Saturday, 14 October 2023 00:00

"ከሥራ ሳላስወጣው አልለቀውም…"

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

“አንድ የ‘ሶሺሌ’  ቀልድ ትዝ አለችኝማ… ምን ትል መሰላችሁ. አንዱ በ"ሶሻሊዝም አቅርቦትና ፍላጎት ምን ማለት ነው?" ተብሎ ሲጠየቅ ምን ብሎ መለሰ አሉ መሰላችሁ… "ገበያ ላይ ያገኘኸውን ነገር ትገዛና ፍላጎትህ እንደሆነ እራስህን ታሳምናለህ።" አሪፍ አይደል!--”

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንድ ከዓመታት በፊት የሰማሁት ነገር ትዝ አለኝማ…  አዳማ ውስጥ ነው አሉ… አንድ ምግብ ቤት ውስጥ የሆነ ‘በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ምግብ ነበረ አሉ። (አሁን ይኑር አይኑር አልተረጋገጠም) ስሙ ምን ይባል ነበር መሰላችሁ…‘ትዕቢት’! አሪፍ ፈጠራ አይደል! ብቻ…. ምን አለፋችሁ… ከአጥንት መቅኒ ጀምሮ የማይገባበት የሚበላ ነገር የለም አሉ። እንዴት መሰላችሁ… ያው ያገኘነውን ሁሉ የምናግበሰብስ ‘የሚነካን ነገር’ ያለ አይመስለንም አይደል! ዘንድሮ ቀላል ትእቢት ነው እንዴ ያለው!
አንተ "ድሮ ወንድም መከታ ነው ይባል ነበር። ዘንድሮ መከታ ፉድና መኒ ብቻ ነው…" ያልከኝ ወዳጄ… እኔ የምለው ይሄ ነገር ተስፋ መቁረጥ ነው ወይስ የአቋም ለውጥ!
እናላችሁ… ትእቢት የ‘ፉድ’ ስምም ይሁንም፣ አይሁንም ዘንድሮ ብዙ ቦታ ትእቢት የሚመስሉ ነገሮች መአት ናቸው። እንግዲህ ወይ ክፉ፣ ክፉውን ብቻ ለማየት ስለሚመቸን ሊሆን ይችላል ግን ብዙ ቦታ በሌለ ትከሻ 6 ሜትር የሚለጠጥባችሁ ሰው አልበዛባችሁም! አንድ ወዳጃችን "ዘንድሮ ሰው በትከሻው ነው የሚያናግርህ…" ያለው ወዶ አይደለም።
ባለሱቁ በትከሻው ያናግራችኋል፣ የቦሱ ጸሐፊ በትከሻዋ ታናግራችኋለች፣ የታክሲው ሹፌር በትከሻው ያናግራችኋል። ብቻ ምን አለፋችሁ… ሁሉም ‘እንደ ትከሻው’ ትእቢት ይሞካክረዋል።
እኔ የምለው በየሱቁ፣ በየሚኒባሱ ምናምን ‘ሪስትራክቸሪንግ’ ዓይነት ነገር የለም እንዴ! አሃ… በትከሻቸው የሚያናግሩን በዙብንና! ገና ለገና ‘ፎርስድ ሊቭ’ ምናምን የለም ተብሎ የስንቱን ፊት እንቻል!
ስሙኝማ… ‘ፎርስድ ሊቭ’ ምናምን ስል የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ! እንደው የዓለም ነገር…አለ አይደል… እንደ አንዳንድ ወዳጆቼ ባህሪ ‘ጠምዛዛ’ ሲሆን፣ ሰው የምር መቀለድ ይችልበታልሳ! ይቺን አንድ ወዳጄ ‘የሰሞኑ የቀልድ ሲንግል’ ነች ብሎ የነገረኝን ስሙኝማ… ሰውየው ያመውና ጠበል ይወሰዳል አሉ። ታዲያላችሁ ከተወሰደ በኋላ ጠበሉን እየተረጨ "ልቀቅ!" ይባላል። ግን ምን ያደርጋል… ‘የያዘው’ በቀላሉ የሚለቅ ዓይነት አልነበረም።
"የያዝከው ማነህ አንተ?"
"እንትን እባላለሁ።" (ስሙ ‘እየተጣራ’ ስለሆነ ነው ‘እንትን’ የተባለው።  ቂ…ቂ…ቂ… "ወደሽ ነው…" ምናምን ይባል የለ!)
"የት ያዝከው?"
"እንትን መ/ቤት ቢሮ ውስጥ።"
"አሁን ትለቀዋለህ፣ አትለቀውም?"
"አለቀውም።"
"ለምን አትለቀውም?"
"ከሥራ ሳላስወጣው አለቀውም"
ይሄ ደግሞ የለየለት ነው! ይሄውላችሁ… እኛ በትንሹ ስንነጫነጭ እንዲህ ያለው ‘ነክሶ የማይለቅ’ አለላችሁ።
እናላችሁ… በምን ላይ ምን እንደሚሉት ከየት መጣ የማይሉት የትዕቢት ወረርሽኝ አለላችሁ። አሃ… ታዲያ የፈለገ አበሻ ኩሩ ነው ምናምን ቢባል ትዕቢት ሌላ፣ ኩሩነት ሌላ! በእኔና በመሰሎቼ ‘ዲክሽነሪ’ ትእቢት የኢቮሉሽን የመጀመሪያው ደረጃ ይመስለናል። ቂ…ቂ…ቂ… አውራ ጣት በሚያሾልክ ካልሲ፣ ትእቢት… የምር መጠናት ያለበት ነው። ለውሳኔ እንጂ ለጥናት ባንታደልም ማለት ነው።
ዘንድሮ ሌላ ምን እየባሰበት ያለ ችግር አለ መሰላችሁ… ከዚህ በፊት ያወራነው ማሳበብ። ይሄ ‘ሪስትራክቸሪንግ’ የሚባል ነገር ከመጣ በኋላማ አንዳንድ ቦታ በሌላው ማላከክ እንደ ‘ሰልፍ ዲፌንስ’ ዓይነት ነገር ሆኗል።
አንድ ነገር ካልተሳካ ወይም ከተበላሸ ጥፋቱ ‘የዚያኛው ወገን’ ነው። ሁሌም እኛ ትክክል፣ እሱ ስህተት እየሆነ "የት ይሆን የምታደርሰን!" ብንባባል ምኑን ነው ጨለምተኛ የሆንነው። አሃ… ልክ ነዋ! ጨለምተኝነት የበራውን አምፖል "አልበራም" ማለት ነው እንጂ ጭል ጭል የሚለውን አምፖል "ግግም ሊል ነው" ማለት እቅጩን መናገር ነው። የቸገረን ነገር መሬቱን ሙጃ ወርሶት "አበባው እንዴት ደስ እንደሚል አየኸው?" መባል ነው።
እኔ የምለው… ጥያቄ አለኝ… ሌላው ላይ ማሳበብ እንደ ኢንፍሉዌንዛ ምናምን ነገር በአየር የሚተላለፍ ነው እንዴ? ግራ ያጋባላ! የሆነ የተበላሸ ወይም ያልተሳካ ነገር "የኔ ጥፋት ነው" የምንል ስንት እንደሆንን ልብ በሉ እስቲ። ዘንድሮ እንደ አመልካች ጣት ሥራ የበዛበት የሰውነት ክፍል አለ እንዴ! ይኸው ‘ያለተጨባጭ ማስረጃ’… አለ አይደል… ‘የተከለከለችው ፍሬ’ ነገር እስካሁን በሔዋን እንደተሳበበ አይደል!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… መቼም እዚህ ሀገር ዘንድሮ ‘ያለምርምር የሚደረስበት ነገር’ መአት ነው። በቀደም አንድ ወዳጄ ከየት እንዳመጣው እንጃ እንጂ ምን አለኝ መሰላችሁ… "አዳም አባታችን አበሻ ነበር"። ምን ግርም ይልሃል አትሉኝም… ዘንድሮ ‘የኖሩ ነገሮችን’ ቦታ ማስለቀቅ እንዲህ ቀላል መሆኑ።
ግን የእውነት ምን አለ መሰላችሁ… አዳም አበሻ ከሆነ እስካሁን ሲነገረን የነበረው የእሱና የእፀ በለሷ ታሪክ መስተካከል አለበት! አሃ… ልክ ነዋ! ዕፀ በለሱን "ሔዋን ለአዳም ሰጠችው" የሚለው ነገር ይስተካከልልን! የምር አዳም አበሻ ከሆነ እንዴት ይመስለኛል መሰላችሁ… ሔዋን ዛፍ ስር ተደብቃ የተከለከለውን ስትበላ ቆጣ ብሎ "ምን እያደረግሽ ነው?" ይላታል። እሷ ስትፈራ ስትቸር "እየበላሁ…" ትለዋለች። እሱም "ምንድን ነው የምትበይው?" ሲላት፤ እየፈራች "የተከለከለችውን ፍሬ" ትለዋለች።
ይሄኔ አበሻው አዳም ምን የሚል ይመስለኛል መሰላችሁ… "እሱን ፍሬ አምጥተሽ ካላጎረስሽኝ ፊትሽን ቀሽም ገበሬ ያበላሸው ማሳ ነው የማደርገው!" እና ሔዋን ታዲያ ምን ታድርግ! ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ… እንደ እኛ ፎካሪ አለ እንዴ! በዛ ሰሞን ሴት በመደብደብ አንደኛ ነው ምናምን ተብለን አልነበር!
