Saturday, 04 November 2023 00:00

ታይለር ስዊፍት ስንት ቦታ ትሁን?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

በኮንሰርትም ሪከርድ ሰብራ፣ በፊልምም ሪከርድ በጥሳ፣ የቴሌቪዥን ተመልካቾችንም ወደ ስፖርት ግጥሚያ ሰብስባ… ስንቱን ትቻለው?
• እሷ ግን ስራዋን እየሰራች ነው። በስድስት ወራት ብቻ፣ ከሩብ ቢሊዮን በላይ ተጨማሪ ሀብት አትርፋለች። ቢሊዮነር ለመባል በቅታለች

ንደ ዛሬ ሳይሆን፣ የአሜሪካ ፊልም ቤቶች በዓመት ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ የትኬት ገቢ ከተመልካቾች ይሰበስቡ ነበር። ኮረና ቫይረስ መጣና ጉድ አደረጋቸው። በ2020 የፊልም ቲኬቶች ሽያጭ፣ 2.5 ቢሊዮን ዶላር አይሞላም ነበር። ከዚያ ወዲህ የኮረና ክፉ መከራ አባርቷል። የፊልም ጥበብ ግን በሠሪዎቹም በተመልካቾችም ዘንድ ገና አላገገመም። በ2022 የሲኒማ ቲኬቶች ሽያጭ 8 ቢሊዮን ዶላር መድረስ አልቻለም። የፊልሞች ብዛትም በሦስት እጅ ቀንሷል።ለወትሮ፣ ለሲኒማ ቤቶች ዋናዎቹ ነፍስ አድን ደራሾች፣ የ”ሱፐርሔሮ”… የሚሏቸው ፊልሞች ናቸው። እነ ባትማን፣ ሱፐርማን፣ ስፓይደርማን፣ ብላክ ፓንተር… የመሳሰሉ። ዘንድሮ ግን የነዚሁ የጀብድ ፊልሞች ጀግንነት በቂ አልሆነም። ብዙ ገቢ በማስገኘት ቀዳሚ ቢሆኑም፣ እንደ ድሯቸው አይደሉም።
እህስ?
ያልተጠበቀ ሲሳይ የሆነላቸው፣ የታይለር ስዊፍት ፊልም ነው። ለዚያውም በጥቅምት ወር።ተመልካቾችን በብዛት የሚስቡ ትልልቅ ፊልሞች ለእይታ የሚቀርቡት፣ ከታሕሣሥና በጥር፣ ከዚያ ደግሞ ከሰኔ እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ነው። የጥቅምት ወር ፊልሞች፣ ደቀቅ ደቀቅ ያሉ ናቸው። ዘንድሮ ግን፣ የታይለር ስዊፍት ፊልም ተገኘ።የተለመደው ዐይነት ፊልም አይደለም። ከመድረኮች የተቀረጸ የሙዚቃ ትእይንት ነው በእርግጥ ካሁን ቀደምም፣ የማይክል ጃክሰን፣ የጀስቲን ቢበር የመሳሰሉ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ከመድረክ ተቀርጸው በፊልም ቤቶች ታይተዋል። የታይለር ስዊፍት ፊልም ግን በዕጥፍ የሚያስከነዳ ሆኗል። እስካለፈው ሳምንት ድረስ 200 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት አዲስ ሪከርድ ሰብሯል።ከፊልም ቤቶች ትኬት ሽያጭ ወደ 28 በመቶ ገደማ ድርሻ ለዘፋኟ ይሆናል ተብሏል።

ቀላል አይደለም። ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች ማለት ነው። ግን የእግረመንገድ ገቢ ነው። ዋናው ሥራ የመድረክ ትዕይንቷ ነው። በርካታ ከተሞችን ያካለለውና ለበርካታ ወራት የዘለቀው የታይለር ስዊፍት ኮንሰርት፣ 1 ቢሊዮን ዶላር የቲኬት ሽያጭ በማስገኘት የአለም ሪከርድ ይሰብራል ተብሎለት ነበር። አምና ሚያዝያ ወር ላይ ነበር እንደ ጉድ የተወራው። በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይም ታትሞ ነበር። በስድስት ወራት ውስጥ ከ50 በላይ የስታዲዮም ኮንሰርቶችን ከሳምንት ሳምንት ማቅረብ ከባድ ነው። በዚያ ላይ 40 ዘፈኖችን በተከታታይ ለተመልካቾች የምታቀርበው። የታዋቂ ዘፋኞች ኮንሰርት በአማካይ ከ22 ዘፈን አይበልጥም። ብዙ የኪነጥበብ ምሁራን ታይለር ስዊፍትን የሚያደንቋት በዘፈን ግጥም ደራሲነቷ ነው። ለበርካታ ዓመታትም ተሸላሚ ሆናለች።ሚሊዮኖች የሚወዷት በዘፈኗ ነው። አለባበሷን እየተከታተሉ እሷን ለመምሰል የሚሞክሩም ጥቂት አይደሉም።


