Friday, 10 November 2023 00:00

በህጋዊ ሽፋን የሚገባው የኮንትሮባንድ ምርት በህጋዊ አምራችና ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ የህልውና አደጋ መፍጠሩ ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል በህጋዊ ሽፋን ያለ በቂ ቀረጥ እየገባ ያለ  ኮንትሮባንድ ምርት መበራከቱ በአገር ውስጥ አምራቾች እና ህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው ተባለ፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ በኩል ያለበቂ ቀረጥ ከፍተኛ የሆነ ምርት በፍራንኮ ቫሉታ እየገባ ነው የሚሉት አምራቾች እና ነጋዴዎች ይህ ሁኔታ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረና ከስራቸው እያፈናቀለን  ነው ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ  ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ተደጋጋሚ አቤቱታ አሰምተናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲባባስ እንጂ ምንም የመርገብ ምልክት አልታየበትም ብለዋል፡፡
እንደመረጃ ምንጮች በተለይ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የግንባታ እቃዎች እና መሰል ሌሎች ሸቀጦች መዳረሻቸውን መሃል አገር አድርገው በድሬዳዋ ጉምሩክ በሚወጣ ዲክላራሲዎን ምንም በሚባል ቀረጥ እየገቡ በገበያ ውስጥም ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል ሲሉ አክለዋል፡፡
ይህ ሁኔታ የአገር ውስጥ አምራች እና ህጋዊ ምርት አስገቢዎችን ብቻ ሳይሆን አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን በቢሊዎን ብሮች የሚቆጠር የመንግስት የቀረጥ ገቢም እንድታጣ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ነው ያከሉት፡፡
በማሳያነት የቆርቆሮ እና አርማታ ብረት ህገወጥ እንቅስቃሴን የሚጠቅሱት ቅሬታ አቅራቢዎች የጉምሩክ ኮሚሽን ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ማህበር አመራሮች ጋር ስለችግሩ መምከሩን መግለጹ የችግሩን መኖር አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ኮሚሽኑ ስለጉዳዩ መወያየቱን ቢገልፅ የችግሩን መኖር በይፋ አላመነም ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎች በጥቅሉ ያሉ ችግሮችን እፈታለው ብሎ መግለጹ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን በማህበራዊ ገጹ ስለውይይቱ ባጋራው መረጃ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ  ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ፣ ዘርፉ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ እያበረከተ የሚገኘው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ማለታቸውን ጠቅሶ ከጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች ጋር የተደረገው ውይይትም እየገጠሙ የሚገኙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ተናግረዋል ሲል አክሏል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሌ አብዲሳ በበኩላቸው የሐገር ውስጥ የብረት አምራቾች የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ ኮሚሽኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡
እንደ ቅሬታ አቅራቢዎች ገለፃ ከፍተኛ የሆነ የብረት ምርት በፍራንኮ ቫሉታ እየገባ መሆኑን ጠቅሰው ይህ እጅግ አነስተኛ ቀረጥ እየተከፈለበት የሚገባ ምርት ገበያውንም በማጥለቅለቅ የአገር ውስጥ አምራቾችን በእጅጉ እየጎዳና አንዳንዶቹም ስራ ለማቆም እንዲገደዱ እያደረገ ነው ተብሏል፡፡
አዲስ አድማስም የተለያዩ የጉምሩክ ሰነዶችን ማየት የቻለ ሲሆን፡፡ ሰነዶቹ  የተለያዩ ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያለው ብረት ከመደበኛው ማስቀረጫ መጠን እጅጉ ያነሰ ቀረጥ ተከፍሎባቸው የብረት ምርቱ እንደገባ ያሳያል፡፡
