Sunday, 12 November 2023 20:13

እጅ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

“እጇ ይጨበጣል፤ ይዘረጋል፡፡ እጄን ሳቀርብላት ትጨብጠዋለች፡፡ ባለሁበት ሆኜ ሳልነቃነቅ እንደ አበባ ስታድግ አያታለሁኝ፡፡ የእኔ ሥራ እንዳትሰበር መጠበቅ ነው፡፡ እንዳትደርቅ ውሃ ማጠጣት፡፡ ወይንስ የእኔ ሥራ ዝም ብሎ መደነቅ ነው? የመጠበቅ እና ውሃ የማጠጣት ስራ
የፈጣሪ ነው፡፡ ከምንም ውስጥ ሁሉንም ነገር መስራት የሚችለው ኃይል፣ በእኔ ላይ ስራውን ሰርቷል፡፡ በእሷ ላይም መስራቱን ቀጥሏል፡፡--“
  
        ህይወት የሚገርም ነው፡፡ እንዲያውም፣ ትንሽ ራቅ አድርገው፣ ለቅፅበትም በምናብ ወጣ ብለው ካስተዋሉት ያዞራል፡፡ እንደ አመለካከት እና አቀባበል አቅም ነው ዙረቱ፡፡ ጡዘቱ፡፡  ደስ የሚል ስካር መሰል ሞኝነት ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንዲያውም ያጥወለውላል፡፡ ተመልሶ፣ ዙረቱ ላይ ተሳፍሮ፣ ዝም ብሎ መጋለብ ይሻላል፡፡
ለነገሩ ከግልቢያው መውረድ፣ ፈፅሞ፣ ጠቅልሎ አይቻልም፡፡ በሞት ካልሆነ በቀር፡፡ በምናባዊ እይታ ራቅ አድርገው የተመለከቱት እንደሆነ ግን፣ ህይወትን ያህል ነገር ይቅርና… የእጅ መዳፍ ፅህፈት ራሱ ይገርማል፡፡
“ይሄ ነው እጅ የሚባለው ነገር…፡፡ ደግሞ እኮ ይጨበጣል፤…ይዘረጋል፡፡ ሌላ እጅ ደግሞ ፈልጎ ይጨብጣል፡፡ ይጨባበጣል፡፡ ደግሞ ሲለው ያጨበጭባል፡፡ በጥፊም ድርግም አድርጎ ያጮላል…፡፡”
ትንሽ እጇን በእጄ ስጨብጥ ገረመኝ፡፡ ከሰባት ወር በፊት እጅም አልነበራትም እኮ፡፡ መዳፌ ውስጥ እጇን በእጄ ለመደበቅ ስሞክር አቃተኝ፡፡ እያደገች ነው፡፡ አልደበቅ አለች፡፡


ከሰባት ወር በፊት እናቷ ሆድ ውስጥ ነበረች፡፡ በአልትራ ሳውንድ ካልሆነ አትታይም ነበር፡፡ በፎቶግራፍ ካሜራ አትነሳም ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ነው የእናቷን ሆድ አፍርሳ የወጣችው፡፡
እናትየዋ ወር እየቆጠረች፣ “አሁን የቴምር ፍሬ አክላለች” ትል ነበር፣ ሆዷን እየደባበሰች፡፡ ምንም የሚታይ ነገር አልነበረም፡፡ ለተወሰኑ ወራት የተለያዩ ፍራፍሬ ስሞችን እየጠራች፣ የጠራችውን ስለማከሏ ስትነግረኝ በሙሉ ልብ አላመንኳትም ነበር፡፡
በኋላ ዶክተሩ የሆነ ፈሳሽ ሆዷን ቀብቶ፣ የሆነ ኳስ መሳይ ነገር እያሽከረከረ፣ ኮምፒውተሩ እስክሪን ላይ የሆነ ነገር አሳየኝ፡፡ የልብ ምቷን ሳደምጥ ነው የእኔ ልብ የቆመው፡፡ ፈዝዤ እስክትወለድ ቆየሁኝ፡፡
አሁን ሰባት ወሯ ነው፤ ግን ሙሉ ለሙሉ አልነቃሁም፡፡ ህይወት የሚገርም ነው፡፡ ሁሌ ግን አይደለም የሚገርመው፤ ብዙውን ጊዜ ይሰለቻል፡፡
 ትንሹ አልጋዋ ላይ ሆና መጫወቻዎቹን እያነሳች ተራ በተራ ትቀምሳቸዋለች፡፡ በአፏ እየለካች፣ በምራቋ ካላራሰቻቸው የመጫወቻዎቿን ህልውና ማረጋገጥ የምትችል አትመስልም፡፡
ጠጋ ብዬ አሸታታለሁኝ፡፡ የአንገቷ ጠረን ያሰክረኛል፡፡ ኡ - ቭ - ቭ  ያደርገኛል፡፡ አጭር፣ የተዋጣለት፣ የምናብ ጥልቀት ያለው ግጥም የተነበበልኝ ያህል ከእውነታው መስመር ያስፈነጥረኛል፡፡
ደግሞ ድምፅ ታወጣለች፡፡ እኔ የማወጣውን ድምፅ ታደምጣለች፡፡ አለች፡፡
 በህልውና አለች፡፡ ከምንም ውስጥ ድንገት የተገኘች ሁሉም ነገር ነች፡፡ አሁን ትሰማለች፡፡ ወደፊት ትናገራለች፡፡ አሁን ታያለች፡፡ ወደፊት ስላየችው ነገር አብራርታ ታስረዳኛለች፡፡ ይገርማል፤ አትታይም ነበር እኮ! ሰዐቱ ውድቅት ሌሊት ነው፡፡ እናቷ ተኝታለች፡፡ እኔ ሰባት ወር በአካል እኛ መሃል መሆኗን ለመቀበል አፍጥጬ አያታለሁኝ፡፡ የሚያዞር ነገር አለው፡፡ ዞሮ ዞሮ አይፈታም፡፡ አይዘረጋም፡፡ እያዞረ የሚቀጥል እሽክርክሪት ነው ህይወት፡፡ “ህይወት” የሚል አርዕስት፣ በማይገባ እጀታ ላይ ተፅፎ ነው የጨበጥነው፡፡ መች እንደተሳፈርንበት፣ ወቼ እንደምንወርድ አናውቅም፡፡ አሁን ደግሞ በሁለታችን መሃል ሌላ ተጓዥ አሳፍረናል፡፡ ሰባት ወር ሆኗታል፡፡ ድምፅ ታወጣለች፡፡


