ቄራው በቀን 300 አህዮችን ያርዳል የቻይና ኩባንያዎች ከፍተኛ በጀት መድበው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል
በቻይናውያን ኩባንያዎች የተቋቋሙና አህዮችን እያረዱ ቆዳዎቻቸውን ወደ ቻይና የሚልኩ ድርጅቶች የአህዮቹን ህልውና አደጋ ላይ መጣላቸው ተገለፀ፡፡ ቄራዎቹ አሁን ባለው የእርድ መጠን ከቀጠሉ ከ20 ዓመታት በኋላ በአገሪቱ የአህዮች ህልውና ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠ ይሆናል ተብሏል፡፡አህያን ጨምሮ የጋማ ከብቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ የተቋቋመው “ብሩክ ኢትዮጵያ” የተሰኘው አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት በገለፀው መሰረት፣ በቻይናውያን ባለሃብቶች የሚተዳደሩት የአህያ ቄራዎች በእንስሳቱ ህይወት ላይ የህልውና አደጋ ደቅነዋል፡፡በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱና አሰላ ከተሞች ላይ የተገነቡት የአህያ ቄራዎች፣ ለእንስሳቱ ህልውና ዋንኛ ስጋት መሆናቸውን የጠቆመው ድርጅቱ፤ መንግስት የቻይና ኩባንያዎቹ እርዱን ለማከናወን እንዲችሉ ፍቃድ መስጠቱ ስህተት ነው ብሏል፡፡
ከአመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ተቋቁሞ የነበረው የአህያ ቄራ፤ በአካባቢው ህዝብ ተቃውሞ የተዘጋ ሲሆን በአሰላ ከተማ ያለው የአህያ ቄራ ግን አሁን ድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ታወቋል፡፡ቻይናውያኑ በአሰላ ከተማ ባላቸው የአህያ እርድ ቄራ ውስጥ በቀን 300 አህዮችን እያረዱ ቆዳቸውን ወደ ቻይና የሚልኩ ሲሆን፤ የአህያ ቆዳውን ለባህላዊ የቆዳ መድሃኒት መሳሪያ እንደሚያውሉት ታውቋል፡፡በአለማችን ካሉ አገራት በአህያ እርድ ቻይና ቀዳሚነቱን ስትይዝ፣ አገሪቱ በምታካሂደው የአህያ ቆዳ ንግድ በአፍሪካ እስያና ደቡብ አሜሪካ አገራት ውስጥ በሚገኙ አህዮች ላይ ከፍተኛ የህልውና አደጋ ደቅናለች ተብሏል፡፡ በርካታ አገራትም ይህንኑ የአህዮችን የህልውና ስጋት ምክንያት በማድረግ በቻይናውያን የተከፈቱ የአህያ እርድ ቄራዎች በመዝጋት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
Sunday, 12 November 2023 08:24
“የአህያ እርዱ የእንስሳቱን ህልውና አደጋ ላይ ጥሏል”
Written by መታሰቢያ ካሳዬ
Published in
ዜና