Saturday, 28 October 2023 20:00

የ ‘ረገጣ ዘመን’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
[አንድ የድሮ ፌዝ አለች። ሴቶቹ ማታ ሲለያዩ አንደኛዋ “ጧት ስንት ሰዓት ነው ቤተስኪያን የምንገናኘው?” ስትል ሌላኛዋ “እንግዲህ ባሎቻችን እንዴት እንዳሳደሩን አይተን ነዋ!” አለች አሉ። የድሮ ሰው ነገር ያውቅበታል።  እኛ እኛ ነን ለዛችን የቸከከው።]  
እኔ የምለው… እንዲያው እንዲህ ዓይነት የዘመን ጠማማ ምን ትሉታላችሁ? በቃ እኮ… ግራ ግብት ነው የሚያደርገው። ብቻ ምን ዋጋ አለው… እንዲሁ ሲገርማችሁ ይኑር ሲለን ነው እንጂ!


ስሙኝማ… መቼም ውሸት ሲለመድ ክፉ ነው። በቃ ‘ሆቢ’ ነው። የሚሆነው። [በጣም የሚያስቀኝ ነገር  አለላችሁ። ባሕርና ሀይቅ ዳርቻ ሊደርስ ቀርቶ በቀበና በኩል አልፎ የማያውቅ ሁሉ… በሆነ አጋጣሚ “በትርፍ ጊዜህ ምን ትሰራለህ?” ሲሉት “ሆቢዬ ውሃ ዋና ነው” ይላል። በቃ… እንደሳቅን ቁጠሩት። እስቲ አንድ ቀን ማለዳ ግንፍሌ ብቅ ብዬ  ስንት ሰው ‘የዋና ሆቢ’ እንዳለው አያለሁ።] እና ውሸት የለመደበት… ሁሉ ነገሩ ውሸት ነው። አገር አገር የሚያክለውን ውሸት አናት በአናት ሲከምረው… ያዝ እንኳን አያደርገውም። የጥንት አራዶች ውሸት ሲበዛባቸው “ረገጥክ” ይላሉ። ወይ ውሸቱ አልቆም ሲላቸው “ወራጅ አለ…” ይሉ ነበር። [ዘንድሮ “ወራጅ አለ…” ሳይሉት አካልቦ የማያወርድ የወያላ መዓት አፍስሶብን…] ውሸት የለመደበትን “ምህረቱን ይላክልህ…” ማለት እንጂ ምን ይደረጋል።
ስሙኝማ… አስቸጋሪው ምን መሰላችሁ? የግዳጅ ውሸት። መቼም ለይሉኝታ እኛን አበሾቹን የሚያክል የለም። በቃ… አለ አይደል… ሌላውን ላለማስቀየም “የሆዴን በሆዴ…” ብለን ፍጥጥ ብለን ውሸታችንን እንተረትረዋለን።


መቼም ቅዳሜ የጨዋታ ቀንም አይደል… እስቲ እንጨዋወት። እንበል ለምሳሌ አንዱ ጓደኛዎ… በቃ ወደፊት ባለቤቴ ምናምን የሚላት ትኖራለች። በቃ ለእሱ ክሌኦፓትራ፣ ዴዝዴሞና፣ ጁሊየት፣ ፊያሜታ… የሁሉም ቅልቅል ነች። እና በቃ ጉራውን በስሙኒ ስድስት ይነዛብዎታል። “ስማ እኔ… እ!... እንደሌላው ከውድድር ‘ዲስኳሊፋይድ’ የሆነችውን አልሰበስብም።… ብታያት’ኮ… በቃ ክሬዚ ነው የምትሆነው። እንዴት አይነት እግዜር እጁን ታጥቦ የሰራት መሰለችህ…” ይላል።
[እኔ የምለው… እግዜር እጁን ሲታጠብ ውሃ ያቀረበለት አለ- የእውነት። ታዲያ እኛ እኛንና እነ እንትናን የፈጠረ ጊዜ ውሃ ጠፍቶ ነበር ማለት ነዋ!]
