Saturday, 04 November 2023 00:00

ፕሮፖጋንዳ ዘ-ፍጥረት

Written by  ሌሊሣ ግርማ) (መጣጥፍ
Rate this item
(2 votes)

ከዚህ በፊት ስለ አንድ ቃል ፍቺ ስፈልግ ባጅቻለሁ፡፡ ቃሉ “ፕሮፓጋንዳ” ይባላል፡፡ እስካሁን የአማርኛ ቋንቋ አምሳያ ላገኝለት አልቻልኩም፡፡ ባገኝለትም… የተለመደውን በአዲሱ መለወጡ እንዲሁ ቀላል አይሆንም፡፡ አዲስ ቃል ከማግኘት የቀድሞውን በአግባቡ መፍታት የተሻለ ነው ብዬ ለራሴ ወሰንኩኝ፡፡
የፕሮፓጋንዳን ትርጉም በደንብ አብራርቶልኝ ያገኘሁት “Institute of Propaganda Analysis” የተሰኘ ተቋም ያቀረበው ትንተና ነው፡፡ ዝቅ ብዬ ሳነብ አርዕስቱ ራሱ ሳበኝ፡፡ “ፕሮፓጋንዳን እንዴት መለየት ይቻላል” ይላል፡፡ ተቋሙ ይሄንን ፍቱን መድሃኒት ፅፎ የለቀቀው እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር 1937 ዓ.ም መሆኑን ጨምሮ ይገልፃል፡፡ ፅሁፉን በራሴ አገላለፅ እንዲሁም አንኳሩን በመጭመቅ እንደሚከተለው አቀርባለሁኝ፡፡
                                               ¤¤¤
ለሰው ልጅ በቀላሉ የሚቀርበው ስሜቱ ነው፡፡ ለስሜቱ ተነጣጥሮ የሚወረወር መልዕክት ደግሞ ከማመዛዘን ቀድሞ ይቆጣጠረዋል፡፡ ለስሜት የተቀነባበረ መልዕክት ተጨባጭ እና እውነት መስሎ የአእምሮን ሚዛን ሲደፋ ያኔ ፕሮፓጋንዳ ግቡን መትቷል ማለት ይቻላል፡፡ የሰውን አዕምሮ በስሜቱ በኩል ማታለል ቀላል ቢሆንም፣ ደጋግሞ የተታለለ አዕምሮ ግን፣ በዛው ሂደት፣ ከሰውነት መንበር መውደቁንም አመላካች ነው፡፡ ደጋግሞ በስሜታዊነት አማካኝነት መታለል፣ ከሰውነት አቅም ብቃት ተገፍትሮ መውደቅ ነው፡፡
ጉዳት የሌለው ፕሮፓጋንዳ ችግር የለውም፣ ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ መጎዳትም ሆነ መጠቀሙ የሚጎላው ግን በአሰራጩ ላይ ሳይሆን የተቀባዩ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ መዘዙም ሰለባየሚያደርገው እሱው ነው፡፡ ይሄም ፅሁፍ የተነጣጠረው ለፕሮፓጋንዳ ተቀባዩ አካል ነው፡፡ የአዕምሮ አቅሙን በቀላሉ በሚሰራጭበት ፕሮፓጋንዳ ለሚነጠቀው አካል እንደ መጠበቂያ/ ማስታወሻ የተፃፈ ፅሁፍ ነው፡፡ ሰለባው፣ አዕምሮው በስሜታዊነት ከመሰለቡ በፊት ቆም ብሎ የማሰብ፣ የማመንታትን ወይንም የማስተዋልን እድል እንዲያገኝ ለማገዝ የተፃፈ ነው፡፡
ይኼው የፕሮፖጋንዳ ምንነትን የሚተነትነው ተቋም፡- በማንኛውም የማሰራጫ መንገድ የሚተላለፍ ማንኛውንም መልዕክት ፕሮፖጋንዳ መሆን እና አለመሆኑን ለማወቅ የሚያግዙ  ሰባት መለኪያዎችን አስቀምጧል፡፡ በእነዚህ መለኪያዎች ምንነቱ የሚካተት ማንኛውም መልዕክት የፈለገ ያህል ስሜታችንን ሰቅዞ ቢይዝ እንኳን ፕሮፓጋንዳ መሆኑን ማወቅ መቻል ይኖርብናል፡፡ መለኪያውን ከእነፍቺው ከዚህ በማስከተል እዘረዝራለሁ፡፡
