Saturday, 28 October 2023 20:12

ወላጆች ለልጆቻቸው ምን እየነገሩ ይሆን ?

Written by  -ብርሃኑ ሰሙ-
Rate this item
(1 Vote)

“-- በዘመነ ኢሕአዴግ የተከሰተው ‹‹መባረር››ን እንደ መልካም እድል በመውሰድ፣ የተለያየ የግል ስራ ጀምረው ሕይወትና ቤተሰባቸውን የለወጡ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለግል ኮሌጆች መስፋፋት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተባረሩ መምህራን ሚና ቀላል አይደለም፡፡ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች ባለቤቶች በአብዛኛው የቀድሞ ሠራዊት አባላት እንደሆኑም ይነገራል፡፡--”
 
        በቀድሞ ዘመን ማዕከላዊው መንግስት፣ የድንበር አካባቢ መሬት ለማካለልና ሕዝቡን ለማስገበር ጦሩን ሲልክ፣ የኃይማኖት አባቶችንም ከሠራዊቱ ጋር አብሮ ይልክ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በአንድ የጠረፍ አካባቢ የተከሰተ ታሪክ ከማስገረምና ማዝናናት አልፎ ብዙ ቁምነገሮች ሊገበይበት የሚችል ነው፡፡ ዘመቻው ቀንቷቸው ሕዝቡን የማስተማር ዕድል ያገኙ አንድ የኃይማኖት አባት፣ በየቤቱ እየዞሩ ሕዝቡን ረቡዕና ዐርብ ሥጋ፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦ ከመመገብ እንዲቆጠብ ያስተምራሉ፡፡ ሕዝቡ ቀን ላይ ‹‹ጾመኛ›› ሆኖ ለመታየት ጥረት ያደርጋል፡፡ ማታ ጀንበር ጠልቃ ቤቱን ከዘጋ በኋላ፤ ‹‹ልጆች ኑ፤ አሁን አባ የሉም፤ ወተታችንን እንጠጣ›› ብለው ጾም ይፈታሉ፡፡
ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የተፈጸመው ይህንን ታሪክ፣ እንደየፍላጎታችን በአዎንታና በአሉታ ብዙ ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን፡፡ ከመንግስት ትዕዛዝ፣ ከኃይማኖት አባቶች ፍላጎት፣ ‹‹የከበሮ ድለቃውን ሞቅታ አይቶ›› አሰላለፉን ከሚያስተካክለው ሕዝብ… ይልቅ፤ ከወላጆቻቸው የሚሰጣቸው ውሳኔና ምክር የተሻለ መሆኑን እያዩ የሚያድጉት ልጆች ጉዳይ ግን ብዙ ያነጋግራል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚያልፉ ልጆች፤ ሀገርና ሕዝብ ላይ የሚኖራቸው መረዳት ምንድነው የሚሆነው? በሚለው መወያየት  ተገቢ ነው፡፡


ከ4 ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ በአንድ መድረክ ሕፃናትና ታዳጊ ልጆች ለቀጣይዋ ሀገር ያሉዋት ተስፋ መሆናቸውን ሲናገሩ፣ ‹‹ከ15 ዓመት በታች ባሉ ልጆች ላይ ተስፋ ማድረግ ያስተማምናል›› ማለታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹አዲስ አበባን በአፍሪካ ለሕፃናት የምትመች ከተማ ለማድረግ›› ታስቦ እየተሰራ መሆኑ በተደጋጋሚ እየሰማን ነው፡፡ ይህ ምኞትና እቅድ ከ‹‹ምርጥ ምርጡን ለሕፃናት›› መፈክር በምን ደረጃ ተሽሎ ሊተገበር እንደሚችል መልሱ በጊዜ ሂደት የሚታይ ይሆናል፡፡


