Saturday, 21 October 2023 19:52

ዓለም በጦርነት ይከሳከሳል ቻይና ይመለከታል

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

       *  የሐማስ መሪዎች እጃቸውን ይስጡ ብሏል - የእስራኤል ጦር።
       *  የእስራኤል ዘመቻዋን ካልቆመች ‘ወዮላት’ ብለዋል - እነ ሐማስ።
       *  ጦርነቱን በቪዲዮ ቀርፀው በኢንተርኔት ለማሰራጨት ነው የሚጓጉት።
       *  የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት “ትራጀዲ” ነው። “ድራማ” የሚያስመስሉትም አልጠፉም።
               
        የዛሬ ሁለት ሳምንት በሐማስ ጥቃት እንደ አዲስ የተጀመረው ጦርነት፣ በየዕለቱ ቀንና ሌሊት በላይ በላዩ እያከታተለ ክፉ ክፉውን እያሳየን ነው።
በየመንደሩ እየዘመቱ መኖሪያ ቤቶችን ማቃጠል፣ ሕፃን ዐዋቂውን ሁሉ እየገደሉ በኢንተርኔት “እዩልኝ” ብሎ ማወጅ ምን ይሉታል? ቢያንስ ቢያንስ የጦርነት መዘዝ እንደሚመጣና ብዙ ሰዎች እንደሚሞቱ አስቀድሞ የሚያስብ ሰውስ እንዴት ይጠፋል?
ሆስፒታል ላይ በወረደው ፍንዳታ ከ500 በላይ ሰዎች በአንድ ቅፅበት ሕይወታቸውን ማጣቸውስ? የፍንዳታው መንሥኤ ማን ነው? ጣት እየተጠቋቆሙ ሲወነጃጀሉና ሲወዛገቡ አይተናል።
ፍንዳታው የእስራኤል ጥቃት ላይሆን እንደሚችል ከተነገረ በኋላ፣ የብዙ ሰዎች ሆይ ሆይታና የዓለም ሚዲያ ዘገባ ወዲያውኑ ተቀዛቅዟል። የብዙዎች ጭንቀትና ሐሳብ፣ በርካታ መቶ ሰዎች መሞታቸው ላይ አይደለም ለካ። ከማዶ ሆነው፣ የጦርነት ቪዲዮ እያዩና እያሳዩ፣ አንደኛውን ጎራ ለማውገዝና ተሽቀዳድሞ ለመፍረድ ነው የሚጓጉት።
ለአብዛኞቹ የእስራኤልና የጋዛ ነዋሪዎች ግን፣ ጦርነቱ ዕለታዊ ተከታታይ ድራማ አይደለም።
እልቂትና ውድመት በእልፍ በእልፍ በሮኬትና በቦምብ ቁጥር ሆኗል።
በመጀመሪያው ሳምንት፣ ሐማስ ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኩሷል።
የእስራኤል አየር ኃይል ጄት አውሮፕላኖችና ድሮኖች ወደ ጋዛ እየተመላለሱ በስድስት ቀናት ውስጥ ከ6 ሺህ በላይ ቦምቦችንና ሚሳዬሎችን ተኩሰዋል።
ያው፣ የጦርነት ቴክኖሎጂ ለሁሉም እየተዳረሰ ነው።
የእስራኤል ጦር በድንበር ዙሪያ ሰው አልባ መትረየሶችን የመትከሉ ያህል፣ ሐማስም ጥቃቅን ድሮኖችን በመጠቀም የእጅ ቦምቦችን ወደ እስራኤል ምሽግ ሲወረውር ታይቷል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል “አይረን ዶም” በተሰኘ ቴክኖሎጂ የሐማስ ሮኬቶችን ከሰማይ ላይ ያከሽፋል።
