Saturday, 11 November 2023 00:00

የኢንቪድያ ነው - ጊዜው። ማን ነው እሱ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 ተአምረኛው ኢንቪዲያ… ዘንድሮ ቀንቶታል፡፡ 2023 የ “በVIDIA” ሆኗል፡፡
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ንግሥናውን በመላው ዓለም አስመስክሯል። ለምኞት የሚያስቸግር ማዕርግ አግኝቷል። ለመሆኑ ኢንቪድያ ማን ነው?
የ1 ትሪሊዮን ዶላር የአክስዮን ዋጋ ያስመዘገቡ የግል ኩባንያዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። የአይፎን አባት “አፕል”፣
የዊንዶውስ ባለቤት “ማይክሮሶፍት”…
የጉግል ጌታ “አልፋቤት”…
የኢንተርኔት መገበያያው የዓለም መነሃሪያ “አማዞን”…
ለተወሰነ ጊዜ ደግሞ…
የቢሊዮን ሰዎች መነሃርያ የፌስቡኩ ሜታ፣
የዓለማችን ቁጥር አንድ ቱጃር ኢሎን መስክ የሚመራው “ቴስላ” ኩባንያ፣…
በቃ እነዚሁ ናቸው ታሪከኞቹ ሻምፒዮኖች።


ዘንድሮ የትሪሊዮን ዶላር ዙፋን ላይ የተቀመጠው ኩባንያ፣ “ኢንቪዲያ” ነው።
ከጊዜ በኋላ፣ እንደ ቴስላ ወይም እንደ ፌስቡክ፣ የአክሲዮን ገበያው ሊወርድ ይችላል። ወይም እንደ አፕልና እንደ ማይክሮ ሶፍት ወደ ሁለት ትሪሊዮን ሊጓዝም ይችላል። ወጣም ወረደ፣ ዘንድሮ ለኢንቪዲያ ሆኖለታል።
ኢንቪዲያ፣ ከአስር ዓመት በፊት በ2013 የ10 ቢሊዮን ዶለር ኩባንያ ነበር።
ከአምስት ዓመት በኋላ፣ በ2018 ለአጭር ጊዜም ቢሆን የአክሲዮን ገበያው ወደ 100 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል (ተዓምር ነው ያስብላል። ገና ሌላ ተዓምር እንደሚመጣ ማን ገመተ?)
በ2023 ዘንድሮ… በሰምንታት ልዩነት እንደሮኬት ሽቅብ እየመጠቀ ወደ 1000 ቢሊዮን (ወደ 1 ትሪሊዮን) ሲደርስ፣ ከዚያም አልፎ ሲሻገር የኦሎምፒያ ተራራ ላይ ተደላድሎ ሲቀመጥ ዓለም ምን ይበል?
በአብዛኛው፣ ምንም አልተባለም። ወሬውን ከሰማንም፣ “ደግሞ ኢንቪዳ ማን ነው?” ማለታችን አይቀርም።


በእርግጥ፣ ኢንቪዲያ በዕድሜ ከፌስቡክ እና ከቴስላ፣ ከጉጉልም ይበልጣል። የአማዞን እኩያ ነው። ቢሆንም ግን፣ እስከ 2016 ድረስ ዕድሜውን ያሳለፈው ከ20 ቢሊዮን ዶላር በታች ነው። ታዲያ ብዙዎች የማያውቁት ትንሽ ኩባንያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ፣ ባልተጠበቀ ፍጥነትና ባልተገመተ መንገድ እንዴት ወደ ገናናዎቹና ወደ ዝነኞቹ ሰፈር ተቀላቀለ?
ለነገሩ፣ ዛሬ ከዝነኞቹ መሃል ከገባ በኋላም፣ የኢንቪዲያ ስም ያን ያህል አይታወቅም።
ያው፣ አንዳንድ ሥራዎች ለእይታ አይመቹም። ተገልጠው አይታዩም። በቀጥታ በችርቻሮ ገበያ ላይ የሚቸበቸቡ አይደሉም። ኮምፒዩተር ስትገዙ… ዴል፣ ቶሺባ፣ ኤችፒ፣ ሌኖቭ የሚሉ የኩባንያ ስሞችን ታይላችሁ።
የኮምፒውተሩ ዋና አንጎልስ? የአብዛኞቹ ኮምፒዩተሮች “አንጎል”፤ ኢንተል ኩባንያ የሚፈበርካቸው ናቸው። መጠናቸው ትንሽ ነው። ከትንንሽ የሞባይል ባትሪዎች ያንሳሉ።


