Saturday, 14 October 2023 00:00

የጦርነት ታሪክ ተደጋገመብን ? ወይንስ ደጋገምነው ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

ከሃይማኖታዊው ትረካ እንዳነበብነው፣ የጥፋት ሩጫ ሀ ተብሎ የተጀመረው በቃየን ነው ብለናል። የመጀመሪያውን ክፉ የግድያ ጥቃት ፈጽሟል። በርግጥ፣ በይፋ የታወጀ ሕግና የዳኝነት ሥርዓት በወቅቱ አልነበረም። ቃየን ፍርድ ቤት አልቀረበም፤ ቅጣት አልተፈረደበትም።
ነገር ግን፣ ቃየን የእጁን አላገኘም ማለት አይደለም። ክፉ ተግባር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ብዙ መዘዞችን ያስከትላል። ቃየንም ከመዘዞች አላመለጠም። እንዲያውም ሕግ ቢኖር ይሻለው ነበር።
አዎ፣ “ሕግ የሌለበት ሥርዓት አልባ ዘመን” ሆነና ቃየን የሕግ ቅጣት አልደረሰበትም።
ነገር ግን የሕግ ቅጣት የማይኖረው ለቃየን ብቻ አይደለም።
ሌሎች ሰዎች ቃየን ላይ ዱላቸውን ቢያሳርፉበት፣ የሕግ ቅጣት አይመጣባቸውም።
ለግድያና ለበቀል አዙሪት፤ አገሬው ሁሉ ወለል ብሎ ተከፍቷል።
የሲዖል በሮችን የሚበረግድ የመጀመሪያው ክፉ ተግባር እንደፈጸመ ቃየን ታውቆታል። የሰውን ሕይወት በጥላቻና በግፍ ሲያጠፋ፣ የራሱንም ህልውና አዋርዷል። ሌሎች ሰዎች እንደ አውሬ ቢቆጥሩት፣ ለአደን እንደወጡ ታጣቂዎች ቢሆኑበት፣ ሊገድሉት ቢያሳድዱት፣ በራሱ መሥፈሪያ ቢሠፍሩበት፤ ምን ሊል ይችላል? የዐጸፋ በቀል መመለስ?
በእርግጥ፣ በዚያን ጊዜ ከወላጆቹ ከሔዋንና ከአዳም በስተቀር ሌላ ሰው ገና አልተወለደም ብለን መከራከር እንችላለን። ይሄ ግን የትረካው “ሰም” ነው። “ወርቁ” ወይም ዋና መልእክቱ ግን፣ አያከራክርም። ግልጽ ነው።
የሰውን ሕይወት አጥፍቶ፤ እንደቀድሞ በሰላም መኖር አይችልም። ከህሊና (ወይም ከፈጣሪ መንፈስ) የመሸሽ እዳ አለበት። የቱንም ያህል ህሊናው ቢዶለዱም፣ ከጭንቀት ይገላገላል ማለት አይደለም። ከጭንቀት ቢገላገል እንኳ፤ የአዕምሮ ጤንነቱን ያጣል እንጂ አይመቸውም።
ግን የህሊና እዳ ብቻ አይደለም ፍዳው። የሕግ ቅጣት ባይኖርበትም፤ በዚያ ምትክ የበቀል ጥቃት ይመጣበታል። ከመኖሪያ አካባቢው መልቀቅና መኮብለል ይኖርበታል። ኮብልሎም በሰላም አይኖርም። የሰውን ሕይወት ማጥፋት የሚችለው፤ ቃየን ብቻ አይደለም። ቃየን እንዲህ ይላል ለእግዚሄር።
“ከፊትህም እሸሸጋለሁ። በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች እሆናለሁ። የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል” አለ ቃየን።
እና ምን የሚል መልስ አገኘ?