የቢዝነስ ሰዎችና የኮንሰርት ተመልካቾች ደግሞ ብርታትና ትጋቷን ያደንቃሉ።ከዚህም ምክንያት ነው ኮንሰርቶቿን በሙሉ ማጠናቀቅ ከቻለች፣ የቲኬት ሽያጭ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን የገመቱላት።ብሉምበርግ ከሰሞኑ እንደዘገበው ግን፣ የኮንሰርቱ የትኬት ሽያጭ 2 ቢሊዮን ዶላር እየደረሰ ነው ተብሏል።በእርግጥ ለኮንሰርት ዝግጅት የሚወጣው ወጪ ቀላል አይደለም። አስደናቂው የመድረክ ግንባታ፤ ልዩ የምትሃት ዓለም እንደመፍጠር ነው ተብሏል። መድረኩ ከዘፈን ዘፈን መልኩ ይቀያየራል። እንደ ዘፈኑ ዓይነትና እንደ ግጥሙ ይዘት፣… አንዴ
አርቴፊሻል በረዶ ይወርዳል። ሌላ ጊዜ ግዙፍ አውሬዎች የሚፈነጩበት አስፈሪ ቦታ ሆኖ ይታያል። በምትሀት ወደተለያዩ ቦታዎች የመጓዝ ያህል ይመስላል።እንዲህ ዐይነት የመድረክ ዝግጅት፣ በየስታዲዮሙ አንዳችም ሳይጓደል ይከናወናል። በዚህም አድናቆን አትርፋለች።

ወጪው ብዙ ቢሆንም ገቢው ያካክስላታል።እጅግ ስለተሳካላትም ነው፣ ከሰሞኑ ሌላ አዲስ ሪከር የሰበረችው። ከኮንሰርቷ በፊት የ700 ሚሊዮን ዶላር ባለሀብት የነበረችው ታይለር ስዊፍት፣ ዛሬ ቢሊዮነር እንደበቃች የፎርብስ ዘገባ ይፋ አድርጓል። በዘፈን የቢሊዮን ዶላር ባለሀብት የሆነች የመጀመሪያዋ ዘፋኝ ናት ብሏል - ዘገባው።የአገሬውን የሙዚቃ ገበያ፣ እንደ አዲስ እንዲሟሟቅ አድርጋለች።ባለፉት ሳምንታት ደግሞ፣ የተቀዛቀዘውን የፊልም ቤቶች ገበያ እንዲነቃቃ አድርጋለች።ምን ይሄ ብቻ! ከሚሊዮን ቤተሰቦች ተጨማሪ ምስጋና አግኝታለች። ለምን?አለልማዳቸው፣ በርካታ ታዳጊና ወጣት ሴቶች አዲስ ጥያቄ አምጥተዋል። “የእግር ኳስ ግጥሚያው ስንት ሰዓት ነው የሚጀምረው?” ብለው የሚጠይቁ ሴቶች በዝተዋል። የእግር ኳስ ግጥሚያ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ፣ ብዙዎቹ ሴቶች፣ አካባቢውን ጥለው ይወጣሉ። ወደየመኝታቸው ይሄዳሉ። አሁን ታዲያ ምን ተገኘ?ታይለር ስዊፍት ስቴዲዮም ገብታ ግጥሚያዎችን ማየት ጀመረች። እናም የብዙዎቹ ሴቶች አዲስ አመል የመጠው ታይለር ስዊፍትን በቴሌቪዥን ለማየት ነው።

በዚህም የግጥሚያ ተመልካቾች ቁጥር በ2 ሚሊዮን እንደጨመረለት የኤንቢሲ ቴሌቪዥን ገልጿል። የማስታወቂያ ገቢውም እንደዚያው። ወላጆች ደግሞ፣ ከልጆች ጋር አብረው በጋራ የሚታደሙበት አጋጣሚ ስለተፈጠረላቸው ዘፋኟን አመስግነዋል። ስንት ቦታ ትሁን ይህች ተዓምረኛ!በእርግጥ፣ የስፓርት ግጥሚያ ላይ መሄድ የጀመረችው፣ አንዱ ተጫዋች አዲስ ፍቅረኛዋ ስለሆነ ነው ተብሏል። ወጣቶችን የሚስብ ለወሬና ለወረት እጅግ የተመቸ ጉዳይ ነው - የፍቅር ሽርጉድ። ግን ደግሞ ለወላጆችም ቅር አያሰኝም። እንደተለመደው፣ የታይለር ስዊፍት ነገረ ሥራ፣ በነጻነትም ነው፤ በቁጥብነትም ነው።ስታዲዬም የምትታደመው በጨዋ ደንብ ነው። ስታዲዬም ውስጥ ከተጫዋቹ እናት ጎን ነው የምትቀመጠው።

Read 161 times