Wednesday, 01 November 2023 00:00

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በታሪኩ የማያውቀው ውርደት ገጥሞታል ።

Written by  Tewodros Teklearegay
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በታሪኩ የማያውቀው ውርደት ገጥሞታል ።
???? በትያትር ገምጋሚ አባላት ተገምግሞ ያለፈ ትያትር በድጋሚ በብልጽግና ካድሬዎች ተገመገመ ።
********************************************************
ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ማንያዘዋል እንዳሻው ምንም ባልል ደስ ይለኝ ነበር ። ግን ምርጫ የለኝም ። በግሌ የአቶ ማንያዘዋል የቅርብ ሰው ነኝ ። የኖረ ወዳጅነት አለኝ ። አንድም ጊዜ በምንም ጉዳይ ተጋጭተን አናውቅም ። ፍጹም ሰላማዊ ግንኙነት ነው ያለን ። ይህ ግን የእውቂያና ርቂያ መለካካት አይደለም ። የፍትሕ ጉዳይ ነው ። በእኔ ዘመን ይህን ውርደት የምቋቋምበት ጫንቃ የለኝም ። የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ስራ የሆነው " ሀሁ ወይም ፐፑ " ትያትር በተስፋዬ ሲማ አዘጋጅነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሊቀርብ መጠየቂያ ደብዳቤ ቀርቦ ይገመገማል ። ገምጋሚ ኮሚቴውም ትያትሩን ገምግሞ ያለምንም የድምጽ ልዩነት እንዲያልፍና በትያትር ቤቱ እንዲቀርብ በቃለጉባዔ ይፈራረማል ። ይኸው ውሳኔም ለአዘጋጅና ፕሮዲዩሰሩ በደብዳቤ ይገለጽለታል ። ከቀናት ቆይታ በኋላ ግን ዋና ዳይሬክተሩ " ትያትሩ ፖለቲካዊ ይዘት ስላለው የብልጽግና አባላት ሊያዩት ይገባል " የሚል ሀሳብ ያመነጫሉ ። እንግዲህ በ1983/4 ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ የተጻፈን ትያትር ነው የብልጽግና ካድሬዎች እንዲያዩት የሚደረገው ።
በነገራችን ላይ በአቶ ማንያዘዋል ኃላፊነት በትያትር ባለሙያዎች ተገምግሞ ያለፈ ትያትር በካድሬ ሲገመገም " ሀሁ ወይም ፐፑ " የመጀመሪያው አይደለም ። የደራሲ አበረ አዳሙ ስራ የሆነ ትያትርም እንዲሁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ገምጋሚዎች እያሉ ከአማራ ክልል በሚመጡ ሰዎች እንዲገመገም ለማድረግ ተሞክሯል ። ከቅርብ ሳምንታት በፊት የዚያው ትያትር ቤት ባለሙያ የሆነው ሳሙኤል ተስፋዬ " አይዳ " የሚል ትርጉም ተውኔት ለገምጋሚው ኮሚቴ ቀርቦ ካለፈ በኋላ በቂና አሳማኝ ምክንያት ሳይሰጥ በዋና ዳይሬክተሩ የግል ፍላጎት እንዳይቀርብ ተደርጓል ። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የትያትር ቤቱ የገምጋሚ ኮሚቴ አባላት " የሙያ ነጻነታችን ተደፍሯል " ሳይሉ ስራቸውን ቀጥለዋል ።
እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በየጊዜያቱ የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠሙት አልፏል ። እንዳሁን የጨቀየ አሰራር ውስጥ ገብቶ ግን አያውቅም ። የፀጋዬ ገ/መድህን ስራዎች ለትያትር ባለሙያዎች እንኳ ለግምግማ የሚያስቸግር ጠጣር ቋንቋና ሀሳብ ያለው መሆኑ ይታወቃል ። ቃላትና ቋንቋን ከፍ ባለ ደረጃ መረዳትን ይፈልጋል ። ይህን በሙያተኞቹ ተገምግሞ ያለፈ ትያትርን ነው እንግዲህ በትያትር ቤቱ ባሉ የብልጽግና ካድሬዎች እንዲገመገም የተደረገው ። የትያትር ባለሙያዎቹ ሳይታመኑ ቀርተው ለጥበብ ፖለቲከኞች የታመኑበት ይህ ውጤት ነገ 5:00 ሰዓት