Saturday, 04 November 2023 00:00

የበቀለ ሙለታ የህይወት ገጽ

Written by  ከእዝራ እጅጉ
Rate this item
(0 votes)

ዘመድ አልባ አንዲት ጠብታ ውሀ በጉሮሮዬ ጫፍ አልፋ ወርዳ ወርዳ አንጀቴን ስታርሰኝ
ጠብታነቷ ተረሳኝ /በቀለ ሙለታ/

“…አንቀጽ፣ አንድ ጽሁፍ ላይ ውብ ተደርጎ ተጽፎ ስመለከት ልቤ በሀሴት ይሞላል”
ይል ነበር - የዛሬ ሳምንት ጥቅምት 17 2016 አ.ም ሥርዓተ ቀብሩ የተፈጸመው ብዕረኛው በቀለ ሙለታ። ጥሩ አንቀጽ ደስታን ስለሚያመጣለትም፣ ከሩብ ክፍለዘመን በላይ የብዕር ስሙን አንቀጸ ብርሀን በማለት የንባብ ውጤቱን አሳየ።በሚያዝያ 2007 የኢትዮጵያ ዜና
አገልግሎትን በዋና የስራ መሪነት እያገለገለ “የከሀዲዎች ወግ” የተሰኘ 14 ልቦለዶችን የያዘ መጽሀፍ አሳትሟል። ቀለም ፍለጋ፣ እንግዳው እና ሌሎቹም ድርሰቶቹ በአጫጭር ዓረፍተነገሮች የተነደፉ መሳጭ የኪነጥበብ በረከቶች ናቸው። በቀለ የማራኪ አንቀጾች አድናቂ ነው ብለን የለ።
ከሳምንት በፊት የተለየን በቀለ በሥነጽሑፍ እና በሚድያ መሪነቱ ባለፉት 36 አመታት ጉልህ አሻራ ያኖረ በመሆኑ ትንሽ ልጽፍ ፈልጌአለሁ።
አባቱ አቶ ሙለታ ቶላ፣ እናቱ ደግሞ ወ/ሮ ወርቄ ዓለሙ ይባላሉ። ሰኔ 16 ቀን 1963 ዓ.ም በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ አካባቢ ነበር የተወለደው።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በወሰን ሰገድ፣ ከዚያም በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። አብሮ አደግ ጓደኛው ጥላሁን ገብረሥላሴ እንዳጫወተኝ፣ በቀለ በትምህርት ውጤቱ ከ1-10 ይወጣ ነበር። ለአማርኛ ትምህርትም ከፍተኛ ፍቅር ነበረው።ትልቅ ጉልበቱ ግን የግል ጥረቱና ውስጣዊ የኪነጥበብ ፍቅሩ ነው። ብዕር ከወረቀት በማዋሐድ መጣጥፎችን መጻፍ የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር። በ21 ዓመቱም ነው፣ “ተስፋ የኪነ-ጥበብ መድረክ” በሚል ስያሜ መርካቶ በሚገኘው የቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት የጥበብ መድረኮችን ማዘጋጀት የጀመረው።በጊዜው የተስፋ የኪነጥበብ ማህበር አባላት በእጅ እየተጻፋች ለሕትመት የምትበቃ “ብርሀን” የተሰኘች ሕትመት ነበረቻቸው። በቀለ በአፍላነት ዘመኑ ጋዜጣዋን በኃላፊነት የማዘጋጀቱን አደራ በብቃት ይወጣ ነበር።ብርቱውና ዝምተኛው ብዕረኛ በቀለ ሙለታ፣ በ1984 ፍካት የስነ-ጽሁፍ ክበብን ከመሰረቱና በመሪነት ካገለገሉ ባለሙያዎች አንዱ ነው። ይህ ማህበር የስነ-ጽሁፍ ምሽቶችን እያዘጋጀ በመጽሀፍት ዙሪያ ያካሄዳቸው የውይይት መድረኮች በብዙዎች ዘንድ በበጎ ይታወሳሉ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
ታዋቂ መምህራንንና ታዋቂ ደራሲዎችን በመጋበዝ የልምድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር።


ክበቡ አድጎ ለቁምነገር እንዲበቃ ከጣሩት እና ምስጋና ከሚቸራቸው አንዱ በቀለ ሙለታ  ነበር።ደራሲ እና ገጣሚ አለማየሁ ታዬ በተለይ በአፍላነት ዘመኑ ፍካትን በተቀላቀለበት ጊዜ በሙያው የማደግ ብርታት እንዲያገኝ የበቀለ ውለታ ትልቅ እንደነበር ይናገራል።
በምክርና በማበረታቻ ብቻ አይደለምአርአያነት በማሳየትም ጭምር ነው - ውለታው። በቀለ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚሆኑ መጣጥፎችን በማዘጋጀት ለመሳተፍ፣ ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ወደሚገኘው ቤተ-መጻሕፍት በየዕለቱ በማቅናት ራሱን በዕውቀት ያጎለብት ነበር።በሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ ጥናት ለማድረግ የተነሳ ገጣሚ ወይም ደራሲ፣ ወደ በቀለ ጎራ ቢል፣ ብዙ ያተርፋል። በቀለ፣ አጥኚዎችንና የሥነ ጽሑፍ ተማሪዎች ለማገዝ ሁሌም በሩ ክፍት ነበር። ጠቃሚ ምክረሀሳቦችን ለመሰንዘርና የሚመለከታቸውን ሰዎች ለመጠቆም ያሳየው የነበረው ተነሳሽነት እና ልበ-ቀናነት በብዙዎች አድናቆት ይቸረው ነበር።