ከኮምፒዩተር ውስጥ የተገጠሙ ስለሆኑም፣… ዞር ብሎ የሚያያቸው የለም።  ኩባንያው፣ “Inte inside” የሚል ጽሁፍ ኮምፒዩተሮች ላይ በመለጠፍ ራሱን ለማስተዋወቅ ቢሞክርም ያን ያህልም በሰፊው ለመታወቅ የጠቀመው አይመስልም።
 አብዛኛው ሰው ኮምፒዩተር ይገዛል፤ ከዚያም ሶፍትዌሮችን (አፕሊከሽኖችን) ይጠቀማል እንጂ፣… ቁሳቁሶችን በችርቻሮ ገዝቶ ኮምፒዩተር ለመገጣጠም አይሞክርም። እናም፣ ዴል እና ማይክሮሶፍት እንጂ፣ ኢንተል ኩባንያ ብዙም አይታወቅም።
የኢንቪዲያ ዕጣ ፋንታም ተመሳሳይ ነው። በኮምፒዩተር ውስጥ ወይም በጌም መጫወቻ ውስጥ የሚገጠሙ “ልዩ ተጨማሪ አንጎል” ናቸው - የኢንቪዲያ ምርቶች። እየከፋፈተና እየፈታ የሚያይ የለም።
ይህም ብቻ አይደለም።


 ጌም ለመጫወት ብሎ፣ ለኮምፒዩተር ተጨማሪ “አንጎል” ለማስገጠም፣ መቶ ዶላርና ከዚያ በላይ ወጪ ለማድረግ የሚጨክን ማን ነው? አብዛኛው ሰው አያስበውም። የጌም አፍቃሪዎች ግን ይጨክናሉ።
የኮምፒዩተር ጌም ከተጫወቱ አይቀር፣ “የኢንቪዳ አንጎል” ይመረጣል ይላሉ። የኢንቪዲያ ዋና ገበያና ዋና ትኩረትም “በጌሞች” ላይ ነበር። ተመራጭ ነው። ግን፣ ገበያው ከዓመት ዓመት እየሰፋና እያደገ ሊቀጥል አልቻለም።
አዲስ ገበያ እንደ ጉድ የተስፋፋለት፣ ባልተጠበቀው ፍጥነት ሳይሆን ባተጠበቀው መንገድ ነው፡፡ ለጌም መጫወቻ ይጠቅማሉ ተብለው የተሰሩ የኮምፒዩተር “ልዩ ተጨማሪ አንጎሎች”፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና አንጎል ይሆናሉ ብሎ ማን አሰበ? የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂ፣… በተፈጥሮው ግዙፍ የኮምፒዩተር መረብ ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ሂደት የቤም መጫወቻ ቴክኖሎጂ ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምትክ የሌላቸው ተመራጭ አንጎል መሆናቸው የታወቀ ጊዜ ነው - ከዛሬ 10 ዓመት ገደማ በፊት።
ግዙፎቹ ኩባንያዎች፣ እነ ማይክሮሶፍትና እነ ጉጉል፣ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን መሽቀዳደም ሲጀምሩ፣ የኢንቪዳ ገበያ ተተኮሰ። አንድ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀን “ማሽን” ለመገንባት፣ 10 ሺ የኢንቪዳ አንጎሎችን ይገዛሉ። አሁን አሁንማ፣ ለአንድ ማሽን 20 ሺ እና ከዚያ በላይ የኢንቪዳ አንጎሎችን መሸመት ጀምረዋል። በ33 ሺ ዶላር ሒሳብ ስታሰሉት፣ ከ330 እስከ 660 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል።