እናላችሁ… ማሳበብ አንዱ ትልቅ ችግራችን ሆኖላችኋል። አንድ ወዳጄ "እንደ ሶሻሊዝም ማሳበብ የሚችል ስርዓት የለም" ሲለኝ ነበር። ለሁሉም ችግር መንስኤው ሌላው ነዋ! አንድ የ‘ሶሺሌ’  ቀልድ ትዝ አለችኝማ… ምን ትል መሰላችሁ. አንዱ በ"ሶሻሊዝም አቅርቦትና ፍላጎት ምን ማለት ነው?" ተብሎ ሲጠየቅ ምን ብሎ መለሰ አሉ መሰላችሁ… "ገበያ ላይ ያገኘኸውን ነገር ትገዛና ፍላጎትህ እንደሆነ እራስህን ታሳምናለህ።" አሪፍ አይደል!
እናላችሁ… ከስርዓት ‘ሶሺሌ’ ሰበበኛ ስርዓት ነው ያለው ወዳጄ፣ የማን ጥናት እንደሆነ አልነገረኝም። ግን የ‘ስርዓት’ ነገር ሲነሳ የሆነ ነገር ትዝ አለኝ። ይችን አሪፍ የሆነች የተለያዩ ስርዓቶች ትንታኔን አንብቡልኝማ! (የ‘ቦተሊካ’ ትምህርት በአዲስ መልክ መስጠት መጀመራችንን እናሳውቃለን። ቂ…ቂ…ቂ…)
ሶሻሊዝም፡- ሁለት ላሞች አሉህ። መንግስት አንዱን ይወስድና ለሌላ ሰው ይሰጥብሃል።
ኮሚኒዝም፡- ሁለት ላሞች አሉህ። መንግስት ሁለቱንም ይወስድና ወተት ይሰጥሃል።
ፋሽዝም፡- ሁለት ላሞች አሉህ። መንግስት ሁለቱንም ይወስድብህና ወተት ይሸጥልሃል።
ናዚዝም፡- ሁለት ላሞች አሉህ። መንግስት ሁለቱንም ይወስድብህና ግንባርህን ይልሃል።
ቢሮክራሲ፡- ሁለት ላሞች አሉህ። መንግስት ሁለቱንም ይወስድብህና ወተቱን በፍሳሽ ገንዳ ውስጥ ያፈስሰዋል።
ካፒታሊዝም፡- ሁለት ላሞች አሉህ። አንዱን ትሸጥና ኮርማ ትገዛለህ።
ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ማለት እንዲህ ነው። "የእኛስ?" ያልከኝ ወዳጄ ‘በውስጥ መስመር’ ጠብቀኝና እንነጋገራለን። ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው… ያ ጠበል ሄዶ "ከስራ ሳላስለቅቀው አልለቀውም…" ያለው ስናወራ ለቆት ይሆን እንዴ! ነገርዬው ምን መሰላችሁ… የዘንድሮ ትእቢትና ማሳበብ ከጀርባቸው "ከሥራ ሳላስወጣው አልለቀውም…" የሚል ነገር ያለ አይመስላችሁም? የአመልካች ጣት ስራ የሚቀንስበትን ዘመን ያምጣልንማ! አንድ ወዳጄ እንዳለው… አንዱ ዶሮ ሲያረባ፣ ጎረቤቱ ሸለመጥማጥ ከሚያረባበት አስተሳሰብ ይገላግለንማ!
 ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1190 times