Thursday, 26 October 2023 05:07

ፍየል በግርግር እናቱን ይሰር፤ ‹‹የ፭ ግጥም ዕድሜ››

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(0 votes)

መንደርደሪያ፡- መሰንበት ደግ ነውና፣ የበድሉ ዋቅጅራ 12ኛ ድርሰት እጄ ገባ። ‹‹የ፭ ግጥም ዕድሜ›› በሚል ርዕስ ከ200 ገጾች የተውጣጣ፤ የስድስት (6) አጫጭር ትረካዎች መድበል ነው እንግዲህ። ሳነበው እንዲህ ሆነ….
ስለርዕሱና ሽፋኑ አጠር ያለች ሀሳብ ልበልና፣ ወደ ጉዳዬ ልከታለፍ፤ ርዕሱ ወካይ ሆኖ የቀረበው ከድርሰቱ ገላ አንድ ታሪክ ተመዞ ሲሆን፣ ከሽፋኑ በሚገባ የተሰናሰለ ይመስለኛል። ሆኖም፣ በአማርኛ ሰዋሰው የብዜት አመልካች (ኦች) በርዕሱ የመጀመሪያ ቃል ተካትቶ (‹‹ግጥሞች››) መሆን ሲገባው ተዟዙሮ ‹‹ግጥም›› ተብሎ ቀርቧል፤ ይኼ ተፋልሶ እንግዲህ ልጆቹን በቁጥር የማያውቃቸው አባት ዓይነት መገርገር ውስጥ ይከታል ብዬ አስባለሁ።
ደጋግሜ፣ ‹በድሉ ዋቅጅራ ግጥም እንጂ ዝርው አይቀናውም› የሚል ቅን አስተያየት መሰንዘሬ ዕሙን ነው፤ በድሉ በግሉ በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ቋንቋ ቀዳማይ፣ ሀሳብ ተከታይ መሆኑን የሚያምን መሆኑን አውቃለሁ፤ ከአንደበቱም ሰምቼአለሁ። ነገር ግን፣ በዚህ ድርሰት የቋንቋ አጣጣሉ ሳይቀር የቸከ ሆኖብኛል። በሥነ-ውበት ረገድ ወዙ የተጨመቀ ሳቅ ሆኖብኛል፤ ከተመጠጠ አገዳ የተውጣጣ ቋንቋ። ደራሲው ቋንቋን ተጠቅሞ እውነትን አይመረምርም፤ ጥሬ ቧልት ይሰፍራል እንጂ…  
….የማነበው ድርሰት እንደ እግር-ኳስ ሊያወናብደኝ ግድ ይለዋል። የእኔን ዕውነት በሌላ፣ በራሱ ዕውነት፣ አለያም ቀንድ ባወጣ ቅጥፈት በርዞና መርዞ ሊያወራክበኝ የቤት ሥራ አለበት። አጀማመሩን እንጂ ምን ብዬ እንደምጨርስ ፍንጭ ሊጠቁመኝ ቢዳዳው በተሃ ይሆንብኛል። በእግር-ኳስ ዓለም ሃያ ሁለት ሰዎች እሜዳ ዘልቀው አንዷን ኳስ ለመነረት ሲራኮቱ ብሎም ለቡድናቸው አቸናፊነት ሲተጉ ያለው የልብ መናጥ አጃዒብ ነው። ኳስ አጀማመሩ ላይ ያማረ ነው፤ እስኪያልቅ ደግሞ ያጓጓል። ብሎም፣ ከተጠናቀቀ በኋላ መልሶ ይናፍቃል። ‹የእግር-ኳስ ልክፍት› ቢባል ያግባባኛል። እንዲህ ዓይነቱ ልክፍት ድርሰትን ሊጣባ ይገባዋል። ከተነበበ በኋላ የሚረሳ፣ ወይም መደርደሪያ የሚያሞቅ መሆን የለበትም።