እናማ፣…
ዘንድሮ፣ የቴክኖሎጂና የቢዝነስ ዓለም ላይ ትልቁ የዘመኑ ፈጠራ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንት ፈጠራ ሆኖ የለ!
ከዚሁ ጎን ለጎን፣ ዘንድሮ የኢንቪዳ ዓመት ሆኗል። ከ10 ዓመት በፊት የ10 ቢሊዮን ዶላር ትንሽ ኩባንያ እንዳልነበረ፣ ዘንድሮ የ1 ትሪሊዮን ታሪከኛ ኩባንያ ሆኗል።
የካፌ ወንበር የሚያጣብቡ ወጣቶች - የያኔው አስተናጋጅ፣ የዛሬ ቢሊዬነር ነው፡፡
የኩባንያው መስራቾች ገና ከመነሻው፣ የኮምፒዩተሮችን አንጎል የሚያፈጥን አንዳች ቴክኖሎጂ ለመፍጠር ነበር ሐሳባቸው። ገንዝብም ቢሮም አልነበራቸውም። ካፌ ውስጥ ነበር የሦስቱ ወጣቶች መገናኛ ቦታ። ሌላ መሄጃ ሲያጡ፣ ካፌውን የስራ ቦታ አደረጉት። ቡና ይጠጣሉ። ደንበኞች ናቸው። ነገር ግን፣ ቡናቸውን ቶሎ ጠጥተው አይወጡም።
ቢሮ የመከራየት አቅም ባይኖራቸው ነው፡፡ ነገር ግን ወንበር ይዘው የካፌውን ገበያ መዝጋት እንዴት ይሆናል? ከግማሽ ሰዓት በኋላ ቡና ይደግማሉ። እንደገና ከግማሽ ሰዓት በኋላ፣ እንደገና ሌላ ቡና፡፡  አንድ ሁለት ቀን ብቻ ቢሆን፣ መቼስ ምን ይደረጋል።  ይታገሧቸው ነበር። የነዚህ ግን በየዕለቱ ሆነ። የየራሳቸውን ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ይዘው ይመጣሉ። ሲያንቀጫቅጩ ይውላሉ። የካፌው ባለቤት ካፈጠጠባቸው፣ የአስተናጋጆች ፊት ከጨፈገገባቸው፣ ቡና ይሰልሳሉ።


 አራት ሰዓት ሙሉ ወንበር ይዘው፣ በየፊናቸው ስምንቴ ቡና ጠጥተው፣ የሒሳብ ቀመርና ስሌቶች ላይ እንዲሁም ህልማቸውንና ተስፋቸው ላይ … የሚያወሩትን ተነጋግረው ይወጣሉ።
የካፌው ሰዎች እንዲህ ሲደጋገምባቸው ትዕግሥታቸው አለቀ። ግን አልጨከኑባቸውም። ወደ ጓዳ በኩል ብዙም የማያገለግል ክፍል ስለነበራቸው እዚያ እንዲሆኑ ፈቀዱላቸው።
ከሦስቱ ጓደኛሞች አንዱ፣ ካፌው ውስጥ አስተናጋጅ ሆኖ መስራቱ ሳይጠቅማቸው አልቀረም። ግን እስከ መቼ? ከበርካታ ወራት በኋላ፣ ኩባንያቸውን ለመመሥረትና ‘ቢሮ’ ለመቀየር ወሰኑ። እንደ ቢሮ የተቆጠረው፣ የአንዱ መኖሪያ ቤት ነው።
ከከተማ ወጣ ያለ ነው፡፡ ቢሆንም ከኪራይ ወጪ ያድናል፡፡ እንግዲህ ቢሮ ከተገኘ በኋላ፣ የኩባንያ ስም መምረጥ ብቻ ነው የቀራቸው። አዲስ ስም መፍጠር አልከበዳቸውም። የላቲን መዝገበ ቃላት ውስጥ ‘INVIDIA’ የሚል ቃል ተገኘ። በላቲን ቋንቋ የሚነጋገር ሰው ዛሬ አይኖርም። ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቅ ሰው ይኖራል? የመጠሪያ ስም እንደ መለያ ቁጥ ነው፡፡ ትርጉም አያስፈልገውም፡፡ ትርጉምና ማእረግ የሚቀዳጀው በነሱ ጥረት ነው፡፡ ለማንኛውም የመጀመሪየውን ፊደል ትተው ‘NVIDIA’ ብለው ለራሳቸው ስም መረጡ (ኢንቪድያ ልንለው እንችላለን)። የኩባንያ ምሥረታው በዚሁ ተጠናቀቀ። 40 ሺህ ዶላር የባንክ ሂሳባቸው ብዙም ሊያቆያቸው አይችልም። ለጊዜው ግን፣  የቢሮ ወጪ የለም። ሌላ ሠራተኛ የለም። ደሞዝም ገና ነው። ሦስቱ በነጻ ይሰራሉ - አዲስ ቴክኖሎጂ ለመፍጠር።