“አይ ማንም አይገድልህም” የሚል ምላሽ አላገኘም። “ግድያ ክልክል ነው” የሚል ሕግ በአንድ ጀንበር አልታወጀለትም። ቃየን፣ በክፉ ተግባሩ ሳቢያ፤ የሚመጣበትን የበቀል መዘዝ ማስቀረት አይችልም። ዋናው ነጥብ የሚወጣ ከዚህ በኋላ ነው። አንዳች ነጥብ፤ ቃየንን የገደለም፣ እንደዚያው የበቀል ኢላማ መሆኑ አይቀርም።
ሁለተኛ ነጥብ፤ የበቀል ጥቃት እንደ ሕግ ቅጣት አይደለም። ልክና ወሰን የለውም። ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ጥቃት ብቻውን አይመጣም። ዐጸፋውን ያስከትላል። ጥቃት በበቀል ይካካሳል ማለት ግን አይደለም። በቀል እንደገና ዕጥፍ የዐጸፋ በቀል ያመጣል።
“የመጠፋፋት ታሪክ ራሱን እየደገመ”፣ እንደ አዲስ እየተመላለሰ ይባባሳል። ነገር ግን፣ ካልዘነጋነው በቀር በፊት ካሁን በፊት ስለ ታሪክ ስናወራ፣ “ታሪክ ራሱን አይደግምም” ተባብለን ነበር።
የጥቃትና የበቀል አዙሪት ግን፣ “የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ” እስኪመስል ድረስ፣ ለዘመናት እየተደጋገመ እንደተከሰተ፣ ራሱ ታሪክ ይነግረናል። እንዲያውም፣ እጅግ እየተደጋገመ የዘወትር መደበኛ የኑሮ ገጽታ ከመሆኑ የተነሳ፣ ታሪክ ራሱን ይደግማል ከማለትም አልፈን፣ ከሰማይ በታች ምንም አዲስ ነገር ሊያስብለን ይችላል።
ጦርነት እግጅ ክፉ መሆኑ ጥርጥር ባይኖረውም፣ ጦርነት ስንት ዘመኑ! ከሰው ልጆች ዘንድ አልጠፋም።
ቃየን ወንድሙን አቤልን ከገደለ በኋላ፣ በቀል እንደሚመጣበት አውቋል። አይ… ከእንግዲህ መጠፋፋት አይኖርም። ከእንግዲህ ሰላም ይሰፍናል አልተባለም።
ለዚህም ነው፤ “ማንም አይገድልህም” የሚል መልስ ያላገኘው።
እናስ?
“ማንም ቃየንን ቢገድል ሰባት ዕጥፍ የበቀል ጥቃት ይቀበላል” የሚል ነበር መልስ ቃየን ያገኘው።
የግድያ ክፋት የተጀመረ ጊዜ፣ ከዚህ ጋር ሰባት ዕጥፍ በቀል ተለመደ ማለት ነው። ሕግ ከሌለ፣ ሌላ ምን ዘዴ አለ? አንዱ ሰባት ዕጥፍ በቀል ይፈጽማል። ሌላውም በዐጸፋው ሰባት ዕጥፍ ይመልሳል። መተላለቅ ነው።
ከትውልድ ትውልድ፤ ግድያና በቀል እየከፋ፣ አዙሪቱ እየከረረ ይሄዳል።
ቃየን የአዳምና የሄዋን ልጅ አይደል? ሁለተኛ ትውልድ ማለት ነው። ሄኖሕ፣ መኤል፣ ኢራድ፣ ማቱሣኤል… እያልን የልጅ ልጆችን እየጠቀስን የቃየንን ታሪክ እየተነተነ” የልጆቹ ስሞቹ አዲስ ባይሆንባችሁ አይግረማችሁ። እንደገና በሌለ ታሪክ በድጋሚ እናገኛቸዋን። ታሪክ ራሱን ይደግማል  ያስብላል ነገሩ።