ሀ) ሰም መስጠት፣ በስም መጥራት
“ስም መጥራት” ገና በቅጡ ያልመረመርነውን ፣ ወይንም በቂ መረጃ ስለሌለን ነገር ቸኩለን ፍርድ እንድንሰጥ፣ ድምዳሜ ላይ እንድንቆም የማድረጊያ አይነተኛ የፕሮፓጋንዳ ማራመጃ ዘዴ ነው፡፡ ስም የተሰጠው ነገር ለጥላቻችን ወይንም ለፍርሃታችን አልያም ለግርታችን የማረፊያ ማገር ይሆናል፡፡ ፕሮፓጋንዳው የሚነካን በችኮላ ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ ነው፡፡ ድምዳሜው ደግሞ ወደ ፍረጃ፡፡ የፕሮፓጋንዳው አላማ በስሜታዊነት አንድን ነገር ለማስጠላት ወይንም ለማስወደድ ሊሆን ይችላል፡፡
እንዲጠላወይንም እንዲወደድ የተፈለገው ግለሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይንም አንዳች ቡድን፣ሀገር፣ፖሊሲ፣ ፅንሰ ሃሳብ፣ አንዳች የሃይማኖት እሳቤ ወይንም ሁሉም የሃይማኖት እሳቤ ወይንም የፖለቲካ አቋም … ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ስሙ የሚነሳው ጥላቻን ለመጫር ሲሆን እንደ ጭቃ ተወርውሮ የሚለጠፍ ይሆናል፡፡ የተለጠፈው ስም በቀላሉ ማይፀዳ ወይንም በሀቅ ሳሙና ቢታጠብም የማይጠራ እና መንችኮ የሚቀር ከሆነ የፕሮፓጋንዳ አማራጩ ሰርቷል ማለት ነው፤ ወይንመ ግቡን መትቷል፡፡ ግቡ የሚቆጠረው ባልጠጣራ ወሬ የስሜትን መንበር በቀላሉ መቆጣጠሩ ላይ ነው፡፡
በእርግጥ፣ ፕሮፓጋንዳ ለዘላቂነት የማይሆን፣ ከተነቃበት በኋላ ረጅም እድሜ የሌለው ነገር መሆኑ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ፕሮፓጋንዳ የሚጭረው ስሜታዊነት ዘላቂ ባይመስልም… ስሜታዊነቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት የሚያደርሰው ጥፋት ግን ለዘላቂነት የሚቆይ ነው፡፡ ከዘመን የሚሻገር እና ብዙ ትውልድን የሚዳስስ ሊሆን ይችላል፡፡ እውነት የሚገለጥበት ጊዜ እስኪደርስ የውሸት አቋራጩ ፈጣን በመሆኑ አስቀድሞ ብዙ ጥፋትን ያደርሳል፡፡ ከብዙ እልቂት እና የህይወት መጥፋት በኋላ ሊሆን ይችላል የእውነት መገለጫው ጊዜ የሚደርሰው፡፡ ሲገለጥም ከደረሰው ጥፋት አንፃር ጉዳቱን እና ጥላቻውን ወደኋላ ለመመለስ የረፈደ ሆኖ ሊቀር ይችላል፡፡ ልክ እንደ ዶ/ር ከበደ ሚካኤል የፅጌረዳዋ አበባ ግጥም፡፡ ፅጌረዳዋ ዝናብን አስትጠማ እና ስትጠብቅ ከኖረች በኋላ ደመናው ሳይደርስላት ደርቃ ትሞታለች፡፡ ያረፈደው ደመና በተቻለው ፍጥነት ሲገሰግስ ደርሶ ዶፉን ቢያዘንብላትም ደርቃለችና እና ወደ ህይወት ሊመልሳት አልተቻለውም፡፡ የእውነት አረስራሽ እና ህይወት አዳኝ ዝናብ እስኪመጣ ፕሮፓጋንዳው ነው በጥም የተቃጠለችውን ፅጌረዳ በፀሃይ ንዳዱ እያንቃቃት የሚቆየው፡፡
