Saturday, 21 October 2023 20:21

ወተት የጠጣ ውሻ ሰርዶ በበላ አህያ አፍ ይጠርጋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 እጅግ የሚፋቀሩ ባልና ሚስት በአንድ የገጠር መንደር ይኖራሉ። ባል ገበሬ ነው። ቀኑን ሙሉ ሲታትር ውሎ፣ ያረሰውን አርሶ ቤቱ ሲደርስ፣ ሚስት ለእግሩ ውሃ አሙቃ እግሩን አጥባ ራቱን አብልታ፣ አሳስቃ-አጫውታ ታስተኛዋለች። እሱም፣ የፍቅሯን ብዛት ለመግለፅ፣
“እንዲያው አንቺዬ አንቺ ባትኖሪ ምን ይውጠኝ ኖሯል?” ይላል።
“እንዴት? ለምኑ?” ትላለች፤ ጥያቄውን በጥያቄ መልሳ።
“ዘንድሮ እንደሰማዩ ባዶነትና እንደመሬቱ አልታረስ ማለት’ኮ የምንልሰው የምንቀምሰው አይገኝም ነበር። አንቺ ግን ያለውን አብቃቅተሽ፣ ስቀሽ አሳስቀሽ ጠግበን እንድናድር ታደርጊያለሽ”
“ያ የእኔ ሳይሆን የአምላክ ፀጋ ነው። ሁለተኛ ደግሞ የአንተ ድካም ፍሬ ነው። ይልቅ ተመስገን በልና ተኛ! ጎረቤታችንን አያ እገሌን አታየውም? ይጭነው አጋሰስ፣ ይለጉመው ፈረስ፣ ይልከው አሽከር ሞልቶ ተርፎት ሲያበቃ፣ ጧት ማታ አምላክን ሲያማርር እንዲህ ደህይቶ ቁጭ ብሎ ቀረ”
“እሱስ እጅግ ያበዛዋል”
“ዛሬ ጠዋት በተስኪያን ቄሱን ሲጨቀጭቃቸው ነበር። እሳቸው ግን የልብ- አውቃ አደሉ አንጀቴን አራሱኝ።”
“ምን ብለው?”
“ምን ይሆንልሃል፤አጅሬ እንደተለመደው ከስብከት በኋላ ይጠብቃቸዋል። እኔም ቤት መጥተው ጠበል እንዲረጩ ልነግራቸው እዚያው ቆሜያለሁ። ጨርሰው ሲመጡ እንዲህ ይላቸዋል። - “አባ ሰሞኑን ክፉ ክፉ ህልም እያየሁ ተቸግሬአለሁና እስቲ ይፍቱልኝ?”
“ምን ችግር ገጠመህ፣ ምን ህልም አየህ አያ?” አሉት ቄሱ።
“ይሄውሎት አባ፤ በህልሜ በየማታው አንድ በሬ ይመጣብኛል። ቀንዱ በጣም የሾለና አስፈሪ ነው። እየመጣ ሊወጋኝ ሲያባርረኝ አያለሁ። አሁን አሁንማ ጭራሽ ሩጫውና ፍጥነቱ አያድርስብዎት! ይኸው ሣምንቴ ስሮጥ ስባረር! ከእንቅልፌ  እየባነንኩ ስጨነቅ አድራለሁ!! እንደው ምን ባደርግ ይሻለኛል አባ?
“አንተ መኝታህ ምን ላይ ነው?”
“ኧረ የረባም መኝታ የለኝ አባ። እንዲያው የሣር ፍራሽ ላይ ነው የምተኛው።”
“ታዲያ ዋና ቀለቡ ላይ እየተኛህ ዱሮስ ላያባርርህ ኖሯል እንዴ?”
