የእስራኤል -ሃማስ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት፣ በእስራኤሏ ኢሜክ ሄፈር ከተማ ውስጥ ያለው የጄሬሚ ዌልፌልድ ቢራ ፋብሪካ፣ በወር 50 ሺ ሊረትር ቢራ ያመርት ነበር። በመላ አገሪቱ ያሉት 14 ምግብ ቤቶቹ ደግሞ በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞችን ያስተናግዱ ነበር። ግጭቱ ከተከሰተ ሁለት ሳምንት ወዲህ ግን የዌልፌልድ የንግድ ተቋማት እግር ከወርች ታሰሩ።
ፋይናንሻል ሪቪው እንደዘገበው፤ የቢራ ፋብሪካው በእነዚህ ጊዜያት ምን ግን ነገር አላመረተም። ከ14 ምግብ ቤቶቹ ውስጥ 12ቱ የተዘጉ ሲሆን፤ ክፍት ከሆኑት ሁለቱ ምግብ ቤቶች በአንደኛው ሃሙስ ዕለት ምሳ ሰዓት ላይ 5 ሰዎች ብቻ መምጣታቸውን ባለቤቱ ይናገራል።
“በሰላሙ ጊዜ በአዘቦች ቀን ከ50 እስከ 150 የሚደርሱ ሰዎች ነበር የሚስተናገዱት። ለመሆኑ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥስ ምግብ ቤት ትከፍታለህ እንዴ? የሥራ ማስኬጃ ወጪውን አልችለውም።” ብሏል- ዌልፌልድ።
የእስራኤል የ500 ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚ፤ በመካከለኛው ምስራቅ እጅግ የዳበረ ኢኮኖሚ ሲሆን በቴክኖሎጂና ቱሪዝም ጥንካሬ የተቀዳጀ ነው። የ2023 አብዛኛውን ጊዜ ጤናማ የእስራኤል ኢኮኖሚ፤ ዘንድሮ የ3 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
ኦክቶበር 7 ቀን 2023 ዓ.ም የሃማስ ታጣቂ ቡድን በፈፀመው ድንገተኛ አሰቃቂ ጥቃት ሳቢያ የተፈጠረው የመጀመሪያ ድንጋጤ፤ የእስራኤል ምግብ ቤቶችንና ባሮችን እንዲዘጉ ያስገደዳቸው ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ የአየር በረራዎችም እንዲሰረዙ አድርጓል። 360 ሺ ገደማ የሚሆኑ ተጠባባቂ ወታደሮች ለግዳጅ መጠራታቸው በአገሪቱ የሰራተኛ ጦርነቱን ተከትሎ በቴልአቪቭ የግንባታ ሥፍራዎች ሁሉ ተዘግተው ነበረ ሲሆን ክሬኖች ለቀናት ቆመው ይታዩ ነበር። በዚህ ሳምንት የግንባታ ስፍራዎቹ ከጥብቅ የደህንነት መመሪያዎች ጋር ዳግም የተከፈቱ ሲሆን በዚህ ዘርፍ እንቅስቃሴው መገታቱ ብቻውን ኢኮኖሚውን በቀን 37ሚ. ዶላር ለሚገመት ኪሳራ ዳርጎታል- ከኢንዱስትሪው የወጣ ሪፖርት እንደጠቆመው።
ግጭቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የጉልበት ሠራተኞች ከጋዛ ወደ እስራኤል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም መግታቱ ተነግሯል።
በጦርነቱ የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት፣ የኢሩሳሌም ትላቅ የገበያ መደብሮች ተንቀሳቃሽ ደረጃዎችና መረማመጃ መንገዶች ኦና ነበሩ። በእርግጥ ቀስ በቀስ ደንበኞች እየተመለሱ ነው።
ሆቴሎች ከድንበር አካባቢዎች ለቀው በመጡ እስራኤላውያን በከፊል የተሞሉ ሲሆን፤ የቀሩት ክፍሎች በአብዛኛው ባዶ ሆነው ሰንብተዋል። ፋብሪካዎች፤ ጋዛ አቅራቢያ ያሉትም ጭምር ሥራቸው አልተስተጓጎሉም፤ ነገር ግን መደበኛ አቅርቦቶችን የሚያጓጉዙ በቂ የጭነት ተሽከርካሪ ሹፌሮች ሁሌ አይገኙም።
የክሬዲት ካርድ ሸመታዎች ባለፈው ሳምንት ከዛሬ ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አንፃር በ12 በመቶ ማሽቆለቆሉ የተመዘገበ ሲሆን፤ ከፍተኛ ማሻቀብ ከታየበት የሱፐር ማርኬት ግብይት በቀር በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ መቀነስ ታይቷል።
በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ያበበው ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው አሁን በትግል ላይ ነው። ዘርፉ ከእስራኤል አጠቃላይ አገራዊ ምርት 18 በመቶውን የሚወክል ሲሆን፤ የአገሪቱን የኤክስፖርት ድርሻ ግማሽ ያህል ይወክላል። “ምርታማነት በእጅጉ አሽልቁሏል፤ ምክንያቱም ነባራዊ አደጋና ስጋት እያለብህ የዕለት ተዕለት ሥራ ላይ ማተኮር አዳጋች ነው።” ብለዋል- Thetaray በተባለው ፊንቴክ ውስጥ ዋና የፋይናንሻል ሃላፊ የሆኑት ባራክ ክሌን።
መቀመጫቸውን በእስራኤል ካደረጉ የተቋሙ 80 ሰራተኞች ውስጥ 12ቱ በተጠባባቂ ወታደርነት ተወስደውበታል። ሌሎች ደግሞ ከት/ቤት የቀሩ ህፃናት ቤት ውስጥ አላቸው። በዚያ ላይ የሮኬት ተኩስ የማያቋርጥ ፍርሃት መደቀኑን አሁንም ድረስ ቀጥሏል።
ጦርነቱ የተጀመረው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ፤ በደቡባዊ እስራኤል ላይ በተፈፀመው ጥቃት፣ ከ1ሺ 400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተከታታይ የአየር ድብደባ የፈፀመች ሲሆን፤ በጥቃቱ ተገደሉት ቁጥር 6500 መድረሱን አልጀዚራ ዘግቧል።
ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር በሰው ህይወት ላይ ከሚደርሰው ተጨማሪ እልቂት ባሻገር የእስራኤልን ኢኮኖሚ ክፉኛ እንደሚጎዳ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር፣ የጋዛ ጦርነት እስራኤልን በየቀኑ 246 ሚ. ዶላር እያስወጣት መሆኑን ከሰሞኑ የገለፁ ሲሆን እስካሁን ከ4.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማውጣቷ ታውቋል።
ጦርነቱ የሚያስከትለው ኢኮኖሚ ኪሳራ፤ እስራኤል በ2006 (እ.ኤ.አ) ከሂዝቦላ ጋር ለአንድ ወር ግጭት ውስጥ ገብታ ከነበረችበት ጊዜ የከፋ እንደሚሆን በ”ፒሳጎት ኢንቨስትመንት ሃውስ” ዋና ኢኮኖሚስት የሆኑት ጉይ ቤይት-ኦር ይናገራሉ። “ረዥም ዘመቻ ጀምረናል፤ ይህም በእስራኤል ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጉዳት ያስከትላል።” ብለዋል። ብዙዎቹ በአላትን፣ ፓርቲዎችን፣ ኹነቶችን እየሰረዙ ነው። ሰዎች ቤታቸው ውስጥ ነው ተቀምጣው ያሉት። ህፃናት ቤት ውስጥ ናቸው፤ ስለዚህም ብዙ ሰዎች መሥራት አልቻሉም።”
በመላ እስራኤል ያሉ ት/ቤቶችም ወደ ርቀት ትምህርት ገብተዋል። በአገልግሎት ዘርፉ ችግሩ የከፋ ነው። በሰሜናዊ እስራኤል የታክሲ ሹፌር የሆነቸው ኒና ሚዝራሂ፤ በአዘቦት ሳምንት፣ በቀን ከ20 እስከ 40 ጉዞዎችን ታደርግ እንደነበር ትናገራለች። ባለፈው ሳምንት ግን በአማካይ አንድ ጉዞ ነው ያደረገችው። “ስራ የለም” የምትለው ሚዛራዊ፤ “አነስተኛ ቢዝነሶች እንዴት እንደሚቀጥሉ በፍፁም አላውቅም” ብላለች።ሌላው የጦርነቱ ሰለባ የሆነው የእስራኤል ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የቱሪዝም ዘርፉ መሆኑን ፋይናንሻል ሪቪው ዘግቧል። የእስራኤል አስጎብኚ ማህበር ሊቀመንበር ጋኒት ፔሌግ እንደገለፁት፤ በጋዛ ላይ የሚካሄደው የአፀፋ ወረራ ወደ ቀጠናዊ ግጭት ይስፋፋል በሚል ስጋት፣ ቀድመው ተይዘው የቆዩ የጉዞ ጉብኝት ፕሮግራሞች ሳይቀሩ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተሰርዘዋል። “የጉዞ ስረዛ በየቀኑ በሚባል ደረጃ ነው ስንቀበል ቆየነው” ብለዋል፤ የቢዝነሱ መውደቅ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት የተከሰተውን የሚያስታውሰን ነው ሲሉ አክዋል። “ከኮቪድ ወረርሽኝ ቀውስ አገግመን ወጥተን ነበር፤ ይኸው ደግሞ እንደገና ሌላ ችግር ውስጥ ተዘፈቅን” ሲሉ አስረድተዋል ፐሌግ።
የኢኮኖሚ ህመሙ ምልክቶች የሌሉበት ቦታ የለም፤ በየቦታው ይታያሉ። ከጦርነቱ በፊት ስዴሮት 30ሺ ህዝብ የሚኖርባት ከተማ ነበረች። በዚህ ሳምንት ከ90 በመቶ በላይ ነዋሪዋ ከአካባቢው ለቅቆ ወጥቶ የ”ጎስት” ከተማ ሆናለች።