ቤተሰብ በቤት ውስጥ ‹‹ከእኔ በተሻለ እውነቱን የሚነግራችሁ ማንም የለም›› በሚል በአንድ በኩል፤ መንግስት ‹‹ሕፃናት ለሀገር የነገ ተስፋ ናቸው›› በሚል በሌላ በኩል፤ ከዚህም ባሻገር ዓለማቀፉ ማሕበረሰብ በደረሰበት የዕድገትና ስልጣኔ ምክንያት በማኅበራዊ ድረ ገጽ በያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ልጆችን በቀላሉ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ስሜትና ዝንባሌያቸውን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ እንዳሉ ይታያል፡፡ እኛ በቀላሉ መቆጣጠር የማንቸለውን የዓለም አቀፉና ጫና ትተን የመጀመሪያ ሁለቱን ብቻ ብንወስድ፣ ልጆችን የሀገርና የህዝብ ተስፋ አድርጎ ለማሳደግ፣ የሁለቱም ሚና አስፈላጊ ቢሆንም ከመንግስት ይልቅ የቤተሰብ አስተዋጽኦ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡
ቀን ‹‹ጾሞ›› ማታ ‹‹የሚፈስከው›› ቤተሰብ ታሪክ አስተማሪ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ታሪክና እውነት፤ በቤተሰቦች ዘንድ ብቻ ሳይሆን መምህራን ለተማሪዎቻቸው፣ ፀሐፊያን ለአንባቢዎቻቸው፣ ፖለቲከኞች ለደቀ መዝሙሮቻቸው፣ የኃይማኖት አባቶች ለተከታዮቻቸው… ያስተላልፋሉ፡፡ ጥቂት ማሳያዎች ላቅርብ፡፡


… ብልኮ ይመስል ጎናነባት - ያቺን እናት
እንዳለችዋን ጥቅልል አደረጋት - ዋጣት
የዕብድ - ዕብዱን አዋከባት፡-
እና ገመናዬ-ን! ብላ ጮኸች
እሱዋም - የኀይል ኀየይዋን እርሪ! አለች
ተፋፍኖዋን - ሢቃዋን
እኩል ለኩሉዋን ታጥፋ እየሳበች
ቁልቁል - ቀሚሱዋን
እና ወደ ታች- እታች ጎተተች
ባለ ባሌለ ኀይሉዋም ተፍጨረጨረች፡፡   
ይህ ግጥም ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፤ ‹‹የተጉዋጎጠ ልብ›› በሚል ርዕስ በ1987 ዓ.ም ባሳተሙት 5ኛ የግጥም መጽሐፋቸው ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ሴትን በሀገር፣ አውሎ ነፋስን በወቅቱ ገዢ በነበረው ፓርቲ (ኢሕአዴግ) ወክለው፤ እርቃኗን በአደባባይ ለመቆም የተገደደች እናት፣ ጎዳና ላይ ድንገት የገጠማት አውሎ ንፋስ ነጠላዋን፣ ዘንቢሏን፣ ዣንጥላዋን፣ ሻሽዋን፣ ቀሚሷን… ቀምቷት በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መውደቋን የሚያሳይ ነው፡፡ በመጽሐፉ የቀረቡት አብዛኞቹ ግጥሞች ከፍተኛ ቁጣ፣ ምሬትና ብስጭት የሚነበብባቸው ናቸው፡፡
ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፤ በዘመነ ኢሕአዴግ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተባበሩት 43 መምህራን አንዱ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በ1983 ዓ.ም የስርዓት ለውጥ ምክንያት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን በማስቀደም፣ በዩኒቨርስቲ፣ በመንግስት መሥሪያ ቤቶች… በስፋት ተግባራዊ የሆነው ‹‹ከስራ መባረር›› በተለያየ መልኩ ሊገለጽ የሚችል ውጤት ማስከተሉ ይታወቃል፡፡


የደረሰባቸው ጥቃት የሀገርና የሕዝብ ጉዳት ነው በሚል ስሜት መጽሐፍ በማዘጋጀት፣ በግል ጋዜጣና መጽሔቶች በጊዜያዊነትና በቋሚነት በመሳተፍ (በማዘጋጀት ጭምር) የታገሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ‹‹መባረሩ›› ቤት ንብረታቸውን ያፈረሰባቸው፣ ለበዛ እንግልትና ሞት የዳረጋቸው አያሌ ናቸው፡፡ ‹‹ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› እና መሰል ሕዝባዊና ሀገራዊ እውነት ላይ የተነገሩ ብሂሎችን እያጣቀሱ፤ ባገኙት አጋጣሚ ለመዝረፍ የተሰለፉ፣ ሌላውም ቀማኛ እንዲሆን ያበረታቱ ስለመኖራቸው ፀሐይ የሞቀው ሀገር የሚያውቀው እውነት ነው፡፡ ይህ እውነት ከ1967 ዓ›ም የአብዮት ለውጥና ትርምስ ጋር በተያያዘ ነበር መታየት የጀመረው፡፡
በ1993 ዓ.ም ‹‹ደመላሽ›› በሚል ርዕስ በዶ/ር ፀሐይ ጀምበሩ ተዘጋጅቶ 6 አጫጭር ልቦለዶችን ባካተተ መጽሐፍ ውስጥ፤ ‹‹ለሀገርና ለሕዝብ መታገላችን ከጉዳት ውጭ ምንም ጥቅም አላስገኘልንም›› የሚሉ ገጸ ባሕሪያት፣ በጥፋት ጎዳና ላይ ስለተጓዙበት፣ ‹‹ምክንያታችን ነው›› ያሉትን እንዲህ ገልጸውታል፡ -  
‹‹ሕሊናዬ እሺ አለኝ፡፡ ታገልኩት፤ ህዝቤ ናቀኝ፡፡ አገሬ ተወችኝ፡፡ ስዘርፈው አከበረኝ፡፡ ስበላት ወደደችኝ፡፡ ታዲያ ምን ላድርግ? መኖር አለብኝ ቢያንስ እንደ እንስሳ፡፡


