Sunday, 12 November 2023 20:06

“…እንኳን የት እንደምትሆን፣ ምን እንደምትሆንም…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ያ በጠራራ ፀሀይ ፋኖስ አብርቶ “ሰው ጠፍቶብኝ እፈልጋለሁ…” አለ የተባለው ዲዮጋን ዓለምን ንቆ በባዶ እግሩ ይሄድ ነበር አሉ - ያውም ያኔ “የሚያስቡ ጭንቅላቶች” በበዙበት ዘመን፡፡ ዘንድሮ ዓለምን የናቀ በምን ይሄዳል መሰላችሁ? በሀመር! ቂ…ቂ… ቂ
ስሙኝማ… መግባባት ቸገረንሳ! አሀ… ልክ ነዋ! ያኛው ወገን ምንም ይበል ምን፣ የሚጥመን ነገር ካልሆነ በቀር “በእጄ…” ምናምን መባባል ቀርቷል እኮ! እሷና እሱ ይጨቃጨቃሉ፡፡ እናላችሁ… እሷዬዋ “ዶቃ ማሰሪያው” ድረስ ትነግረዋለች፡፡ ይሄኔ አጅሬው ዝም ብሎ ያዳምጣል፡፡
“ምን ይዘጋሃል፣ አትናገርም እንዴ!” ትለዋለች፡፡ እሱም… አለ አይደል…” ይኸውልሽ ምን መሰለሽ..” ምናምን እያለ መናገር ይጀምራል፡፡ እሷዬዋ አቋርጣው ምን ትላለች መሰላችሁ… “ዝም በል! ደግሞ አፍ አለኝ ብለህ ታወራለህ!” እንዴት ነው ነገሩ… አሀ… አንዳንድ እንትናዬዎች እንትናዎቻችሁን እንዲናገሩ “ታይም አውት” ምናምን ነገር ስጧ!


እሷዬዋ እስኪበቃት ተናግራ “እኔ እየተናገርኩ ታዛጋለህ?” ብትለው ምን አለ መሰላችሁ… “ኧረ እያዛጋሁ አይደለም፣ መልስ ለመስጠት እየሞከርኩ ነበር፡፡” ስሙኝማ… የእንትናዎችና የእንትናዬዎች መበሻሸቅ እኮ ስንት የፊልም ታሪክ ይወጣው መሰላችሁ! እሱ በሆነ ነገር በእሷ ተናዶባታል፡፡ እናላችሁ… የሆነ እሷን የሚያበሳጭበት ነገር ይፈልጋል፡፡ አንድ ቀን ጥምብዝ ብሎ ይመጣና ምን ይላታል.. “እግዜሐር ሴትን የፈጠረው መጨረሻ ሰዓት  ላይ ነው፡፡ ይህም ማለት ቅዳሜ ማታ ነበር ማለት ነው፡፡  ለዚህ ነው የድካም ስራ መሆኑ የሚያስታውቅበት…” ይላታል፡፡ እሷ ምን አለች መሰላችሁ… “እናንተ ደግሞ እንቅልፍ  ከወሰደው በኋላ እንደ ነገሩ ጠፍጥፏችሁ ምን እንደምትመስሉ እንኳን ዘወር ብሎ አላያችሁም፡፡” እኔ የምለው… እንትናና እንትናዬ በተጣሉ ቁጥር፣ አርፈን የተቀመጥነው ሁሉ በአንድ ሙቀጫ የምንወቀጠው ምን ፈርዶብን ነው፡፡ ልክ አይደለማ!