አቃቂር ቢመስልም፣ አንድ መጻሕፍ ካነበብኩ በኋላ እንዲሰማኝ የምሻው ስሜት የሕጻን ጡት እጦት፣ በበረኸ መሀል የጠብታ ናፍቆት፣ ወይም የሚወዷትን እንስት ከሌላ ጋር ማየት ዓይነት መብገንን፣ መብከንከንን እና መፋጨርን ነው። ነፍሲያዬ ቁስሏ ጠግጎ፣ ዕውነትን ለማጤን ያጎነቆለ ጥያቄዋ ጠውልጎ ድርሰቱን ላገባድደው አልፈቅድም - ክንፌ ረግቦ ኩምሽሽ እላለኋ! የዚህ ዓይነቱ ጽሑፍ ከድርሰትነት ይልቅ ነፍሳችንን ኩም አድርጎ ከዓላማችን የሚያናጥበን አፈ-ታሪክ፣ ወይም ተረት-ተረት መባል ይቀለዋል።
ብሎም፣ ለሚቆፍነኝ ብርድ ቡልኮ የሚያከናንበኝ ጽሑፍ ቃባዥዋ ነፍሴን አሞኝቶ እንቅልፍ ከመልቀቅ ውጭ ሌላ ፋይዳ አይፈይድላትም። ይልቅ ቡልኮዬን ገፍፎ ለብርድ የሚያጋልጠኝን፣ የአሳሽነት ስሜት የሚጥልብኝ ቢሆን ምኞቴ ነው።
እንሆኝ ማሳያ፡-
ገጽ [143] ላይ ‹‹የሞላ ‘ለት›› በሚል ርዕስ የሰፈረውን ታሪክ ማንሳት ተገቢ ነው፤ ታሪኩ የሚያጠነጥነው በአንዲት የልብ ታማሚ ላይ ሲሆን፤ የሚያክማት ሐኪም ቶሎ ባለመዳኗ ሰበብ የሚይዘውን ሲያጣ እናስተውላለን፤ እሷን ካልፈወሰ ሙያው እንደማይመጥነውና ሥራውን ለመተው እንደሚገደደ ይተርካል።
ነገር ግን ‹‹ልብ-ወለድ ነው›› ብሎ ባበቃ ቅጽበት ሐኪም አድርጎ የቀረጸውንና ‹‹መላ ካላፈላለኩ ሞቼ እገኛለሁ›› የሚሰኘውን ዶ/ር መኪናውን ሸጦ የሚያሳክምበት ቅርቃር ውስጥ ከተተው፤ በሞንታርቦ እየዞረ እርዳታ እንዲያሰባስብም አደረገው። በ‹‹ልብ-ወለድ›› ዓለም ከዚህ ውስጥ የቱ ነው መላው?! ማናችንንም ያንገሸገሸን ጭብጥም ሆነ የየለቱ ክስተት ይኼ አይደለምን? ደራሲው ልብ-ወለድ ብሎ በሰየመው መጻሕፉ፣ የገጸ-ባሕሪይውን (የዶ/ሩን) ዕጣ-ፈንታ በዚህ ልክ ማጨለም አልነበረበትም፤ ይልቅዬ አዲስ የልብ ሕክምና መድኀኒት አግኝቶ ታማሚዋን ሲፈውስ ማሳየት ነበረበት እንጂ በእየለቱ የምናከናውነውን ነገር መልሶ መናገር አልነበረበትም። ቆጭቶኛል።
ማጣቀሻ መጻሕፍት፡-
የዓለማየሁ ገላጋይ ‹‹ታለ/ በዕውነት ሥም››፣ ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› እና የፍሬ ዘር ‹‹ራስ››….፡፡ ሆኖም አንዳንድ ታሪኮች የተውጣጡት ከጥልቅ የንባብ ልምድ ቢሆንም በዲያሎግ አለያም በሌላ ቴክኒክ ጠንክረው አልቀረቡም፡፡ ይባስ ብሎ፣ ገጸ-ባሕሪያቱ የደራሲውን ሕልዮ የሚያስተጋቡ በቀቀኖች ናቸው፤ ማሳያ ቢባል፡- ‹‹የአምስት ግጥም ዕድሜ›› በተሰኘ ርዕስ፣ ገጣሚውን ገጸ-ባሕርይ መጥቀስ ተገቢ ነው፤ ትምህርትንና ሥነ-ግጥምን አስመልክቶ የሚጮኸው ጩኸት ተጠቃሽ ነው፤ ደራሲው በዚህ ልክ ሊያሰንፈው አይገባም ነበር፡፡ ሲበዛ ኢምፕሬሺኒስቲክ ሆነብኝ፤ ብሎም ሮማንቲሲዝም ተጫነው፤ የሆነው ሆኖ ፍዝ አልያ ዘጋቢ አተራረክን ወደ ጎን በመተው መተረክ ይችል ነበር። ይቆጫል!  
