Saturday, 14 October 2023 00:00

አገር ያልኩህ በረሀ፣ ዱባ ያልኩህ ቅል ያላልኩህን ታበቅል?!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በቡዲዝም ሃይማኖት የሚተረት አንድ የታወቀ ተረት አለ፡፡
ሰውዬው አስማተኛ ነው፡፡ አስማቱ የሚሰራው ግን ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ተስተካክለው የሚደረደሩበትን ወቅት ጠብቆ ነው፡፡ አስማተኛው የሰማዩ ፍጥረታት የተወሰነ ቦታ ላይ ሲደርሱ ጠብቆ ይመለከትና ድግምቱን ያነበንባል፡፡ ከዚያም ከሰማይ ብዙ ሀብት ይዘንባል፡፡ ወርቅና አልማዝ ይፈስሳል!
አንድ ቀን ልክ ከሰማይ ሊያዘንብ በተቃረበበት ሰዓት ዘራፊ ወንበዴዎች ደርሰው ያዙትና ገንዘብ አምጣ አሉት፡፡ “ገንዘብ የለኝም ደሀ ነኝ፡፡ ግን በአስማት ሀብት ላዘንብላችሁ እችላለሁ!” ብሎ ድግምቱን ደገመ፡፡ ወርቅና አልማዝ ዘነመላቸው፡፡ እየተሻሙ ከረጢታቸው ውስጥ ይከቱ ጀመር፡፡ ይህን እያረጉ ሳሉ ከየት መጡ ሳይባሉ ሌሎች ዘራፊ ወንበዴዎች ድንገት ከበቡዋቸው፡፡፡ “በሉ አደጋ ሳይደርስባችሁ ከረጢቶቹን ሁሉ ቁጭ አድርጉዋቸው!” ሲሉ አስጠነቀቁዋቸው! የመጀመሪያዎቹ ወንበዴዎች አለቃ እንዲህ አለ፡-
“ጎበዝ! እኛንና እናንተን የሚያጣላን ነገር የለም፡፡ ሀብት እንደሆነ የምትፈልጉት እኛም ያገኘነው ከዚህ ሰው ስለሆነ እርሱን ጠይቁት”
የኋለኞቹ ወንበዴዎች ወደ አስማተኛው ሰው ዞረው፤ “በል ለኛም እንደነሱ ወርቅና አልማዝ ስጠን” አሉት፡፡ አስማተኛውም፤ “ሀብት ለማዝነብ የምችለው ፀሀይ ጨረቃና ከዋክብት ተስተካክለው ሰማይ ላይ በሚሰለፉበት በአንዲት በተወሰነች ቅጽበት ነው፡፡ ይቺ ቅጽበት በዓመታት ውስጥ አንዴ ብቻ የምትገኝ ናት፡፡ ስለዚህ ያቺ ቅጽበት እስክትገኝ መጠበቅ አለብኝ” አላቸው፡፡
ወንበዴዎቹ በጣም ተናደዱ፡፡ ከፊተኞቹ ወንበዴዎች ጋርም ኃይለኛ ድብድብ ጀመሩ፡፡ በዚህ መካከል አስማተኛው ሰው የማምለጫ እድል ስላጋጠመው ሹልክ ብሎ ወደ ጫካው ገብቶ ተደብቆ መጨረሻውን ይመለከት ጀመር፡፡
ወንበዴዎቹ እርስ በርስ ተጫረሱና ሁለቱ መሪዎች ብቻ ቀሩ፡፡
አንደኛው መሪ፤ “ይሄን ሰው በድብድብ አልችለውም፡፡ ስለዚህ በአንዳች ዘዴ ብገድለው ይሻላል” ብሎ አሰበና “ስማ ወዳጄ፣ እኔና አንተ መጋደል አይጠቅመንም፡፡ ይልቁንም ተመካክረን በሰላም መኖር እንችላለን” አለው፡፡
ሁለተኛው የወንበዴ መሪ በሀሳቡ ተስማማ፡፡ ግን እሱም በልቡ፤ “በሌላ ዘዴ አጠፋዋለሁ! ከዚያ ሀብቱ በሙሉ የእኔ ይሆናል” ብሎ አስቦ ነው፡፡ ሀብቱን ሁሉ ተሸክመው ወደ አንድ ዋሻ ገቡ፡፡ ገና ውይይት ሲጀምሩ ግን አንደኛው በጣም እንደራበው ገለጠ፡፡ ስለዚህ አንዳቸው ሀብቱን ሲጠብቁ ሌላኛው ተዘዋውሮ ምግብ ፈልጎ ሊያመጣ ተስማሙ፡፡