እናላችሁ… መናገርም፣ ዝም ማለትም አስቸጋሪ የሆነበት ዘመን ሲመጣ ነቃ ማለቱ አሪፍ ነው፡፡ተናጋሪ ከተሆነ ምን ይባላል መሰላችሁ… “እኔ የምለው…. እሱ ሰውዬ ሁልጊዜ የማይጠፋ ቴፕ ተገጥሞለታል እንዴ! እራሱን የቻለ የአስራ ስምንት አመት ኤፍ.ኤም. ሬዲዮ ነው እኮ! (ቂ…ቂ…ቂ) እሱ አንዴ ተናግሮ እስኪጨርስ እኮ የደረሰው እህል ታጭዶ፣ ተወቅቶ ጎተራ ይገባል፡፡”
እናላችሁ… “እንደ እኛ” ዝም ሲባል ደግሞ ሌላ ጣጣ አለው፡፡ “ይሄ ሰውዬ ዘላለሙን ተዘግቶ…የሆነ የአዕምሮ ችግር ምናምን ቢኖርበት ነው እንጂ…” አይነት ነገር ይባላል፡፡ ወይም ምን ይባል መሰላችሁ… “ልጄ…እንዲህ ዝም ብሎ ያወራነውን እየቀዳ ሄዶ ለማን እንደሚያሳብቅ ማን ያውቃል!” እናማ… አስቸጋሪ ነው፡፡ እንትናዬ … እኔ ብዙ የማልናገረው ከ“አንዳንድ የአማርኛ ፊደላት” ጋር ጠበኛ ስለሆንኩ… በቃ ነገር ባላሰብኩት “ይጠመዝዙብኛል” ብዬ ነው፡፡ እኔ የምለው… እናንተ “ደግሞ ይሄን ውሰድና ጋዜጣ ላይ አውጣው አሉ…” ምናምን የምትሉ ወዳጆቼ፣ በቀደም ጂን ምናምን ላይ ያወራናት ነገር ጠፋችኝማ!


እናላችሁ… ትክክል ያላችሁት ነገር አንድ ሺ አንድ “አረ እሱስ አፈር በልቶ ባረፈው…” አይነት ውግዘት ሲያመጣባችሁ… አለ አይደል… ማድረግ በሚገባንና በማይገባን መካከል ያለው ልዩነት ግራ እየገባን ነው፡፡ ለምሳሌ ስብሰባ ላይ በሰአቱ የምትገኙ ከሆነ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ የዘንድሮ ነገር እንዲህ፣ እንዲህ ነዋ! “ይሄ ደግሞ ማንን ለማሳጣት ነው ቀድሞ የሚመጣው! አጨብጫቢ!” ምናምን ያስብላል፡፡
መቼም “አብሮ መኖር በአለም ዙሪያ …” ምናምን ነገር ጥሩ ነው ትሉና… “ሰው የሆነውን” ለመሆን አርፍዳችሁ ስትመጡ ምን ይባላል መሰላችሁ… “እሱ ከማን ይበልጣልና ነው በዚህ ሰአት የሚመጣው! ይሄኔ … ከአለቆች ጋር ተሞዳምዶ የሚናገረኝ የለም ብሎ ነው! አጨብጫቢ!” እኔ የምለው… እንዴት ነው ነገሩ… ስርአት ሲይዙ “አጨብጫቢ!”፤ ስርአት ሲጥሱም “አጨብጫቢ!” ብቻ… “እኛና ዘንድሮ” ምናምን ነገር የሚል ዲክሽነሪ የታተመ እለት ጉዳችን ታይቶ!