በዚህ ረገድ በታሪክ ውስጥ ብዙ ሰለባ ሆነው የቀሩ ተጠቂዎች አሉ፡፡ እርግጥ ታሪክ ያስታውሳቸዋል፡፡ ችግሩ ሰው ከታሪክ አለመማሩ ነው፡፡ መማር ከቻለምከቂም ስለሚሆን የቀሰመው ትምህርት የበለጠ እልቂትን ለማምጣት ከመሆን አያልፍም፡፡ ማስተዋሉ የጥላቻ ማስተዋል ይሆንበታል፡፡ የታሪክ ትውስታ ግን ወደፊት የሚመጣውን  ዘመን ዋጅቶ ከተመሳሳይ ጥቃት መታደግ ባለመቻሉ ትውስታውን ትርጉም አልባ እናበድን ያደርገዋል፡፡ የሰለባዎቹ ህልውና ጨርሶ ከተፋቀ በኋላ በሃውልት መልክ ተመልሶ ተተክሎ በመልካምም ይሁን በመጥፎ ብቻ ሲታወስ ይኖራል፡፡
ስለዚህ ፕሮፓጋንዳን በትክክለኛው ሰዐት እና የመጫወቻ ቴክኒክ ማራመድ የሚችል ሁሌ ያንን ዳፍንት በሰፊው ሰለባ ላይበማልበስ ድሉን ደጋግሞ ይቀዳጃል፡፡
ለምሳሌ፡- መናፍቅ (Heretic) የሚለው ቃል በመጠራቱ ብቻ ብዙ ሰለባውችን ከህይወት ወደሞት እንዲጨመሩ ምክኒያት ሆኗል፡፡ አዲስ ነገር ይዘው ከመጡ አይን ገላጭ የጥበብ ሰዎች ጀምሮ ፣ እስከ እምነት ሰዎች ፣ ከመንፈሳዊያን እስከ ማህበረሰብ አናፂያን  በዚህ “መናፍቃን” በሚል ሰም ተጠርተው እንዲጠፉ ተደርገዋል፡፡
እነ ኮፐርኒከስ፣ ጋሊሊዮ፣ ክርስቶስ፣ ጆርዳኖ ብሩኖ … ብለን ብዙዎችን መዘርዘር እንችላለን፡፡ አሁን እንኳን በምንኖርበት ዘመን እና ሀገር  በአንድ የመርህ መፅሐፍ ( ቅዱስ ) እንተዳደራለን የሚሉ፣ በተናጠል ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ ፣ እርስ በራሳቸው “መናፍቅ” እየተባባሉ ሲካሰሱ እናያለን፡፡ ፕሮፖጋንዳ በአንድ ስሜት ወደ አንድ እውነት ጠቅልሎ ከሚሰበስበው ይልቅ፣ እርስ በራስ አጋጭቶ የመለያየት አቅሙ የበለጠ መሆኑ ታሪክ የተፃፈበት ቀይ የደም ቀለም የሚመሰክረው ሀቅ ነው፡፡
የሚለጠፉ ስሞች አንድ አይነት የሰው ልክነትን ወደ ብዙ ማንነቶች እና የባላንጣ ንዑስ ቡድኖች እንደሚከፋፍሉት ግልፅ ሆኖ ይታያል፡፡ ለምሳሌ በኮሚውኒዝም ፅንሰ ሃሳብ ውስጥ መናፍቆቹን ፡- አምስተኛረድፈኛ፣ ጠባብ፣ ፋሺስት፣ ዴመጎግ፣ አናርኪስት… ወዘተ ተብለው ስም ተሰጥቷቸዋል፡፡ ግቡ ስም ሰጥቶ ስም ማጥፋት ነው፡፡ የስም ቅጭት መፍጠር፡፡ ስም አጥፍቶም በማስከተል ህይወት እና ህልውናውን ማጥፋት፡፡
በምክኒያታዊ የሰከነ ሚዛናዊነት ይሄንን ፈጣን የስሜት ፍርድ ለመስጠት እንዲሁ ቀላል አይሆንም፡፡ አንዴ መቁረጥ አይቀልም በምክኒያታዊነት፡፡ ብዙ ጊዜ መለካት ያስፈልጋል፡፡ እውነት እና ምክኒያታዊነት በእኩል አይን ማየትን፣ ግራ እና ቀኙን በእኩል መመዘንን፣ መስቀላዊ ጥያቄ ደጋግሞ መጠየቅን፣ የተፈረጀውን ነገር ለማስጣል ማስተባበያ ማቅረብን ባህሪው ራሱ ይጠይቅበታል፡፡
