Saturday, 21 October 2023 20:01

እርም ማውጣት ሀዘን ይቀንሳል

Written by  -ብርሃኑ ሰሙ-
Rate this item
(2 votes)

 (ሀገራችንም እርሟን ታውጣ!)
                    
          ይህ ግጥም ‹‹ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ›› በሚል ርዕስ ደበበ ሠይፉ በ1967 ዓ.ም የጻፈው ነው፡፡ ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› በሚል ርዕስ በ1992 ዓ.ም ባሳተመው የግጥም መጽሐፉ ተካትቷል፡፡ ግጥሙ መቸገርን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ችግርና ርሀብ ብቻ ሳይሆን፤ በእርስ በእርስ ግጭትና ፍጅት ‹‹ዘመን›› ጭምር ‹‹የተሰላቸብን›› ሕዝብና ሀገር ስለመሆናችን፣ ባለፈው ሳምንት በትግራይ ለሦስት ቀናት የታወጀው መርዶ ማለፊያ  ማሳያ ነው፡፡  
በቃየልና አቤል የተጀመረው የሰው ልጅ እርስ በእርስ የመገዳደል ታሪክ መገለጫ ምክንያትና ዓላማው፣ መጠሪያ ስምና አፈጻጸሙ፣ የጊዜው ማጠርና መርዘም እየተለዋወጠ፣ ከጥንት እስከ ዛሬ የዘለቀ  ነው፡፡ ዓለማችን ከዚህ ችግር መቼም ነጻ ትሆናለች ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህ መራራ እውነት በሚያስከትለው ጣጣ በተለይ እናቶች የመጀመሪያው ተጠቂ መሆናቸውን፣ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፣ በሦስት ከፍለው ባቀረቧቸው ስዕሎች ገልጸውታል፡፡
የሰዓሊውን ሦስት ተራኪ ስዕሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋቸው በ1980ዎቹ መጀመሪያ በብሔራዊ ሙዚየም ለሕዝብ በቀረቡበት ወቅት ነበር፡፡ ዘመኑ በደርግና በሰሜን ኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ ብዙ ሕይወት፣ ሀብትና ንብረት የሚወድምበት ነበር፡፡ በመጀመሪያው ስዕል ቃየል አቤልን ሲገድል ይታያል፡፡ በሁለተኛው ብላቴናው ዳዊት ኃያሉን ጎልያድ በወንጭፍ መግደሉን ይተርካል፡፡ በሦስተኛው ስዕል፣ ወንድማማቾችም ይሁኑ ኃያላንና ደካሞች ሲጋደሉ፣ ሀዘኑ የእናቶችን አንገት እንደሚያስደፋ ያመልክታል፡፡ እነዚህ ስዕሎች በቅርቡም በእንጦጦ ፓርክ የተሰራው አዲስ የስዕል ጋለሪ የተመረቀ ሰሞን፣ በተሰናዳ  የስዕል አውደርዕይ ላይ ቀርበው ነበር፡፡
ቃየል አቤልን የገደለበት የቅናት፣ የስግብግብነትና የጥላቻ ስሜትም ይሁን፤ ኃያላን ደካሞችን ይበልጥ አዳክመው ሁሌ የበላይ ሆኖ የመኖር ፍላጎት… በቀላሉ ይቆማል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በመንፈሳዊ መረዳት ካልሆነ በስተቀር፤ ዓለም ከጦርነት ነጻ የምትሆንበትን ዘመን መጠበቅ የዋሕነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሀገራት ሉአላዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ በ‹‹ቅዱስ ጦርነት›› ሕዝባቸውን አስተባብረው፣ ምድርና ሕዝባቸውን መከላከል የሚጠበቅባቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን የውጭ ወራሪን በመመከት ረገድ  ለሉአላዊነት መከበር ባደረጓቸው ጦርነቶች አንፀባራቂ ታሪክ ካላቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዚህ ዓይነቱ መስዋዕትነት ‹‹ልጅሽ አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ›› ተብለው የሚወደሱት እናቶችም ቢሆኑ፤ ሀዘኑ አንገታቸውን ከሚያስደፋቸው ይልቅ ልባቸው ኩራት እንዲሰማው የሚያጀግናቸው፣ ጦርነቱ ‹‹ቅዱስ ጦርነት›› መሆኑ ስለሚገባቸውም ጭምር ነው፡፡