እናላችሁ… አስቸጋሪ ነው፡፡ ምንም ነገር ላይ አንድ አስረኛው ቢያመሰግናችሁ፣ ዘጠኝ አስረኛው “ሲጥ ቢያደርጋችሁ” ደስ የሚለው ነው የሚመስለው፡፡ እኔ የምለው… አንዳችን ስለአንዳችን ጥሩ መናገር… አስራ አንደኛው ሀጥያት ሆኗል እንዴ!
ይቺን ስሙኝማ… ሁለቱ ጓደኛሞች ተመሳሳይ ጅንስ አድርገው ሸልለዋል፡፡ እናላችሁ… አንደኛዋ ሌላኛዋን ምን ትላታለች… “ይህን ጅንስ ስትለብሺ ከእድሜሽ አስር አመት ነው የምትቀንሺው” ትላታለች፡፡ ያችኛዋም በተራዋ “ለመሆኑ አንቺ እራስሽ እድሜሽ ስንት ነው?” ትላለች፡፡ “የእኔማ ሀያ ዘጠኝ ነው” ብላ ትመልሳለች፡፡ የዚህን ጊዜ አስር አመት ትቀንሻለሽ ምናምን የተባለችው ምን አለች አሉ መሰላችሁ …. “ማለቴ፣ ጅንስ ሳትለብሺ…” አሪፍ አይደል፡፡ ለጣይም ፈንጋይ እንዳለው እየረሳን እኮ ነው “ማሞ ዘ ፉል” ምናምን ነገር የምንሆነው!
ትናንትና… አይደለም ማመስገን… “ትከሻዬ ላይ እንኮኮ ብዬ የአዲስ አበባን ቀለበት መንገድ ካልዞርኩ” ሲል የነበረው ሰውዬ በአራተኛ ቀኑ ግልብጥ ይልና፤ “ይሄን ሰውዬ ላለማየት ገዳም መግባት አለብኝ እንዴ!” ምናምን ማለት ይጀምራል፡፡ እናማ… አስቸጋሪ የ“አየር ጠባይ” ነው፡፡
(ስሙኝማ… እንዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… በቲቪ “ዜናዎቻችን ላይ አስተያየት ካላችሁ …” ምናምን እንደሚለው አይነት ሌላ እንዲጨመርልን የምንፈልገው ነገር አለ፡፡ “በቴሌቪዥን ስታይዋቸው ቡአ ሊያስወርዷችሁ ምንም የማይቀራቸው ሰዎችን ስም በስልክ ቁጥራችን…” ምናምን የሚል “የግርጌ ፅሁፍ ይፃፍልንማ! ሁለት ጉርሻም ቢሆን እራታችን አይበላሽብና!
እኔ የምለው …. እዛ ባንኩ አጠገብ ያለው ህንጣ አካባቢ በመኪና “መለስ ቀለስ” የሚሉት ሰዎች አሁንም አሉ እንዴ! አሀ… ልክ ነዋ! አንድ ሰሞን ማታ እንትን ፕሮግራም ላይ እንትናዬን  “በአካል አድናቆቴን ካልገለጽኩ” የሚል መአት ነበራ፡፡ እኛ መኪና ባይኖረንም የኤፍ.ኤሞቹን “ከእነ አሳሳቃቸው እንደምናውቅ” ልብ ይባልልንማ፡፡ እኔም ሲመቸኝ አድናቆቴን በአካል እገልፃለሁ፡፡
እናላችሁ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የዛሬን ሰው ነገ “ምን ቦታ” ላይ እንደምናገኘው እየቸገረን ግንኙነታችን ሁሉ፣ የ“ሀያ አራት ሰአት ኮንትራት” ነገር  ብቻ እየሆነ ነው፡፡
እናማ… በእርግጠኝነት ስለሌላው መናገር የምር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
እዛ ሆሊውድ የሚሉት ሰፈር ነው አሉ፡፡ የአንዲቷ ተዋናይት ልጅ አስተማሪ፤ “በተከታዩ ወር እናትህን እንድትመጣ ንገራት…” ምናምን ነገር ይባላል፡፡ ልጁም፤ “ልነግራት አልችልም…” ሲል ይመልሳል፡፡
አስተማሪውም፤ “ለምንድነው ልትነግራት የማትችለው! የሚቀጥለው ወር የት እንደምትሆን ስለማታውቅ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ልጅ ሆዬ ምን ብሎ መለሰ አሉ መሰላችሁ… “የሚቀጥለው ወር እንኳ የት እንደምትሆን፣ ማን እንደምትሆንም አላውቅም፡፡” ደግነቱ እኛ አገር በባል ስም መጠራት የለም እንጂ ይሄኔ… የሚቀጥለው ወር ማን እንደምትሆን አላውቅም…” የምትባል በየክፍለ ከተማው ሁለት፣ ሁለት የእድር መዝገብ ባትሞላ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ … “ከድጡ ወደ ማጡ” አይነት የባህሪ ለውጥ በወራት ሳይሆን፣ በሰአታት በሆነበት ዘመን አፍን ሞልቶ ከመናገር “…እንኳን የት እንደምትሆን፣ ማን እንደምትሆንም…” ማለቱ ሳያዋጣ አይቀርም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 386 times