የፅንስ አቀማመጥ ከልጅ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው። የሽንት ውሀ ብዙ በሚሆንበት ወቅት ፅንስ በደንብ ይንቀሳቀሳል። ጤናማ የሆነ ፅንስ እንቅስቃሴ ይኖረዋል። የፅንስ አቀማመጥ በእርግዝና 9 ወራት ውስጥ የተለያየ ሊሆን ይችላል። በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ፍላጎት ታደሰ እንደተናገሩት የፅንስ አቀማመጥ ሁኔታ ላይ በይበልጥ ክትትል የሚደረገው ከ36 ሳምንት የእርግዝና ወቅት በኋላ ነው። እንደ የህክምና ባለሙያዋ ንግግር ከ36 ሳምንት በፊት ባለው የእርግዝና ወቅት የፅንስ አቀማመጥ መለዋወጥ (መንቀሳቀስ) በወሊድ ወቅት የሚፈጥረው ተፅእኖ አይኖርም። ከ36 የእርግዝና ሳምንት በኋላ ፅንሱ ከፍተኛ እድገት ይኖረዋል። እንዲሁም በተፈጥሮ የውሀ ሽንት መጠን ይቀንሳል። ስለሆነም ከዚህ ቀደም አቀማመጡ ያልተስተካከለ ፅንስ ከዚህ የእርግዝና ወቅት በኋላ በተፈጥሮ የመስተካከል እድሉ አነስተኛ ነው።
በወሊድ ወቅት የሚኖር የፅንስ አቀማመጥ አይነቶች
በጭንቅላት ወደ ማህፀን በር መምጣት; ይህ የፅንስ አቀማመጥ ትክክለኛ ወይም ተመራጭ ነው። ከዚህ የፅንስ አቀማመጥ ውጪ ያሉ የፅንስ አቀማመጦች ትክክል (ተመራጭ) ያልሆኑ ናቸው።
ትክክለኛ ያልሆኑ የፅንስ አቀማመጦች;
መቀመጫ ወይም እግር አስቀድሞ መምጣት
ወደ ጎን የተቀመጠ ፅንስ (ትከሻ ወይም እጅ አስቀድሞ ወደ ማህፀን በር መምጣት)
ወደ ማህፀን በር በግንባር ወይም በፊት መምጣት
ጭንቅላት እና እጅ አስቀድሞ መምጣት
እትብት ቀድሞ መምጣት
የፅንስ አቀማመጥ የተስተካከለ እንዳይሆን የሚያደርጉ አጋላጭ ሁኔታዎች (ምክንያቶች)
ከዚህ ቀደም በነበረ እርግዝና ላይ የፅንስ አቀማመጥ ችግር አጋጥሞ ከነበረ
1, ከእናት ጋር የተያያዙ ችግሮች
በተፈጥሮ የማህፀን መጥበብ (ከአጥንት ጋር የተያያዘ ችግር); የፀሀይ ብርሀን ባለማግኘት የሚመጣ የአጥንት ችግር፣ የአጥንት ስብራት እና መሳሳት የማህፀን መጥበብ ሊያስከትል ይችላል። እንዲሁም በተፈጥሮ የማህፀን መጥበብ ካለ የፅንስ አቀማመጥ እና አወላለድ ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል።
የማህፀን እጢዎች
ብዙ ልጆች መውለድ; በይበልጥ 5 እና ከዛ በላይ በወለዱ ሴቶች ላይ የአቀማመጥ ችግር የማጋጠም እድል ይጨምራል።
2, ከፅንስ ጋር የተያያዙ ችግሮች
ከመውለጃ ጊዜ (ከ36 ሳምንት በፊት) አስቀድሞ ምጥ መምጣት
የፅንሱ ጭንቅላት ላይ የአፈጣጠር ችግር መኖር
መንታ (ሁለት እና ከዛ በላይ) ፅንስ መሆን
3, ከእንግዴ ልጅ እና ከውሀ ሽንት ጋር የተያያዙ ችግሮች
የእንግዴ ልጅ በቦታው አለመሆን
የውሀ ሽንት መብዛት ወይም ማነስ; የውሀ ሽንት መብዛት ከሚፈለገው በላይ የፅንስ እንቅስቃሴ እንዲለዋወጥ(እንዲቀያየር) የሚያደርግ ሲሆን የውሀ ሽንት ማነስ ደግሞ ልጅ እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ የፅንስ አቀማመጥ የተስተካከለ እንዳይሆን ያደርጋል። የውሀ ሽንት እንዲበዛ የሚያደርጉት የስኳር መጠን፣ አንጀት አከባቢ ያለ የአፈጣጠር ችግር እና ከዘረ መል ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው። የውሀ ሽንት ማነስ የፅንሱ የኩላሊት እና የሽንት ፊኛ ላይ ችግር ሲኖር እንዲሁም እናት ላይ የደም ግፊት እና የኩላሊት ህመም ሲኖር የሚከሰት ነው። ይህም የእንግዴ ልጅ በቂ ደም እንዳያደርስ ስለሚያደርግ ነው ፅንሱ(ልጅ) ሽንት ማነስ የሚያጋጥው። በተጨማሪም የፅንስ እድገት የተስተካከለ አለመሆን (ከሚፈለገው የክብደት መጠን በታች መሆን) የፅንስ አቀማመጥ ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል።