ውጤቱ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል ። አሁን ትያትሩ ከ30 ዓመት በኋላ ፖለቲካ ሆኖ ፖለቲከኞች እጅ ላይ ይገኛል ። ፖለቲከኞቹ " ይታይ "ም ፣ " አይታይ "ም ቢሉ ትያትርን አንገት የሚያስደፋው ድርጊት ተፈጽሟል ። ከዚህ በላይ ማንነትን መሸጥ ገጥሞኝ አያውቅም ። ይህ እንዲሆን የመንግሥት ጥያቄና ፍላጎት አይደለም ። ሙያተኛው ራሱ ለመንግሥት የሚያቀርበው እጅ መንሻ ነው ። ያልተጠየቁትን መመለስ ከዚህ በላይ የለም ። በነገራችን ላይ ይህ መንግሥትን መጥቀም ሳይሆን ማሰደብ ነው ። መንግሥት በአንድ ቀን አይፈርስም ። እንዲህ ያሉ አሰራሮች ተጠራቅመው ነው ስርዓትን የሚያፈርሱት ። ለእኔ ከዚህ በላይ መንግሥትን ለመጣል መንቀሳቀስ የለም ። መቸም ሿሚዎቹ ይህን አሰራር ይታዘቡታል ። " አበጀህ " ሊሉ አይችሉም ።
በነገራችን ላይ " ሀሁ ወይም ፐፑ " ትያትር በ1984ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሊቀርብ ብሎ በአሁኑ የትያትር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማንያዘዋል እንዳሻው ( በዚያ ወቅትም ለተወሰኑ ዓመታት የትያትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ ነበሩ ) ትያትሩ እንዳይታይ ታግዶ ከጋሽ ፀጋዬ ጋር ከቃላት መወራወርና መካሰስ ጀምሮ እስከ መጽሔት ላይ ንትርክ ደርሰዋል ። በወቅቱ ጋሽ ፀጋዬ እነ ታምራት ላይኔ ጋ ደርሰው በግዴታ ተፈቅዶ በግፊያና በፖሊስ ጥበቃ ሕዝብ በግፊያ አይቶታል ። " ይህን ትውልድ በጫት ትገዛዋለህ " የሚለው የጋሽ ፀጋዬ የ " እፎይታ " መጽሔት ቃለመጠይቅ መነሻው ያ ነው ። ዛሬ ጋሽ ፀጋዬ የለም ። ያ ቁጣው የሚያስፈራ ፣ ሁሉን በር የሚከፍተው የወርቅ ቁልፉ ፀጋዬ ገ/መድህን ዛሬ ሀውልቱ ( ስራው ) ሲቆፈር ምንም ማድረግ አይችልም ። ራሱን መከላከል አይችልም ። አቶ ማንያዘዋል በሕይወት ስላሉ ዛሬም ለፀጋዬ ስራዎች ልባቸው አልሻረም ። በትያትር ቤቱ ተደርጎ በማያውቅ መልኩ ቀድሞ በተያዘ ውል " እሳት ወይ አበባ " ለሦስት ወር ብቻ ታይቶ እንዲወርድ ተደርጓል ። " ሀሁ ወይም ፐፑ " ደግሞ ይኸው መከራውን ያያል ።
ለ " ሀሁ ወይም ፐፑ " አዲስ ያልተጻፈ ሕግ እየወጣለት ፣ የትያትር ጥበብ ተዋርዶ በሙያተኛ የተሰጠው አስተያየት ተሽሮ በካድሬ እንዲገመገም ለመደረጉ ሦስት አካላት ተጠያቂ ናቸው ። አቶ ማንያዘዋል እንዳሻው ፣ አርቲስት ተስፋዬ ሲማ እና የትያትር ቤቱ ገምጋሚ ኮሚቴ አባላት ። አቶ ማንያዘዋል ብዙዎች እንደሚሉት በቂም ወይም ቀኑን ለራሳቸው ስራ እያቆዩ ብቻ አደረጉ ። የትያትር ባለሙያና መምህሩ ተስፋዬ ሲማ የገምጋሚው ቃለ ጉባዔ በእጁ እያለ ጥበብ በፖለቲከኞች ትዳኝ ሲባል ለሀቅ መቆም እያለበት በእሺታ ጥበብን ማሳነቁ ። ምንድነው ይህን ያህል ትያትር ባይሰራስ ? ትያትር ከሀቅና ከፍትሕ አይበልጥም ። ያውም የፀጋዬ ገ/መድህን ፣ የዚያ በማንነቱ ክብር የማይደራደርን ሰው ስራ እንዲህ እንዲልከሰከስ መተባበር በታሪክም ያስጠይቃል ። መቸም እንዲሁ እንደተጨላለምን አንቀርም ። አንድ ቀን ለእውነትና ለፍትሕ ፀሐይ ይወጣላታል ። የትያትር ቤቱ ገምጋሚ አባላት ሙያቸውና የእውቀት ክብራቸው ተንዶ ያሳለፉት ሲጣልባቸው ፣ ሙያው ያለሙያቸው በተጠሩ ፖለቲከኞች ሊዳኝ ሲጠራ ምንም ምላሽ ሳይሰጡ ቀጥሎ ሊገመገም የሚመጣን ስራ በመጠበቃቸው የዚህ ጥፋት ተባባሪዎች ከመባል አይድኑም ።
በነገራችን ላይ ፦ " የሁለት ጌቶች አሽከር ስለሚባለው ጣሊያናዊ ትያትር እጅግ ዘግናኝ ፣ ገፋ ከተደረገም ኃላፊዎችን በወንጀል የሚያስጠይቅ ሸፍጥ ተፈጽሟል ። እሱ ለጊዜው ይደር ።

Read 241 times