Thursday, 26 October 2023 05:17

“FATUM” (እጣ- ፈንታ)

Written by  - ሌሊሣ ግርማ -
Rate this item
(0 votes)

 “--የኦዲፐስ እጣ ፈንታ፣ የሚሆነው መሆኑ እንደማይቀር አምኖ ሳይሆን፣ አረጋግጦ የሚጠብቀው ይመስላል፡፡ እጣ ፈንታው ስለ ኦዲፐስ ያወቀውን ለደራሲው ሶፎክልስም አሳውቆታል፡፡ ፈጠራ አድርጎ እንዲያቀርበው፡፡ “ Art is a lie which reveals the truth-”
        

           ኦዲፐስ ኦሪታዊ የግሪክ ንጉስ እንደነበር የሚነግረን ሶፎክል ነው፡፡ የንጉሱ ታሪክ የውርደት ነው፡፡
አባቱን ገድሎ እናቱን ያገባል፡፡ ውርደት ስለመሆኑ የሚገለፀው መጀመሪያ ላይ አይደለም፡፡ መጀመሪያ ላይ፣ ንጉሱ ገና ልጅ ሳለ፣ መጨረሻ ላይ ስለሚመጣበት እርግማንና ውርደት እንደ ትንቢት ይነገረዋል፡፡ ይደርስብሃል ከተባለው ውርደት ለመሸሽ ገና በልጅነቱ ሀገሩን ጥሎ ይሰደዳል፡፡ ግን እጣ ፈንታን በስደት ማምለጥ አይቻልም፡፡ ንጉሱ ግን ይደርስብሃል ከተባለው ንግርት ለማምለጥ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ታሪኩን የበለጠ አሳዛኝ የሚያደርገውም ይሄ ሙከራው ነው፡፡ እጣ ፈንታ ግን በሙከራና ጥረት የመሆን አቅሙን አይነጠቅም፡፡ ስደት ጀምሮ በመንገድ ላይ ሳለ አንድ ሰው ይገጥመውና አንባጓሮ ያነሳበታል፡፡ ኦዲፐስ ሳይቀድመኝ ልቅደም ብሎ ጠላቱን ይገድለዋል፡፡ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ተጉዞ ወደ አንዲት ሀገር ይደርሳል፡፡ የደረሰበት ሀገር የተቀበለችው ንግስት ወደደችው፡፡ ባል ስላልነበራት ኦዲፐስ አገባት፡፡
አግብቶ ሲኖር ልጆችም ያፈራል፡፡ ሁለት ወንድ ልጆችና አንዲት ሴት፡፡ ሴቷ አንቲገን ተብላ የምትጠራ ናት፡፡ ወልዶና ከብዶ ሲኖር ሳለ ሲሸሸው የነበረው ንግርት እዛው የነገሰበት ቦታ ዞሮ መጥቶ አፈፍ ያደርገዋል፡፡
…ስደተኛ ሆኖ በመንገድ ሲንከራተት ተጣልቶ የገደለው ሰውዬ የራሱ አባት እንደነበረ ይሰማል፡፡ በደረሰበት ሀገር ሚስት አድርጎ ያገባት ንግስት ደግሞ እናቱ መሆኗን፡፡ ያፈራቸው የልጆቹ እናት በአንድ ላይ አያታቸውም ናት ለካ፡፡ እናቱን ደግሞ ሚስት አድርጎ ወስዷል፡፡
ሲፈራውና ሲሸሸው የነበረ ነገር ነው፡፡ ይሆናል የተባለው ንግርት ባልጠበቀው መንገድ ሆኖ ሲያገኘው ግን በፀጋ አልተቀበለውም፡፡ ሁለት አይኑን በራሱ እጅ ደንቁሎ  አጠፋ፡፡ በምድረ በዳ የሚንከራተት ሰው ሆነ፡፡ ይሄ የታሪኩ መጨረሻ ነው፡፡ ለንጉሱ ይሄ የታሪኩ መዝጊያ ነው፡፡
ግን እርግማን በአንድ ሰው ህይወት ታሪክ ላይ ብቻ የመገቻ ዳርቻውን አያገኝም፡፡ ወደ ትውልድም ይቀጥላል፡፡ አንዳንዶች እርግማን እስከ አራት ትውልድ ይቀጥላል ይላሉ፡፡ ሌሎች ከዛም የከፋ ርቀት ይጓዛል ባይ ናቸው፡፡ ዞሮ የተነሳበት ቦታ ላይ ቢመለስ እንኳን በጉዞው ወቅት የሚያደርሰው ጉዳት ተመልሶ ሲመጣ፣ የሚቆምበትን ቦታ ሁሉ አጥፍቶ ሊሆን እንደሚችል ይተነብያሉ፡፡