ምግብ ፈላጊው እንደወጣ ሀብታቸውን ሊጠብቅ ዋሻው ውስጥ የቀረው ጎራዴውን መሳል ጀመረ፡፡ “ቆይ! ምግቡን ይዞ ሲመጣ አንገቱን ቀንጥሼ እጥልለታለሁ!” አለ፡፡
ምግብ ፍለጋ የሄደው ደግሞ ልክ ምግቡን እንዳገኘ፤ “ይሄን ምግብ መርዝ አስነክቼ አጅሬ እበላ ብሎ ሲስገበገብ ያልቅለታል!” አለና ምግቡን መርዞ ይዞ መጣ፡፡ ሆኖም ለማውራት እንኳን ጊዜ ሳይኖረው ባለጎራዴው አንገቱን ቀንጥሶ ጣለው፡፡
ባለጎራዴው ባገኘው ድል ተደስቶ፤ “አለቀልህ! በእቅድ መመራት ጥቅሙ ይሄ ነው! ጠላትን በዘዴ መጨረስ ነው እንጂ ጉልበትን ተማምኖ ጠብ-መግጠም ዋጋ የለውም! እንግዲህ ምግቤን ልከስክስና ሀብቴን ተሸክሜ ወደ አገሬ ልግባ!” ብሎ ያመጣለትን ምግብ በደስታ መብላቱን ተያያዘው፡፡ ዳሩ ግን ምግቡን እንኳ በቅጡ ሳይመገብ ህይወቱ አለፈች፡፡
አስማተኛው ከተደበቀበት ወጥቶ እየሳቀ ሀብቱን ሰብስቦ ይዞ ሄደ፡፡
***
ለሁሉ ነገር ወቅት ወሳኝ  ነው፡፡ ፀሐይ፣ ጨረቃና ኮከብ ተገጣጥመው ደግ ቦታ ላይ ካልተደረደሩ መልካም ነገር አይመጣም፡፡ ያቺ አመቺና የተስተካከለች ቅጽበት ካልተፈጠረች አገር ሀብት አይዘንብላትም፡፡ ሀገር የምትመኘውን ሰላም፣ የምትናፍቀውን ብልጽግና አታመጣም፡፡ ይህንን ለማየት ብልህና መልካም ዕይታ ብቻ ሳይሆን ቀና ልቡና ይፈልጋል፡፡ “ቆይ እንዲህ አድርጌ በዚህ ዘዴ አጠፋዋለሁ” ብሎ መዶለት ሳይሆን ልባዊ ውይይትን ይሻል፡፡ ደባ ሳይሆን ግልጽነት፣ ጠባብ ወገናዊነት ሳይሆን ሆደ-ሰፊ የሆነ ህዝብን አሳታፊነት፣ በርን ዘግቶ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ማለት ሳይሆን “እስቲ ሌሎች የሚሉትን ልስማ” ማለትን ይጠይቃል፡፡ የፖለቲካ ቡድኖች፣ የተቀናቃኝ ወገኖች መሪዎች ወይም የአንድ ቡድን ዋና ዋና ኃይሎች እርስ በርስ እስኪጠፋፉለት እንደአስማተኛው ተሸሽጎ ውጤቱን የሚጠባበቅ ማህበረሰብ ሳይሆን፤ “የሁሉም ሀብትና መብት ባለቤት እኔ ራሴ ነኝ!” የሚል ንቁ ተሳትፎ ያለው ህዝብ እንዲኖረን ነው የምንሻው፡፡ “በሬ የቀለበውን ትቶ የቀጠቀጠውን ይልሳል” ይሏልና ብዙ መስዋዕትነት ለከፈለለት፣ ባደባባይም በሚስጥርም ለደማ ለቆሰለለት ወገኑ ሳይቆረቆር ከረገጠውና ከበደለው ጌታ ስር የማይንበረከክ ህብረተሰብ ነው መኖር ያለበት፡፡ ለመብቱ የሚቆምና ለሀገሩ አሳቢ ሀቀኛ ዜጋ መፈጠር ነው የሚኖርበት፡፡ ነገ አርአያነት ያለው መሪ (Role Model) ቢያሻ ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ ዝግጁ የሆነ ዜጋ ማፍራት ነው የሚገባው፡፡