የሆነ ሆኖ ላሜሕ ከቃየን የልጅ ልጆች በኋላ ነው የሚመጣው። ያኔ፣ በሰባተኛው ትውልድ፤ በላሜሕ ዘመን ላይ የእልቂት ፉከራ ከጣሪያ በላይ ይተኮሳል። ተስፋ የሌለው የቅዠት ጫፍ ላይ ይደርሳል።
ላሜሕ ለሁለት ሚስቶቹ እንዲህ ብሎ ይፎክራል። ትረካውን ሳናጎድል ሳንቆጥር አናንብበው።
ላሜሕም ለሚስቶቹ እንዲህ አላቸው፡
“ዓዳ እና ጺላ ሆይ፣ ቃሌን አድምጡ፤
የላሜሕ ሚስቶች ሆይ፣ ለነገሬ ጆሮ ስጡ፤
ያቆሰለኝን ሰው ገድያለሁና፤ የጎዳኝንም ወጣት እንዲሁ።
ሰባት ዕጥፍ ነውና የቃየን በቀል
የላሜሕ ደግሞ ሰባ ሰባት ዕጥፍ!” (ዘፍ 4፡ 23-24)
And Lamech says to his wives: “Adah and Zillah, hear my voice; Wives of Lamech, give ear [to] my saying:
For I have slain a man for my wound,| Even a young man for my hurt;
For sevenfold is required for Cain,/ And for Lamech seventy-sevenfold.”
እውነትም፣ በቀል መልክና ልክ የለውም። ላሜሕ ነገሩን ሲያጦዘው፤ ሌላውም ሰው ከማዶ ሆኖ የዚያኑ
ያህል መፎከር ይጀምራል። በዚህ ሁኔታ በሕይወት የሚተርፍ ሰው ይኖራል? ተጠፋፍተው ያልቃሉ እንጂ።
ታሪክ ለማውራት በሕይወት የሚተርፍ ባይገኝ ነው፤ የቃየን የትውልድ ታሪክ፤ በላሜሕ ፉከራ የተቀጨው። ከዚያ በኋላ ምንም የተጻፈ የቃየን ወይም የላሜሕ ታሪክ የለም። ወሬ ነጋሪ አልተረፈም።
ከሰባት ዕጥፍ ዐጸፋ፤ ወደ ሰባ ሰባት ዕጥፍ የበቀል አዙሪቱ ሲያጦዙት እንዴት ሰው ይተርፋሉ? ሌላ ምን ይጠበቃል? ያኔ ሕግ አልነበረም።
በአጭሩ የመጠፋፋት ታሪክ ምልክት ነው ላሜህ፡፡ ላሜሕ ታይቶ የማይታወቅ ተአምረኛ ገድል ለመስራት፣ ወይም ዓለምን የሚያስበረግግ መዓተኛ ታሪክ ሊያመጣ  ፎክሯል። በእርግጥም የላሜሕ ዛቻ ታይቶ የማይታወቅ የአዲስ ታሪክ መንደርደሪያ ነው። ግን የታሪክ መጨረሻም ነው። አዲስ የመጠፋፋት ታሪክ አምጥቷል። የታሪክ ማብቂያ ሆኗል። ወሬ ነጋሪ አልተገኘም። ለታሪክ የተረፈ ሰው የለም።
እንዲህ ሲባል ግን ታሪካቸው ከንቱ ነበር ማለት አይደለም። እንዲያውም ትረካቸውን በደንብ ካየነው፣ የነ ቃየን የነ ላሜሕ ዘመን የእድገት ዘመን ነበር፡፡ ከትውልድ ትውልድ በርካታ ጥበበኞች እንደተወለዱና በጣም አስገራሚ ታሪክ እንደሰሩ ይነግረናል።