እስከ 300 ሺ ቶን ብረት በአንድ የጉምሩክ ሰነድ በአንድ ግለሰብ እንዲገባ መፈቀዱን የጠቀሱት የመረጃ ምንጮች፡፡ በተመሳሳይ 120 ሺ ቶን፣ 150 ቶን በሌላ ግለሰብ እንዱም ሌሎች በርካታ የብረት ጭነቶች በተለያዩ ግለሰቦች ስም በድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ በኩል እንዲገቡ ይሁንታ ያገኙበት ሰነዶችምን በመረጃነት ቀርበዋል ።
ባለፉት ጥቂት ወራት የወጡት የጉምሩክ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ግለሰቦቹ የከፈሉት የጉምሩክ ቀረጥ መጠንም በኪሎ ግራም ከ92 ሳንቲም፣ 74 ሳንቲም እና 50 ሳንቲም ብቻ መሆኑን የተረዳን ሲሆን፡፡በአንጻሩ በተመሳሳይ ወቅት በህጋዊ መልኩ የገባ ብረት በኪሎ ግራም 35 ብር አካባቢ እንደተከፈለባቸው  ያገኘናቸው የጉምሩክ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም በህጋዊ የጉምሩክ ሰነድ እጅግ ባነሰ የቀረጥ መጠን እየገቡ የሚገኙት ብረቶች የሁለት አስገቢዎች ብቻ ተሰልቶ እንኳን ለአገሪቱ መግባት የነበረበትን ከ 14 ቢሊየን ብር በላይ ያሳጣ ነው ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ያብራራሉ፡፡በጉዳዩ ከትናንት በስቲያ  መግለጫ የሰጠው የመሰረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ  ኢንዱ ስትሪዎች ማህበር ልዩ ልዩ የማጭበርበሪያ ዘዴ እና ህጋዊ ሽፋን በመጠቀም እየገባ የሚገኝ የተለያየ የብረት ምርት በአምራች ኢንደስትሪው ህልውና ላይ አደጋ ጋርጧል ሲል አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ በመግለጫው እንደተናገሩት 76 የሚሆኑ የማህበሩ አባላት አርማት ብረት (Reienforcment bar)፥ ጋልቫናይዝድ ቆርቆሮ (Galvanized sheet)፥ ቱቦላሬና የበርና የመስኮት ዘንጎች( Tubular sections)፥ እንዲሁም ልዩ ልዩ የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ምርት ውጤቶች ለመሰረተልማት የጀርባ አጥንት የሆኑ የኮንስትራክሽን ግብአቶችን እንደሚያስመጡ ገልጸዋል። አያይዘውም በአገራችን የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የብረት ማምረት አቅም  10 ሚሊዮን ቶን በአመት መድረሱንና  በአንጻሩ ፍላጎት ደግሞ እስከ 2 ሚሊዮን ቶን በአመት እንደሚሆን ይገመታል ብለዋል።
ይህም ሆኖ ያለቀላቸው ምርቶች ከውጭ አገር በህጋዊ መንገድና ስርአትን ባልተከተል መንገድ የሚገቡ በመሆኑ በገበያው ላይ ኢ-ፍትሃዊ የንግድ ውድድር በመፍጠር ኢንዱስትሪዎች ላይ የህልውና አደጋ  እንዲጋረጥባቸው እያደረጉ ይገኛል ሲሉ ነው ያከሉት።
እነዚህን ምርቶች የሚያመርቱ የአገር ውስጥ አምራቾችን ከገበያ ውጭ ሊያደርጉ የሚችሉ የኮንትሮባንድና ሌሎች ህግን ሽፋን አድርገው የሚፈፀሙ ህገ ወጥና ምንጫቸው ያልታወቁ ምርቶች ከማምረቻ ዋጋ በታች በሆነ ዋጋ የሚሸጡና ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ገበያውን እየተቆጣጠሩት በመምጣታቸው በተለያዩ መድረኮች ድምፃችንን በማሰማትና ለሚመለከታቸው ሁሉ አቤቱታችንን በደብዳቤ ጭምር እያሳወቅን ቆይተናል ያሉት የማህበሩ ዋና ስራ አሰስኪያጅ።
በአሁኑ ወቅት ለቆርቆሮ ለቱቦላሬ ምርት የሚያገለግሉ የጥቅል ጥቁር ብረቶችና የአርማታ ብረት ምርቶች በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት  በስፋት እየታየ እንደሚገኝ መረጃዎች እየደረሱን ይገኛሉ ሲሉ ነው ያከሉት።
ማህበራቸው የዘርፉን አጠቃላይ ሁኔታ የመቃኘትና የመከታተል ኃላፊነቱን በመወጣት ሂደት ላይ ሳለ በቀርቡ  ለማመን የሚያስቸግሩ መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን አቶ ሰለሞን ጠቅሰው፤  እነዚህ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቢሊዮኖች የመንግስትን ገቢ ሊያስቀሩ የሚችሉና የአገር ውስጥ አምራቾችን ሙሉ ለሙሉ ሊያዘጉ የሚችሉ ችግሮች ሆነው አግኝተናቸዋል ብለዋል። በመሆኑም በዚህ መንገድ ፈፅሞ ሊታመን በማይችልና በየትኛውም ዓለም ሊኖር በማይችል ዋጋ የብረታ ብረት ምርቶች እንደተገዙ ተደርጎ የጉምሩክ ቀረጥ ለማስፈፀም ማቅረብ ምን ያህል የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ የሚታወቅ ሲሆን በተለይ ደግሞ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ አፍስሰው በማምረት ተግባር ላይ የተሰማሩትን የአገረ ውስጥ አንዱስትሪዎች አሽመድምዶ ከገበያ ውጭ ሊያደርጋቸው የሚችል ድርጊት እንደሚሆን ለማንም ግልፅ ነው ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።Read 1173 times