ትምህርት ጥሩ ነው። ኮሌጅ መግባትም አሪፍ ነው። ግን ኮሌጅ ስለገባህ ብቻ እራስህን ትለውጣለህ፣ ሀገርን ትቀይራለህ ማለትም አይደለም። በሀገራችንም ፊደል ከመቁጠር ውጭ ብዙ ትምህርት የሌላቸው፣ ሆኖም በተፈጥሮ ባላቸው ችሎታ ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡
ወደ ውጭም ስንሄድ .....
ታዋቂው የኦቶሞቢል አምራች የፎርድ ኩባንያ መሥራች የሆነው ሔነሪ ፎርድ፣ አይደለም ኮሌጅ መግባት መደበኛ ትምህርቱን እንኳን በወጉ ማጠናቀቅ ያልቻለ ሰው ነበር። ልክ 15 አመት ሲሆነው ትምህርቱን አቆመ። ሆኖም ህልም ነበረው። ያ ህልሙን ያለ አንዳች የመደበኛ ትምህርትና የኮሌጅ ዲግሪ ማሳካት ቻለ፡፡
........
አዶልፍ ዳስለርም እንደዛው ነው። ዝነኛው የስፖርት ትጥቅ አምራች የአዲዳስ ባለቤት ከሁለተኛ ደረጃ የዘለቀ ትምህርት አልነበረውም። ሆኖም የኮሌጅን በር አለመርገጡ፣ በአለም ዝነኛ የሆነውን አዲዳስን ከመመስረት አላገደውም። ስለዚህ ተማሪዎች ኮሌጅ ቢገቡ፣ ቢማሩ ጥሩ ነበር፤ ሆኖም በወደቀው የትምህርት ፖሊሲና በተለያዩ ምክንያቶች ይህን አላሳኩምና፣ እንደ እርባና ቢስ መቁጠር ትክክል አይደለም። ማን ያውቃል፣ ወደፊት ሀገራችንን የሚለውጡት ዛሬ የኮሌጅ መግቢያ ውጤት ማምጣት ያልቻሉ ተማሪዎች ይሆናሉና፣ ለአእምሯቸው እንጠንቀቅ።
(ዋሲይሁን ተስፋዬ)
Published in
ባህል