ፕሮፓጋንዳ ለዚህ ጊዜ የለውም፡፡ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ አለበት፡፡ ግቡ ፈጣን ነው፡፡ እንዲጠላ የተፈለገውን በዐይን እርግብግቢት ፍጥነት ማስጠላት፡፡ መወደድ ያለበትን ደግሞ ለምን እንደተወደደ የዋጋ ተመኑ ሳይሰላ በፊት፣ በግር ግር ውስጥ ገና ሳለ ማስወደድ መቻል ነው ግቡ፡፡ ይህ ግብ  ሊመታ የሚችለው፣ መቺው ወደሚመታው ነገር ስሜታዊነትንእየዘራ መገስገስ ከቻለ ብቻ ነው፡፡ ስሜትን መንካት የሚችልበትን ስሌት የቀመረ የተሸለ ፕሮፖጋንዲስት ነው፡፡ ስም መስጠት፣ ወይንም ታርጋ መለጠፍ… ይሄንን በቀላሉ የማከናወኛ የጥበቡ ብልሃት ነው፡፡
አንፀባራቂ ድፍን መጠቅለያዎች( Glittering  generalities )
ድፍን መጠቅለያዎች በቀላሉ አንድን ነገር አምኖ እንዲወድ ከማድረጊያ የፕሮፖጋንዳ ዘዴዎች አንዱ ነው፡፡ ሰናይ፣ ወይንም የሚከበሩ ተብለው በስሜት ደረጃ  ምንነታቸውን ግልፅ ማድረግ ወይንም ተፈላስፎ መረዳት ሳያስፈልግ የምንቀበላቸው ነገሮች አሉ፡፡ በእነዚህ መጠቅለያዎች ስም ወይንም እኒዚህን ጥቅሎች ይዞ ለመጣ ማንኛውም አጀንዳ ብዙም መመርመር ሳያስፈልገው ወደ አድማጩ ልቦና መሰስ ብሎ እንዲዘልቅ ይፈቀድለታል፡፡
እነዚህን አብረቅራቂ ወይንም አንፀባራቂ ጥቅሎች እንደ ወርቅ ወይንም አልማዝ ማየት ይቻላል፡፡ አልማዝ ምን ዋጋ አለው ብሎ የሚመረምር የለም፡፡  በዘመናት ሂደት ሆኖ ተፈጥሯል ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የፕሮፓጋንድ  አብረቅራቂ መጠቅለያዎች ግን ከአልማዝም የበለጠ ለመመዘን አስቸጋሪ ናቸው፡፡ አልማዝ ቢያንስ በውድ ድንጋይ መመዘኛዎች ክብደቱ፣ ካራቱ ወይንም ጥራቱ ይመረመራል፡፡ በመልካም ዋጋቸው ከፍ ተደርገው የተቀመጡ እሴቶች አሉን፡፡ ግን እነዚህን እሴቶች ይዤ መጥቻለሁ የሚለው ሰው (ለምሳሌ ፖለቲኛ) በእውነት ይዟቸው እንደሆነ መመርመር አይቻልም፡፡ ሚዛኑ ስሜት ብቻ ነው፡፡ ለመጠርጠር ወይንም ለመመርመር ምንም እድል ገና በሌለበት የንግግር ቅፅበት፣ ተናጋሪው በአድማጩ ጆሮ ላይ እነዚህን አማላይ ቃላት ይወረውርበታል፡፡ ከመቀበል እና በስሜት ከመመራት ውጭ አድማጩ አማራጭ የለውም፡፡
የተወሰኑ የአንፀባራቂ መጠቅለያ ምሳሌዎችን ልስጥ ፡- ወንድማማችነት፣ ሰላም፣ እውነት፣ ፍቅር፣ ዴሞክራሲ፣ ማህበራዊ ፍትህ፣ የስራ እድል፣ ልማት…. ወዘተ…
ለአድማጭ አእምሮ የማገናዘብ እድል የማይሰጡ፣ ከዋጋቸው የተነሳ በመልካም የመንፈሱ ጎን የሚጓጓላቸው እንቁዎቹ ናቸው፡፡ ይፈልጋቸዋል፡፡ ይመኛቸዋል፡፡ እነዚህን አንፀባራቂ እምነቶቹን፣ ተስፋዎቹን ተገን አድርጎ የሚመጣው ግን  ከለላ ያደረገውን ውድ ነገር የማይወክል ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ፐሮፓጋንዲስቱ በአማኞቹ ስሜት የራሱን ስሌት ተግባራዊ ያደርግበታል፡፡ “መስሎን ነበር” የሚለው የቅሬታ ዘፈን የሚሰማው ከዘገየ በኋላ ነው፡፡ ኪሳራው በሰለባው ላይ ከደረሰበት በኋላ፡፡