መቼም እኮ እንደወደደ ሰው አሪፍ ልብ-ወለድ ፀሐፊ አይኖርም-የምር። መቼም እንናገር ሆኖብን ነው እንጂ… ብሪቲሽ ካውንስልን የሚሞላ ታሪክ አለ! (እስቲ እንዲህ የልብ ወለድ መጽሐፍ በጠፋበት እናንተ በ‘ላቭ ክሬዚ’ የሆናችሁ ጣል አድርጉብን።)
እና እርስዎ የጓደኛዎን ጉድ አያለሁ ብለው “ታዲያ ለምን አታሳየኝም?” ይሉታል። ለነገሩ ትንሽም እኮ ቅናት (‘ቅ’ ነው የሚሏት) አትጠፋም። በሆድዎ ስንቱን ያወርዱበታል። “አሁን ይሄን የመሰለ የስፒል ጫፍ የሚያክል ሰውዬ ቆንጆ ሊያገኝ!” ይላሉ በሆድዎ። “ለራሱ ከባቄላ አቁማዳ ያመለጠ ጥሬ የሚያክል!”
ታዲያ አንድ የሆነ ቀን ጓደኛዎ ከሆነች ሰው ያስተዋውቅዎታል። በቃ… አለ አይደል- ዝም ብሎ ነገር። (ከአፍ እላፊ ይጠብቀን…) በነገራችን ላይ አንዳንዴ “ተዋወቀው” ወይም “ተዋወቂው” ሲባል “እምቢ!” ማለት ቢቻል ጥሩ ነው። አሀ… አለቅን እኮ! ማታ በቴሌቪዥን የሆነ ጽዳት ዘመቻ ላይ ባሬላ ሲገፋ የታየው ሁሉ “ተዋወቀው” ሲባል… በቃ ቀላል ይሸልላል መሰላችሁ! እኔ የምለው አንዳንድ በሆነ ነገር ሰው ያውቀናል የሚሉ ሰዎች… እንዴት እንዴት ነው የሚሆኑት። የሆነ የካዛንቺስ ቡና ቤት ውስጥ አንዱ ጠጪ ላይ “እንዴት እኔን አታውቀኝም!” ሲል የደነፋ ዘፋኝ ያገኘውን መልስ ታውቃላችሁ? “ምንድነህ… ኳስ ተጫዋች?”
እና… በቃ ያቺ የተዋወቋት ሰው እንደሄደች ጓደኛዎ እንደ ማይክ ታይሰን ደረቱን ነፍቶ፣ እንደ ቢል ኮስቢ እየሳቀ፣ እንደ ሪኪ ማርቲን እየተውረገረገ፤ “ታዲያ… አየሀት አይደል!” ይልዎታል። ደንገጥ ይላሉ። “ሰውዬው ሳይነጋ የጎጃም በረንዳን ዳግም አረቄ ጨልጦ ነው እንዴ የመጣው? ይላሉ- በሆድዎ።
“ማንን...? “ ይሉታል። በቃ… ብሽቅ ነው የሚለው።
“ያቺ ያልኩህን ነዋ… አሁን ያስተዋወቅሁህ።”
‘የዲማው ጊዮርጊስ’ የሚለው ማን ነበር? በቃ… ክው ይላሉ። ‘ጉድ!’ ያሰኘችው ውብ ይቺ ኖራለች እንዴ!... ቅናትዎ ሁሉ ይለቅዎታል። ግን ምን ዓይነት መልስ ነው የሚሰጡት? አበሽነትዎ ታስጠነቅቅዎታለች። ‘አጉል ሀቀኛ እሆናለሁ ብለህ ወዳጅ እንዳታጣ!’ ትልዎታለች።
ዘንድሮ ሃቅ ያለው የድራፍት ሂሳብ ላይ ብቻ ነው- እነሱም ትንሽ አይተው፣ እኛም አሳልፈን አንሰጥ። በቃ እርሶም ይረግጡታላ- አሳምረው። “አንተ!” ይሉታል። “ጉደኛ አይደለችም እንዴ? እድለኛ ነህ… ለመሆኑ እንዴት ነው የሚሳካልህ?” በቃ ምን አለፋዎት በደስታ ይፍነከነካል።
“እኔ ያንተ ወንድም… እኔ ነኝ የምትል አታቅተኝም! [አንዲት በጋዜጠኞች ላይ የተቧለተች ነገር ትዝ አለችኝ። መቼም ለእኛ የማይበረታ የለም።