ሐማስ ደግሞ ምድር ለምድር እየማሰ ያከማቸውን ሮኬቶች ወደ እስራኤል በእሩምታ ያስወነጭፋል።
ምንም እንኳ የጋዛ መሬት ከጫፍ እስከ ጫፍ ከ40 ኪ.ሜትር ባይበልጥም፣ ሐማስ ከምድር ስር የከፈታቸው የመተላለፊያ ዋሻዎች ግን ከ500 ኪ.ሜትር ይበልጣሉ ተብሏል። ዋሻዎቹ መተላለፊያ ናቸው። የሮኬት መጋዘኖችም ናቸው።
ምሽግም፣ የታጋቾች ማጎሪያም ናቸው - የሐማስ ዋሻዎች።
የእስራኤል ጦር ወደ ጋዛ በሚያደርገው ዘመቻም፣ የሐማስ ዋሻዎች ዋና ፈተና ይሆኑበታል ተብሏል። የእስራኤል ጦር ይህን አይክድም። ሐማስን ከጋዛ ለማስወገድ በሚካሄድ ዘመቻ ከ1 ሺህ በላይ ወታደሮች ሊሞቱብኝ ይችላሉ ብሎ ሲሰጋ የቆየው አለምክንያት አይደለም።
የከተማ ጦርነት ውስጥ በሺ የሚቆጠሩ ወታደሮችና ታጣቂዎች የሚሞቱ ከሆነ፣ ስንት ዕጥፍ ሲቪሎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ለማሰብ ይከብዳል።
ጦርነቱ ገና “ጅምር” ላይ ነው እየተባለ፣ ከወዲሁ እስካሁን በእስራኤልና በጋዛ 5 ሺህ ሰዎች ሞተዋል። ጦርነቱ ሲጦዝስ? አሳዛኝ እልቂትና ውድመት ነው የጦርነት ውሎና አዳር። እንዲያም ሆኖ፣… እንደ መዝናኛ ወይም እንደ መበሻሸቂያ ሆኖ የሚታያቸው ሰዎች በዓለም ዙሪያ በዝተዋል።
የዘመናችን ጦርነት ለቀረፃ ታስቦ የሚዘጋጅ እየመሰለ መጥቷል። ቪዲዮ ለመቅረፅና በኢንተርኔት ለማሰራጨት፣ በቲክቶክና በትዊተር፣ በፌስቡክ፣ በዩቱብና በቴሌግራም ላይ ለመልቀቅ ታስቦ የተፈፀመ የጭካኔ ዘመቻ አይመስልም?
“ጦርነት በቀጥታ ስርጭት” ለመላው ዓለም ለማሳየት የተሞከረበት ሁለተኛው ጦርነት ነው ማለት ይቻላል - የእስራኤልና የጋዛ ጦርነት። ከዩክሬን እና ከራሺያ ጦርነት በመቀጠል ማለት ነው።
የራሺያ ወረራ የተጀመረው ጦርነት በአጭር ጊዜ የሚያልቅ አይመስልም። ለራሺያና ለዩክሬን “ይብቃችሁ” የሚላቸው ኃይል ከሰማይ የሚወርድላቸው አይመስልም። ከሁለቱም አገራት ከ00 ሺ በላይ መሞታቸው ብቻ አይደለም መከራው።
ኢኮኖሚያቸውም እየወደመ ነው። ለዚያውም ራሳቸውን የሚያወድሙት በራሳቸው ወጪ ነው።
ራሺያ የራሷን ሚሳየሎች ከመጋዝን አራቁታ እየጨረሰች ከሰሜን ኮርያና ከኢራን የጦር መሳሪያ መሸመት አብዝታለች፡፤ በጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ ከአሜሪካ ጋር እፎካከራለሁ ስትል የነበረችው ራሺያ፣ ዛሬ ከኢራንና ከቱርክ “Dron” የምትገዛ ሆናለች።
ዩክሬንም የጦር ዓውድማ ሆና በየዕለቱ እየወደመች፣ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ግዙም የመድፍ አረሮችን ትተኩሳለች። የአንድ አረር ዋጋ ከ700 ዶላር ይበልጣል። ያው ዩክሬን ከአውሮፓና ከአሜሪካ በእርዳታ እየተቀበለች ትተኩሳለች።