የንጉስ ኤዲፐስ ታሪክ ማጠፊያ የሌለው በር ነው፡፡ እንደ ግድግዳ፡፡ በር ይመስላል ግን ዞሮ ዞሮ ግንብ ነው፡፡ ከግንቡ ጋር ሳይጋጭ ማምለጥ የሚችለው  ህልመኛ ወይንም “የቢሆን ኖሮ” የምኞት አቅም ያለው ብቻ ነው፡፡ ተጨባጩ ያበጠው መፈንዳቱ ነው፡፡ ከእጣ ፈንታው ያመለጠ ማንም እንደሌለ ማስረገጡ፡፡ የታሪኩ ጭብጥ ይሄ ብቻ ነው፡፡
በአይኑ እያየ የፈፀመውን ታሪክ ማመንና መቀበል ስላልቻለ… አይኑን አጥፍቶ መቀመጥን መረጠ፡፡ ከዚህ ጥንታዊ ታሪክ የሚገኘው ጭብጥ ሁሌም ያወዛግባል፡፡ ሁሉም በህይወት ላይ ለመኖር አቅም ተሰጥቶት የተንከባለለ ሁሉ የእጣ ፈንታው እንቆቅልሽ እስኪገለጥ ድረስ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ የተቻለውን ያህል ርቀት በመሰለው ጎዳና ይጓዛል፡፡ የተነገረበትን እጣ ፈንታ አውቆም ሆነ ሳያውቅ፡፡ ልክ ነው ብሎ የሚያምነውን ይዞ በውልደትና ሞት መሃል እውቀትና እድገትን እንደ ማያያዣ አድርጎ መኖር ይቀጥላል፡፡ የሚቀጥለው አስቀድሞ የተወሰነበትን ለመሆን ቢሆንም እንኳን፡፡
የኦዲፐስ ታሪክ የማይሆን ተስፋን የሚመግብ ሳይሆን፣ እንዲያውም ተስፋ የደንቆሮዎች መፅናኛ መሆኑን የሚያመለክት ታሪክ ነው፡፡ ግን እንደዚህ ያለ ድፍን የእጣፈንታ ውስንነት ይዞ ማንም በህይወት መቀጠል አይችልም፡፡
“ምንም ማድረግ አይቻልም” ብሎ ከደመደሙ በኋላ መኖር መቀጠል ይከብዳል፡፡ ስለማይቻል፣ የኤዲፐስን ታሪክ በተለያየ አንፃር የመተርጎሚያ፣ እንቆቅልሽ መፍቻ፣ የመፍትሄ ጮራ አመላካች አንፃራዊ መተርጎሚያ ከውስጡ ማስፈትለክ ግድ ይሆናል፡፡
በእርግጥም፤ የትኛውም በሽታ ከበሽተኛው ጋር እስካለ ድረስ እንደ እርግማን ነው፡፡ በሽተኛው፤ አንድም፣ በህይወት እያለ ከበሽታው ጋር ይለያይና ጤነኛ ይባላል፡፡ ወይንም፣ በሽታው በታማሚው ላይ ጠንክሮ የእድሜ ዘመኑን ያሳጥርበታል፡፡ ለሞት እንጂ ለጤና አሳልፌ አልሰጠውም… ብሎ የጭካኔ እጁን ሳያላላ አቅበዝብዞ ይገድለዋል፡፡
የኤዲፐስ ሁለተኛው ነው፡፡ በሽታው እጣ ፈንታው ነው፡፡ የትም ሀገር በመሸሽ በምድር ላይ እስካለ ድረስ… ሽሽቱ መልሶ የሚጥለው በእናቱ ጉያ ነው፡፡ ማለትም በሚስቱ፡፡ መንገድ ላይ ጠብቆ የሚጣላው ሰው አባቱ መሆኑን ተጠንቅቆ ጠብቆ ቢነቃበት እንኳን ነፍስ ከማጥፋት የሚያስጥለው የለም፡፡ እጣ ፋንታው አስቀድሞ ጨዋውን ሰውዬ ነፍሰ ገዳይ አድርጎታል፡፡በደረሰበት ሀገር የወደዳት ሴትና ለማግባት ያጫት ዞሮ ዞሮ ንግስትና እናቱ መሆኗ አይቀርም፡፡ እሱ ራሱም የንጉስ ልጅ መሆኑን ባይፈልገው እንኳን ወደ ዙፋን እንዲያማትር ያደርገዋል፡፡ ያገባት ሴት ሌላም ሆና ቢሆን ኖሮ የግድ ንግርቱ መፈፀም ስላለበት ወደ እናቱ ትቀየራለች፡፡