የሰውን ተዓምረኛ ኃይል አሳይተዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ የሥልጣኔ ታሪክ የተመዘገበው በእነሱ ዘመን ነው። በነባር የገጠር ኑሮ ላይ የከተማ ግንባታ፣ በነባሩ እርሻ ላይ የብረታ ብረት ስራ ጨምረውበታል። የእድገት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ነባሩን ከማሳደግ ባሻገር፣ አዳዲስ ነገሮችንም ፈጥረዋል። እጅግ በርካታ የኑሮና የሙያ አማራጮችን ተከፍተዋል። የሰው ልጅ ግዛት ተስፋፍቷል። የሥልጣኔ ታሪካቸው ግን በግስጋሴ አልቀጠለም።
በየአቅጣጫው እያደገ ሲስፋፋ፣ ፍጥነቱ “አጃ ኢብ” ያስብላል፡፡ ምን ዋጋ አለው? በቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን በኪነጥበብም እየተራቀቀ ሲገሰግስ የነበረ የሥልጣኔ ጉዞ… የላሜሕ ዘመን ላይ ሲደርስ ተቆርጦ እንዳልተፈጠረ ሆኖ ጠፋ። ከታሪክ መዝገብ ተጎርዶ ጅረቱ ደረቀ።
“ከዚያ በኋላ” ተብሎ የማይወራለት፣ ተመልሶ የማይመጣ፣ ተነሥቶ የማያንሰራራ፣ ለዘላለም ብርሃን የማይታይበት ጭር ያለ ባዶ ጨለማ ሆኖ ቀረ።
የመጀመሪያ የሰው ልጅ ታሪክ እልም ብሎ ሲጠፋ፣ የዓለም ፍፃሜ የሚሉት ዓይነት “የሆረር” ስሜት አለው።
የኦሪት ዘፍጥረት የምዕራፍ 4 ትረካ፣
የመጀመሪያው ዙር የሰው ልጅ ታሪክ ምን እንደሚመስል፣ ከአነሣሡ እስከ ውድቀቱ ድረስ ከተረከልን በኋላ፣ ምዕራፉን ሲዘጋው ወደ ሁለተኛው ዙር የሰው ልጅ ታሪክ የሚያሸጋግር በር በመክፈት ነው።
የሰው ልጅ ታሪክ እንደገና ከአዳምና ከሔዋን “ሀ” ብሎ ሲጀምር ታያላችሁ። ሁለት ልጆቻቸውን በክፉ የግድያ ተግባር አጥተዋል። ሟቹ ልጃቸው አቤል ነው። ገዳዩም ልጃቸው ቃየን ነው - አገር ጥሎ ኮብልሏል።
አዳምና ሔዋን ሌላ ልጅ ወለዱ። የልጅ ልጅም መጣ። ስሙም ሄኖስ ተባለ…
“ሄኖስ” እና “አዳም” ተመሳሳይ ቃላት ናቸው። “ሰው” የሚል ትርጉም አላቸው። ሄኖስ ዳግማዊ አዳም ነው ማለት ይቻላል። የሰው ልጅ ታሪክ “ሀ” ተብሎ ተጀመረ የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ይመስላል።
አዳም ቃየንን ወልዷል።
ሄኖስ ዳግማዊ አዳም ነውና ቃይናንን ይወልዳል።
በሁለቱም በኩል በመንታ የታሪክ ጅረቶች የተዘረዘሩ የትውልድ ስሞችን ማነጻጸር ትችላላችሁ።
በአዳም በኩል ቃየን ተወልዷል፡፡ በሄኖስ በኩል ቃይናን ተወልዷል፡፡ ከዚያስ?