የፅንስ አቀማመጥ ችግር የሚያስከትሉ አጋላጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም ምክንያቶቹ ግን ሙሉ በሙሉ የሚታወቁ አለመሆናቸውን ዶ/ር ፍላጎት ታደሰ ተናግረዋል። እንዲሁም የአቀማመጥ ችግር መኖሩን የሚያመላክቱ ምልክቶች የሚስተዋሉ አይደሉም። ነገር ግን “አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ እናቶች ጭንቅላት ቀድሞ የሚመጣ ከሆነ ጭንቅላት ያለበት አከባቢ የመጨነቅ ሁኔታ ይኖራቸዋል። እናም አንዳንድ እናቶች ምልክቱን (ችግር መኖሩን) ያውቃሉ” በማለት ተናግረዋል ዶ/ር ፍላጎት ታደሰ።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ21 በመቶ በላይ የሚሆኑ ልጆች የሚወለዱት በቀዶ ጥገና አማካኝነት ነው። ለቀዶ ጥገና መደረግ ምክንያት ከሚሆኑ ሁኔታዎች መካከል ፅንስ በወሊድ ወቅት ያለው አቀማመጥ ይጠቀሳል። ለወሊድ በተቃረበች አንዲት እናት ላይ ምርመራ መደረግ እና መታወቅ ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የፅንስ አቀማመጥ ነው።
የፅንስ አቀማመጥ በጎን በኩል ከሆነ እና በወሊድ ወቅት እትብት ቀድሞ ከመጣ ልጅ በቀዶ ህክምና እንዲወለድ ይደረጋል። ነገር ግን በመቀመጫ፣ በፊት እና በግንባር በኩል ወደ ማህፀን በር የመጣ ፅንስ በምጥ እንዲወለድ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል። ለምሳሌ በእግር ወይም በመቀመጫው በኩል ለመጣ ፅንስ የህክምና ባለሙያው እጆቹን በመጠቀም አቀማመጡ እንዲስተካከል ያደርጋል። ነገር ግን ይህ የህክምና አገልግሎት የሚሰጠው የፅንሱ ክብደት ከ3.5 ኪ.ግ በታች ከሆነ እና የእናት ማህፀን ጠባብ ካልሆነ ነው። አቀማመጡ ያልተስተካከለ ፅንስ በቀዶ ጥገና አማካኝነት እንዲወለድ ይደረጋል። “እንደ ፅንሱ አቀማመጥ ሁኔታ የሚጠበቁ ችግሮች ይኖራሉ። ነገር ግን በቀዶ ጥገና መወለድ የማይቻል የፅንስ የአቀማመጥ ችግር የለም” በማለት ዶ/ር ፍላጎት ታደሰ ተናግረዋል። በዩኒሴፍ መረጃ መሰረት መከላከል በሚቻልበት ችግር(መንስኤ) ምክንያት 2.8 ሚሊዮን እናቶች እና ህፃናት በየዓመቱ ህይወታቸውን ያጣሉ። በቤት ውስጥ የሚወለዱ ህፃናት በሆስፒታል ከሚወለዱት ህጻናት በእጥፍ ህይወታቸውን የማጣት ሁኔታ አላቸው። ፅንስ ያለውን አቀማመጥ ሳያውቁ መውለድም ለሞት እና ለሌሌች ችግሮች ይዳርጋል።
በወሊድ ወቅት ትክክለኛ ያልሆነ የፅንስ አቀማመጥ መኖር የሚያስከትለው ችግር
የማህፀን መተርተር
ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ
የምጥ ጊዜ እንዲረዝም ማድረግ; የተራዘመ ምጥ ለማህፀን ኢንፌክሽ ሲያጋልጥ ኢንፎክሽን ደግሞ ካልታከመ ወደ ሰውነት ሊሰራጭ እና ሞት ሊያስከትል ይችላል። እንዲሁም የተራዘመ ምጥ ማህፀን እንዲተረተር በማድረግ ለደም መፍሰስ እና ሞት ሊያግልጥ ይችላል።
የፅንስ መታፈን
ፅንስ ላይ ከኢንፌክሽን ጋር የተያያዙ ችግሮች
የህፃናት እና የእናቶች ሞት
የተወለደ ልጅ ላይ ፈጣን እድገት አለመኖር; ከሌሎች ልጆች ጋር ሲነፃፀር በትምህርት እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ፈጣን(ንቁ) ያለመሆን ሁኔታ ሊያስከትል ይችላል።
የፅንስ አቀማመጥ ችግርን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲደረጉ የሚመከሩ ጉዳዮች የሉም። እንደ የህክምና ባለሙያዋ ንግግር የፅንስ አቀማመጥ ችግርን ሳይሆን በአቀማመጡ ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶችን ነው አስቀድሞ መከላከል የሚቻለው። ስለሆነም ትክክለኛ ባልሆነ የፅንስ አቀማመጥ ምክንያት በእናቶች እና ህፃናት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የህክምና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። እናቶች የቅድመ ወሊድ የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ፍላጎት ታደሰ መልዕክት አስተላልፈዋል።