ግን ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የተሳሰረ እንቅፋት ስለሆነ በድጋሚ የሚከሰተውም ያው ነገር ነው፡፡ የፕሮፓጋንዳውን ዜማ ጥሩ አድርጎ መጫወት የሚችል ሙዚቀኛ እስከመጣ፣ ዘወትር ሰምቶ የሚሸነፍለትን ዞሮ ዞሮ አያጣም፡፡

የማሻገሪያው ድልድይ ( The transfer device )

ፕሮፖጋንዲስቱ ተቀባይነት እንዲያገኝለት የፈለገውን ነገር፣ ከፍ ያለ ዋጋ በምንሰጠው፣ በምናከብረው ፣ በእኛ ላይ ስልጣን አለው ብለን በምናምነው ነገር ጀርባ ላይ ጭኖ ነው ሳይነቃበት የሚያሻግረው፡፡ የማሻገሪያው ድልድይ ይ የሚታከከው ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ነገር ነው፡፡፡፡ ለምሳሌ ብዙሃን ህዝብ ሀገሩን ወይንም ቤተ እምነቱን ያከብራል፣ ይፈራል፡፡ ፕሮፖጋንዲስቱ፣ ይዞ የመጣውን ዘመቻ ሀገራዊ ምልክቶችን ካንተራሰበት ወይንም የቤተ እምነቶችን ድጋፍ ካፀደቀበት፣ ይዞየመጣው አጀንዳ ከምናከብራቸው እነዛ ነገሮች እኩል በእኛ ላይ ባለስልጣን ይሆናል፡፡
ብቻውን ቢሆን ልንቀበለው የማንችለውን ጉዳይ፣ ዋጋ በምንሰጠው ነገር በኩል በማምጣቱ ሳንወድ በግድ እንቀበለዋለን፡፡
ምልክቶች ብዙውን ጊዜ እንደ ማሻገሪያ ድልድይነት አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ የመስቀል ምልክት (መስቀሉም አይነት አይነት አለው!) ፕሮፖጋንዲስቱ በራሱ አንገት ወይንም በድርጅቱ አርማ ላይ ካስቀመጠ መስቀሉ ይወክለናል የሚሉ አማኞችን ከነምንክታቸው የራሱ ያደርጋቸዋል፡፡ምልክቶች በቀላሉ ስሜቶችን ይቀሰቅሳሉ፡፡ አንዳንድ ምልክቶች ገና አይናችንን ስናሳርፍባቸው ከትልልቅ እምነት እና ከሚከፈሉ ዋጋዎቻቸው ጋር በቀላሉ በአንድ እንድንቆም ያደርጉናል፡፡ ፕሮፖጋንዲስቱ የማሻገሪያ ድልድዩን በምልክት መልክ በመጠቀም ከአንዳች አጀንዳ ጎን በሙሉ ቁርጠኝነት እንድንቆም ወይንም የፈለገውን አጀንዳ ደግሞ እንድንቃወም ሊያደርገን ይችላል፡፡

ምስክርነት ( Testimonial )

ምስክርነት፣ በቀላሉ የራስ ተሞክሮን ከአጀንዳው ጋር አስተሳስሮ ተጨባጭ ለማድረግ የሚጠቅም ወሳኝ መሳሪያ ነው፡፡ ምስክርነቱ የተሰጠው ስለ ገላ ሳሙናም ሆነ ስለ ሀይማኖት ድርጅት ወይም ስለ አምላክ ሊሆን ይችላል፡፡
