኖረው።



Read 246 times