***
በሰው ቀለብ ላይ መተኛት በሰው ህይወት ሂደት ላይ ጋሬጣ መሆን ነው። በሰው እንጀራ መግባትም የዚያኑ ያህል የሌላውን ህይወት መቀማት ነው። ሠራተኛ የሚጠበቅበትን ያህል ሥራ ሰርቶ፣ የሚገባውን መብትና ጥቅም ማስከበር ይፈልጋል። ይህ መብትና ጥቅም ከሚሰራው ስራ ጋር ሁነኛ ትስስር ያለው እንደመሆኑ፣ አንዱ ሲጎድል ሌላኛው መነካቱ፣ ያንዱ ፍሰት ሲቋረጥ የሌላኛው ቧንቧ እንደሚዘጋ አያጠያይቅም።
በሀገራችን ሥራና ሠራተኛ በትክክልና በውል ተገናኝተዋል ለማለት አይቻልም። ሥራና ሠራተኛ የሚገናኙበት ቦታ ደግሞ የሥራ-ብቃት ያለው ሠራተኛ ሞልቶ ተትረፍርፏል ለማለትም ከቶ አያስደፍርም። በዚያ ላይ ሁለቱም በወግ ሰምረው የተገናኙበት ቦታ ደግሞ ጥሩ የሥራ ከባቤ- አየር (Atmosphere) አይኖርም። የግሰብ አለቆች ማንነት፣ የፖለቲካው ንፋስ፣ የሥራ ባህል ድክመት፣ የቢሮ ሥርዓት ማጣት ወዘተ… ብርቱ እንቅፋት ሆነውበት ይገኛል። በዚህ ምክንያት ብዙ ስፍራ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሲሆን ይታያል። የታሰበው ግብ አይመታም። እድገት የለም። የሠራተኛ መማረርና ብሶት የዕለት- የሠርክ እሮሮ ይሆናል። ሁሉም በወጉና በሥርዓቱ በቅርበት መመርመር አለባቸው።
ዋናው ባለጉዳይ እያለ አጃቢው የሚያስቸግርበት ሁኔታ ሞልቷል። የሚመለከተው ሹም እያለ ምንዝሩ አለሁ አለሁ የሚልበት ሁኔታ ጎልቶ ይታያል። ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ የሚለው መርህ፣ አንዱ መሰናከያው ይሄ ነው። “የምትወልደው ገበያ ሄዳ የምታዋልደው ቤት አልጋ ላይ ትተኛለች” የሚባለውም ይሄ ነው። አጃቢና አጫፋሪ በበዛ ቁጥር ዋንኛው ሰው ኃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣበትን እድል ያጣብቡበታል። አንድም ደግሞ ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ የሆኑ ሰዎች ጣልቃ እየገቡ ሥራውን ያበላሹበታል ማለት ነው። እንዲህ ያለው ጉዳይ በተለይ በፖለቲካው መስክ ሲታይ ደግሞ የበለጠ ጎጂ ይሆናል። በሀገራችን በታዩት ለውጦች ውስጥ ሁሉ፣ ዋናው የፖለቲካ ሃላፊ ወይም መሪ በእርጋታ በሚወያይበት ቦታ፣ ካድሬው ከልክ ያለፈ ልፈፋና መፈክር ሲያበዛ፣ ዋናው ባለሥልጣን በመግባባትና በመቻቻል ይፈታል የሚለውን ጉዳይ ካድሬው ጦር ሲሰብቅለት ይገኛል።
ይህም  በወጉ ካልተያዘ ለማናቸውም ሥራ እንቅፋት መሆኑ አሌ አይባልም።