“የፈለገ ያህል ድብርት ቢሰማኝም አንድ ብርጭቆ ****  ስጎነጭ እንደገና በሃይል እሞላለሁኝ” በሚለው ቅርፅ የቀረበ ማስታወቂያ የውሸትም ይሁን የእውነት፣ ተጨባጭም ይሁን  ሆን ተብሎ ለተውኔት የተፃፈ እስክሪብት… ያው በመሰረቱ ምስክርነት ነው፡፡ ይሄንን አቀራረብ ለብዙ ነገር መገልገል ይቻላል፡፡ የምስክርነቱ አላማ አማኝ ለማግኘት ነው፡፡ ከእምነት በኋላ ተገልጋይነት ወይንም ዋጋ ከፋይነት በቀላሉ ይገኛል፡፡
ምስክርነቱን ለአዎንታዊ መልዕክትም ሆነ አንዳች ነገርን በአሉታዊ ጎኑ እንዲሳል ለማጣጣል ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ እንዲያውም አንድን ነገር ሆነ ብሎ በማጣጣል ከጀመረ ከፍ ብሎ እንዲታይ የፈለገው ነገር ላይ ቁመት ለመጨመር በጣም ቀላል ይሆናል፡፡

ተራው ህዝብ( Ordinary folks )
“ተራው ህዝብ” የሚለውን ካርድ ብዙውን ጊዜ መጣል የሚያበዙት ፖለቲከኞች፣ የሞያ ማህበራት መሪዎች እና የቢዝነስ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰፊውን፣ ተራውን ህዝብ ከራሳቸው ( ከተናጋሪዎቹ ጋር )  አንድ እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ፣ በብዙሃኑ ህዝብ ዘንድ ተአመኒነትን የመፍጠሪያ የፕሮፓጋንዳ ቴክኒክ ነው፡፡
“እኔን የመሰለ ተራ የህዝቡ አካል እና ከህዝቡ ማህፀን የተገኘ ዜጋ” ብሎ ንግግርን ማሟሸት የተለመደ አቀራረብ ዘዴ ነው፡፡
በተለይ የምርጫ ወቅት ሲደርስ፣ ተመራጮች ትንንሽ ህፃናትን ሆነ ብለው አዘጋጅተውበማቀፍ ወይንም ተራ የሚባሉ ( የሚመስሉ ) ደሃ ገበሬዎችን (ካድሬዎችን) እና የማህበረሰቡ አባላት ዘንድ ወርደው፣ አልባሳታቸውን ለብሰው በመገኘት ይሄንን ንግግር ሲያደርጉ መሰማት የተለመደ ነገር ነው፡፡
“ቅርብ ነኝ” ፤ “እኛም እንደናንተው ነን” ፣ “እናንተ በእኛ መወከል እንደምትችሉ ጥርጣሬ አይግባችሁ”… የሚል ነው ማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት፡፡ በመልዕክቱም፣ “ተራ” የተባለው ህዝብ በእርግጠኝነት እንዲመርጣቸው አድርጎ ማጥመድ ነው፡፡

ካርታ እየሳቡ በባላንጣ ላይ መጣል ( Card stacking )
ፕሮፖጋንዲስቱ ባላንታውን ለማጠልሸት ከሚጠቀምባቸው የስም ቅጭት መፍጠሪያ መንገዶች መሃልይሄኛው ተጠቃሽ ነው፡፡ እባላንጣው ላይ የተከማቸውን ድጋፍ እና ተቀባይነት ወስዶ በራሱ ላይለማስቀመጥ ይሄንን ዘዴ ይጠቀማል፡፡ ካርታውን የሚጥለው በሚያሳምን መንገድ አዋዘወቶ ግን በውሸት አቅጣጫ ነው፡፡
ማጋነን ( Over - emphasis ) እና ማቃለልን ( under – emphasis ) በመጠቀም አጀንዳዎችን ለመሸወድ እና ተጨባጭ መረጃን ውድቅ ለማድረግ ይጣጣራል፡፡ ወደ ውሸት ፣ ስም አጥፊነት እና ሆን ብሎ ማጣመም ያደላል፡፡ የአድማጭን ድንጋጤ የሚያጭሩ የጭስ ማደናገሪያዎችን በመጠቀም በእሱ ራሱ ላይ የተሰነዘረበትን ( ለምሳሌ አሳፋሪ መረጃ ) አስጥሎ ሌላ አቅጣጫ አድማጩን ላመስያዝ ይሞክራል፡፡ እንዲገለፅ የማይፈልገውን እውነት ከትኩረት ለማውጣት ነው ጥረቱ፡፡ እውነት ያልሆነው እውነት መስሎ እንዲጋነን፣ እውነቱ ደግሞ ውሸት መስሎ እንዲቃለል የምድረጊያ ዘዴ ነው፡፡