በእድሜ ከእሱ ያነሰች መሆኗን አስመርምሮ፣ ከእሱ ጋር የደም ዝምድና እንደሌላት አረጋግጦ ቢያገባት እንኳን… ዞሮ ዞሮ እሱ ኦዲፐስ እስከሆነ ድረስ ያገባት ማንኛዋም ሴት ታሪኩ ሲጠናቀቅ እናቱ መሆኗ አይቀርም፤ እሱም በሆነበት መደንገጡ፤ በድርጊቱ አፍሮ አይኑን ማጥፋቱ አይቀርም… እንደማለት ነው፡፡ሌላው የደራሲው ስራ ነው፡፡ ደራሲው ሶፎክለስ ነው፡፡ በኤዲፐስ ታሪክ ሊነግረን የፈለገው ነጥብ “ማንኛችንም ከተፃፈልን የእጣ ፈንታ ንግርት ወይንም እስራት ንግርቱ እስካልተፈፀመ ድረስ ልንፈታ አንችልም” የሚለውን ነው፡፡
እንደዛ ቢሆን ነው እንጂ…እንዴት ሰው የገዛ አባቱን መንገድ ላይ አግኝቶ ሲገድል አያውቅም?!( ወይንም በወቅታዊው አለም እንዴት ሰው በመልክም በቋንቋም የሚመስለውን የሀገሩን ልጅ ገሎ ጠላት ገደልኩ ይላል? እንደማለት)
…በህይወቱ አባቱን ቢያንስ በአይነ ስጋ አይቶ የሚያውቅ ልጅ ይቅርና … አባት እንዳለው ሰምቶ የማያውቅ እንኳን ቢሆን…. በእድሜ እሱን ለመውለድ የደረሰ ወንድ ባየ ቁጥር “አባቴ ይሆን እንዴ?” ብሎ ሳይጠራጠር ዝም ብሎ አያልፍም፡፡ ሊሆን የሚችልበትን አጋጣሚ አስፍቶ “አይሆንም” የሚለውን እርግጠኝነቱን ያጠባል፡፡
የኤዲፐስ አባት የእጣ ፈንታውን ብሉ ፕሪንት ተከትሎ… የገዛ ልጁ እንዲገድለው ተመቻችቶ… ሞቷን በመናፈቅ ሆን ብላ የድመት አፍንጫ የምታሸተውን አይጥ መስሎ መጣ፡፡ መጥቶ እንደ እስክሪፕቱ ሞተ፡፡ …ኤዲፐስ በቀጣይ ባል የሌላት ንግስት ፈልጎ ማግባት ብቻ ነው የሚቀረው፡፡ እናት ግን እንዴት ልጇን ረሳች? ያውም በመልክ እሷን የሚመስል? የማይመስል ታሪክ የሚፅፈው ሶፎክልስ የተባለው የትራጀዲ ደራሲ ነው እንዴ ታዲያ? …. የማይመስል ከሆነ እንዴት ሁለት ሺ ስድስት መቶ አመት ታሪኩ እንደ ሽብልቅ የስነልቦናችንን ማዕከል ሰንጥቆት ተቀመጠ፡፡ ከዚህ ታሪክ ጋር የህይወት ዘመናችንን መፍጀት የሰው ልጆች እጣ ፈንታ ሳይሆን አልቀረም፡፡… እኛ መሃል የከረመው በእርግጥም እኛን ስለሚመስልና ስለሚገልፀን ነው፡፡
ንግስቲቱ ተቀምጣ ስትጠብቅ እንኳን  ኦዲፐስ አልጠረጠረም፡፡ አይን አለው እንጂ ማየት ግን አይችልም፡፡ እንዳይችል አድርጎ የተፃፈለት የእጣ ፈንታ ብሉ ፕሪንት አውሮታል፡፡ ኤዲፐስ አይኑን ደንቁሎ ማጥፋቱ ለታሪኩ አድማጭ የባሰ አሳዛኝ አድርጎ ለማቅረብ የሚጠቅም ይመስለኛል፤ የታሪኩን እውነት ከመደገፍ የበለጠ፡፡አይኑን ደንቁሎ አጠፋውም አላጠፋውም…ድሮውኑ ኦዲፐስ አይን አልነበረውም፡፡ በራሱ አይን ስላልነበረ የሚያየው… በሚያይበትም ጊዜ እንደጠፋ ይቆጠራል፡፡ ከእጣ ፈንታው ግድግዳ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ለመጋጨት እንዲችል የሚመራው እንጂ የራሱ አይደለም፡፡ አልነበረም፡፡ በንግርት ያደርጋል የተባለውን አስነዋሪ ተግባር ለማከናወን እንዲችል የሚመራው አይን፣ እንደ ሞባይል ካሜራ አይን የመሰለ ነው፡፡ በህይወቱ ላይ እጣ ፈንታውን የቀረፀበትን እጅ ምርጫና ምሪት የሚከተል ነው (የስልኩን አምራች!!!)