‹‹ሕዝብህ ስትሰቃይለት ይንቅሀል፤ ይጠላሀል፡፡ ስትቀማው ያከብርሃል፤ ስለዚህ የሚወደውን አደረግሁለት፡፡…
‹‹አባቶቻችን ስትሞትላቸው ያደንቁሀል፤ ያከብሩሀል፡፡ ስትዘርፋቸው ሌላው ቢያቅታቸው ይጠሉሀል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ወረድ ብሏል፡፡ ስትቀማው ያፈቅርሃል፡፡››
እነዚህ ማሳያዎች በተለያየ ጊዜ የተፈጠሩ ሀዘኖች፣ የሀዘነተኞችን ቁጥር እያበዙ ዘመናት መሻገራቸውን ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ፈተናውን እንደ ችግር ማየት ያልፈለጉ አካላትም ነበሩ፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ የተከሰተው ‹‹መባረር››ን እንደ መልካም እድል በመውሰድ፣ የተለያየ የግል ስራ ጀምረው ሕይወትና ቤተሰባቸውን የለወጡ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለግል ኮሌጆች መስፋፋት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተባረሩ መምህራን ሚና ቀላል አይደለም፡፡ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች ባለቤቶች በአብዛኛው የቀድሞ ሠራዊት ዐባላት እንደሆኑም ይነገራል፡፡
በ1983 ዓ.ም በውርደት እንዲባረሩ ከተደረጉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ጥቂቶቹ ችግሩን እንደ መልካም ዕድል ተጠቅመው ራሳቸውን መለወጥ ቢችሉም፣ አጠቃላይ ምስሉንና ትርጉሙን ሊለውጠው እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ የዚያ ጉዳት አካል የሆኑ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ ጀንበር ጠልቃ በር ከተዘጋ በኋላ፣ ለልጆቻቸው የሚያስተላልፉት መልዕክት ድምር ውጤት፣ ሀገርና ሕዝባችንን በተለያየ መልኩ ዋጋ ማስከፈሉ አልቀረም፡፡


የመነሻዬም መዳረሻ ይኸው ነው፤ መንግስት በአደባባይ የሚያቀርበውን ንግግር፣ ትርዒትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ… በየቤቱ ስንቱ ወላጅ ተጋርቶት ለልጆቹ ያስተላልፋል? የሚል፡፡ በያዝነው ሳምንት የተከበረው 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በዓልን በማስመልከት ከተነገሩ መልዕክቶች መሐል፤ ‹‹ሰው በላ›› ይባል የነበረው ደርግ፤ የሕዝብን አንድነትና የሀገርን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በሚል ዓላማ፣ በተለያዩ ቦታዎች አቋቁሟቸው የነበሩ የመከላከያ (የጦር መሣሪያ ማምረቻ) ኢንዱስትሪዎች፣ ኢሕአዴግ አውድሟቸው፣ አሁን በአዲስ መልክ ለማደራጀት ጥረት የተደረገ መሆኑ ምስክርነት መሰጠቱ አንዱ ነበር፡፡


ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ሜክሲኮ የሚገኘው የመከላከያ ኢንጂነሪንግን ጎብኝተው፣ በአደባባይ ከሰጡት ምስክርነት፣ በተለይ ሀገርና ሕዝብ ለዛሬ የደረሰው (የሚሰራ መሳሳቱ እንዳለ ሆኖ) በቅብብሎሽ ነው የሚለው እውነት፤ ጀምበር ከጠለቀም በኋላ በየቤተሰቡ ቅቡልነት አግኝቶ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስተላልፉት ከሆነ፤ ሀገራችን በአደባባይ እርቃኗን ቆማ ሀፍረት በተሰማት ሴት ልትመሰል የምትችልበት መከራ ይቀንሳል፡፡
Read 1284 times