ነገርዬዋን አጫውቻችሁ ከሆነ ‘ቢስ’ እንዳላችሁ ተቆጥሮ ልደግምላችሁ። ጋዜጠኛው ድምጽ ማጉያውን ወደ ተጠያቂው እያስጠጋ፤ “የወንድሜን ስም ማን ልበል?” ይለዋል። ሰውዬውም በሆዱ ‘እነኚህን ቱልቱላ ጋዜጠኞች አገኘኋቸው’ ብሎ ነው መሰለኝ፤ “የወንድምህን ስም ራስህ እወቅ እንጂ እኔ የት አውቅልሃለሁ” አለው አሉ። ]
እና በቃ ጓደኛዎን ላለማስቀየም ግጥም አድርገው ‘ይረግጣሉ’። በቃ ሙገሳውን ያዥጎደጉዱታል። እንደውም የአማርኛው ቃል ስለማይበቃዎ  ‘ፋንታስቲክ’ ምናምን እያሉ የማያውቁትንም ቋንቋ ይደበላልቁታል።
ስሙኝማ… እዚህ እኛ እንጽፋለን የምንል ሰዎች አካባቢም ስንት አበሳ አለ መሰላችሁ! መቼም ለሰው ያሳዩት ነገር ሸጋ ነው። ታዲያ እኛም አልፎ አልፎ ጽሁፍ እይልኝ እዩልኝ መባባላችን አልቀረም። እና ታዲያ የሆነ ሰው ጽሁፍ ይዞ ይመጣና “እስቲ ይቺን አየት አድርግልኝ…” ይልዎታል። የምር ጭንቅ ነው። አማረብኝ ብለው የአንጀትዎን “ጽሑፍህ የሚጎድሉት ነገሮች አሉት…” ካሉ ወዳጅ አጡ ማለት ነው። አይገርምም?!
እና… በቃ ፊት ለፊት ወገቡን ይዞ ‘ኬሬዳሽ’ እያለ ባይሸልልብዎ ለሌሎች ስምዎን በቃ… አይደለም ክትፎና ጎረድ ጎረድ፣ እንደተፈጨ ሹሮ እህል ብን ያደርግዎታል። [ “አንተ በቃ ስለምግብ ሳታነሳ አታልፍም” ያላችሁኝ ወዳጆቼ ግን ልክ አይደላችሁም… በነገራችን ላይ ዛሬ ምሳ ይመቻችኋል?]
“የእኛ ፀሐፊ” ይልዎታል። እሱ ደግሞ ብይ እንኳ ስንጫወት ሰው ሲበላ ደስ አይለውም ነበር።… አይደለም መታወቂያ፣ ፓስፖርት ያለው ምቀኛ ነው። እስቲ ሰው ደግ በሰራ ይሄ ሁሉ! ሌላውም እንዲሁ አይደለም ለአምስት ለአስር ዓመት መርሀ ግብር የሚያበቃዎትን ይሰጥዎታል።
“ይሄ አጭበርባሪ አላውቀውምና ነው። እሱ እኮ መጻፍ ቢችል ጥሩ። ከየመጽሐፉ እያገለበጠ አይደለም ስሙን እየለጠፈ የሚያወጣው!” እና… ልጄ ዘንድሮ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ‘መርገጥ’ ስለሆነ እርሶም ጥሩ አድርገው መራገጥ ነዋ።
“በጣም ግሩም ነው። ቋንቋው፣ ልብ ሰቀላው፣ ታሪኩ… አንተ፤ አይደለም በዓሉ ግርማና ሀዲስ አለማየሁን፣ ዶስቶቭስኪን ትተካለህ… ስታይልህ እኮ ቁርጥ የእሱን ነው። በቃ የሐምሌና የነሐሴ የድራፍት ሒሳብ ተዘጋ በሉት። ብቻ ምን አለፋችሁ… ዘንድሮ ውሸታምነት ሳይኖርብን ለ‘አብሮ መኖር በዓለም ዙሪያ’ ብለን ይኸው ቋጥኝ ቋጥኝ የሚያህለውን ውሸት እንንደዋለን። አንተ እንትና… እንዲህ መዝፈን ትችላለህ እንዴ! ማይክል ጃክሰን ወገብህም አይደርስ።
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1479 times