 ያሰቡትን ቴክኖሎጂ እስከ ጥግ አስበው ባይጨረሱም እንኳ መልክ ካስያዙት፣ ‘ዲዛይኑን’ ካጋመሱት፣ ኢንቨስተር አያጡም። ደግሞም ቀላል ሰዎች አይደሉም። አንዱ ተሸላሚ፣ ሌላኛው የማእረግ ተማራቂ፣ ሶስተኛው የነ አይቢኤም ተቀጣሪ ነው፡፡
ወጣቶች ቢሆኑም ለቴክኖሎጂ አዲስ አይደሉም።ኮምፒዩተሮችን የሚያፈጥን ቴክኖሎጂ እጅግ ተፈላጊ እየሆነ ይመጣል የሚል ነው ዋና ሐሳባቸው። እስከዚያውስ? ከፍተኛ የኮምፒዩተር አቅም ለሚጠይቁ “ጌሞች” የሚያገለግል ቴክኖሎጂ በመፍጠር ወደ ገበያ ለመግባት አነጣጥረው መስራት ጀመሩ። “ጂፒዩ” የተሰኘው አጋዥ የኮምፒዩተር አንጎል ላይ አተኮሩ።ጊዜ ቢፈጅባቸውም ከሦስት ዓመት ጥረት በኋላ የመጀመሪያ ምርታቸውን ለገበያ አቀረቡ - የዛሬ 25 ዓመት።


ብዙም ሳይቆይ ገበያ ውስጥ ዋና ተመራጭ የሆነ “ጂፒዩ” ሰርተው አቀረቡ። ከዚያ በኋላማ ገበያ ደራላቸው። ገበያው ራሱ እነሱን ፍለጋ መምጣት ጀመረ። ለጌም መጫወቻ አዲስ “ጂፒዩ” እንዲሰሩ የ200 ሚሊዮን ዶላር ቀብድ የሚሰጥ ደንበኛ አገኙ - የ’ኤክስቦክስ’ አምራች ማይክሮሶፍት። እንዲህ እንዲህ እያሉ የ10 ቢሊዮን ዶላር ኩባንያ ለመሆን  በቁ። ከዚያ በኋላ ግን፣ ኩባንያቸው ብዙም መነቃነቅ አልቻም፡፡  የ10 ቢሊዮን ዶላር ኩባንያ ለመሆን 10  ዓመት  አልፈጀባቸውም፡፡   

 
የኩባንያው ሃያኛ ዓመት ላይ ግን “የ10 ቢሊዮን ኩባንያ” ከሚለው ስያሜ አልተነቃነቁም እስከ 2016 ድረስ ማለት ነው።
እና ዛሬ በስድስት ዓመት ልዩነት ዛሬ የትሪሊዮን ዶላር ኩባንያ ለመሆን የቻለው እንዴት ነው?
አርቴፊሻል ኢንተለጀንሲ መጣ! ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂም በዓለም ዙሪያ፣ ከኢንፊዲያ ምርቶች ጋር የሚስተካከል ቴክኖሎጂ እስከ ዛሬ አልተገኘም፡፡

    የአክሲዮን ጠቅላላ ዋጋ
የዊንዶውስ ባለቤት “ማይክሮሶፍት” $2,680 ቢሊዮን 2.68 ትሪሊዮን
የጉግል ጌታ “አልፋቤት” $1,640 ቢሊዮን 1.64 ትሪሊዮን
የኢንተርኔት ገበያ “አማዞን” $1,475 ቢሊዮን 1.475 ትሪሊዮን
ኢንቪዲያ $1,135 ቢሊዮን 1.13 ትሪሊዮን
የፌስቡኩ ሜታ $820 ቢሊዮን 0.8 ትሪሊዮን
የኢሎን መስክ “ቴስላ” $700 ቢሊዮን 0.7 ትሪሊዮን

Read 404 times