ከወዲህኛው ጅረት በኩል፣ ሄኖሕ የሚል ስም እናገኛለን። በሌላኛው ጅረት ደግሞ፣ ሄኖክ የሚል ስም።
ተመሳሳይ ስሞች ነው በሁለቱም የሰው ልጅ ታሪኮች ውስጥ የምናገኘው
መኤል እና መላልኤል፣
ኢራድና ያሬድ፣
ማቱሣኤልና ማቱሳላ፣
ላሜሕ እና ላሜሕ…
በአዳም እና በሄኖስ በኩል የተዘረዘሩ ትውልዶች ላይ እደምታዩት ተመሳሳይ ስሞችን እናገኛለን። የቅደም ተከተል ጉዳይ ካልሆነ በቀር ማለቴ ነው።
 የመጀመሪያው የሰው ልጅ ታሪክ በክፉ የመጠፋፋት እልቂት ሳቢያ እስከ ወዲያኛው ከሕይወት መዝገብ ተሰርዟል። በዳግማዊ አዳም (በሄኖስ) እንደገና ሀ ብሎ ይጀምሯል። ግን የተለየ ታሪክ የሚያመጣ አይመስልም። የትውልዶች ስሞች ተመሳሳይ ናቸው።
አዲስ ነገር አዲስ ታሪክ ይኖረው ይሆን? እስቲ እንየው። የቀድሞው ጅምር ሥልጣኔ ድራሹ ጠፍቷል። ብዙ ሕይወት አልቋል። ብዙ ሥቃይ ደርሷል፡፡ የሚያሳዝንም የሚዘገንንም ነው - እልቂትና መከራው። ቢሆንም ግን፣ እንደገና ከአፈር ላይ ቀና ለማለትና ነፍስ ለመዝራት የሚሞክሩ ሰዎች አይጠፉም። ምንም ሩቅ ቢሆን ወደ ሥልጣኔ ማማተራቸው አይቀርም።
የዕውቀትና የሙያ ሰዎች ምስጋና ይግባቸውና፣ የሰው ልጅ ታሪክ ከባዶ ተነሥቶ እንደገና ወደ ሥልጣኔ መራመድ ይጀምራል። በቴክኖሎጂና በኪነጥበብ፣ በኑሮና በሙያ እየጎለመሰ በሥልጣኔ ጎዳና ላይ ይጓዛል።
ድሮ ያልነበረ አንድ ነገር እንደተጨመረ ግን ልብ በሉ። በሄኖስ ዘመን፣ “በእግዚሄር ስም መጠራት ተጀመረ” ተብሏል። ዝርዝር ማብራሪያ የለውም።
“የመጀመሪው የኃይማኖት ቡቃያ እነሆ ታየ” ብለን ልናስበው እንችላለን። ገና ቡቃያ ነው። “አምላክ” የሚል ሐሳብ በሰዎች ዘንድ ተፈጠረ ለማለት ያህል ይመስላል። ቅርጽና መልክ የያዘ ኃይማኖትማ ገና ፍንጩ አልታየም። የተሟላ የኃይማኖት መልክና ቅርጽ ለማየት፣ ከኖኅ አልፈን፣ በነ አብርሃም ተሻግረን፣ እስማኤልንና ይሳቅን፣ ያዕቆብና ኤሳውን፣ ዮሴፍና ወንድሞቹን ሁሉ እያየን የሙሴ ተአምራዊ ስራዎች ላይ መድረስ አለብን። ለንባብ ረዥም ባይሆንም፣ በጊዜ ርዝመት ከለካነው ግን የብዙ ምዕተ ዓመታት ትረካ ይጠብቀናል።
በሄኖስ ዘመን ብቅ ያለው የኃይማኖት ቡቃያ ግን ቀላል ታሪክ አይደለም። የረዥሙ ትረካ መነሻ እርሾ ነውና።