ቅዱስ ጦርነትን በተመለከተ በዓለምም ሆነ በሀገራችን፣ ታሪክ የመዘገባቸው ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኃያላን መንግስታት በጥቅምና ፍላጎታቸው ተጋጭተው፣ ልዩነታቸው የፈጠረውን ጸብ፤ በሌሎች ሀገራትና ምድር ከሚካሄዱ ጦርነቶች ግራና ቀኝ በመሰለፍ እርስ በእርስ እንደሚዋጉት  ሁሉ፣ በ1940ዎቹ ኮሪያን ለሁለት በሰነጠቃት ልዩነትም፣ ተመሳሳይ እውነታ ነበር የተስተዋለው፡፡
ለኮሪያ በሁለት መከፈል ካፒታሊዝምና ሶሻሊዝም፣ በአሜሪካንና ራሽያ ተወክለው ያካሄዱት ትግል፣ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በሰሜንና ደቡብ ተለያይተው የሚጋደሉትን ኮሪያውያን በተመለከተ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ‹‹ለጋራ ደህንነት›› በሚል ዓላማ ያቀረበውን ጥሪ ኢትዮጵያም ተቀብላ ወደ ደቡብ ኮሪያ ወታደሮቿን ማዝመቷ ይታወቃል፡፡ በ5 የተለያዩ ዙሮች ከ6 ሺህ በላይ ወታደሮችን ለዚሁ ዓላማ ልካለች፡፡ ለመጀመሪያው ዙር ወታደሮች ሽኝት ሲደረግ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ የነበሩት አቡነ ባስልዮስ፣ ዘማቾቹን፤ ‹‹ያገኛችሁትን ብሉ፤ እኛ እዚህ እንጾምላችኋለን›› ብለው ጦርነቱ ቅዱስ መሆኑን ባርከው ነበር የሸኟቸው፡፡ የኮሪያ ዘማቾች አሁን ታሪካቸው አንፀራቂ ሆኖ የምናገኘው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ከዚህ ተቃራኒ የሆነው የእርስ በእርስ ጦርነት ታሪካችን ግን እናቶችን ብቻ ሳይሆን፣ ሀገርና ሕዝባችንን አንገት በማስደፋት ይታወቃል፡፡ እንዲህም ሆኖ በተደጋጋሚ ለብዙ ዘመናት፣ በዚህ ችግር ውስጥ ብናልፍም ‹‹ተምረንበታል›› የሚያስብል ማሳያ የለንም፡፡ መስቀል አደባባይ የሚገኘው የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም፣ “መቼም፤ የትም እንዳይደገም” በሚል መርህ ቢቋቋምም፤ ሙዚየሙ ከተከፈተ በኋላ እንኳን በብዙ የእርስ በእርስ ግጭቶች ውስጥ አልፈናል፡፡ የ1997 ምርጫ ውዝግብን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት፣ ለሞት የተዳረጉ ወጣቶችን ፎቶግራፍ በማተም፣ የግል ጋዜጦች፣ የፎቶግራፍ አልበም እስከመምሰል ደርሰው ነበር፡፡  
እርስ በእርስ በምናደርገው ጦርነት ሳቢያ በሌሎች ዘንድ ለትዝብት ስለመዳረጋችን፤ “ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ (አባ መላ) 1844 -1919” በሚል ርዕስ፣ በቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ተዘጋጅቶ፣ በ1997 ዓ.ም በታተመው መጽሐፍ፤ ፊታውራሪ ከአንድ ጣሊያናዊ ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉት ጥያቄና መልስ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
‹‹ከዕለታት አንድ ቀን ለወሬ የታጠቀ አንድ ኢጣሊያዊ ጋዜጠኛ (ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን) ሊያነጋግራቸው ፈልጎ ቀጠሮ ጠየቃቸው። እሳቸውም ጥያቄውን ተቀበሉና የሚገናኙበትን ቀንና ሰዓት ወሰኑለት። በቀጠሮው ቀን ምን ይናገር ይሆን ብለው ሲጠባበቁ፤ የሰገሌው ጦርነት በምን እንደተነሳና ማን ድል እንዳደረገ ጠየቃቸው። መቼም ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ የኢጣሊያኖችን ተንኮል በማወቅ ረገድ በጊዜው ከነበሩት ታላላቅ ሰዎች ሁሉ በላይ ችሎታ ነበራቸውና ፣አጠያየቁ ለመዘባበቻ መሆኑን ከመቅፅበት ተረዱና፤ ‹አዬ ጉድ! አዬ ጉድ! እኔ ሌላ ቁም ነገር የምትጠይቀኝ መስሎኝ ነበር። ይህ አሁን የምትጠይቀኝ ነገር የሁለት ወንድማማቾች ግጭት ስለሆነ የጦርነት ስም የሚሰጠው አይደለም። ይልቅስ የዓድዋውን ጦርነት ሁኔታ ጠይቀኝና እንዴት እንደነበር፣ ማን ድል እንዳደረገ ደህና አድርጌ ላስረዳህ› አሉት።››