ሕጽናዊነት፡-
ደራሲው ሕጽናዊነትን ከአዳም ረታ ብዙነህ ተውሶ በገጽ 67 እና 183 ላይ የተነሱ ሀሳቦችን ያስተሳሰረ ይመስለኛል፡፡ ጥሩ ሙከራ ነው!!
#ቀጣዩ ነጥቤ ደራሲው ሕጸናት ገጸ-ባሕሪያትን ከአቅማቸው በላይ የሆነ የሥራ ድርሻ እንዲሸከሙ አድርጓቸዋል የሚል ነው፤ ማሳያ፤-
እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ፣ የሰው ልጅ በዕድሜው ልክ (ዕድሜው ከፍ እያለ በመጣ ቁጥር) አስተሳሰቡም/ግንዝቤውም እየሰፋ መሄዱን ነው። በዚህ ሀሳብ ዛቢያ፣ ስዊዘርላንዳዊው የሥነ-ልቡና ባለሙያ ጂን ፒያጄት (Jean Piaget) በማናችንም ዘንድ ማወቅ/መጠንቀቅ የሚባል ነገር ዕውን የሚሆነው የማገናዘብ/የማመዛዘን ዕድሜአችን ሲያድግ መሆኑን ይመሰክራል፤ እንዲህ ይከፋፍላልም፡- Four levels of cognitive development are explained: first, sensorimotor stage, begins with (0-2 years) and intelligence develops through sensory experiences and movement. Second, preoperational stage, starts from (2-6 years) and intelligence includes the use of symbols such as pictures and words to represent ideas and objects. Third, concrete operational stage, from (6-11 years) and cognitive development includes logic but requires physical examples to which the logic can be applied. Finally, formal operational stage, begins with (11+ years) and thinking includes abstract concepts. This allows analytical and logical thought without requiring references to concrete applications. And it is argued that learning occurs through adaptation to interactions with the environment. Disequilibrium (mental conflict which demands resolution) gives rise to Assimilation of a new experience which are added to existing knowledge, or Accommodation, which is modification of existing understanding to provide for the new experience. ታዲያ ‹‹ጨረር፣ ጥብቆና እግር›› (ገጽ 7 ላይ) ብንመለከት ተሞጣሟጭ ምዋት እናገኛለን፡፡ ከአቅም/ከዕድሜ በላይ የሆኑ ሀሳቦችን የተሸከሙ ሕጣናት አስተውዬአለሁ፡፡ እናም ከላይ ከተጠቀሰው ሀሳብ ጋር ይሳከራል፡፡ በሽቄአለሁ!!!
ሌጣነት፡-
ሌጣ የአተራረክ ይትባሐል በድርሰቱ ውስጥ አስተውዬአለሁ፡፡ አንድ ድርሰት በቴክኒኮች የታጨቀ መሆን እንዳለበት አምናለሁ፤ ነገር ግን ደራሲው በዚህ መጽሐፍ ‹ነጋሪ› እንጂ ‹ደራሲ› አልመስል ያለበትን፤ ሌጣ ታሪክ የመረገበትን አንድ ማሳያ ላስቃኛችሁ፡-
ገጽ 49 ‹‹የእድር ቁና›› ይሰኛል፤ አስመሳይ፣ አጭበርባሪ፣ አረብራቢ…. ዓይነት ሰዎችን ያስቃኘናል፡፡ በአጠቃላይ ደራሲው ሕይወትን በሥነ-ውበት የመፈከር ትልሙን ከምንም ሳያደርስ ቀርቷል፡፡ በግኜአለሁ!!
እንደመውጪያ፡-
ደራሲው፣ በተለያዩ ሥራዎቹ (በተለይ በሥነ-ግጥም ሥራው) ተነባቢ መሆኑን በሚገባ ያምናል፡፡ እኔም ከ‹‹እውነት ማለት የኔ ልጅ›› በተረፈ መድበሎቹ ጥዑም እንደሆኑ አልሽርም፡፡ ነገር ግን በዚህች ግርግር መሽሎክ የለበትም - በ‹እነበባለሁ› ተዐብዮ አይድረስ፤ አጫጭርም ሆነ ረጅም ልብ-ወለድ ሲደርስ ለቴክኒኮች ተገቢውን ትኩረት ይስጥ እላለሁ!!


Read 559 times