ባልተጋበዙበት ድግስ የሚመጡ፣ የማይመለከታቸው ጉዳይ ላይ ንግግር የሚያደርጉ፣ ባልሰለጠኑበት ሙያ ከባለሙያው በላይ ዘራፍ የሚሉ አያሌ ናቸው። እነዚህም ሥራን በማበላሸት ረገድ ጉልህ ድርሻ አላቸው። እንደዚህ ያሉት “ወይ ትንሽ የምትበላ አይደለህ”፣ ወይም ከበላን በኋላ አልመጣህ” የሚባሉት ዓይነት ሲሆኑ፤ በራሳቸውና በተመደቡበት ስራ ላይ ሳይሆን በቅልውጥ ሥራ የተካኑ ናቸው። ለዚያውም ድግስ ያበላሻሉ። ገበታ ያዘበራርቃሉ። ሥራና ሠራተኛን ያለያያሉ።
በማናቸውም የሥራ መስክ ላይ፣ በቢሮ አካባቢም ሆነ በፖለቲካው የሥልጣን መዋቅር ዙሪያ እጅግ አስቸጋሪና ጎጂ የሆነው ባህል፣ ጥፋትን በሌሎች ላይ የመላከክ (Blame-Shifting) ተግባር ነው።  ይህ አሉታዊ ተግባር ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፣ ከትላልቅ የፖለቲካ መሪዎች እስከ አማካዩ ሟች ፍጡር (Average mortal) ድረስ ሥር-የሰደደ አባዜ ነው።
ቀበሌው በወረዳ፣ ወረዳው በቀጠና፣ ቀጠው በመስተዳድሩ ያላክካል። ሚኒስትሩ በምክትሉ፣ ምክትሉ በሥራ አስኪያጂ፣ ሥራ-አስኪያጁ በመምሪያው እያለ እስከ ዜጋው እርከን ድረስ ይወርዳል። ሁሉም “እሱ ነው!” እንጂ “እኔ ነኝ” ለማለት ዝግጁ አይደለም። አንዱ አንደኛውን “ባጋለጠ” ቁጥር የራሱን ንፅህናና ትክክለኝነት ያረጋገጠ እየመሰለው በግብዝነት መደገጉ የተለመደ ክስተት ሆኗል። የሌሎችን ጉድለት በማጉላት የራስን ትልቅነት ማሳየት የሚቻል የሚመስላቸው አያሌ ናቸው። ይህ ደግሞ የአሉታዊነት ባህሪን እያደበረ አገርን እያኮሰሰ ወደ ውድቀት፣ ህዝብ እያጎሳቆለ ወደ ድቀት የሚያመራ፣ ከቶም በቀላሉ የማንሽረው ባህል ነው።
 ዛሬ እኛ በሌላው ላይ ክፉ ስናደርግ ባህሉን ማጠንከራችን ነውና፣ ነገ በእኛ ላይ ላለመድረሱ ምንም ዋስትና እንደማይኖር ልብ ማለት ያስፈልጋል። ለጊዜው እንደ ህልውና የምንቆጥራቸው ትናንሽ ድሎች፣ ከቶም ለጠዋት ድምቀትና መታያነት ያገለግሉ እንደሆነ እንጂ ማምሻው ላይ በዋናው ሰዓት ከተጠያቂነት አያድኑም። “ቀርክህ ጠዋት ለብሶ ማታ ይራቆታል” እንደሚባለው መሆኑ ነው። መንግሥታዊው ፓርቲ በተቃዋሚ፣ ተቃዋሚው በመንግሥታዊ ፓርቲ ላይ ድክመቱን አያሻገረና እያጋባ ይኖራል። የራስን ሥራ የሌላው ሥራ አድርጎ ከወቀሳ ማምለጥ እንደ ዋና ኑሮ ተይዟል። የራስን ጥፋትና ወንጀል የሌላው አድርጎ፣ ሌላውን ማስገምገም ከቀን ቀን እየከፋ የመጣ የአገር በሽታ ሆኗል- እንደቆላ ቁስል አልድን ያለ እክል ነው! በወደቀው መንግሥት በተሸነፈው ፓርቲ፣ በተባረረው ሠራተኛና በተጣሉት ወገን ላይ ጥፋትን እያላከኩ መኖር  እጅግ ክፉ እርግማን ነው። ወላይታ ሲተርት “ወተት የጠጣ ውሻ ሰርዶ በበላ አህያ አፍ ይጠርጋል” የሚለውም ይሄንኑ ነው።

Read 1850 times