በእርግጥም ጥያቄና መልሱ፣ የአባ መላን፣ ‹‹መላ›› አዋቂነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ጋዜጠኛው፤‹‹የሰገሌው ጦርነትና ድል ወደፊት ለኢትዮጵያ ምን ጥቅሞችን ያስገኝላታል? ምንስ ጉዳት ሊያስከትልባት ይችላል ?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ቢሆን ኖሮ፣ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ምላሽ ምን ይሆን ነበር? የሚል ሌላ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በወቅቱ ባልቀረበ ጥያቄና ምላሽ ባልተሰጠበት ጉዳይ ላይ ብዙ ማለት ቢያዳግትም፣ ዛሬ ሀገራችንንና ሕዝቧን ለፈተና የዳረጓት ጉዳዮች፣ ከትላንት ተንከባልለው የመጡ መሆናቸውን ግን መካድ አይቻልም፡፡   
ከስልጣን ሹኩቻ፣ የጠረፍ አካባቢዎችን ከማስገበርና ከመሳሰሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የተደረጉ የእርስ በእርስ ግጭቶች ተከማችተው ለቁርሾ ምክንያት መሆናቸው በግልጽ ይታያል፡፡  ከቅርብ ዘመን ታሪካችን ብንነሳ፤ ከዘመነ መሳፍንት እስከ አብዮቱ ድረስ  ከተካሄዱ የእርስበርስ ግጭቶችና እልቂቶች፣ ከተማርንባቸው ይልቅ ለባሰ ቀውስና እልቂት መፍጠርያ የተጠቀምንባቸው እንደሚልቅ ታሪካችን  ይመሰክራል፡፡  
እንደ አለመታደል የቀድሞ ታሪካችን በ‹‹ቀውስ ነጋዴዎች›› እጅ እየወደቀ የፖለቲካ መቆመሪያ በመሆኑ ነው እንጂ፤ ከጥፋቱ ይልቅ በረከቱ  ያመዝን ነበር፡፡ የጠረፍ አካባቢዎችን ለማስገበር የተደረጉትን ዘመቻዎች በምሳሌነት ብንወስድ፣ ዘመቻው መሬት ከማካለሉ በተጨማሪ ያስገኛቸው በርካታ ጥቅሞች ነበሩ፡፡ የሸጎሌው ‹‹ሼህ ሆጀሌ ቤተ መንግስት››፤ ሆላንድ ኤምባሲ አካባቢ የሚገኘው ‹‹የአባ ጅፋር ግቢ››፣ የመርካቶ ‹‹አደሬ ሠፈር››፣ የተክለሃይማኖት ‹‹ገጃ ሠፈር››  የግዛት አንድነት ከማስጠበቁ ሂደት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ሀገራዊና ሕዝባዊ በረከቶች ነበሩ፡፡
የ700 ወጣቶች ሕይወት ቀጥፏል የሚባለው የጨለንቆ ጦርነት ሲጠናቀቅ፣ 120 እስረኞች በምርኮኛነት ወደ አዲስ አበባ መጥተው፣ አሁን ጣሊያን ሠፈር በሚባለው ስፍራ የቁም እስረኛ ሆነው ነበር፡፡ እስረኞቹ ከቁም እስር ነጻ ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ በአራዳ ገበያ ውስጥ በንግድና የተለያየ ሙያ ተሰማሩ፡፡ በ1930 ዓ.ም መርካቶ ለኢትዮጵያውያን ተመርታ በአካባቢው ከተቋቋሙ መንደሮች አንዱ መሆን የቻለው ‹‹አደሬ ሠፈር››ን የመሠረቱት 38 የአደሬ ቤተሰቦች፤ ለዚያ ደረጃ የበቁት የጠረፍ አካባቢዎችን ለማስገበር የተደረገው ዘመቻ በሂደት መልካም ዕድል ስለፈጠረላቸው ነበር፡፡ የዚያ ዕድል ተጠቃሚዎች በኋላ ላይ መርካቶ ውስጥ ትላልቅ ሕንፃዎችን እስከመገንባት የደረሱ ባለፀጋዎች ሆነዋል፡፡
ማዕከላዊው መንግስት ጉራጌን ለማስገበር ከንጉስ ሣህለስላሴ ዘመን ጀምሮ እስከ አጼ ምኒልክ የዘለቀና 15 ዓመታት ያስቆጠረ ጦርነት ማካሄዱ ይታወቃል፡፡ ዘመቻው ከባድ ስለነበር ‹‹በጉራጌ ጦርነት ያልተለቀሰበት የአማራ ቤት የለም›› የሚል ምስክርነት ሁሉ አለ፡፡ በኋላ ላይ ጦርነቱ በማዕከላዊው መንግስት አሸናፊነት ሲጠናቀቅ፤ በትግል ከተሰውት ውጭ በምርኮ ወደ አዲስ አበባ የመጡት የጉራጌ ተወላጆች፤ በንግድና መሰል የተለያዩ ስራዎች ውስጥ አልፈው ተጠቃሚነታቸውን ሲያዩ ‹‹ጉራጌ ተማረከ ወይስ ተባረከ?›› የሚል ጥያቄ አንስተው፤ ‹‹ተባርከንበታል›› ስለማለታቸው፣ በተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