እጇ ይጨበጣል፤ ይዘረጋል፡፡ እጄን ሳቀርብላት ትጨብጠዋለች፡፡ ባለሁበት ሆኜ ሳልነቃነቅ እንደ አበባ ስታድግ አያታለሁኝ፡፡ የእኔ ሥራ እንዳትሰበር መጠበቅ ነው፡፡ እንዳትደርቅ ውሃ ማጠጣት፡፡ ወይንስ የእኔ ሥራ ዝም ብሎ መደነቅ ነው? የመጠበቅ እና ውሃ የማጠጣት ስራ የፈጣሪ ነው፡፡ ከምንም ውስጥ ሁሉንም ነገር መስራት የሚችለው ኃይል፣ በእኔ ላይ ስራውን ሰርቷል፡፡ በእሷ ላይም መስራቱን ቀጥሏል፡፡ በአይኔ ዐይኗን ሳይ እና ስታየኝ ኡ - ቭ -ቭ ያደርገኛል፡፡
ብድግ አድርጌ አቅፋታለሁኝ፡፡ የአንገቷን ጠረን አሸታለሁኝ፡፡ ትፈራገጣለች፡፡ ሆድ ውስጥ ሳለችም ትፈራገጥ ነበር፡፡
ገና ትራመዳለች፡፡ ወደኔ ትሮጣለች፡፡ ስትጎረምስ ደግሞ ወደ ሌላ፡፡ ሮጣ ሮጣ ሌላ የሚሮጥ ለመተካት ትሄዳለች፡፡ ትሄዳለች ግን ልትጠይቀኝ ትመለሳለች፡፡ እሷ ውስጥ ያስቀመጥኩት ደም አለ፡፡ እግዜር እሷ ውስጥ ያስቀመጠው ነብስ ግን ይበልጣል፡፡ እሱ ዋና ኢንቬስትመንት ነው፡፡ እኔ ስጋ እና አጥንቷን ነው የምታዘበው፡፡ ጠረኗን ነው የማሸተው፡፡


ትበላለች፡፡ ታድጋለች፡፡ ከፊት ለፊቷ ያለው ለጥ ያለ ህይወት ነው፡፡ ወይንም አባጣ ርባጣ ወይንም አዙሪት፡፡ ዋናው ህይወትን መያዟ ነው፡፡ በደንብ አድርጋ እየያዘች ነው፡፡
በቀላሉ ትተኛለች፡፡ እኔ ደግሞ በቀላሉ ይገርመኛል፡፡ መተኛቷም ይገርመኛል፡፡ መንቃቷም፣ መሳቋም፣ ማልቀሷም፡፡ በተለይ ልብስ መልበሷ ይገርመኛል፡፡
ልትተኛ ነው፡፡ ማንኮራፋትም ችላበታለች፡፡ የራሴን የማንኮራፋት ልማድ በሌሎች ሲታማ እንጂ በራሴ ጆሮ አድምጬው አላውቅም፡፡ በእሷ አፍ የራሴን ባህሪ ማድመጥ ጀምሬአለሁኝ፡፡ ህይወት ይገርማል፡፡ ከህይወት ባቡር ሳልወርድ፣ ወደ ውጭ ጠልጠል ብዬ ነው ለመታዘብ እየሞከርኩ ያለሁት፡፡ በቁሜ ነው የማልመው፡፡ ደስ የሚል ህልም ነው፡፡
እጇን እየጠባች ተኛች፡፡ ራሷን ለማረጋጋት እጇን ትጠባለች፡፡ እንደምትፈልገው የመረጋጋት መጠን፣ በሙሉ ጨብጣ ለመክተት ልትሞክር ትችላለች፡፡ የእሷ እጅ ለእኔም መፅናኛዬ ነው፡፡ ስጨብጣት ህልም አለመሆኗን አረጋግጣለሁኝ፡፡ እጅ የሚገርም ነገር አለው፡፡
ራቅ አድርገው ካስተዋሉት፣ እጅ በራሱ የህዋን ያህል ሰፊ ነው፡፡ የህይወት ስፋት ከአቅሜ በላይ  ነው፡፡ እጅ ላይ አትኩሬ መጠነኛ መረዳትን ማግኘት ይሻለኛል፡፡




Read 306 times