የነ ቃየን ታሪክ፣ ማለትም፣  ከቀዳማዊ አዳም የተነሳው የታሪክ ጅረት “በቀዳማዊ ላሜሕ” ዘመን ተጎርዶ ሲቀር፣ በዳግማዊ አዳም በሄኖስ ዘመን የሰው ልጅ ታሪክ እንደአዲስ ከባዶ የተነሣ ጊዜ፣ ድሮ ያልነበር አዲስ ተጨማሪ ነገር መጥቷል። በመጀመሪያው የታሪክ ውድቀት ማግስት፣ የኃይማኖት ቡቃያ ተፈጥሯል።የሄኖስ የታሪክ ጅረት ከዳግማዊ ላሜሕ በኋላ በኖኅ ድራሹ ሲጠፋ፣ ማለትም ከሁለተኛው የታሪክ ውድቀት በኋላ፣ ደግሞ የሕግ ቡቃያ ብቅ ይላል።
የሰውን ደም ያፈሰሰ፣ በሰው ደሙ ይፍሰስ የምትል አንዲት የህግ አንቀፅ የታወጀች በኖህ ዘመን ነው፡፡ ሁለተኛው የእልቂት ጥፋት ከደረሰ በኋላ ማለት ነው፡፡ የጥፋት ታሪክ እንደገና ይደገማልና፡፡  
የሄኖስ የትውልድ ጅረት ከጥፋት አላመለጠም። ከምድረ ገጽ ተጠራርጎ ይጠፋል። ለምልክት ያህል ምንም ሳያስቀር እንዳልነበረ ይሆናል። አስገራሚው ነገር፣  የሰው ልጅ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ድምጥማጡ የሚጠፋው ከላሜሕ ዘመን በኋላ ነው። ሌላ ሞክሼ “ላሜሕ” ማለት ነው።
በቃየን የታሪክ ጅረት ሥር በሰባተኛ ትውልድ የሚመጣው የመጀመሪያው ላሜሕ፣ “የናዕማ አባት” ብለን ልንለየው እንችላለን። ቀዳሚው የሰው ልጅ ታሪክ በዚሁ ተቀጭቶ ይቀራል።
ለሁለተኛ ከዳግማዊ አዳም ከሄኖስ የሚጀምረው በሁለተኛው የሰው ልጅ ታሪክ ሥር የሚመጣው ላሜሕ ደግሞ፣ “የኖኅ አባት” ልንለው እንችላለን። እዚህ ላይም ዓለምንና ታሪክን የሚያጠፋ መዓት ይከሰታል።
 የኖኅ ቤተሰቦች ብቻ (ስምንት ሰዎች ብቻ) በሕይወት ተረፉ እንጂ፣ ሌላው ሕዝብ አልቋል። ሁሉም ነገር ውኃ ወስዶታል፤ አፈር በልቶታል። የሰው ልጅ ታሪክ እንደገና ለሥስተኛ ጊዜ ከባዶ ይጀምራል።
የሰው ልጅ ታሪክና የሥልጣኔ ጅምር በየጊዜው እየተጎረደ የሚጠፋው፣ በየጊዜው የጥፋት መዓት የሚመጣው፣ የሰው ሕይወት የሚረግፈው ለምንድነው? ነገሩ ተደጋገመ።
ከአመድ ላይ እንደገና ሌላ አዲስ ታሪክ ሲነሣ፣ አንዲት ተጨማሪ ነገር ይዞ እንደሚነሣ የኦሪት ዘፍጥረት ታሪክ ይነግረናል።
ከሁለተኛው እልቂት በኋላ፣ ሰውን መግደል በሞት ያስቀጣል የምትል አንዲት ሕግ ተፈጠረች። ጥፋትና እልቂት እየተደጋገመ መምጣቱ ያሳዝናል። ነገር ግን የያኔዎቹ ሰዎች ቢያንስ ቢያንስ ከቀድሞ ታሪክ አንዳች ትምህርት ለማግኘትና ጥፋት እንዳይደገም መጠንቀቃቸውን እናያለን። ከተማሩበት ታሪክ ራሱን አይደገምም ማለት ነው፡፡
እኛ ግን ከታሪክ ምንም ትምህርት ለማግኘት እየሞከርን አይደለም። የጥፋትና የጦርነት አዙሪቱን ከዓመት ዓመት እንደ አዲስ እንደጋግመዋለን። ሰዎች እንጂ ታሪክ ራሱን አይደግምም ማለት ነው፡፡

Read 768 times