እውነታው ይህ ቢሆንም “የቀውስ ነጋዴዎቹ”፤ በየቦታው ‹‹የሰማዕታት ሐውልት›› እያቆሙ፣ ችግር ያልነበረውን ‹‹ችግር›› እግር ሰጥተው አስሮጡት፣ አንደበት ሰጥተው አስጮኹት፡፡ ችግሩ ፖለቲካ ሰራሽ ባይሆን ኖሮ፣ የሰማዕታት ሐውልት በቆመባቸው ትግራይ፣ አማራ ኦሮሚያ… ዳግም የወጣቶችን ደም የሚያፈስስ ቀውስ ባልተፈጠረ ነበር፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ለሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሆኑ ታስበው የተሰሩት ሐውልቶች፤ ለሀገሪቱና ሕዝቧ ምን ጥቅም አስገኙ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በድንገት ግርግር በተፈጠረበት አንድ ዕለት፤ የሕንፃ መስታወቶቹ ተሰብረውበት ጠጋኝ ያጣው፤ በመስቀል አደባባይ የሚገኘው የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም፤ ‹‹መቼም፤ የትም እንዳይደገም›› በሚል ዓላማ ቢቋቋምም፤ ከሙዚየሙ አስተማሪነት ይልቅ ‹‹የመስዋዕትነት ታሪካችንን አላካተተም›› የሚሉ ውዝግቦች መፍጠሪያ መሆኑ ተስተውሏል፡፡ ኑሯቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉት፣ ፕሮፌሰር ጴጥሮስ ቶጃ፣ ከ1966 እስከ 1972 ዓ.ም ለስድስት ዓመታት በመኢሶን ዐባልነት ያሳለፉትን ታሪክ ‹‹የጭድ እሳት - ቆሳስለው የተረፉ ትዝታዎች›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ አዘጋጅተው፣ በ2014 ዓ.ም ለአንባቢያን ያቀረቡ ሲሆን፤ “በቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም መስዋዕትነታችን አልተካተተም” የሚል ቅሬታ በመጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡ በዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ደርግ፣ ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ኢሕአዴግ… መቼም ይስማማሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ልዩነቶቹ ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሀገሪቱና ሕዝቧ በተደጋጋሚ የጦርነት ሰላባ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ዘላቂውን መፍትሔ ከፖለቲከኞቹ ሳይሆን ከሕዝብ መጠበቁ የተሻለ የሚሆነው፡፡ ሕዝቡን አወያይቶ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያመጣ ኃላፊነት የተሰጠው ሀገራዊው የምክክር ኮሚሽንም፣ ይህንን አንድ አጀንዳ አድርጎ ሊወስደው ይችላል፡፡
በቅርቡ በተፈጠረው የእርስ በእርስ ግጭት በሞት ላጣቸው ልጆቹ፣ የትግራይ ሕዝብ እርም የማውጣት ዕድል አግኝቷል፡፡ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ … በሚል ሳይከፋፈል መላው ኢትዮጵያውያን መቼ፣ የትና እንዴት እርማቸውን ያውጡ? ሀገራችን የሞተባቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ከሞተባቸው ጋር ቁጭ ብሎ እርም ማውጣት እየፈለገ ዕድሉን ያጣ ብዙ ሕዝብ ያለባት ምድር ናት፡፡ እርም ማውጣት ሀዘን ይቀንሳል፤ ሀገራችን እርሟን ታውጣ!

Read 1313 times