ጦርነቱ ያሣረፈው የተፅዕኖ መጠን ግልፅ እየሆነ ሲመጣ፣ ከተለያዩ ወገኖች የመንግስት እርዳታን የመፈለግ ጥያቄ ጨምሯል። ባለፈው ሐሙስ የእስራኤል ገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች፣ ገቢያቸው በጦርነቱ የተጎዳባቸው የንግድ ተቋማት ቋሚ ወጪያቸውን ለመሸፈን እንዲሁም ወደ ሥራ ለመሄድ ላልቻሉ ሠራኞች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል። የእስራኤል ማዕላዊ ባንክም፣ ባለፈው ሳምንት፣ የእስራኤልን ብሔራዊ ገንዘብ-ሼክል፤ ለመታደግ፣ የ30ቢሊዮን ዶላር መጠባቂያን ለሽያጭ እንደሚያቀርብ ይፋ አድርጓል። በድጋፍ ዕቅዱ የተነሳ ዘንድሮ የመንግስታት ባጀት ጉድለት ወደ 3.5 በመቶ (ቀድሞ ካለመው 1.1 በመቶ በላይ) እንደሚያድግ ስሞትሪች ተናግረዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ በሚቀጥለው ዓመት እጅግ ከፍተኛ የባጀት ጉድት እንደሚከሰት እየተነበዩ ነው። በIBI ኢንቨስትመንት ሃውስ ዋና ኢኮኖሚስት የሆኑት ራፊ ጎዝላን፤ እስራኤል ወደ ጦርነቱ የገባችው ከቀድሞዎቹ ግጭቶች በተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ውስጥ ሆና ነው ይላሉ። የአገሪቱ ዕዳ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ጋር ያለው ምጣኔ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ 60 በመቶ ገደማ መሆኑን የገለጹት ጎዝላን፤ ማዕከላዊ ባንክም 200 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ አስቀምጦ ነው ወደ ጦርነቱ የተገባው ብለዋል። “የአሁኑ በእጅጉ የተለየ ሁኔታ ነው። ይህም የእስራኤል ባንክም ሆነ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምረውን የባጀት ጉድለት ለመሙላት ያስችላቸዋል።” ብለዋል፤ ጎዝላን። “በእንቅስቃሴ ላይ የተወሰነ ጉዳት እናያለን፤ ነገር ግን እሱም ቢሆን ከወታደራዊ ዘመቻው ርዝመትና ጥልቀት ጋር የተያያዘ ነው።” ሲሉ አስረድተዋል።
እስራኤል በ75 ዓመት ታሪኳ በርካታ ጦርነቶችን ብትዋጋም፤ ኢኮኖሚዋ ሁልጊዜም መልሶ እንደሚያንሰራራ በተደጋጋሚ ታይቷል። መቀመጫውን በኢየሩሳሌም ያደረገው “Our Crowd” ዋና ስራ አስፈፃሚም፤ ኢኮኖሚው መልሶ ያንሰራራል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። በዚህ ምስቅልቅል ወቅትም መሃልም እንኳን በከፍተኛ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ውስጥ የሚሰሩ አንዳንድ ሠራኞች ወደ ሥራ እየተመለሱ መሆኑ ታውቋል። “ወደ ሥራ መመለስ በእርግጥም በእጅጉ አስፈላጊ ነው። አንድ ሰው ለዚህ ጦርነት ዋጋ መክፈል ይኖርበታል” ብለዋል፤ ዋና ስራ አስፈፃሚው።ዌልፌልድ ግን ይልጥ በጥንቃቄ ነው ሁኔታዎች እየተከታተለ ያለው። ለጊዜው ነገሮችን ዕለት በዕለት መመልከቱን መርጧል። “በሚቀጥለው ሳምንት ጥቂት ምግብ ቤቶቻችንን በመክፈት ባንክ ጥቂት ሠራተኞች ጋር ወደ ሥራ ተመልሰን፣ የሚሆነውን እናያለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።” ብሏል።
“ግን ገርዬው የተወሳሰበ ነገር ነው። በእጅጉ የተወሳሰበ ነው። ምክንያቱም የገባንበት ይሄ ትንሽ ትርኢት-ለጥቂት ጊዜ ይቀጥላል የሚል ስሜት አለኝ።” ሲል የ14 ሬስቶራንቶችና ቢራ ፋብሪካ ባለቤት የሆነው ጄርሚ ዌልፌልድ ሃሳቡን ገልጿል።
Saturday, 28 October 2023 20:09
ጦርነቱ የእስራኤልን ኢኮኖሚ ዋጋ እያስከፈለ ነው የጋዛ ጦርነት በቀን 246 ሚ. ዶላር ያስወጣታል
Written by ኤሊያስ
Published in
ፖለቲካ በፈገግታ