Friday, 10 November 2023 00:00

አይቲ ፓርክ ከሁለት ሳምንት በኋላ በይፋ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ቋሙ በአፍሪካ የአይቲ ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል


       በአፍሪካ የአይቲ ማዕከል ለመሆን ራዕይ ሰንቆ በአዲስ መልክ እየተዋቀረና እየተደራጀ መሆኑ የተነገረለት የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ በይፋ  ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡ በአይቲ ፓርኩ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ  የሆነው  የግል  የዳታ ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመሩም ተጠቁሟል፡፡
ይህ ይፋ የተደረገው ባለፈው ረቡዕ ጠዋት በሸራተን አዲስ ሆቴል፣ “የዳታ ማዕከል አገልግሎት ሥነምህዳር ዕድሎችን ለፋይናንስ ዘርፉና ለቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው ማመቻቸት” በሚል ርዕስ፣ ለግማሽ ቀን በተካሄደ ጉባኤ ላይ ሲሆን፤ ጉባኤውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽንና የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል  በትብብር እንዳዘጋጁት ታውቋል፡፡
የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽኑን  የሚያስተዳድረው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር በለጠ ሞላ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር እውን በማድረግ ረገድ አይቲ ፓርኩ ጉልህ ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡ ከዚህ አንጻር ጉባኤው ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን ሚኒስትሩ አስምረውበታል፡፡
የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሔኖክ አህመድ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ፣ የኮርፖሬሽኑ ትልቁ ዓላማው ቢዝነስ መሥራት የሚያስችል ሥነምህዳር መፍጠር መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ሁሉም በጋራ የሚጠቀምበት ሪሶርስ በአንድ ቦታ ያቀርባል ብለዋል፡፡
 ራዕያችን የአፍሪካ የአይቲ ማዕከል መሆን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህን ለማሳካትም  የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣትና አቅምን በማሳደግ ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ጉባኤ ላይ  በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የግል የዳታ ማዕከል፣ በአይቲ ፓርክ ገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የጠቆመው ዊንጉ አፍሪካ የዳታ ማዕከል ኩባንያ፤ በምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊላንድና ታንዛንያን  ጨምሮ በአራት አገራት በዘርፉ አስተማማኝ አገልግሎት እየሰጠ  የሚገኝ ስመ-ጥር ኩባንያ ነው ተብሏል፡፡   
ኩባንያቸው በቀጣናው ተጠቃሽ  የዳታ ማዕከል አገልግሎት አቅራቢ መሆኑን የገለጹት የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል  ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ፤ በኢትዮጵያም ዓለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አስተማማኝ የዳታ ማዕከል መገንባቱን ጠቁመው፤ በዋናነት  የፋይናንስ ዘርፉና የቴክኖሎጂ ተቋማት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡ዊንጉ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ሥራ ከጀመረ 18 ወራት ማስቆጠሩን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ የዚህ ጉባኤ አንዱ ዓላማ እነዚህ የፋይናንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት ከፍተኛ ወጪ አውጥተው፣ የየራሳቸውን የዳታ ማዕከል ከመገንባት ይልቅ በኛ ማዕከል ቢጠቀሙ፣ የበለጠ እንደሚያዋጣቸው መረጃና ግንዛቤ ለመስጠት ነው ብለዋል፡፡ ጉባኤው አጋርነትና ትብብር የመፍጠሪያ መድረክ እንደሚሆንም ጨምረው አመልክተዋል፡፡
የዳታ ማዕከሉን ከሚመሩት ውስጥ 90 በመቶው ኢትዮጵያውያን መሆናቸው የገለጹት የኩባንያው አመራሮች፤ ማዕከሉ ለወጣት ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ ኢንጂነሮች ትልቅ የሥራ ዕድል መፍጠሩን አውስተዋል፡፡የዘርፉ ዓለማቀፍ ተዋናዮች በአጋርነት አብረውን እንዲሰሩ መሳብ ችለናል ያሉት አመራሮቹ፤ የመንግሥት ደንብና መመሪያዎች ወጥተው እንደተጠናቀቁ እኒህ ተዋናዮች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡ ማይክሮሶፍት፣ ቲክቶክና ሜታ (የቀድሞው ፌስቡክ) የመሳሰሉ ግዙፍ ዓለማቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ወደዚህ አገር እንዲመጡም እየሰራን ነው ብለዋል - የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል ኩባንያ  አመራሮች፡፡ የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል፣ በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መገንባቱ  ይታወቃል፡፡በዚህ ለግማሽ ቀን በሸራተን አዲስ በተካሄደው ጉባኤ ላይ፣ የአይቲ ኢንዱስትሪው መሪዎች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የፋይናንስ ተቋማት አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡


Read 1209 times