አሁን የአውሮፓና የአሜሪካ መጋዘኖች ውስጥ የመድፍ አረር ጠፍቷል። “ለመጠባበቂያ ለአደጋ ጊዜ” ከተከማቸው የመድፍ ተተኳሽ በቀር የነ አሜሪካ ትጥቅ ተመናምኗል።
ዛሬ ደግሞ፣ በእስራኤልና በሐማስ ጦርነት ሳቢያ አሜሪካና ኢራን እንደገና እየተፋጠጡ ዛቻ እየተወራወሩ ነው። በየፊናቸውም የጦር መሳሪያ እርዳታ ከመስጠት አልቦዘኑም።
ራሺያና ዩክሬን፣ አሜሪካና አውሮፓ፣ እስራኤልና የአረብ አገራት፣ ኢራንም ጭምር በጥቃትና በአፀፋ አዙሪት ይቀጣቀጣሉ።
ከዳር ሆኖ ማን ያያል?
የቻይና መንግስት!
“ከአላስፈላጊ ጦርነት መራቅ አለብን” የሚል መርህ ለቻይና አዲስ አይደለም። ከጦርነት የመቆጠብ መርህ የዛሬ 40 ዓመት ገደማ በቻይና መንግሥት ዘንድ ጎልቶ የታየ መርህ ነው። ከአላስፈላጊ ጦርነት መራቅ፣ ወደ ጦርነት ዘው ብሎ አለመግባት ትክክለኛ መርህ ስለሆነ ያስመሰግናል፡፡
በዚህ ቢቀጥል ጥሩ ነበር። ነገር ግን፣ ዛሬ ዛሬ የቻይና መንግስት ባሕርይ እየተቀየረ ነው። ጉልቤ ልሁን እያለ ነው። አሁን ራሱ፣ የቻይና መንግሥት ከዳር ሆኖ የጦርነት ተመልካች መሆኑ፣ የጤና ላይሆን ይችላል የሚሉ ዐዋቂዎች ጥቂት አይደሉም። ዓለም ሁሉ ግራ ቀኝ ሲቆራቆስና ሲደማ፣ የቻይና መንግሥት አሳቻና አመቺ ጊዜ ጠብቆ የዓለም ገናና ለመሆን አድፍጦ የሚጠብቅ ይመስላል ይላሉ። የህንድ መንግስት ቻይናን በስጋት የሚመለከተውም በዚሁ ሳቢያ ነው።
ለነገሩ የህንድ መንግሥትም፣ ለሌሎች ትናንሽ አገራት የሰላም ስጋት መሆኑ አይቀርም።
በዚህ መሐል፣ የእስራኤል መንግሥት የአየር ኃይል ድብደባውን ካላቆመና ወደ ጋዛ የምድር ጦር ካዘመተ… “ወዩለት!” እያሉ የሐማስ መሪዎች ሲዝቱ ሰምታችኋል። ሄዝቦላም እንደዚሁ። የኢራን መንግስትም ተጨምሮበታል።
በእርግጥ ባዶ ዛቻ አይደለም። ሄዝቦላ በሮኬት ትጥቆች ከሐማስ በዕጥፍ ይልጣሉ። በዚያ ላይ በሶሪያ ጦርነት ውስጥ የሄዝቦላ ታጣቂዎች የውጊያ ልምድ አግኝተዋል።
ቢሆንም ግን በዚሁ ዛቻ ምክንያት የእስራኤል ጦር ዘመቻውን ይሰርዛል? የማይመስል ነገር ነው። ዛቻው ብዙም ለውጥ አያመጣም። እንዲሁ ለይስሙላ እንጂ።
የእስራኤል መንግስት በበኩሉ፣ ከትናንት በስቲያ ለሐማስ መሪዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። “እጃችሁን ስጡ” በማለት አሳስቧል። እጃቸውን ይሰጣሉ? የማይመስል ነገር ነው። ማስጠንቀቂያው ብዙም ትርጉም የለውም። እንዲሁ ለይስሙላ ያህል እንጂ።

Read 1164 times