አንድ ተራ የሆነ የፖለቲካ ተመራጭን በዚህ ዘዴ ምሁር አስለስሎ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ተራ እና ቀላል ሚዛን የቦክስ ተወዳዳሪን የአለም ቻምፒዮን አድርጎ ለማስቀመጥ ይረዳል፡፡ ታማሚውን… አዳኝ ፈዋሽ አድርጎ መሣል ይቻላል፡፡
ፖለቲከኞች፣ ዘዴውን በደንብ አድርገው በመጠቀም…ጅምላ ጨራሽ የሆነ አሰቃቂ ጦርነትን… ለሃቅ እና ፍትህ የተከፈለ ዋጋ እና የህልውና ውጊያ ስለመሆኑ አይናቸውን በጨው አጥበው ሊያሳምኑ ይችላሉ፡፡ አሳምነውም በለኮሱት እሳት ብዙዎችን በጦርነቱ አሳትፈው ለጥፋት እና እልቂት ሲማግዱ ታይተዋል፡፡

ተያይዞ መግተልተል ( Band wagon )
ይኼኝኛው፣ አንድ ላይ ሁሉም ሳያስተውል “ሆ” ብሎ እንደ መንጋ እንዲግተለተል የመቀስቀሻ ፕሮፖጋንዳዊ ዘዴ ነው፡፡ የፕሮፖጋንዲስቱን ፕሮግራም በህዝብ ደረጃ እንዲደገፍ የመቀስቀሻ ዘዴ፡፡
በዚህ መንገድ ላይ የምትዘወተር የማነቃቂያ ሀረግ አለች፡፡ “በአለም አቀፍ ደረጃ እየተደረገ ያለ ነገር ነው እኮ” የምትል ናት፡፡
በዚህ ዘዴ፣አንድ አይነትመድሃኒትን በአንድ ላይ ሁሉም እንዲወስድ በማነሳሳት ከማስቸኮል ጀምሮ፣ ለሆነ ዘመቻ አደባባይ ነድቶ እስከማውጣት ድረስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በማስታወቂያ ሸማችን ወደ አንድ ኤክስፖ አንጋግቶ ከማሰለፍ፣ እስቴዲየምን አፍ እስከ ገደፍ እንዲሚላ እስከማድረግ ወይንም በሚሊዮኖች ህዝብን ለድጋፍ ሰልፍ ለማንጋጋት ዘዴው ይጠቅማል፡፡
ማንጋጋት እንዲቻል ምልክቶችን፣ አርማዎችን፣ ቀለሞችን፣ ሰንደቆችን፣ ሙዚቃዎችን ወይንም ማንኛውንም ድራማ ተኮር ጥበቦችን ለጥቅሙ ያውላል፡፡ ፍላጎቱ ሁሉም “መንጋውን ተከትሎ” በህዝብ ባህር መልክ ተቀላቅሎ እንዲፈስ ነው፡፡
የሀገር ዜግነት፣ ሀይማኖት፣ ብሔር/ ዘር፣ ፆታ፣ የስራ መደብ… ይሄንን አላማ እንደማሳኪያ ሆነው በአገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ለአንድ አላማ ለማነሳሳት፣ ከዛ አላማ በተቃራኒ የቆሙ ሌላ አላማ አንጋቢዎችን የሚነካ መልዕክት መያዝ ወይንም የቡድን ስም መጥራት የበለጠ ቁጥር ያለውን ህዝብ ለመንዳት ጠቃሚነት አለው፡፡ ለምሳሌ፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት ወይንም አይሁድ የሚሉ የማንነት ገላጭ ልጥፎች የበለጠ ህዝብን ለመጥራት ፕሮፖገንዳዊ ፋይዳ አላቸው፡፡