ከሰዎች ጋር መልካም ግንኙነት ያዳበረ በመሆኑም “የመረጃ ቋት” የሚል ማዕረግ ሰጥተውታል።ታዲያ የበቀለ የመረጃ ቋትነት መንታ ባህሪይ ነበረው። ለሰዎች ዕውቀትና ለሰዎች የጥናት ውጤት ሁሌም ክብር ይሰጣል። አንድም ስነ-ጽሑፋዊ ጥናትን ለማድረግ የተነሳን ተመራማሪ በጥናት ርዕሰጉዳይ ዙሪያ ቀደም ሲል የተሠሩ ሥራዎችን ሳያዛባና ሳይሰስት በመጠቆም በአርአያነት ሃላፊነቱን ይወጣ ነበር። ይህም የዕውቀት ደረጃውን ከፍታ ያሳያል። አንድ ሰው አቶ በቀለ ሙለታ ጋር ደውሎ የአንድን ሰው መገኛ ፈልጎ ከሆነ ሊያጣው አይችልም።በቀለ ሙለታ የመጀመሪያ ዲግሪውን በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሊድስታር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ወስዷል።ከቀብሩ ቀን አንድ ቀን በፊት ያወራኋት ታናሽ እህቱ መስከረም ሙለታ ወንድሟ እንደ መከታ የምትቆጥረው ታላቅ ሰው መሆኑን ታስረዳለች። “በቄ እንደ ታናሽ አይቶ ብዙ ምክሮችን ይመክረኝ ነበር። በተለይ በትምህርቴ እንድገፋ ፍላጎቱ ነበር” ብላለች።ባለቤቱ ደኗ ግዛውንም አነጋገርኳት።


በትዝታ ወደ ኋላ ትመለሳለች። አይኗ አንድ ቦታ ላይ ይቆምና በትካዜ ትነጉዳለች። ለ21 ዓመት አብሯት የኖረው በቀለ 4 ልጆቻቸውን በሃላፊነት ታሳድግ ዘንድ አደራ ብሏታል። ባለቤቱ ደኗ ልብ ብሎ ላስተዋላት ጥንካሬዋ በግልጽ ይነበባል። ስለ በቀለ ስትናገር የስነጽሑፍ ችሎታው ይደንቃታል።በቀለ ሙለታ በራሱ ጥረት ቀድሞ ያዳበረውን የስነ-ጽሑፍ ችሎታ በመያዝ በ1986 ዓ.ም በመስራች ጋዜጠኝነት በማህቶት ጋዜጣ በሳል አርቲክሎችን እና ወጎችን ወደ አንባቢ በማድረስ ልዩ የሙያ ችሎታ ባለቤት መሆኑን በሚገባ አስመስክሯል።እስከ ጥር 2000 ዓ.ም የተለያዩ ህትመቶች ላይ ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ሰርቷል።ከ2000 ዓም ጀምሮ በዋልታ ሚዲያ ኮሙኒኬሽን በአማርኛ ዜና፣ በአርቲክልና መጽሔት ዋና አዘጋጅነት፤ ከዚያም የፕሮሞሽን ዋና ክፍል ኃላፊ፤ የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች ዋና ክፍል ኃላፊ፤ የጥናትና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ መምሪያ ስራ አስኪያጅ በመሆን ለ6 ዓመት ሰርቷል።

በ2006 ዓም ጀምሮ የኢዜአ የዜናና የፕሮግራም ፕሮዳክሽን ዳይሬክተር፤ በ2007 ዓም ድረስ የኢዜአ ዋና ዳይሬክተር በመሆን እስከ 2011 ዓም ተቋ፣ም መርቷል።በተለይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤጽ ወጥቶ ራሱን ችሎ ዳግም እንደ ኤጀንሲ እንዲዋቀር የበቀለ ሙለታ አስተዋጽኦ ትልቅ እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ። በዜና የረጅም አመት ታሪክ ያካበተው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስሙን እና ክብሩን በጠበቀ መልኩ በባለሙያ እና
በግብአት የተሟላ፣ ከዘመኑም ጋር የሚራመድ የሚድያ ተቋም እንዲሆን በቀለ ትልቅ አሻራ አሳርፏል።በቀለ እስከ ነሐሴ 2012 ዓም ድረስ ለአንድ ዓመት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ነበር። በጊዜው ፋና ብሮድካስቲንግ ውስጥ መሰረታዊ የአሰራር
ለውጥ እንዲመጣ ጥረት አድርጓል።በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክም ለሁለት ዓመት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖም አገልግሏል።ጥሩወርቅ ተካ ስለ በቀለ ስትናገርም “…
በቀለ ለሰው ሀሳቡን ሲያስረዳ በእርጋታ ነው። ስራ ሲሰጥ ከስር ጀምሮ ያስረዳል። የተናገረውበትክክል ከተሰራ አድናቆት ይቸራል። ካልተሰራ ደግሞ ቀስ ብሎ ያስረዳል” በማለት ሀሳቧን ገልጻለች።በቀለ ሙለታ ቅዳሜ ጥቅምት 10 ቀን 2016 ደህና ሆኖ እንዳገኙት ጓደኞቹ
ይናገራሉ። ማክሰኞ ድንገት ሆስፒታል ገባ። ጥቅምት 15 ማረፉ ተሰማ። ጥቅምት 17 ቀን 2016 ሲኤምሲ በሚገኘው ሳህሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ተፈጽሟል። የሰው ልጅ ዕድሜ ዘመኑ በፈቀደለት መጠን ይሠራል። በፈጣሪ ፈቃድ ደግሞ ያልፋል። ታሪኩ ግን እየተነበበ ይኖራል። ነፍስህን በገነት ያኑር በቄ።

Read 1417 times