ዛሬ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት መብቱን አስከብሮ የሚያከብር ሲቪክ ማኅበረሰብ የመገንባት ሀላፊነት ነው ያለብን፡፡ የፕሬስ ነጻነት የህዝብ የማወቅ መብት መሆኑን ደግመን ደጋግመን ማሳየት ነው ያለብን፡፡ ፕሬስ የህዝብ ዐይንና ጆሮ ነው፡፡ የጉልበተኛን ጉልበት መገደቢያ፣ የሞሳኙን እጅ መሰብሰቢያ ፕሬስ ነው፡፡ ፕሬስ አንደበት ላጡ አንደበት ነው፡፡ አገራዊውን አባባል ተውሰን ብንገልፀው፤ “ፕሬስና ጭስ መውጪያ አያጣም!” ለማለት ይቻላል፡፡  የክፉ ጊዜ የኖህ መርከብ ነው፤ ፕሬስ-ለጥፋት ውሃ ደራሽ!
እንደ ወቅቱ ወረት (ፋሽን) በየአደባባይ ሸንጎው የሚነሱ የዲሞክራሲ መብቶች፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህና የልማት መርሆዎች እንደመፈክር ከሚሰግሩበትና ለለጋሽ አገሮች ፍጆታ ብቻ በቃል ከሚነበነቡበት በቀቀናዊ ባህሪ ተላቀው መሬት የያዘ ተግባራዊ ህልውና እንዲኖራቸው ጥረት ሲደረግ ብቻ ነው ከድህነት መላቀቅ የሚቻለው፡፡ ግምገማ ተፈርቶ በፈጣን ልማት ስም የሚሯሯጡበት እቅድና ጥናት፣ የአለቃን ወይ የኃላፊን መሪ-ቃል “እንደ ፍካሬ እየሱስ ትንቢት ካልደጋገምኩ የት-አባቴ እገባለሁ” በሚል ስጋት የሚለፈፍ ባለ ጭምብል ግልጽነት፣ ከቶም የማደግ ምልክት ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በውጥረት ሰዓት የሚሰራው ሥራ ሁሉ፣ ለድቀት ፈውስ (Crisis management) ፍለጋ የሚነደፍ ፖሊሲ ሁሉ፣ እንደ ቀበርቾና እንደ ወገርት ከጓሮ የሚቆረጥ ያገረ-ሰብ መድሀኒት አይሆንም፡፡ እንደ ረጅም ግብ መምቻ አብሪ ጥናት ተደርጎ ሊታሰብም ከቶ አይችልም፡፡
የአዛዥና የታዛዥ፣ የአለቃና የምንዝር ግንኙነት ባለበት ቢሮክራሲያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ “ታላቅየው ሲመቸው ታናሽየው ሳይድህ በእግር ይሄዳል” የሚባለው ተረት ዓይነት ሁኔታ ቢታይ አይገርምም፡፡ ታላቅም ታናሽም ሩቅ ሳይሄዱ “የእኔ እበልጥ” “እኔ እበልጥ”፣ “የእኔ ልሰማ” “እኔ ልሰማ” ሽኩቻና ጠብ ውስጥ እንደሚገቡ የሩቅና የቅርብ የሀገራችን ገዢ መደቦች ሂደት ታሪካዊ ማህተሙን የረገጠበት ጉዳይ ነው፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ በሲቪክ ማህበረሰብ ግንባታ ውስጥ ሁሌም አስቸጋሪ የሚሆኑ ሁለት ፊት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉትን ሰዎች “የአንድ አራሽ ንግግር” የተሰኘው የኦሌ ኤሪክሰን መጽሐፍ እንዲህ ይጠቅሳቸዋል፡-“ክፎች እንኳ ትጋትን ይወዳሉ፡፡ ሌቦች ተግተው ስለሚሰርቁ ደህና ሰዎች ይመስላሉ፡፡ ጎበዝ የሚገኝበትን ቦታ ብታውቅ ደግነት ያለው አይታጣም፡፡ ከጅብ ጋር የሚጮህ ከበግም ጋር ባ ባ የሚለውን ሰው ግን ከሰይጣን በቀር የሚያመሰግነው የለም፡፡ ካንድ ባርኔጣ በታች ብዙ ጊዜ ሁለት ፊቶች ይታያሉ፡፡ ብዙዎች ከዶሮች ጋር እያሽካኩ ከቀበሮ ይመሳጠራሉ፡፡ አያሌ ሰዎች ቅቤ ባፋቸው የማይቀልጥ እየመሰለ የሚጠቅማቸው እንደ ሆነ እሳትን ይተፋሉ፡፡ በርኖሳቸውን እንደ ነፋሱ ይለውጣሉ፡፡ ከጥንቸል ጋር እየሮጡ ከውሾች አብረው የሚያድኑ ሰዎች እስካሁን ይገኛሉ፡፡ ይህ ለዐይን የሚከፋ፣ ለአፍንጫ የሚከረፋ ነው፡፡ ዝባድ ከውሻ፣ እምነትና ቅንነት ከባለጌ አይገኝም፡፡ ገልበጥባጦች በሁሉ ይቆዩናል፡፡ ከመልአክ ጋር መላዕክት፣ ከጋኔን ጋር አጋንነት ናቸው፡፡ ውሃ መስለው በእሳት ላይ ይገነፍላሉ፡፡ ሲበርድ ይረጋሉ፣ እንደ በረዶ ይሆናሉ፡፡ የሚመሩበት መቀንያ የላቸውም፡፡ በጣራ የሚቆም አውራ ዶሮ ምስል ጭራውን ንፋስ ወደሚነፍስበት ያቀናል፡፡ መልካም ቢሆን ክፉ፣ ግድ የላቸውም፡፡ ትርፍ በሚያገኙበት ነገር ያምናሉ፡፡ ሰው በሚያልፍበት ወጥመድን ይጠልሉ፡፡ እንደ ጥቅማቸው መጠን ውሻ ወይም አንበሳ መስለው ይታያሉ፡፡” ሌላው ብርቱ ጉዳይ በአናቱም ይሁን በጀርባው፣ በሸንጎም ይሁን በቡድን የሚወሰኑ ውሳኔዎች፣ አገርን በሚመለከት የሚታቀዱ ታላላቅ እቅዶች፣ ወደ ተግባር ከመመንዘራቸው በፊት የህዝብን የማወቅ መብት የረገጡ አለመሆናቸውን ማስተዋል ነው፡፡ ማንም ይሁን ማን ይዋል ይደር እንጂ በህዝብ ላይ የፈፀመው ጥፋት፣ ያደረሰው ጉዳት ካለ፣ ነገ ታሪካዊ ተጠያቂነት እንደሚኖርበት አሌ አይሉት ሀቅ ነው፡፡ እንደተጠያቂነቱ መጠን ተመጣጣኝ ፍርድ አለ፡፡ ዛሬ በማስመሰልና ባልባለቀ አዕምሮ የሚያጥሩት የመብት አጥር፣ ነገ አጥሩ የፈረሰ ሰዓት ፀሐይም፣ ጨረቃም፣ ከዋክብትም ይገጣጠሙና ላንዱ ሲነጋ ላንዱ መምሸቱ ግድ ይሆናል፡፡ በተለይ ለዘመናት የተደከመለት የመናገርና ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ የምንመኘው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት፣ የምናቅደው መልካም አስተዳደር፣ እናሰፍነዋለን የምንለው ፍትሐዊነትና እንገላገለዋለን የምንለው የሙስና አባዜ፣ ያለህዝብ ድጋፍና ያለ ህዝባዊ ልቡና መቼም ፍሬ ሊያፈራ እንደማይችል ለአንዲትም ደቂቃ መርሳት አይገባም፡፡ ያ ካልሆነ “አገር ያልኩህ በረሃ፣ ዱባ ያልኩህ ቅል ያላልኩህን ታበቅል?!” የሚያሰኘን ይሆናል፡፡

Read 1395 times