ሁሉም ስያሜዎች ማባበያ ወይንም መተንኮሻ ናቸው፡፡ የተጠራው ስም በተለያየ አንፃር ይመለከተኛል ብሎ የሚያምንን አካል ፍርሐት፣ ጥርጣሬ፣ እምነት፣ መደናገር ወይንም አቋም በአንድ ላይ አስተሳስሮ “ሆ” ብሎ እንዲወጣ እና እንዲከማች ያደርገዋል፡፡፡፡ ስለዚህም በፕሮፓጋንዳ የተግተለተለውን ህዝብ በአንድ አላማ የተሳሰሩ አስመስሎ፣ አንድ ሳይሆኑ አንድ መስለው በመንጋ እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል፡፡
በሶሻል ሚዲያ በሚቀርብ መልዕክት ላይ፣ ወይንም በጋዜጣ ፅሁፍ ወይንም በንግግር በሚቀርብ ቃል… ይኼው መንጋን ለመንዳት የሚደረግ ፕሮፖጋንዳዊ ዘዴ እለት እለት ይታያል፡፡
“የምርጫ ካርዳችሁን አታባክኑ! ማሸነፉ በምንም አይነት ለማይቀረው ለእኛ እጩ ድምፃችሁን ስጡ!” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ሁሉም ተመራጭ በእየምርጫ ውድድሩ ስለማሸነፉ እርግጠኛ ሆኖ ነው የሚናገረው፡፡ ከምርጫው በኋላ ደግሞ ስለ መጭበርበሩ መናገር ይጀምራል፡፡ ሌላ የመግተልተል ሰልፍ ይጠራል፡፡ የድጋፍ የነበረው ወደ ደቃውሞ ተቀይሮ፡፡
ፕርፖጋንዳ እና ስሜታዊነት
በተዘረዘሩት ንዑስ አርዕስቶች ውስጥ መገንዘብ የሚቻለው ፡-ፕሮፖጋንዲስቶች በዋናነት የሚጠቀሙት ስሜቶቻችንን ስለመሆኑ ነው፡፡ ስሜቶቻችንን ያለ እኛ ፈቃድ መቆጣጠር መቻላቸው ነው አቅማቸው፡፡ ስሜታችንን እንደፈለጉ በመቆጣጠራቸው በኩራት እንድንወጠር ወይንም በጥላቻ እንድንንገበገብ የማድረግ ይችላሉ፤ ወይንም ሁለቱንም በአንድ ጊዜ እና በአንድ ላይ፡፡ እንዲፋፋም ለፈለጉት አጀንዳ ቆራጥ ታጋይ እና ተገዢ ያደርጉናል፡፡ እንድንጠላው ለፈለጉት አላማ ደግሞ ጠላት እና ፅዩፍ፡፡
ስጀምር እንደገለፅኩት ፕሮፖጋንዳ አንዳች ግብን የያዘ፣ ለግቡም ግለሰቦችን እና ቡድኖችን በአንድ እንዲነሱ የማድረግ አቅም የሚፈጥር፣ ወደ ተግባር የሚያመራ የዘዴ አይነት ነው፡፡ ይኼንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የስሜቶቻችንን አውታሮች ጠንቅቆ በማወቅ እና ወደአስፈለገው አላማ በቅኝት አስማምቶ በመጫወት ነው፡፡
እዚህ ላይ እምዲሰመርበት የሚያስፈልገው፣ ስሜቶቻችን የድካማችን  ምክኒያት ተደርገው መቆጠር እንደሌለባቸው ነው፡፡ስሜቶቻችንን በአግባቡ እስከተጠቀምንበት ድረስ የተፈጥሮአችን በረከት ነው፡፡ ወይንም ደግሞ ሁሉም አይነት ፕሮፖጋንዳ አጥፊ ነው ለማለት ታቅዶ የተፃፈ ፅሁፍ አይደለም፡፡
ነገር ግን፣ ማስተዋል የሚችልንየግለሰብ አዕምሮ ማንም ፕሮፖጋንዲስት ተነስቶ ስሜቱን ከእሱ ቁጥጥር ውጭ በማጦዝ ገንዘቡ አድርጎ እንዳይነግድበት ለማንቃት፣ መጠቀሚያ እንዳይሆንማስተዋሉን እና ምርጫውን በንቃት እንዲጠቀም፣ ግራ እና ቀኙን በአንክሮ እንዲያስተውል ለማገዝ የተፃፈ ፅሁፍ ነው፡፡

Read 272 times