፡፡ እየተከተለ የሚያመራው ደግሞ ወደሚወድቅበት ገደል ነው፡፡ የኦዲፐስ ገድል… ገደልን ሸሽቶ በሽሽቱ መጨረሻ እዛው ገደል ገብቶ መሞትን የሚተርክ ነው፡፡
ኦዲፐስ ተጠያቂ አይደለም፡፡ ለኦዲፐስ እጣ ፈንታ ተጠያቂው ሶፎክልስ ነው፡፡ ግን እንዳልኩት ስለ ኦዲፐስ መከራ የሰው ልጅ አዕምሮ ሊረሳ ያልቻለው( ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊኒየም በኋላም)፣ ከራሱ የእጣ ፈንታ እስራት  ጋር ስለሚመሳሰልበት ነው፡፡
ህፃናት ከልጅነታቸው “ተጠንቀቁ” ተብለው ከተመከሩት ነገር ሲያመልጡ አይታይም፡፡ “እንዳይደርስባችሁ” ተብለው እንዲፈሩት የተደረገው ነገር፣ እየፈሩትም ቢሆን ሲያገኛቸው ነው የታየው፡፡ ለምሳሌ ልጃገረዶች “እንደዚህ አይነት ወንድ እንዳትወጂ” ተብለው በማስጠንቀቂያ ሲመከሩ ያድጋሉ፡፡ ማስጠንቀቂያ ሰጭዎቹ ከራሳቸው ተሞክሮና መከራ በመነሳት ነው ምክራቸውን የሚለግሱት፡፡ የሚለግሱት ለሴት ልጆቻቸው ነው እንበል፡፡ … ታዲያ የሴት ልጆቻቸው የማን ልጆች ሆነው የማንን ምክር ይሰማሉ?.... አራት ትውልድ የሚከታተል እርግማን እድሜውን የሚያረዝመው እንደዚህ እያለ ሊሆን ይችላል፡፡
የተወለዱ ሁሉ ውልደታቸው ከእጣ ፈንታቸው ጋር ነው፡፡ ሲጎረምሱ የጉርምስና እጣ ፈንታና ፈተና ሰለባ መሆናቸው ብዙውን ጊዜ አይቀርም፡፡
 ሞት የእጣ ፈንታቸው የማይቀር መዝጊያ መሆኑን እያወቁም እንደማሞቱ አይነት ህልማቸውን እስከ ዘላለም ለጥጠው የሚኖሩ ይመስላሉ፡፡ ምርጫ ያላቸው መስለው ሲመፃደቁ በእውቀትና በምኞታቸው ስልጣን ነግሰው ያሉ ይመስላሉ፡፡  አንዳንዴ በፍቃዳቸው እስከመረጡ ድረስ ራሳቸውን ከሌላ አባትና እናት መርጠው ማፍራት የሚችሉ ሁሉ ያስመስላቸዋል፡፡ ኤዲፐስም እንደዛ መስሎት እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ንግርቱን ለመሸሽ የተቻለውን ያህል ተፍጨርጭሯል፡፡ ሀገሩን ጥሎ ተሰዷል፡፡ በእጣ ፈንታው ላይ አስቀድሞ የነቃና በነቃበት ላይ ደግሞ መፍትሄ ስራዩን ለመቀመም የተዘጋጀ ይመስል ነበር፡፡ ብዙ መንገድ መፍትሄ ነው ያለውን ለመቀመም ሳይሄድም አልቀረም፡፡ እጣ ፈንታው ግን ያሰመረውን መስመር ሳያደበዝዝ እስኪመጣ ይጠብቀው ነበር፡፡ የኦዲፐስ እጣ ፈንታ፣ የሚሆነው መሆኑ እንደማይቀር አምኖ ሳይሆን፣ አረጋግጦ የሚጠብቀው ይመስላል፡፡ እጣ ፈንታው ስለ ኦዲፐስ ያወቀውን ለደራሲው ሶፎክልስም አሳውቆታል፡፡ ፈጠራ አድርጎ እንዲያቀርበው፡፡ “ Art is a lie which reveals the truth “

Read 234 times